Wednesday, 30 March 2016 12:06

 

ኢንጅነር ይልቃል- የፓርቲውን ሐብት ለግል ጥቅም በማዋልና 

ሰነድ በማጥፋት ተከሰው ተሰናበቱ

በሳምሶን ደሳለኝ

ሰማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 16 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን ባደረገ ጊዜ የፓርቲውን የሶስት አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን፣ ባሳለፋቸው ሶስት አመታት ያከናወናቸውን ተግባራት አንስቶ ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል። ጉባኤው አስመልክቶ ፓርቲው በሰጠው መግለጫ፣ ፓርቲው ራሱን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ስራ እንደሰራ አውስቶ አደረጃጀቱን በተመለከተ ግን ስፋትና ጥልቀት እንደሌለው መገምገሙን ይፋ አድርጎ ነበር።
ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጥራት ከፍተኛ የሆነ ጭቅጭቅ ማሳለፉን መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ የፓርቲው ፕሬዝደንት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጥራት ፈቃደኛ አይደሉም። ጠቅላላ ጉባኤ ከተጠራ ስልጣናቸው አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል የሚሉ ውዝግቦች ሚዲያዎችን አጨናንቀው መሰንበታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ጠቅላላ ጉባኤው ከተጠራ በኋላ የነበረው እውነታ ግን ሌላ ሆኖ ብቅ አሉ። ይኽውም ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤው ባደረገው ማጠቃለያ ስብሰባ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን ለመገናኛ ብዙሃን አስታወቁ።
በወቅቱ አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ያካሄደው ሰማያዊ ፓርቲ በመጀመሪያ ቀን ውሎው የፓርቲውን የሶስት ዓመት የብሄራዊ ምክር ቤት፣ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እንዲሁም የሂሳብ ሪፖርቶችን አዳምጦ ውይይት ማድረጉ የሚታወቅ ቢሆንም አብዛኛው አባላት ውይይቱን ሾላ በድፍኑ ሲሉ ተደምጠው ነበር። በሊቀመንበር ቦታው ላይ ለውድድር ይቀርባሉ ተብለው በጠቅላላ ጉባኤ ይጠበቁ የነበሩ አባላትም ራሳቸውን ከምርጫ ውድድር ማግለላቸው፣ በጊዜው በፓርቲው ውስጥ የአስተሳሰብ ልዩነቶች መኖራቸውን ጠቋሚ ነበር።
የተፈጠሩት ልዩነቶች ዋል አደር እያሉ መልክ እየያዙ ብቅ ማለት ሲጀምሩ ውዥንብር እየፈጠሩ መጥተዋል። ይህም ሲባል በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ያለው ልዩነት በዲስፕሊን ጥፋቶች ማዕቀፍ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው ወይንስ መሰረታዊ የፖለቲካ ንድፈሃሳብ ልዩነታቸው ናቸው በሚሉ መከራከሪያዎች ዙሪያ ሁሉም ነገር መተንተን በመጀመራቸው ነው። አለፍ ሲልም የሶስተኛ ወገን አራማጅ ሃይሎች ስውር ደባ ነው የሚሉም ወገኖች አሉ። እስካሁን ባለው ሂደት አሸንፎ የወጣ ሃይል ባይኖርም የሃይል ሚዛን መዛባት ግን እየተስተዋለ ነው ያለው።
በተለይ መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. የተሰየመው የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ያስተላለፈው ውሳኔ አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን ፓርቲው ወደ መሰረታዊ የለውጥ ሂደቶች እያኮበኮበ መሆኑን ጠቋሚ ናቸው። በስብሰባው ላይ የተገኙት የፓርቲው የዲስፒሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሃና ዋለልኝ፣ አቶ ሀሰን ዘብር ፀሐፊ፣ አቶ ዮሴፍ (አባል)፣ አቶ ካሳሁን ጥላሁን (አባል) እና አቶ ተክለሚካኤል አብርሃ (አባል) ናቸው።
የስብሰባው አጀንዳና ጭብጥ በጥቅሉ ሲቀመጥ፣ “ተጠርጣሪዎች ታህሳስ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት በቀረበባቸው ክስ መሰረት ሥነሥርዓት ኮሚቴው እሁድ መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጉዳዩ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገው ስብሰባ የተሰበሰቡትን የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 42 ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት የፓርቲያችን ገንዘብና ሃብት በተደጋጋሚ ለራስ ጥቅም ማዋል፣ የፓርቲ ሰነድ ማጥፋት እንዲሁም የፓርቲውን ስልጣን እና ሃላፊነት በመጠቀም በቀጥታና በተዘዋዋሪ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ማግኘት እና በፓርቲ ውስጥ የታየውን ፋይናንስ እና የአሰራር ችግርን …” እና ሌሎች ጉዳዮችን በጥልቀትና በስፋት ከተወያየ በኋላ ውሳኔዎችንም አስተላልፏል።
የሰማያዊ ፓርቲ የሥነ ስርዓት ኮሚቴ የፓርቲውን ሊቀመንበር ጨምሮ በሌሎች አራት የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ያስተላለፈው ውሳኔ ከዚህ በታች እንደሰፈረው ነው። ይኽውም፣ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት እና የብ/ም/ቤ አባል አቶ ወረታው ዋሴን ከፓርቲው ሙሉ ለሙሉ እንዲወገዱ ወስኗል። እንዲሁም ወ/ሮ ወይንሸት ሞላ እና አቶ ስለሺ ፈይሳን ለ2 ዓመታት ከፓርቲው ማንኛውም ዓይነት ሃላፊነት እንዲወገዱ ውሳኔ አስተላልፏል። አቶ ጌትነት ባልቻ ለሶስት ወራት በብ/ም/ቤት ውስጥ ያለምንም ድምፅ እንዲቆይ ተወስኖበታል።
ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሰማያዊ ፓርቲ የሥነ ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን ወ/ሮ ሃና ዋለልኝ አነጋግረናቸው በሰጡን ምላሽ፣ “በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተሰበሰብንበት አጀንዳም ይሁን ያስተላለፍነው ውሳኔ ሂደቱን ሳይጨርስ መግለጫ መስጠት አልችልም። ያስተላለፍነው ውሳኔ ለሚመለከተው የፓርቲው አካል እንዲደርሰው ተደርጓል። ከዚህ ውጪ የምለው ነገር የለም” ብለዋል። “ለአደባባይ በበቃ ጉዳይ ላይ እንዴት ፍሬነገሩን እና ውሳኔው በተመለከተ አስተያየት አይሰጡንም?” ብለን ላቀረብነው ጥያቄ “የፓርቲውን ውሳኔ መጨረሻው ሳይታወቅ ለአደባባይ ያበቃው ሰው በመተዳደሪያችን መሰረት አለምንም ቅድመ ሁኔታ መባረሩ አይቀርም። መታወቅ ያለበት ግን ሌላው ከሕግ ውጪ ስለተንቀሳቀሰ እኔም ይህን መንገድ መከተል ያለብኝ አይመስለኝም” ሲሉ ወ/ሮ ሃና መረጃ ከመስጠት መቆጠብን መርጠዋል።

“ሆኖም ግን ውሳኔ የተላለፈባቸው አካሎች በአስራ አምስት ቀኖች ውስጥ ውሳኔውን አስመልክተው ይግባኝ የማቅረብ መብታቸው የተጠበቀ ነው። ይህን መብታቸውን መጠቀም ካልቻሉ ግን ውሳኔው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፀና ይሆናል” ብለዋል።
ከውሳኔው ጋር በተያያዘ ምክርቤቱን በመወከል ክስ የመሰረቱት የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ውሳኔውን ተከትሎ በተፈጠሩት ልዩነቶች ላይ ባስነበቡት ጽሁፋቸው ሲያብራሩ፣ “ግልፅነትና ተጠያቂነት በፓርቲ ውስጥ መኖሩ ሊደገፍና ሊበተረታታ የሚገባው ተግባር ነው። የዛሬውን ብቻም ሳይሆን ነገ መፍጠር የምንፈለገውን ለማየት የምንሻ ከሆነ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለተቃውሞ ጎራው የህልውናም ጉዳይ ነው! ስለሆነም ሰማያዊ ፓረቲ እንደ አንድ አማርጭ ሃይል ሆኖ እንዲወጣ የምንፈልግ ከሆነ ለግለሰቦች ከማልቀስ በዘለለ ፖለቲካው እንዲዘምን ተነሳሽነት ማሳየት አለብን። አሁን ከተከሳሽ ወገን ሆነን ከሳሽ ላይ አሮጌውን ፖለቲካ ማካሄድ ትንሽም ቢሆን የተካበውን ከማፍረስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ግለሰቦቹንም አይጠቅምም፣ ፓርቲውንና ትግሉንም አይጠቅምም።” ብለዋል።
መለስ ብለው ወደኋላ በመሄድ፣ “‹በፓርቲ ውስጥ ያሉ የትኞቹም ክፍሎች ደካሞች ቢሆኑ ለፓርቲው ምን ይጠቅማሉ? ጥርስ የሌለው ብሄራዊ ምክር ቤት፣ጥርስ የሌለው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ምን ይስራል? ስለዚህም ለእነዚህ አካላት ስልጣን ሰጥቶ ለምን ጠየቁ፣ለምን ከሰሱ፣ ለምን ውሳኔ አሳለፉ ብሉ ማልቀስ አሮጌውን መንገድ በአዲስ ቅላጼ” እንዳይሆን ያላቸውን ስጋታ አቶ ይድነቃቸው ይፋ አድርገዋል።
አያይዘውም፣ “ሰርጎ ገቦች ምናምን ከሚል አሮጌ ፖለቲካ በዘለለ ለምን ነገሮችን አንዳንዴም መልካም ጎናቸውንም ለማየት እንደሚከብደን አይገባኝም። ሌላው ሁሉ ቀርቶ የስነ ስርዓት ኮሚቴው የፓርቲውን የበላይ አካላት ጭምር የመጠየቅ አቅም መፍጠሩ ለምን አያስመሰግነውም? ሌላው ነጥብ ኢ/ር ይልቃልን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰቦች ከፋፋዩን ስርዓት ለመታገል ወስነው በሂደቱም መስዋዕትነት መክፈላቸውን እንዲሁም በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚመጣውን ለመቀበል የማያመነቱ ብርቱዎች መሆናቸውን የምንክደው አይደለም። አይበገሬዋ እንስት ወይኗ ደጋግማ ወደ ገዢዎች ማጎሪያ ብትወረወርም ደጋግማ ጥንካሬዋን ያሳየች የዘመናችን ፈርጥ ነች። ይህን እንርሳው ብንለው የሚረሳ አይሆንም። እነኚህ ጠያቂ የለውጥ ሃይሎችን ለምን ይጠየቃሉ ማለት ግን “double standard” አይነት ይሆናል። ጠያቂ መሆናቸው ተጠያቂ የማይሆኑበትን ሁኔታ ሊፈጥር አይገባም። መጠየቃቸው በምንም መንገድ እንደነውር መታየትም የለበትም። ሊያስጨንቀን የሚገባው የግለሰቦቹ መጠየቅ ሳይሆን ከፍረጃና ከስሜት በመሻገር ነገን መፍጠር ለምንፈልገው ስርዓት መሰረቱን እያስቀመጥን ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው” ሲሉ አቶ ይድነቃቸው ግልፅ መከራከሪያ አስቀምጠዋል።
አያይዘውም የይግባኝ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑ የገለጹት ሰብሳቢ፣ “ከዚህ በፊት ግን ፍረጃ ከቀደመ ሰልጡኑን ቁጭ ብሎ የመነጋገር እድልን በመዝጋት ለከፋፋዮቹ ሴራ የመጋለጥ አደጋ ያስከትላል። ስለሆነም በዚህ ሂደት ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦች ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል። ከጠቅላላ ጉባኤውና ከብሔራዊ ምክር ቤቱ ቀጥሎ ከፍተኛ ስልጣን ያለው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽንም የተጣለበትን ከፍተኛ ሃላፊነት በተሻለ እንዲወጣ እያንዳንዱ የፓርቲ አባል ከጎኑ በመቆም የተቃውሞውን ጎራ አድሮ ቃሪያ ከመሆን ሊታደጉት ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
እንደሚታወቀው እሁድ የካቲት 06 ቀን 2008 ዓ.ም. በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አቅቷቸው በፓርቲው ጽ/ቤት የፖለቲካ ሪሲሊንግ አመራሮቹ መፈጸማቸው ብዙዎችን ማሳዘኑ የሚታወስ ነው። ለመደባደብ ያበቃቸው የፓርቲው የብሄራዊ ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ አራት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ‹‹የፓርቲውን ዓላማ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲ ጥሰዋል…›› በሚል ህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም በብሄራዊ ምክር ቤቱ የቀረበለትን ክስ [ከሳሽ ብሄራዊ ምክር ቤቱ እንደሆነ የም/ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ አረጋግጠዋል] መርምሮ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም አራቱም ከፓርቲው መባረራቸውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው። ይህን ውሳኔ ለመቃወም ሥራ አስፈፃሚውን የቀደመው አልነበረም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ወ/ሮ ሃና እንደገለጹልን ከዚህ በፊት በአራት የፓርቲው አመራሮችና የምክር ቤት አባላት ላይ የተላለፈውን የዲስፕሊን እርምጃ በመቃወም ይግባኝ የጠየቀ አካል የለም። ስለዚህም የተላለፈው ውሳኔ ጸንቷል ብለዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply