የሽንጎው እይታና ራዕይ
የኢትዮጵያ እውነታዎች
አሁን በስልጣን ላይ ያለው በህወሓት የበላይነት የሚመራው ቡድን በተለያዩ የውጭ ሃይሎች ድጋፍና በመሳርያ ሃይል ሀገሪቱን ከመቆጣጠሩ በፊት፣ ለሀገሪቱ ሁለንትናዊ ችግር ምንጭ የብሄር ጭቆና መሆኑንና ብቸኛውና ዋናው መፍትሄ ደግሞ በዋናነት በዚህ ችግር ላይያተኮረ መሆን እንዳለበት ሲያቀነቅን፣ በርዕዮተ-ዓለም ደረጃም የአልባንያን ሶሽያሊዝም እንደመርህ ይዞ ሁለገብ ዴሞራሲያዊ መፍትሄዎችን እንደማይቀበል ሲገልጥ እንደነበር ይታወቃል።
ይህን አስተሳሰቡን ይዞ ሀገሪቱን የተቆጣጠረው ኃይል፣ የመጀመሪያው እርምጃው የነበረው ይህን አስተሳሰቡን የማይቀበሉትን የፖለቲካ ኃይሎች (በተለይም ሀገር አቀፍ ድርጅቶች)ማጥቃትና ከፖለቲካው ሂደት እንዲገለሉ ማድረግ ነበር። የማግለል ፖለቲካውን በነዚህ ሀገራዊ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የጀመረው ህወሀት/ኢህአዴግ የሽግግሩ መንግስት ሊፈጠር አጥቢያ ተቋቁመውም ይሁን ቀደም ብለው ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ብሄር ተኮር ድርጅቶች በሽግግር ሂደቱ እንዲሳተፉ ቢፈቅድም፣ (የነዚህን ድርጅቶች ማሳተፍ መቀበሉ ለጊዜአዊ ጠቀሜታ የተቀየሰ እንጂ ነጻ ሆኑ ድርጅቶችን ለማሳተፍ ከመነጨ እምነት አልነበረምና) ብዙም ሳይቆዩ ከሂደቱ እንዲገለሉና የተወሰኑትም በህገወጥነትና በጠላትነት ተፈርጀው ”ሰላማዊ“ ከሚባለው ፖለቲካዊ ሂደት በፍጹም እንዲወጡ አድርጓል።
የስርዓቱንአራማጆች ይህንኑ አመላካከት በመቀጠል እስካሁን ድረስ የተለያዩ አስተሳሰብና ራዕይ ያላቸውን ዜጎች በሰላምና ህግንበተከተለ መልክ በፖለቲካው ምህዳሩ እንዳይሳተፉ የሚከለክልፖለቲካዊ አካሄድ እንዲከተሉ ያደረጋቸውም ይኽው በአግላይነት ላይ የተመሰረተ ፍራቻን፣ጥላቻንና ለራሳቸው የሚሰጡት የተጋነነ አመለካከትን አካቶ የሚገለጸው ቅኝታቸው ነው።
በመሆኑም፣ ሐገራችን ኢትዮጵያና ህዝቧ ላለፉት 25አመታት እጅግ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋል።ስርአቱ ምንም እንኳን ዴሞክራሲያዊና ባለ ብዙ ፓርቲ ስርአትን ያመላከቱ በመሠረታዊ የሕግ ሠነዶች (“ሕገመንግሥት፣ ሕጎችና ደንቦች”) ያሠፈረ ቢሆንም፣በተግባር የሚታየው ግን የህወሀት/ኢህአዴግን በተለይም ደግሞ የህወሀትን የበላይነት በሚያረጋገጥ መልኩ ተቀይሶና ተዋቅሮ የሚንቀሳቀስ ብሄርን/ዘውግን መሰረት ያደረገ የአንድ ድርጅት ፣ ከዚያም አልፎ የጥቂት ግለሰቦች አምባገነንንት የሰፈነበት መሆኑን ነው። ይህ ስርአት በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚውበኩል የሚያሳየው አግላይነት፣ የመብት መጣስ፤ ጭካኔና መጠነ ሰፊ ግፍ ህዝቡን ወደ ታላቅ ቁጣና ህዝባዊ እምቢተኛነትእየገፋው ነው።
ይህ የህዝብ ቁጣ በተለያየ መልክ፣በተለያየ ጊዜ፣የተገለጠ ቢሆንም፣ በአንድ በኩል በስርአቱ ዘግናኝ አፈናበሌላ በኩል ደግሞ በተቃዋሚ ድርጅቶች መከፋፈል፤ ብቃት ማነስና ተባብረው መቆም አለመቻል፣ተፈላጊውን ግብ ሳይመታ ቆይቷል።
አሁን ደግሞ ይኸው የህዝብ የለውጥ ፍላጎትና አልገዛም ባይነት በተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች ተቀጣጥሎ ቀጥሏል። በሽንጎው እይታ ይህ የህዝብ በቃኝ ባይነት፣የሀገርን አንድነትና የህዝብን መልካም ትስስር ሳያበላሽ የስርአት ለውጥን እውን እንዲያደርግ፣ ከዚያም አልፎ የግጭቶች እና መጠፋፋት አዙሪትን ለመስበር በተቃዋሚዎች በኩል ምን መደረግ አለበት ብሎ መቀራረብ፤ መመካከር፣ እና ከቃላት በላይ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ የወቅቱ ዋነኛ ጥያቄ ነው።
ሕወሀት ኢህአዴግ ለ25 አመታት ተግባራዊ ያደረገው ስርአት በራእዩም በተግባሩም በቅራኔና በግጭት የተወጠረ እንዲሁም የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎት ሊያረካ የማይችል በመሆኑ ነው ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጋር እየተጋጨ የራሱን መጨረሻ በፍጥነት እያቃረበ የሚገኘው። ስርአቱ የሚያራምደው በብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካና ተግባረዊ ያደረገው ያስተዳደር ክልል በበቂ ጥናትና ህዝብን ባሳተፈ መልክ የታለመና የተተገበረ ስላልሆነ እነሆ ራሱ ህወሀት/ኢህአዴግን ሳይቀር ራሱ ባጠመደው ወጥመድ እርስበርስ ወደመባላት ያደረሰው ሲሆን ሀገሪቱንም ወደ መፈራረስና ህዝቡንም ወደ እርስ በርስ ግጭት አደጋ ጠርዝ አድርሷታል።
በህዝብ እና በስርአቱ መካከል ያለው ቅራኔ የስርአቱ ባለስልጣናት እንደሚሉት በጥቂት “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ምክንያት ወይም በየተዋረዱ የሚገኙ ባለስልጣናት ስራቸውን በደንብ ስላልሰሩ ወይም “ካፈጻጸም” ጋር በተያያዘ ምክንያት ብቻ የተከሰተ ሳይሆን ስርአቱ የህዝብን መሰረታዊ መብት ሊያከብር ባለመቻሉ፣ የህግ የበላይነትን ሊያከብር ባለመቻሉ የመንግስት ስልጣን ከህዝብ አመኔታ ብቻ መምጣት እንዳለበት ሊቀበል ባለመቻሉ፣ የሀገሪቱን ዳር ድንበርና ብሄራዊ ጥቅም ሊያሰጠበቅ ባለመቻሉ ህገመንግስት ተብሎ የቀረበው የፖለቲካ ፕሮግራምም የህዝብን አመኔታም ከበሬታም ያገኝ ባለመሆኑ፣ ህዝብ መንግስቱንም፤ ስርአቱንም የኔ ብሎ ስላልተቀበለው ነው። ቅራኔው በህዝብ የነጻነት ፍላጎትና በስርአቱ በአምባገነንነት እድሜልክ ለመግዛት ባለው ቅዥት መካከል ነው። ስርአቱ ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል፣ እርስ በርስ ለማጋጨትና ተደላድሎ ለመግዛት ያጠመደው ፈንጂ ባሁኑ ሰአት በእጁ ላይ ፈንድቶ የሚያደርገውን አሳጥቶታል።
የስርአቱንና የህዝቡን ቅራኔ ባጭሩ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡
በፖለቲካና ሰብአዊ መብት ገጽታው፤
ያለፉትን 25 አመታት የሀገራችንን ሁኔታ ስንመረምር መረዳት እንደሚቻለው፤ የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻ የሚንቀሳቀሱበት ምህዳር ጭራሽ ጠቧል፣ የብዙሀን መገናኛወች ፣ ከተራ ወከባ እስከ ግድያ በደረሰ መንግስታዊ ተጽእኖ ድምጥማጣቸውን ለማጥፋት ጥረቱ ቀጥሏል። የብዙሀን ድርጅቶች እንዳይመሰረቱ ከማገድ አልፎ ከተመሰረቱም አቅም የሌላቸው ሆነው እንዲቀሩ እየተደረገ ነው። ስርአቱ የዕምነት ነፃነትን በተደጋጋሚ ገፏል። የዕምነት ተቋማትንም አፍርሷል፣ በጣልቃገብነት አተራምሷል። የዜጎችን የመጻፍ የመናገር፣ በነጻ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ ተቃውሞን የመግለጥ መብት ወዘተ አፍኗል። ህዝብ የሚያስተዳድሩትን መሪዎቹን በራሱ ድምጽ የመሾምም የመሻርም መብቱ ተገፎ፣ እነሆ ህወሀት ኢህአዴግ በ2005 አይን ያወጣ ያደባባይ የድምጽ ዝርፊያ አካሂዶ አሽንፌአለሁ አለ በመቀጠልም በ 2010 በተካሄደውን ምርጫ በ99.6 % በ2015 ቱ ደግሞ በ100% አሽንፌአለሁ የሚል አስገራሚም አሳዛኝም ፖለቲካዊ ፊዝ ተከስቷል። ይኼ ተደጋጋሚ የምርጫ ማጭበርበር ኢትዮጵያዊያን በምርጫ ተስፋ እንዳይኖራቸው አድርጓል።
የኢኮኖሚያዊሁኔታዎችን ስንመለከት፣
ገዥው ህወሀት/ኢህአዴግ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከአመት አመት ከ 10% እና 12% እድገት አሳይቷል ሲል ቆይቷል። ሆኖም፤ የድሀው ፣ የበረንዳ አዳሪው፣ በቀን አንድ ጊዜ መብላት የማይችለው ህዝብ ቁጥር፣ የስራ አጡ ቁጥር ወዘተ እጅግ ከፍተኛ ነው። የኑሮ ውድነት ህዝብ ሊቋቋመው ከማይችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። ባለፉት 25 አመታት እጅግ ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብ በረሀብ አለንጋ ተገርፏል። ብዙወችም በየቦታው ሞተዋል። ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው ከምታውቀው ሁሉ የበለጠ ቁጥር ያለው ህዝብ ( በፊበርዋሩ 2016 የዩኤስ አይ ዲ ዘገባ መሰረት ከ10-15 ሚሊዮን ያክል ህዝብ) ዛሬ ተርቦ ይገኛል። የሚወራው የሁለት አሰርት አመታት የኢኮኖሚ እድገት ውጤት ለብዙሀኑ በተጨባጭ በህዝብ ህይወት መሻሻል ላይ አይታይም። በተጻራሪው የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት ቤተሰቦችና ተቋማት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ገቢና ኃብት ሰብስበዋል። የድሎትና የቅንጦት ኑሮ ይኖራሉ።
በሀገሪቱ የተለያየ ክፍሎች በከተማ መስፋፋትና በልማት፣ ባለሀብቶችን በማግባባትና በመሳብ ስም ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ከኖሩበት መሬት ያለፍላጎታቸው በጉልበት እንዲፈናቀሉ እየተደረገ ነው። የመሬት ነጠቃ በጋምቤላ፤ በቤነሻንጉል፤ በደቡብ፤ በኦሮሚያ፤ በአማራና በአፋር ወዘተ ክልሎች በሰፊው ተካሂዷል፤ እየተካሄደም ነው። ሁኔታው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በከተሞችም በሚያሳዝን ሁኔታ ህዝብን ማፈናቀሉ በሰፊው መካሄድ ከጀመረ አመታት አስቆጥሯል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ነዋሪ ግለሰቦች ሶስት እና አራት ትውልድ ከኖሩበት ቤታቸው በልማት ስም፣ መኖሪያ ቤታችሁ ለሰፋፊ ህንጻ ስራ ይፈለጋል ተብለው ያለፍላጎታቸው እና ያለበቂ ካሳ እያለቀሱ እንዲፋናቀሉ እየተደረገ ነው።
በአዲስ አበባ በፍልውሀ አካባቢ፣ በዶሮ መነቂያ አካባቢ በአራት ኪሎ፣ በሜክሲኮ አደባባይ ወዘተ ብዚ ሽህ ኢትዮጵያውያን የተፈናቀሉት በዚህ መልክ ነው። ተመሳሳይ ማፈናቀል እና የመሬት ነጠቃ በባህርዳርና በመቀሌ ወዘተ ተካሂዷል።
በቅርቡ በኦሮምያም የተቀሰቀሰው የህዝብ መነሳሳት አንዱ ምክንያት ይኸው ቅጥ ያጣ፣ የመሬት ነጠቃና የህዝብን መሰረታዊ መብት እና የመኖር መብት ቅንጣት ያክል የማያገናዝበው የስርአቱ ስግብግብ ፖሊሲና የባለስልጣናቱም አልጠግብ ባይነት ነው።
የማህበራዊ ሁኔታ
በማህበራዊ ጉዳዮች እንጻርም የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ አሰቃቂ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ወጣቱ ተስፋ አጥቷል። ኑሮን ለማሽነፍ ሲባል ሴተኛ አዳሪነት እጅግ በርክቷል። አሁን ደግሞ ወጣት ወንዶችም በዚሁ ተግባር ተሰማርተዋል። ኢትዮጵያ ወጣቶች በገፍ ከሚሰደዱባቸው አገሮች መካክል አንዷ ናት። ወላጆች እጅግ ተስፋ ከማጣታቸው የተነሳ የወለዷቸውን ልጆቻቸውን፣ አባት እናት የሌላቸው በማስመሰል ለማደጎ መስጠት የተለመደ ሆኗል። ህጸናትን በማደጎ ለባእዳን እንደሽቀጥ በመላክ ኢትዮጳያ ካፍሪካ ግንባር ቀደም ሆናለች።
የጋራ በሆነው የሀገርና የታሪክ እሴት መኩራት እየተቡረቦረ ነው። የህዝባችን አንድነት ተናግቷል፣ በመርዘኛ ከፋፋይ የሆነ ፖለቲካ የተነሳ በህብረተሰቡ ውስጥ መፈራራት፣ በጥርጣሬ መተያየት እጅግ አስፈሪ በሆነ ፍጥነት ተስፋፍቷል። ኢትዮጵያውያንን ካንዱ ክልል የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ስለሆንክ ልቀቅ ብሎ ማባረር የዚህ ቋንቋ ተናጋሪወች እንዳይመጡብን ማለት ዛሬ የተለመደ ሆኗል።
የዚህ ሁሉ መሰረት ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ህወሀት ኢህአዴግ ያለህዝብ ተሳትፎ፣ ያለበቂ ምክክርና ጥናት “ህገመንግስት“ ብሎ ተግባራዊ ያደረገው የፓርቲው ፕሮግራም እንዲሁም በቀጣይነት እየተተገበረ ያለው በጥላቻ ላይ የተማከለ የመንግስት ፖሊሲ ነው። ኢትዮጵያ ከዓለም አገሮች በተለየ ሁኔታ በብሄር/በዘውግ እንድትለያይ ተደርጓል። አንቀጽ 39 የመገንጠል መብትን ህጋዊ አድርጓል። ይህን የብዙ ችግሮቻችን መሰረት የሆነውን ህገመንግስት አንቀበልም የሚሉትን አንዳንዶች ጸረ ፊደራሊዝም፤ የብሄርን የብሄረሰብን መብት ለመንጠቅ የተዘጋጁ ወዘተ አድርጎ ለማቅረብ ይጥራል። ይህ ሁኔታውን አለመረዳት ወይም ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው። ፊደራሊዝምን የማይቀበሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢኖሩም እጅግ ጥቂት ናቸው፡ ፡ እኛም ሆን ብዙ ኢትዮ/ጵያውያን የማንቀበለው በፊደራሊዝም ስም ተግባረዊ እየተደረገ ያለውን፣ አድልኦ የተሞላበት፣ ተገንጣይነትን የሚቀበል፤ ግጭቶችንና ቅራኔዎችን ቀፍቃፊ የሆነ ከፋፋይ ሥርኣትና አሰራርን ነው። የጋራ ማንነት የጋራ እሴት ከማዳበር ይልቅ ማዳከምን የሚያበረታታውን “እኛና እነሱ” የሚለውን አጥር የሚያጠናክረውን ህግ ነው። በተፈጥሮ ኃብት ላይ፤ በተለይ በመሬት ላይ የሚካሄደው ግጭት የህገመንግሥቱ ውጤት ነው። የኛ ራእይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋው ባህሉ፤ ማንነቱ የሚከበርነት አንድነታችንን የሚያጠናክር የሁሉም ዜጎች መብት ሙሉ በሙሉ የሚከበርበት፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በማንነታቸው ኮርተው ንብረታቸውን ሳይነጠቁ፣ ከቀያቸው ሰይፈናቀሉ፣ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያለፍራቻ የሚኖሩበትን ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ስርአትን እውን ማድረግ ነው።
በሀራዊ ሉአላዊነት ሰላምና መረጋጋት
በኢህአዴግ የመጀመሪያ አመታት መረጋጋት የነበረ ቢመስልም ይህ ግን ብዙም አልቀጠለም። በ2010 የክራይስስ ግሩፕ ዘገባ እንደተረጋገጠውም ከዘጠኙ ክልሎች ውስጥበኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በሶማሊያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኔሻንጉል፣ በትግራይ ይነስም ይብዛም እስከ መሣሪያ መጠቀም የደረሱ ግጭቶች ይታያሉ። ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ መረጋጋት እየጠፋባት፣ የውጭ ጠላት አገሮች ጣልቃ እየገቡባትና እየከበቧት፤ በፍጥነት ከባድ ወደሆነ ቀውስና ውድቀት እየገባች ነው። ለዚህ አመቻች የሆነው ሁኔታ የአገር ውስጥ መከፋፈል መሆኑ የሚያከራክር አይመስለንም።
ስርአቱ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት እና ሉአላዊነት ግድ የሌለው መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። የኢትዮጵያን ህጋዊም ታሪካዊ ሁኔታን እንዲሆም ጥቅም ችላ ባለና ሀላፊነት በጎደለው አካሄድ ህወሀት ኢህእዴግ የኤርትራን መገንጠል አመቻችቶ ሀገራችንን የባህር በርም አሳጥቷታል፡፡ ይህ ሀላፊነት ጎደለው ውሳኔ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ለታላቅ አደጋ እንድትጋለጥ አድርጓል።
አሁን በቅርቡ ደግሞ በምእራቡ የሀገራችን ክፍል በኩል ለም ወሀ-ገብና ደን-ለበስ ሠፊ መሬት ለሱዳን እያስረከበ ነው ። ይህ አርቆ አሳቢነት የጎደለው ተግባር ዛሬ በራሱ በህወሀት ኢህአዴግ አባላት ሳይቀር ግንዛቤን እያገኝ ነው።
የግፍ ሞልቶ መፍሰስ እና የህዝብ በቃኝ ማለት
የስርአቱ የግፍ በትርና ያላቋረጠ አፈና የህዝብን የነጻነት ፍላጎትና ትግል ሊያከስመው ከቶውንም አልቻለም። በአሁኑ ሳአት ወገኖቻችን በኦሮሚያ በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ፣ በአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮች ወዘተ እነሆ በታላቅ ቁጣ በቃኝ ብለው ተነስቷል።
አሁን የሚታየው ትግል አበረታች ገጽታወቹ ውስጥ የሚከተሉትን ጉልህ ሁኔታወች ማንሳት እንችላለን፡
የሰላማዊ ትግሉ ተስፋ ሰጭነት መታደስ
የህወሀት/ኢሕአዴግ አገዛዝ የህዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ደረጃ በደረጃ ሊያልፈሰፍሰው እና ደብዛውን ሊያጠፋ ሲጥር እነሆ አመታት ተቆጥረዋል። ይህ በህዝብ ሰላማዊ ትግል እና በገዝው ቡድን ረገጣ መካከል የሚካሄደው ትግል አንድ ጊዜ ሲጎለብት ሌላጊዜ ደግሞ ሲዳከም ቆይቶ ባለፈው አመት (2007) ምርጫ ዋዜማ እጅግ የተቀነባበረ የጥቃት እርምጃ በመንግስት ደርሶበታል። ከዚህም የተነሳ ብዙወችሰላማዊ ታጋዮች ተገድለዋል ታሰረዋል፣ ሌሎች ለስደት ተዳርገዋል፣ ድረጅቶችምበጉልበት ህጋዊነታቸውን ተነጥቀው ተበትነዋል:: አንዳንዶች ደግሞ የሰላማዊ ትግሉ ተስፋ የለውም በኢትዮጵያ ውስጥ አይሰራም፤ በፍጹም ሊያንሰራራ ወደማይችልበት ደረጃ ደርሷል ብለው ተስፋ እሰከመቁረጥ እንዲደርሱ አድርጓል።
ይህ አይነቱ ተስፋ መቁረጥ በተለይም በሊህቃኑ በኩል አየተከሰተ ባለበት ሁኔታ ነው ሰላማዊ ትግሉ እጅግ ባልታሰበ ሁኔታ ፈንድቶ በሰፊ የሀገሪቱ ክፍል እየተቀጣጠለ የሚገኘው። ይህ ሰላማዊ የህዝብ ትግል ህዝባዊ እምቢተኛነት በኦሮሚያ ክልል በአማራ ክልል በተለይም በጎንደር የተለያዩ አካባቢወችና በወልቃይት በጠገዴ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ወዘተ በሰፊው እየተቀጣጠለ ይገኛል።
ህዝባችን የጭቆናውን ስርአት ለማስወገድ በህይወቱ ሳይቀር ዋጋ እየከፈለ ቆርጦ መነሳቱን እያሰመሰከረ ነው። ይህ እውነታ ባኦሮሚያ፣ በጎንደር በደቡብ ኢትዮጵጵያ፣ ባዲስ አባባ፣ በባህርዳር ወዘተ ተመስክሯል
የስርአቱ ድጋፍ እየተሟጠጠ መምጣት
በአሁኑ ሳአት በየቦታው በመቀጣጠል ላይ የሚገኘው የህዝብ መነሳሳት ገዥው ቡድን የድጋፍ መሰረቱ እጅግ እየጠበበ እንደሆነ ይደግፈኛል በሚለው በከተማው ብቻ ሳይሆን በገጠርም በሞስሊሙም በክርስትና ሀይማኖት ተከታዮችም፣ በኦሮሞ፣ በአማራ፣ በቤነሻንጉልም በአፋር፣ በኦጋዴን፣ በትግራይም በደቡብም ክልል የሚኖረው ህብረተሰብ ውስጥ ቦታ ማጣቱን ያሳያል። ስርአቱን ያዋቀሩት ህወሀትና ሶስቱ ድርጅቶች እርስበርስ መተማመን፣ እየመነመነ ነው፣ አንዱ ሌላውን ይከሳል፤ እርስበርስ ባይነ ቁራኛ ነው የሚተያዩት። ይህ ሁሉየስርአቱ እድሜ ወደመጨረሻው እየደረሰ እንደሆነ አመላካች ነው።
በተጨማሪም በህዝብ ትግል ግፊት የአዲስ አበባና የአጎራባች ከተሞች የተቀናጀ የልማት ዕቅድ የተባለውን ኦህዴድና ህወሓት በዘገምታም ቢሆን መሠረዛቸውአንዳንድ ችግሮቹን አባብሰዋል፣ መልካም አስተዳደር የሚባለውንም በጎላ መልኩ አበላሽቷል፣ በሙስናም ተጋልጠዋል የሚላቸውን ዝቅተኛና መለስተኛ ሹማምንት ገዥው ቡድን ከስልጣናቸው ማንሳት መጀመሩ የህዝብ ትግል እያስገኘ ያለውን ድል አመላካች ነው። ይህ ድል ዘላቂነት እንዲኖረው እንመኛለን፤ እንፈልጋለን።
ከድርጅቶች ባሻገር ህዝብን መሰረት ያደረገ ትግል መጠናከር
ሌላው በኦሮሚያም፣ ይሁን በአማራው ክልሎች አሁን የተነሳውን የህዝብ እንቅስቃሴ ካለፉት ሁሉ ለየት የሚያደርገው በቀጥታ ከላይ ወደታች የሚመራ ሳይሆን በህብረተሰቡ መሀል በተፈጠረ አመራር ከህዝቡ መሰረታዊ ኑሮ ጋር በተዛመደ አጀንዳ በህብረተሰቡ ታቅፎ የሚንቀሳቀስ ዳይንሚክ ሀይል መሆኑ ነው።የዚህ አይነቱ መሰረት ያለው የህዝብ እንቅስቃሴ ሰፋ ያለ ውጤትን ለማስመዝገብ ያለው ችሎታ ከፍተኛና አበረታች ነው
ተጓዳኝ አደጋወች
ተስፋ ሰጭ ሁኔታወች እንደሚታዩት ሁሉ አሳሳቢ የሆኑና የሁሉንም ኢትዮጵየዊ ልዩ ትኩረት የሚሹ ዋና ዋና ጉዳዩች ውስጥ የሚከተለውን እንመለከታለን።
የሀገር አንድነት መናጋት አደጋ
የሀዝቡ ትግል እየተጠናከረ ሲመጣ “የትግሉ ባለቤት እኔ ነኝ አመራር ሰጭውም እኔ ነኝ “ የሚሉ የተለያዩ ክፍሎች ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛል። ይህ አካሄድ አልፎ አልፎ አግላይ የሆነ አዝማሚያን የሚከተል ሲሆን አንዳንድ ጊዜም እኛና አነሱ የሚለውን አጥር እጅግ በማጠናከር የተወሰነውን ህዝብ ትግል ለተወሰነ አግላይ የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ የማድረግ አዝማሚያ ይታያል። ለምሳሌም በኦሮሞ ክልል የተከሰተውን እንቅስቃሴ ከሌላው ጋር የማይያያዝ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው የብቻ ወይም የተናጠል ጉዳይ እንደሆነና የሌላው ኢትዮጵያዊ ተግባር በተራ አጋርነት ደረጃ ማገዝ እንጂ ከዚያ ያለፈ፤ ሊሆን እንደማይገባው፤ በተወሰኑ ክፍሎች/ቡድኖች ተደጋጋሚ ቅስቀሳ ሲደረግ ተደምጣል። ይህ ህዝብን በጎራ ለይቶ በተለያየ ጠርዝ አስቀምጦ የሚያይ አካሄድ የሚያጠናክረው መቻቻልንና አንድነትን ሳይሆን ሩቅ ለሩቅ መተያትንና መከፋፈልን ነው
ቀረብ ብሎ ሲመረመርም ደግሞ አልፎ አልፎ ባንዳንድ ክፍሎች የሚገፋው የተቃውሞ አካሄድ፣ “አኛና እነሱ” የሚለውን አመለካከት ጽንፍ አድርሶ ኢትዮጵያዊነትንና የሀገሪቱን የግዛት አንድነት በጥያቄ ውስጥ የሚያሰገባ ቅኝት ይታይበታል።ለምሳሌ ባለፉት ጥቂት ወራቶች አንድን ያሀገሪቱን ክፍል ከጎረቤት ሐገር ጋር የማመሳሰል ሙከራ በተደጋጋሚ ተደምጣል።
ምንም እንኳ ከህዝብ አኳያና ከኢትዮጵያ ረዢም ታሪክ አንጻር ሲታይ፤ የኢትዮጵያዊነት መሰረት ጥልቅ ቢሆንም እንዲሁም ሀገሪቱ በታሪኳ እጅግ ብዙ ከፋፋይ አደጋወችን ያለፈች እንደሆነ ቢታወቅም በብሄር ላይ ያተኮረና ኢትዮጵያዊነትን በጥያቄ ውስጥ ያሰገባ አካሄድ በጊዜ ካልተገታ በኤርትራ እንዳየነው ሁሉ ማእከላዊው መንግስት እየተዳከመ ሲመጣ የሀገሪቱ ህልውናም ሆነ የህብረተሰቡ ደህንነት በአደጋ ላይ ሊወድቁ የሚችሉበት ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል በግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በእኛ እይታ ይህን አደጋ ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ያሰፈልጋል።
ኢትዮጵያዊነትን አልቀበልም ያለ የብሄረተኛ ድርጅቶች መጠናከር አደጋ
ይህን አሁን የተጀመረውን የህዝቡ እንቅስቃሴ ለማፈን ህወሀት/ኢህአዴግ የሚወስደው የግፍ እርምጃ ብዙወችን በማንነት ላይ ያተኮረ አመለካከት እንዲያጠናክሩ ያበረታታል። በአንድ በኩል መብት ረጋጩ መሪ ፓርቲ በብሄር ላይ የተመሰረተ አገዛዝ በመሆኑ በሌላ በኩልም የሀገሪቱ ስርአት ማንነት ላይ አተኩሮ የተዋቀረ በመሆኑ ሁኔታውን በቀላሉ የብሄረተኛነት ሰለባ እንዲሆን ያደርገዋል። በዚህ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የሚደረግ እያንዳንዱ የጅምላ ጥቃት ብሄረተኞችን እያጠናከረ እንደሚሄድ የሻብያእንዲሁም የህወሀትእንቅስቃሴና የእድገት ታሪክ ብዙ ያሰተምረናል።
በአንዳንዶች በኩል ዛሬ የሚታየውን የህዝብ እምቢተኛነት የአማራ ትግል፣ የኦሮሞ ትግል፣ የጋምቤላ ትግል የእነገሌ ትግል በሚል ጥቅል የተጠቃሹ ቋንቋ ተናጋሪ ሁሉ አንድ ወጥ አስተሳሰብና አመለካከት ያለው አስመስለው ሲያቀርቡ ይስተዋላል። የትግሉ አቅጣጫም በሰፋፊ የቋንቋ ተናጋሪወች ተመድቦ እንዲቃኝ የማድረግ አዝማሚያ ይታያል። በኛ አመለካከት አሁን ሀገራችን ባለችበት ውስብስብና የተካረረ ሁኔታ አደጋን ለመከላከል የሚያግዘው በቋንቋ ከፋፍሎ በያለበት ጎራ እንዲጸና የሚገፋፋ አመለካከት ሳይሆን ክፍፍሉን የሚያጠብ አንድነቱን የሚያጎላ ቅኝትና አሰራር ነው።
በሁሉም የሀገራችን ማህበረሰብ ውስጥ የተለያየ ፖለቲካ አመለካከትና የፖለቲካ አጀንዳ አለ። የትናውም ማህበረሰባ አንድ ወጥ አይደለም። የማህበራዊ ፍትህን ( ሶሻል ጀስቲስ ) መሰረት በማድረግ፣ የማንነት ጥያቄ አግባብ ያለው ምላሽ እንዲኖረው የሚታገሉ፣ኢትዮጵያዊነትን መሰረት አድርገው ዘረፋን፣ ምዝበራን ታሪካዊም ይሁን አሁን የሚታይን አግላይነት፣ ኢፍትሀዊነትን ወዘተ የሚታገሉ አንዳሉ መደገፍም እንዳለባቸው ምንም ጥርጥሬ የለንም። በኛ በኩል ከነዚህ ክፍሎች ጋር እጅ ለጅ ተያይዘን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሙሉ መብት የተከበረበት ዴሞክርሲያዊ ህገመንግስታዊ ስርአት እንዲመሰረት የምናደርገው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መቀጠል የለባትም፣ እንዲያውም ኢትዮጵያ የችግራችን መሰረት ስለሆነች መፈራረስ አለባት ብለው የሚታገሉ መኖራቸውን በትክክል መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይህን ሁኔታ እንደሌለ ማስመሰል ፤ተዛማጅ አደጋውን ደግሞ ዝቅ አድርጎ ወይም ከሚገባው በላይ አጋኖ ለማሳየት መሞከር ተገቢ አይሆንም። ይህ ለሀገርም ለህዝብም አይጠቅምም። ይህ ሁኔታ ሁላችንም ባጽንኦት ልንመለከተው እና ለመፍትሄ ፍለጋውም በጥንቃቄ ልንመክርበት የሚገባን ጉዳይ ነው።
የእርስ በርስ ግጭት አደጋ
የህዝባችን ለዘመናት አብሮ መኖር፣መዋለድና በአያሌ ማኅበራዊ ሀይማኖታዊና ባኅላዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፣ ወዘተእሴት እንዳለ ሆኖ፣ ከፍ ብሎ የተገለጸው ከፋፋይ ሁኔታ እየጦዘ ሊመጣ እንደሚችል በጊዜው በመገንዘብ አደጋውን መቀነስ ካልተቻለ እጅግ አሳሳቢ የሆነ የእርስ በርስ ግጭትን ሊጋብዝ የሚችል ሁኔታ በሀገራችን ውስጥ መኖሩን እንመለከታለን። ይህ የህዝብ እርስ በርስ ግጭት በሕወሀት/ኢህአዴግ ወይም በተቃዋሚ ውስጥ በማንነት ላይ የተመሰረተ ግጭትመካረር ይጠቅመናል ብለው በሚያሰቡ ክፍሎች ተንኳሽነት ሊቀሰቀስ ይችላል። በተጨማሪም ሀገሪቱ በማያባራ የእርስ በርስ ግጭት እንድትዘፈቅ የሚሹ የውጭ መንግስታትም (ለምሳሌ ከ2 አመት በፊት ሾልኮ የወጣው የግብጽ መንግስት ባለስልጣኖች ውይይት እንደሰማነው) የዚህ አይነቱን እኩይ ተግባር፣ በቀጥታም ሆነ በእጅ-አዙር፣ ለመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ መገንዘብ ተገቢ ነው::
የሀገር አንድነት መናጋት አደጋና የእርስበርስ የግጭት ፍራቻ አሉታዊ ተጽእኖ
እጅግ ብዙው ኢትዮጵያዊ የሕወሀት/ኢህአዴግን መወገድ እና የሰርአት ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ቢሆንም ለሀገሩ አንድነት የሚጨነቀው፤ የእርስ በርስ ግጭት የሚያሰጋውና ሌላ ያግላይ ድርጅት ስልጣን መያዝ የሚያሰሳስበው የህብረተሰብ ክፍል ስጋቱ ለህዝባዊ ትግሉ ድጋፉን እንዳይሰጥ ፣ ከዚህ የተነሳም የትግሉ አካልም ከመሆን እንዲቆጠብ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ትግሉንየሚያስፈልገውን በቂ ሀይልያሳጣዋል ያዳክመዋል፡፡ ተበታትኖለመጠቃት በር ይከፍታልም:: ምናልባትም ለገዥው ቡድን እንደገና መጠናከር ያልተጠበቀ ሁኔታ ሊፈጥርለት ይችላል፡፡ ይህ አደጋ የአለም አቀፍ ህብረተሰቡንም ላይ ተመሳሳይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።
ስለሆነም ህዝብን ለምን አልተነሳም ብሎ ከማማረር በፊት በተቃዋሚው በኩል ህዝብን ከመነሳት ወደ ኋላ እንዲል የሚያደርገው እምነት እንዲያጣ የሚያደርግ ወይም እንቅስቃሴውን በጥርጣሬ እንዲያየው የሚያደርገው ምን ጉዳይ አለ ብሎ ወደውስጥ ተመልሶ መመልከት አስፈላጊውንም ማስተካከያ ማድረግ ተገቢ ይሆናል።
ስርአቱ እንዳለ መቀጠል በሀገር አንድነት መናጋታና እና በእርስበርስ ግጭት አኳያ ያለውን አደጋ እጅግ በማወሳሰብ ታላቁን ሚና ይጫወታል። በመሆኑም የችግሮቻችንን መፍትሄ ስናስብ የስርአት ለውጥ አስፈላጊነትን ለደቂቃም መዘንጋት የለብንም። የምሆኖ ግን በተቃዋሚው በኩል ያለውንም ሁኔታ ደግሞ በተጨባጭ መገንዘብ ተገቢ ነው።፤
ተስፋን ለማጠናከርናአደጋውን ለመቀነስ ምን ይደረግ?
በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን የለውጥ መነሳሳት አጠናክሮ አደጋውን ቀንሶ የህዝቡን ተስፋ በማደስ ወደሚፈለገው ቦታ ለማድረስ እንዲሁም በሀገራችን ውስጥ የግጭት አዙሪትን ሰብሮ፣ ዘላቂ ሰላምን ተግባራዊ ለማድረግና ለልማት መሰረት ለማጣል የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሲቪክ ማህበራትና ምሁራን ታላቅ ሀላፊነት አለባቸው። ለዚህ የሚበጀው ከሁሉም በላይ ከቡድን በላይ የሃገርንና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም ነው።
ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎችንም በግምት ውስት በማስገባት ትግሉን በተቀነባበረ መልክ የመላ ሀገሪቱን ህዝብ ያሳተፈና የአለም አቀፉንም ህብረተሰብ ድጋፍ ሊያገኝ በሚያሰችለው መልክ ወደፊት ለመግፋት የሚከተሉትን አራት ነጥቦች ላይ ያተኮረ ተግበራዊ እንቅስቃሴን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።
የተቃዋሚው መሰባሰብና መተባበር
ተደጋግሞ እንደተነገረው የህወሀት ኢህአዴግ መንግስትና ስርአት እድሜ የረዘመው በስርአቱ ጥናካሬ ሳይሆን በተቃዋሚው መከፋፈል፤ አለመሳባሰብ እና አለመጠናከር ነው። በሌሎች ከአምባገነን ስርአት ወደ ዴሞክራሲ የተሸጋገሩ ሀገሮች ልምድ (ለምሳሌ ፖላንድ፣ ቱኒስያ፣ ፊሊፒንስ፤ በርማ) የምንረዳው በግልጽ አላማ ዙሪያ የተሰባሰበ ተቃዋሚ ለስርአት ለውጥ ብቻ ሳይሆን ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታም ወሳኝ እንደሆነ ነው። በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥም አሁን ያለውን የህዝብ መነሳሳት ወደሚፈለገው የስርአት ለውጥ እንዲያመራ ለማድረግ አንዱና ዋነኛው አጣዳፊ ተግባር በተወሰኑ ሀገራዊ ዓላማዎች (መርሆወች) ላይ የተሰባሰበ ሰፋ ያለ የተቃዋሚወች የጋራ ትብብር ባስቸኳይ መመስረት ነው።
ይህ ስብስብ ህብረተሰቡን በተቀናጀ መልክ እንዲታገልና፣ የእርስ በርስ ግጭትን ለማስወገድ ትልቅ መሳሪያ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በተለያየ ቦታ የሚታየውን አለመተማመንን ለመቅረፍ በመላ ሀገሪቱም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ገዥውን ቡድን ለመተካት የሚችል፣ የተባበረ፣ ሀገር ለመመምራት ብቃት ያለውና ሀላፊነት የሚሰማው ስብስብ (ድርጅት)፤ አመራርና ሀይል መኖሩን የሚያበስር ይሆናል።
በሽንጎው እይታ ፣ ከምስረታችን ጊዜ ጀምሮ እንደምንለው ይህ ስብስብ የሀገራችንን ግዛታዊ ሉአላዊነት እና የህዝቧንም መብትና አንድንት ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ኢትዮጵያውያን ህወሀት /አህአዴግን ሲያሰወግዱ የሀገራቸው አንድነትና፣ የወደፊት ህልውናቸው ደግሞ ለሌላ አደጋ የማይዳረግ መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ህወሀት/ኢህአዴግን ለመተካት የሚጥረው ሌላ አግላይ ቡድን፣ ከህወሀት ኢህአዴግ ያውራ ፓርቲ ፍልስፍና ያልተላቀቀ ሀገራችን አሁን የምትገኝበት አደጋ ውስጥ የጣላትን ፖሊሲ ባዲስ መልክ ለመቀጠል የሚፈልግ ስብስብ እንዳልሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ። ይህ ሳይሆን የህዝብን አመኔታና ቆራጥ ተሳትፎ ማግኝት አስቸጋሪ ነው።
በሽንጎው እይታ ይህን ሰፋ ያለ የተቃዋሚወችን ስብሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የሆነ የተቃዋሚወች ጉባኤ መጥራትና ባአሰቸኳይም እንዲካሄድ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
በዚህ አንጻር ሽንጎ የጉዳዩን አንገብጋቢነትና የሁኔታውን አጣዳፊነት በመረዳት ይህ የተቃዋሚወች ሰፊ ትብብር ባጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻወች ገና ከጅምሩ የሂደቱም የውጤቱም ባለቤት እንዲሆኑ ሰፊ ተግባራዊ እንቅስቃሴን እያካሄደ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ባጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንደሚሆን ታላቅ ተስፋ አለን።
የተቃዋሚውን አቅም ግንባታ ማጠናከር
በሀገራችን የስርአት ለውጥን ለማስገኘትም ሆነ በግብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉትን አንዳንድ አደጋወች ለመቀነስ ተቃዋሚው አቅሙን በተለያየ መልክ ለምሳሌም በድርጅት ጥንካሬ ፣ በተለያዩ ቦታወች መዋቅር በመዘርጋት፣ በቅራኔ አፈታት ክህሎት፤ በገንዘብ አቅም፣ በመገናኛ አቅም፣ በአመራር ብቃት በዲፕሎማኪክ ስራ ብቃት ወዘተ ሊያጠናክር ይገባዋል። አንድ ድርጅት ብቃትና ጥንካሬ ከሌለው ከሰርአቱ ጥቃት በደረሰ ቁጥር መፍረክረክ እና ቀጣይነት ማጣት ይከተላል። ይህም ትግሉን በተደጋጋሚ በገዥዎች እንዲኮላሽ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡
ምንም እንኳ እያንዳንዱ የትግል እንቅስቃሴ ለቀጣዩ ትግል ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ቢሆነም ተደጋጋሚ ጥቃት ደግሞ ሊያሰከትል የሚችለውን ስነልቦናዊ ጉዳት በግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያሰፈልጋል።
ሰላማዊ ህዝባዊ ትግልን ማጠናከር
በሽንጎው እይታ ይህ አስከፊ ስርአት በህዝባዊ ሰላማዊ ትግልና የሕዝብ እምቢተኛነትዝብ አ ሊወገድ ይችላል። ይህ እንደሚቻልም በ1997 የታየው የህዝብ መነሳሳት፣ ረዘም ላለ ጊዜ በመቀጠሉ አርአያነት ያለው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሠላማዊ ትግል፣ በተለያየ ወቅት ህዝቡ በተለያዩ ከተሞች በሽወች በመውጣት ለተቃዋሚ ድርጅቶች ያሳየው ድጋፍ አሁን ደግሞ በኦሮሚያ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚታየው የህዝብ አመጽ ያዲስ አባባ ታክሲ ሾፌሮች የስራ ማቆም አድማ አመላካች ናቸው። የተለያዩ አለም አቀፍ ጥናቶች እንደምንገነዘበው ሰላማዊ ትግልና ሕዝባዊ ዐመጽ ዴሚክራሲያዊ ስርአትን ለማዋለድ፣ ጦርነት የሚያሰከትለውን ጥፋት ለመቀነስና ያልተጠበቀ ምስቅልቅልን ለማስወገድ ታላቅ አማራጭ ነው። ሀገራችን ውስጥ የሚታየው በተወሰኑ ሃይሎች የሚቀነቀነው እጅግ ግልጥ የሆነ ኢትዮጵያን የመገነጣጠል አደጋ ደግሞ ሰላማዊ ትግልና የተሳሰረ ሕዝባዊ ዐመጽን ይበልጥ ተመራጭ ያደግረዋል። ሌላው የሰላማዊ ትግልና ሕዝባዊ ዐመጽ ጠቀሜታ ደግሞ ትግላችን ከውጭ ጥገኝነት እንዲላቀቅ የሚያግዝ መሆኑ ነው። ሰላማዊ ትግልና ሕዝባዊ ዐመጽዝብአሕሕ የሚመካው በራሱ በተጨቋኙ ህዝቡ ላይ ነው።
ሁሉም እንደሚገነዘበው፤ ዛሬ የህዝባችን ትግል ከስር ፈንቅሎ በመነሳት ከፍተኛ አልበገሬነትን እያሳየ በመጓዝ ላይ ነው። የህዝብ ትግል ከአምባገነን ስርአትም መወገድም በኋላ ወደ ተደላደለ ዴሞክራሲ ለማምራት የተሻለ እድል የሚኖረው በሰላማዊና በሕዝባዊ ዐመጽ መንገድ የተካሄደ ለውጥ ሲሆን እንደሆነ ብዙ ጥናቶች አሳይተዋል። ከነዚህ ጥናቶችም ወስጥ ከ1990 እስከ 2006 የተካሄዱ 320 ያክል ሳላማዊና የሕዝብ ዐመጽን ያካተቱ ትግሎችን የገመገመ (Why Civil Resistance Works ) በሚል ርእስ በማርያ ስቲፋን እና ኤሪክ ቸንወርዝ (Maria J. Stephan and Erica Chenoweth፤ The Strategic Logic of Nonviolence) የቀረበው ጥናት እንዲሁም በ2005 ለንባብ የበቃው የ35 አመታት የስልጣን ሽግግር ታሪካን የፈተሽው “ነጳነትን እንዴት መጎናጸፍ ተቻለ”፤ ከህዝባዊ እምቢተኛነት ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲ” (How freedom is won ; from civic resistance to Durable Democracy ) የሚለው የፍሪደም ሀውስ ጥናት በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
ብሄራዊ መግባበት እና አርቅ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ መሻት
ለብሄራዊ መግባባት እና እርቅ በዋናነት እንቅፋት የሆነው ህወሀት/ኢህአዴግ ቢሆንም በሽንጎው እይታ ሀገራችን ከምትገኝበት እጅግ ውስብስብ ሁኔታ ወደ ሀገመንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚደረገው ሽግግር ሁሉን አሳታፊ በሆነ ብሄራዊ መግባበት እና አርቅ መሆኑ አማራጭ የሌለው ነው። ይህ ምርጫችን የፖለቲካ አግላይነትን ለማስወገድ፣ ቂም በቀል የተሞላበት ፖለቲካ እንዲወገድ ያጥፊኛ ጠፊ አዙሪትን ለማክተም ሁሉም ባለ ድርሻወች በሀገራችን ችግሮችም መፍትሄወችም ላይ ባለቤትነት እንዲኖራቸው ለማስቻልና ለረዥም ጊዜ ያልተፈቱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ብሶቶችንና፣ ቅሬታወችን በመነጋገር፣ በመግባባትና፣ አንዱ የአንዱን መከፋት፣ ብሶትና ምኞት ወዘተ በማዳመጥ ለመፍታት የተሻለ አማራጭ ሆኖ ሰላገኘነው ነው፡፡
ሽንጎው ፖለቲካኞች ከስልጣን በተወገዱ ቁጥር መጨረሻቸው እስርቤት የሚሆንበት፣ አንድ መንግስት ከስልጣን ሲወርድ የመንግስቱ ደጋፊወች ንብረታቸው ተወርሶ ወደ ድህነት የሚገፉበትን ፣ የፖለቲከኞች ቤተሰቦች መጨረሻቸው ስደት የሚሆንበት የፖለቲካ አዙሪት እንዲቆም ይፈልጋል ይታገላልም።
ማጠቃለያ።
ከ24 አመታት የህወሀት ኢእአዴግ ከፋፋይና አግላይ ስርአት በኋላ እነሆ የስርአቱ መጨረሻ እየተዳረሰ ነው። ይህን የለውጥ ሂደት ለመቀልበስና የሚታየውን ተስፋ ለመዳፈን ገዥው ቡድን አሁንም የመጨረሻ ሙከራ እያደረገ ይገኛል፤፡የስርአቱ እንዳለ መቀጠል ለሀገር አንድነትም ሆነ ለህዝባችን ሰላም እጅግ ሰፊ አደጋን ይጋብዛል። በመሆኑም የስርአቱ መቀየር ለነገ የማይባል ተግባር ነው። አሁን መለወጥ አለበት።
የህዝባችን የለውጥ እንቅስቃሴ በዝቅተኛ የሰው ህይወት መጥፋትና የየንብረት መውደም የሚፈለገውን የስርአት ለውጥ እውን እንዲያደርግ መጭውንም ጊዜ የሰላም የመረጋጋት እና የዴሞክራሲአዊ ስርአት ግንባታ እውና ለመድረግ የሚያሰፈልገው ስራ መሰራት መጀመር ያለበት ካአሁኑ ነው።
ይህን እውን ለመድረግ በኢትዮጰያ ብሄራዊ አንድነት እና የህዝቧም የሉአላዊነት ሙሉ በሙሉ መረጋገጥ አለበት። በሀገራችን ውስጥ የተለያዩ ወገኖቻችን የተለያየ ብሶት አንዳላቸው፣ ግልጽ ነው፤ በወደፊቱ ስርአት ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገራችን ችግሮች በሀገራችን አንድነት ስር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መነጋገር፤ መወያየት፤ መደራደር፤ መሰማማትና ለዚህም መስራት ይኖርብናል።
ከዚህ ውጭ በሰበብ ባስባቡ ሀገራችንን ለመበታተን የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ያለምንም ማወላወል ልንቃወመው ይገባናል። አሁን በህዝባችን ላይ የተጫነው ስርአት ተወግዶ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበረባት፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቋንቋው የተከበረበት፣ ማንነቱ የተከበረበት የህግ የበላይነት የሰፈነበት ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ስርአት መመስረት አጣዳፊ ተግባራችን ነው።
ይህንንም ለማድረግ አግላይ ያልሆነ የተቃዋሚ ሰፊ ግንባር/ትበብብር መመስረት አስፈላጊ ነው።በተበታተነ መልክ የሚካሄደው ትግል ለየብቻ በሚደረግበት ጥቃት ሰለባ ከመሆን አልፎ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብሎ መገመት ያዳግታል። እንዲያውም ባለቤትና አስተባባሪ የለለው በመሆን አንድም እንደ ስልሳ ስድስቱ የሀገራችን አብዮት ህዝብ ፍሬውን ይነጠቃል፣ አለያም ድህረ አረብ ጸደይ በሊቢያየመንና በሌሎቹ እንደሆነው ሁሉ ትርምስ ሀገሪቱን ይወርሳል። ስለዚህም በርግጥም ለሀገራችን ብሩህ ተስፋ ሰንቀው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ይህንን ተገንዝበው መላን የተላበሰ የተባበረ ትግል ማድረግ እጅግ አስፈላጊነው። ለዚህም ተግባራዊነት ሽንጎ ዝግጁ ነው። የተቃዋሚው ክፍል መተባበር፤ ቢያንስ ህወሓት/ኢህአዴግን ለማስገደድ አስፈላጊ መሆኑን እናሳስባለን።
የሀገራችን ችግር እጅግ ውስብስብ ነው፣ መፍትሄውም እንዲሁ ቀላል አይደለም። በሆይ ሆይታና ባሳካሪ ፖለቲካ (intoxiicating politics) አጥጋቢ መፍትሄ ማግኝት እንደማይቻል ያለፈው 25 አመት ታሪክ አሳይቷል። ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደደሴት ለብቻዋ ተነጥላ የምትገኝ አይደለችም፣ በጎረቤቶቻችንም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው ሁኔታ እኛንም ይመለከተናል በበጎም በክፉም እኛንም ይነካናል።
ተቃዋሚው ከአግላይ ፖለቲካና ከየአውራ ፓርቲ አባዜ ራሱን ማላቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው እንላለን ። እነዚህ ሁለት አባዜወች ሀገራችንን ላለፉት 25 አመታት እና ከዚያም በፊት ወደጥፋት አረንቓ የወሰዱ አሁን ለምንገኝበት ምስቅልቅልና ችግር መሰረት የሆኑ መሆኑን ተገንዝበን ይህን ስህተት ላለመድገም መጣር የግድ ነው እንላለን።
በህገራችን ውስጥ የነጻነት ትግሉ በስፉት ቀጥሏል። ወገኖቻችን በተለይም ወጣቶች ለሰብአዊና ዴሞካራሲያዊ መብታቸው መከበር እንደሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ መኖር እንዲያበቃ ለማድረግ ቆርጠው እየታገሉ፣ ውድ ህይወታቸውንም እየገበሩ ነው። ይህን መሰዋእትነት ለውጤት ለማብቃት በጋራ እንነሳ። የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ታላቅነት፣ የዚች ታሪካዊ ሀገርና ህዝቧ ታላቅነት፣ እንዲሁም ብሩህ ቀን ከፊት ለፊታችን ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ