09 NOVEMBER 2014 ተጻፈ በ 

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በፓርቲው አመራሮችና አባላት ላይ ከምንጊዜውም በላይ የተጠናከረ ወከባ፣ እስራትና ማንገላታት በገዥው ፓርቲ አማካይነት እየተፈጸመበት እንደሆነ ገለጸ፡፡

ፓርቲው ይህን ያሳወቀው ዓርብ ዕለት ቀበና አካባቢ በሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ‹‹በአገሪቱ ላሉት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች እስርና ወከባ መፍትሔ አይሆንም›› በሚል በሰጠው መግለጫ ላይ ነው፡፡ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሥራት አብርሃምና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን ናቸው፡፡ ሁለቱም የፓርቲው አመራሮች እየተፈጸመ ነው ያሉትን በደል በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ አንድነት ከምሥረታው ጀምሮ አመራሮቹና አባላቱ የተለያየ ሽፋን በመጠቀም ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን አስታውሰው፣ ‹‹በቅርብ ደግሞ ለየት ባለ ሁኔታ አጠቃላይ ፓርቲውን በሚያዳክም መልኩ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የአንድነት አባላትን እያሳደደ በማሰር ላይ ይገኛል፤›› በማለት መንግሥትን ክፉኛ ተችተዋል፡፡

‹‹አሁን እየተካሄደ ያለው እስር፣ ማወካብና ማጉላላት ደግሞ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ለማሸነፍና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማጥበብ ያለመ ነው፤›› በማለት አቶ ዘካርያስ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ ‹‹በወላይታ ዞን የአንድነት አመራር አባላት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ድብደባ የተፈጸመባቸው ግለሰቦች ደግሞ አቶ ማሞ ጎሙ የዞኑ የአንድነት ሰብሳቢ፣ አቶ ወኖ መነሻ የዞኑ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊና አቶ አልታየ አቦታ የዞኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በምዕራብ አርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የሚገኙ የፓርቲው አባላትን ‹‹የፌዴራል ፖሊሶች የቤታቸውን በር ገንጥለው በመግባት እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸውና ከዚያም ወዳልታወቀ ቦታ ወስደው እንዳሰራቸው ለማወቅ ተችሏል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ደግሞ በመቐሌ የአንድነት አባል የሆነው ወጣት ሺሻይ አዞናው ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በመንግሥት የደኅንነት አባላት ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት እንደተወሰደ በመግለጫው ተጠቅሶ፣ ‹‹ወደ ቤቱ በመሄድ ያገኙትን ወረቀት ሁሉ ወስደው በመኪና ወዳልታወቀ ሥፍራ ይዘውት ሄደዋል፤›› በማለት በመንግሥት ደረሰብኝ ያለውን በደል የፓርቲው አመራሮች አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ‹‹በቀጣይነት ለምናደርጋቸው ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ከጎናችን ሆኖ ለለውጥና ለነፃነት በሚደረገው ሰላማዊ ትግል ላይ በመሳተፍ የማይተካ ድርሻውን ይወጣ፤›› በማለት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፓርቲው ጥሪውን አስተሏልፏል፡፡

በቅርቡ ከተመሠረተው የዘጠኝ ፓርቲዎች የጋራ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ሲሳተፍ ቆይቶ በመጨረሻ ወጥቷል በሚል ከጋራ ትብብሩ የተሰጠውን መግለጫ አስመልክቶ የፓርቲው አቋም ምን እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ አቶ ዘካርያስ፣ ‹‹የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በቀጣይ ሳምንት በሚያደርግው ስብሰባ ጉዳዩ አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል›› በማለት የመለሱ ሲሆን፣ በወቅቱ ትብብሩን ያልፈረሙበት ምክንያት ደግሞ ፓርቲው በአዲስ አመራር እየተዋቀረ ስለነበረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

Leave a Reply