on Thursday, 24 Mar 2016 08:05 PM
የፓርቲዎች መሪዎች ነን የሚሉን ሰዎች ግን ለእብደታቸው መድኃኒት እንዲያገኙ ሆስፒታል ወይም እንዲፈወሱ ጸበል የሚወስዳቸው ወገን እንዴት አጡ? እነዚህ ቡድኖች በዚህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ህዝባቸውን በባርያ ስርዓት ዘመን ይደረግ ወደነበረ ጦርነት መምራታቸው እብደት ካልተባለ ምን ሊባል ይችላል?
የወልቃይት ጸገዴ ጥያቄ የማንነት ከሆነ ሁለቱ ቡድኖች ጣልቃ ከመግባት እጃቸውን ቢያወጡና ቅምጥ የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህግ የተቀመጠለትን ኃላፊነት ቢወጣ ጥሩ ነበር፡፡ ችግሩ ግን ምክር ቤቱን የሚነዱት ስለሚነዱት ውጤቱ የተለየ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በጋንቤላና በአኙዋክ እልቂት፣ በደቡብ ህዝቦች በአናሳ ጎሳዎች መካከል በተረደገ ግጭት የተመለከትናቸውን ልዩነቶች አባብሰው ከማውጣት ውጪ መፍትሄ ሲያበጅ አልተመለከትንም አሁን ደግሞ በኦሮሞ ጉዳይ፣በአኙዋክና ኑዌር፣በአማራና ቅማንት እንዲሁም በወልቃይት ዙሪያ አባባሽ ድርጊቶች እየተፈጸሙ እየተመለከትን ነው፡፡
በእኔ እምነት እነዚህ ቡድኖች የህዝቡን መፋቀር፣አንድነትና መተሳሰብን አይፈልጉም፡፡ህዝብ ተፋቅሮና ተከባብሮ ከኖረ ወዳጅና ጠላቱን በመለየት የገዢዎችን ዕድሜ ስለሚያሳጥር አንድነቱን አይፈልጉትም፡፡ህውሓትና ብአዴንም ሽኩቻውን የሚፈልጉት በዚሁ ሰበብ ነው፡፡
ቡድኖቹ ለህዝብ ችግር ከምር ቢቆረቆሩ የበሰበሰው አስተዳደራቸውና ኢልኒኖ የፈጠሩትን ድርቅ፣ ረሀብ ፣ስደትና በሽታ ለመከላከል በተረባረቡ ነበር፡፡እነዚህን ለማድረግ አለመረባረባቸው የሚያሳያውም ቡድኖቹ ስለህዝብ ደንታቢሶች መሆናቸውን ነው፡፡
የቡድኖቹ ችግር ይህ ብቻ ነውን?
በእኔ እምነት ዋነኛው ችግራቸው የበታችነትና የበላይነት ወይም ጌትነትና ሎሌነት የፈጠረው ፍጥጫ ነው:: እንደሚታወቀው ብአዴን በህወሓት መሪዎች የተሠራና በሰሪው የተሠጠውን ፕሮግራምና መመሪያ በጄ ብሎ እየተቀበለ በመምጣቱ የህወሓት መሪዎችም አባታዊነታቸውን በኦህዴድም ፣በደህዴንና በሁሉም አጋር የክልል ፓርቲዎች ሁሉ እንዲሰርጽ በማድረጋቸው ህወሓትን በበላይነት አቆይቶታል፡፡
በጊዜ ሄደትም የብአዴን አመራር ለሁለት ተሠንጥቆ ፣ የፓርቲው መሥራችና አንጋፋ አመራር ተብለው በሚታወቁና በአዳዲሥ ተተኪ አመራሮች መካከል መናናቅና አለመተማመን እየሠፈነ መጣ:: አዲሡ ትውልድ ለአንጋፋዎቹ ከህወሓት አባታዊ ተጽኖ እንውጣ ሲላቸው አንጋፋዎችም የህወሓትን አባታዊነት ለማውረሥ በወጣት አመራሮች ላይ ተጸእኖ ማሣደር ጀመሩ :: የአማራ ህዝብም የብአዴንን አንጋፋ ቡድን የህወሓት ብአዴን በማለት ያናንቃቸው ጀመር፡፡ የብአዴን አዲስ አመራርም የበታችነት እየተቃወመው ሄደ ::
የህወሓት መሪዎችም ከበላይነታቸው እየወረዱና አባታዊነታቸውን እያጡ እንደሆነ እየገባቸው መጣ:: ህወሓቶች የነበራቸው የበላይነት በኦህዴድና በዓፋር ሣይቀር እየተናቀ መጣ:: መናደድ ጀመሩ፣ በተለይ ደግሞ አቶ መለስ በዚሁ ሰበብ ለህመም ተጋለጠ::
አጀንዳዬ የብአዴን በመሆኑ ይህንኑ ላጣቃልል ፣ የብአዴንና የህወሓት አመራር ቡድኖች በጎን መተያየትና መደፋፈር ከጀመሩ 6 ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ቀደም ሲል የህወሓት አመራር በጉባኤ ወይም በኮንፈረንስ የወሰነውን ውሳኔና ፖሊሲ እንደአባትነታቸው ወደ አባልና አጋር ፓርቲዎች በማውረድ ፖሊሲና መመርያ በማድረግ ተግባራዊ ያስደርጉ ነበር:: ሁሉም ክልሎችም በትግራይ የተሰሩ ሥራዎችን እንዲኮርጁ ለተሞክሮ እየተባሉ ብዙ ገንዘብ ለውሎ አበል እየተከፈላቸው ይዘሩ ነበር ፡፡ የሚቀስሙት ተሞክሮ ግን ጭቆና እና አፈናን ነበር::
የብአዴን አመራሮች ድሮ የነበራቸውን ታዛዥነት በመጣስ ከመለስ ጋርም መፋጠጥ ጀመሩ:: በአገር ውሥጥና በውጪ ያለ የአማራ ህዝብም ‹‹ነጻነት የላችሁም፣እናንተ የአማራ ህወሓት ናችሁ›› ብሎ ስለሰየማቸው ከዚህ ለመውጣት መጣር ጀመሩ::እናም
ብአዴኖች የበታችነታቸውን ለመሸፈን አራት አጀንዳ ይዘው ተነሡ፣እነሱም
1) በብዙሐን የመገናኛ ዘዴዎች ብአዴን የየትኛውም አካል ጥገኛና ተላላኪ አይደለም በማለት እየተጠነቀቁ መናገር ጀመሩ::
2) ጭራሹን ባልሰሩትና ባልዋሉበት የትግራይን ህዝብና ልጆቹን ታሪክ በመቀማት የውሸት ታሪክ በመጻፍ ብቅ አሉ:: ታሪኩ ውሸት በመሆኑም የሰሜን ጎንደር ፣ወልቃይት ጸገዴ፣ አርማጭሆ ፣ጋይንት፣ ንፋስ መውጫ፣ ጉና፣ ድብረታቡር፣ ፋርጣ፣ ሰሜን ሽዋ፣ በተለይም እነአለም ከተማ፣ መኸል ሜዳ ፣ መላው መርሀቤቴ ፣ አትባራ፣ የጎጃም ህዝብ በመጠኑ፣ ወሎ፣ ሀይቅ ማርሳሳ፣ ተንታ፣ ጭፍራና አፋር፣ ሠቆጣ፣ የላስታ ህዝቦች አይቀበሉትም ፡፡በተግባር ልጆቻቸውን ለህወሓት ሰጥተው እጅግ ብዙ መስዋእትነት በመክፈላቸው፣አዲስ አበባ እስከምንገባም አብረው ሥለነበሩ ሀቁን ያውቁታልና የተፈጠረውን ታሪክ ሊቀበሉት አይችሉም :: ይህ የብአዴን ታሪክ ሽሚያም በትግራይ ህዝብና በትግሉ በተካፈሉ ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል::
3) ባንዳንድ የብአዴን መድረኮች ከህወሓት አባታዊ አመራር ውጪ የሆኑ ወይም የተቃረኑ ውሣኔዎች መተላለፍ በመጀመራቸው የህወሓት አመራሮችን በጣም ያናድዳቸው ነበር ::
4) ብአዴኖች የወልቃይት ጸገዴን ጥያቄ የገቡበትም የነበሩበትን የበታችነት ስሜት ለመስበርና ‹‹ብአዴን የበታችነት ስሜት የለውም›› በማሰኘት ከአማራ ህዝብ ያጡትን ተቀባይነት ለማግኘት ያደረጉት የወረደና ኋላ ቀር እርምጃ ነው::
ስለዚህ የብአዴን ቡድኖች በጸገዴና በወልቃይት ያለውን የማንነት ጥያቄ በህዝብ ፍላጎትና በነጻ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንደመፍታት ህዝብ ከህዝብ በመጋጨት ድሮ የወደቀን የበታችነት ለመመለስ መሞከራቸው በአማራም ይሁን በትግራይ ህዝብ ተቀባይነት አይኖረውም::ከዚህ ይልቅ እጃቹህን አውጡ :: ህዝብ የራሱን እድል በራሱ ይወስን::
በሌላ በኩል የህወሓት የአመራር ቡድንና ተላላኪ ካድሬዎቹ በትግራይ ክልል በማንም ዘመን ያልታየ ድርቅ ተከስቶ፣ ህዝቡ በመልካም አስተዳደር እጦት እየተሠቃየና 5ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብን በውሀ ችግር ያሰቃየ ስርዓት ዘርግተው በውሸት ልማት እያጭበረበሩ ይገኛሉ:: ይህ ቡድን ህዝቡ በመኖርና ባለመኖር የጨለማ አዘቅት ተውጦ እያለ እንደብአዴን የ42 አመት የውሸት ታሪክ ለማጻፍ 200 ሚሊዮን ብር በመመደብ የመሪዎቹን የውሸት ታሪክ ለማጻፍ እየተሯሯጠ ይገኛል:: ህዝብን ለማዳን እርዳታ እንደማሰባሰብ በመጽሀፍ እናጽፋለን ሰበብ በመጽሀፉ አመካኝተው በሀገር ውስጥና በውጪ ካሉ የትግራይ ተወላጆች ገንዘብ ለመሰባሰብና የባንክ ጎተራቸውን ለመሙላት እየተሯሯጡ ናቸው::
እነዚህ ቡድኖች ከብአዴን የሚያደርጉት ሽኩቻ አባታነታቸውንና የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ህዝብ ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉት ሩጫም የውስጥ ሽኩቻቸውን ለመሸፈን ነው::
ስለነዚህ የተባለሹ ቡድኖች ብዙ በጻፍኩ ነበር፡፡ነገር ግን አንባቢን ላለማሰልቸት ስል ለኢትዮጵያ ህዝብ በመጨረሻ ወደ ማስተላልፈው መልእክት ላምራ ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ደግሞ ቡድኖቹ አሁን እያናከሷችሁ የምትገኙ የአማራና የትግራይ ህዝቦች ሆይ ፣የቡድኖቹን የተደበቀ ፍላጎት ተመልክታችሁ የፍላጎታቸው መሳሪያ አትሁኑ፡፡ ዛሬም ነገም ለዘለአለሙም ወንድማማቾች ነንና ::
አስገደ ገ/ስላሴ