ፓርቲውን በጊዜያዊነት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ይመራዋል

ለወራት የዘለቀው የሰማያዊ ፓርቲ የዲሲፕሊን ኮሚቴና የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ውዝግብ በዲሲፕሊን ኮሚቴው የማባረርና የእግድ እርምጃ መቋጨቱን ከፓርቲው አካባቢ የተሰራጩ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡በሰባት የፓርቲው አባላት የሚመራውን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ወይዘሪት ሐና ዋለልኝ ትመራዋለች፡፡

በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሰረትም የዲሲፕሊን ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ቢሆንም በተቀመጠለት መመሪያ መሰረት ከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለት ታይቶባቸዋል ያላቸውን አባላት ከፓርቲው ማባረርና እግድ መጣል ይችላል፡፡ኮሚቴው ስብሰባውን በማድረግ የቀረበለትን ጉዳይ መመልከት የሚችለውም ከሰባቱ አባላት ቢያንስ አራቱ ሲገኙና የሚሰጡት የውሳኔ ድምጽም እኩል የሚመጣ ከሆነ ሰብሳቢዋ የምትደግፈው ሐሳብ ውሳኔ በመሆን ስራ ላይ ይውላል፡፡

ከዚህ በፊት የፓርቲው የዲሲፕሊን ኮሚቴ በጥር ወር 2008 አራት የምክር ቤት አመራሮችን ማስወገዱን መግለጹን ተከትሎ ከፓርቲው አመራር ጋር መወነጃጀል ውስጥ መግባቱ አይዘነጋም፡፡በወቅቱ የፓርቲው የስነስርዓት ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ፣ አራት የምክር ቤት አባላት “የታሪክና የጎሣ ጥላቻ የሚቀሰቅስ፣ የኢትዮጲያን ህዝብና የተለያዩ የሀገራችንን መንግስታት ታሪኮች የሚያጎደፍ፣…” በአጠቃላይ ከፋፋይነት ያላቸው ፅሁፎችን በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በማሰራጨታቸው፣ በከፍተኛ የሥነ-ስርዓት ጥሰት ክስ እንደተመሰረተባቸውና በዚህም ምክንያት ከፓርቲው መባረራቸውን መጥቀሱ ይታወሳል፡፡

የዲሲፕሊን ኮሚቴው ይህንን ውሳኔ ባሳለፈ ማግስትም ከሊቀመንበሩ ቢሮ የወጣ ሌላ መግለጫ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የወሰደው እርምጃ ህገ ወጥ መሆኑን በመጥቀስ አባላቱ እንደማይባረሩ ማስታወቁም የፓርቲውን የኦዲትና ኢንስፔክሽን መግለጫ እንዲያወጣ አድርጎታል፡፡

ኦዲትና ኢንስፔክሽን ባወጣው መግለጫ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው በመሆኑ የፓርቲው አመራር በራሱ በመነሳት ውሳኔውን መሻሩ አግባብ አይደለም በማለት ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፡፡ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየው የዲሲፕሊን ኮሚቴውና የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ፍጥጫ ለዛሬው ዕለት ይፋ ለተደረገው የእግድና ስንብት ዜና በቅቷል፡፡

የፓርቲው ምንጮች የኢንጂነሩንና የሌሎቹን አመራሮች ስንብትና እግድ ዜና ይፋ ከማድረግ በዘለለ ለምንና በምን አይነት ስምምነት የፓርቲው የስነ ስርዓት ኮሚቴ ውሳኔውን ለማሳለፍ እንደበቃ አልገለጹም፡፡በዛሬው ዕለት የመባረራቸው ዜና ይፋ የተደረገባቸው የሰማያዊ አመራሮችም

-ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት -ሊቀመንበር

-አቶ ወሮታው ዋሴ -የቀድሞው የፋይናንስ ሐላፊ ሲሆኑ ረዘም ላለ ጊዜ እግድ የተጣለባቸው አመራሮች

ወይንሸት ሞላና ስለሺ ፈይሳ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡ሁለቱ አመራሮች ለሁለት አመታት ከማንኛውም የፓርቲው እንቅስቃሴ ተገልለው እንዲቆዩ የወሰነው የዲሲፕሊን ኮሚቴ አንድ የፓርቲው አመራር በጤንነት ችግር ላይ የሚገኝ በመሆኑ የተላለፈበትን ውሳኔ ማዘግየቱም ምንጮች ይጠቅሳሉ፡፡

የፓርቲው አመራሮች በውጪ አገራት ከሚገኙ የፓርቲው ደጋፊዎች ያደረጉት የገንዘብ ድጋፍ፣የአባላት መዋጮ፣በስልጣን ያላግባብ መጠቀም፣የፓርቲውን ገንዘብ ለግል በማዋል፣ቡድን በመስራትና አባላቱን በመከፋፈል በሚሉ የስነ ምግባር ግድፈቶች መከሰሳቸውንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

የተባበረሩት አመራሮች በዲሲፕሊን ኮሚቴው የተላለፈው ውሳኔ ህገ ወጥ መሆኑን ካመኑና ቅሬታ ካላቸውም ለኦዲትና ኢንስፔክሽን ቅሬታቸውን በ90 ቀናት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርባቸው ተወስቷል፡፡የስነ ስርዓት ኮሚቴው በሊቀመንበሩ ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት ካገኘ ኢንጂነሩ መባረራቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡

የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ከዛሬው ውሳኔ ቀደም ብሎም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ በማድረግ በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሰማያዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ጠቅላላ ጉባኤው እስከሚጠራ ድረስም ፓርቲውን የሚመራው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ይሆናል እየተባለም ነው፡፡የኦዲት ሰብሳቢ የሆኑት ደግሞ አቶ አበራ ገብሩ እንደሚባሉ ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን አቶ አበራ የእነ ኢንጂነር ይልቃልን መግለጫ ህገ ወጥ ነው በማለት ከዚህ ቀደም መግለጫ በማውጣታቸው በኢንጂነሩ ቡድኖች ተቀባይነት የላቸውም ተብሏል፡፡

Sorce  www.ethiopiaprosperous.com

Leave a Reply