Wednesday, 30 March 2016 11:56
“በዚህ መንግስት የስልጣን ዘመን ‘አማራ ሆኖ መወለድ’ ወንጀል ነው”
አቶ ዘመነ ምህረት
በይርጋ አበበ
የታሪክ መምህር የነበሩትና ለአንድ ዓመት ከሁለት ወራት በፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ለእስር ተዳርገው ቆይተው በቅርቡ በዋስ የተለቀቁት አቶ ዘመነ ምህረት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አባልና የስራ ኃላፊ ናቸው። አቶ ዘመነ ምህረት ከጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ለእስር የተዳረጉት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ቢሆንም ከአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ምርመራ በኋላ ግን በዋስ ተለቀዋል። ለመታሰሬ የፓርቲዬ (መኢአድ አባላትና አመራሮች) እጃቸው አሉበት የሚሉት አቶ ዘመነ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
ሰንደቅ፡- ከፓርቲዎ ጋር ከመቼ ጀምሮ ነው አብረው መስራት የጀመሩት? የኃላፊነተዎ ድርሻስ ምንድን ነው?
አቶ ዘመነ፡-ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢኣድ) አባል መሆን የጀመርኩ ሲሆን ከዚያ ጊዜ በኋላ ያሉትን ጊዜያት ደግሞ በተለያዩ የርከን ተዋረዶች በአባልነት በኃላፊነትና በአመራርነት ስሰራ ቆይቻለሁ። ለአብነት ያህልም በወረዳ ደረጃ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በዞን ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆኜ ሰርቻለሁ።
በ2005 ዓ.ም በተካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ ስሆን በ2007 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው የመኢአድ ጉባኤ ላይ የሰሜን ቀጠና አስተባባሪ ሆኜ ተመርጫለሁ። ከዚያ ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም በሽብር ተግባር ተጠርጥሬ ለእስር ተዳርጌ ቆይቻለሁ።
ሰንደቅ፡-የታሰሩበትን ምክንያት ዘርዘር አድርገው ቢገልጹልን?
አቶ ዘመነ፡- እኔን ለእስር የዳረገኝ ትልቁ ምክንያት በፓርቲያችን ውስጥ (መኢአድ) የገዥው ፓርቲ ቅጥረኞች ሰርገው በመግባታቸው ነው። እነዚህ ቅጥረኛ ሰላዮች በ2005 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው የፓርቲያችን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እነ አቶ አበባው መሃሪ የፓርቲው ኃላፊዎች ሆነው ሲመረጡ በተፈጠረው ግርግር እነ አቶ አበባውን የማይደግፈውን እየመለመሉ ከፓርቲው ማስወገድና የሀሰት ክስ እየመሰረቱ መክሰስ ጀመሩ። እኔም የዚያ ሰለባ ሆኜ ነው የታሰርኩት።
ይህ ሴራ ደግሞ አዲስ አይደለም። ከቅርብ ጊዜው እንኳ ብንመለከት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የፓርቲው ጠንካራ አመራሮች እየተመነጠሩ ታስረዋል። እኛም መኢአድ በ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎችን እየሰራንና አባላትንና ደጋፊዎችንም እያፈራን በነበረበት ሰዓት የፓርቲው ሊቀመንበር (አቶ አበባው መሃሪን) ሆን ብለው እንቅፋት እየፈጠሩ ስራችንን ማስተጓጎል ጀመሩ። ከዚህ በተጨማሪም አቶ አበባው ለመኢአድ ከሚቆረቆሩ ጠንካራ አመራሮች ጋር መስማማት ስላልቻሉ ከፓርቲው ማባረር ጀመሩ። ይህ ደግሞ አብሮ እንዳንሰራ እያደረገን መጣ። በዚህም ምክንያት ጥር 11 ቀን የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ለማክበር በተዘጋጀሁበት ሰዓት “ጥምቀቱ ላይ ቦምብ ሊጥል ሲዘጋጅ ይዘነዋል” በሚል ክስ ተመስርቶብኝ ወደ ማዕከላዊ መጣሁ።
ሰንደቅ፡-አሁን እየነገሩን ያለው “ለመታሰሬ ምክንያቱ የመኢአድ አመራሮች ናቸው” እያሉን ነው። ይህንን ሀሳበዎን በማስረጃ ቢያቀርቡልን?
አቶ ዘመነ፡-እንዴት መሰለህ በመጀመሪያ የአንድነት እና የመኢአድ አመራሮች በአንድ ላይ ለመስራት በሚያደርጉት ጥረት ሲፈርስ በነበረው አለመግባባት አበባው መሃሪ ውህደቱ እንዳይሳካ ምክንያት ሲፈጥሩ ነበር። በዚህ ጊዜ “ለምንድን ነው ውህደቱ እንዳይሳካ ያደረከው?” ብለን መጠየቄ የመንግስት ደህንነቶች እየደወሉ ያስፈራሩኝ ነበር። ከአቶ አበባው ጋር ተስማምተህ የማትሰራ ከሆነ እናስርሃለን እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር።
ሌላው ደግሞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሆንኩበት በኋላ በማዕከላዊ እስር ቤት የቀረቡልኝ ሁለት አማራጮች ብቻ ነበሩ። የመጀመሪያው ከእነ አቶ አበባው መሀሪ ጋር ተስማምቶ ምርጫ ቦርድ የወሰነውን ውሳኔ ተቀብሎ ለመስራት በመስማማት ከእስር ቤት መውጣት የሚል አንድ አማራጭ ቀርቦልኝ ነበር። ሌላው አማራጭ የቀረበልኝ ደግሞ ጎንደር ላይ ቦንብ ሊያፈነዳ ሲል ተይዟል የሚል ክስ ቀርቦብሃል በዚህ ክስ መሰረት ወደ እስር ትወሰዳለህ። እስር ደግሞ እንኳንስ አንተን አስራትንም እንኳ (ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን) አስረናል የሚል ዛቻ ያዘለ አማራጭ ነበር የቀረበልኝ።
ጥር 18 ምርጫ ቦርድ ለእነ አበባው መሃሪ እውቅና ሰጥቶ እኔን ጥር 28 ቀን ማዕከላዊ ላይ እንደዛ ተብዬ ስጠየቅ የሚያመላክተው እነዚህ ሰዎች ከማን ጋር ሲሰሩ እንደነበረ እና እኔንም ሆን ብለው የሀሰት ክስ መስርተው እንድታሰር ለማድረግ ማሰሴራቸውን ነው።
ሰንደቅ፡-ለአንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ በማዕከላዊ ከቆዩ በኋላ በቅርቡ ነው ከእስር በዋስ የተለቀቁት። በሽብር የተጠረጠረ ሰው በዋስ አይለቀቅምና እርሰዎ እንዴት በዋስ ሊለቀቁ ቻሉ?
አቶ ዘመነ፡-እንደነገርኩህ በመጀመሪያ ቀርቦብኝ የነበረው ክስ የሽብር ተግባር ለመፈጸም መንቀሳቀስ የሚል ነበር። ጎንደር ላይ ቦምብ ለማፈንዳት መሞከር ከግንቦት ሰባት ጋር በመሆን በመንግስት እና በህዝብ ላይ የሽብር ተግባር ለመፈጸም መንቀሳቀስ የሚል ነበር። ሆኖም በምርመራ ወቅት እኔ ከግንቦት ሰባት ጋርም ሆነ ከኤርትራ መንግስት ጋር አብሬ መስራቴንም ሆነ ለመስራት መንቀሳቀሴን በተግባር የሚያረጋግጥ ማስረጃ አቃቢ ህግ ማቅረብ ስላልቻለ ፍርድ ቤቱ ክሱን ወደ ወንጄል ቀይሮታል።
ክሱ ከሽብር ወደ ወንጄል የተቀየረው “መንግስትን በሀይል ለመገልበጥ መንቀሳቀስ” በሚል ነው። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አባላትን በማደራጀት መንግስትን በሀይል ለመገልበጥ ተንቀሳቅሷል አስተባብሯል የሚል ነው። ለዚህ ነው የፍርድ ሂደቴን በውጭ ሆኜ እንድከታተል የዋስትና መብት የተሰጠኝ።
ሰንደቅ፡-ክሱ ከከሽብርተኝነት ወደ ወንጀል ተቀይሮ በዋስ እንዲለቀቁ ተደርገዋል። ለዋስትና ያቀረቡት ምንድን ነው?
አቶ ዘመነ፡- እንደነገርኩህ ክሱ ከተቀየረ በኋላ የዋስትና መብት ሲሰጠኝ በአስር ሺህ ብር ዋስ ነው የወጣሁት። ከአንድ ዓመት በላይ በምርመራ ሲመረምሩኝ ከቆዩ በኋላ በነጻ ለማሰናበት ዳኞቹ ጫና ያረፈባቸው ይመስላል እንጂ በነጻ ሊለቁኝ ይገባ ነበር።
ሰንደቅ፡-ከእስር ከተፈቱ በኋላ በምን ስራ ላይ ነው ያሉት?
አቶ ዘመነ፡-ለ14 ዓመት በታሪክ አስተማሪነት እና በተለያዩ የመንግሥት ሥራ ላይ ያገለገልኩ ብሆንም፤ ከእስር ከወጣሁ በኋላ ግን ወደ ስራዬ ሊመልሱኝ አልቻሉም። አሁን አንተ እያነጋገርከኝ ባለበት ሰዓት እንኳ ጉዳዬን እንዲመለከቱልኝ ለሚመለከታቸው የመንግስት ቢሮዎች ቀርቤ እያመለከትኩ ቢሆንም ሊሰሙኝም ሆነ ሊያነጋግሩኝ አልፈቀዱም። ደመወዜም እስካሁን አልተከፈለኝም።
ሰንደቅ፡- አሁን እየነገሩን ያለው በፍርድ ቤት የቀረበበዎት የሰነድም ሆነ የቃል ማስረጃ እንዳልተገኘበዎት ነው። ያለ ምንም ማስረጃ ይህን ያህል ጊዜ እንዴት በእስር ቤት ሊቆዩ ይችላሉ?
አቶ ዘመነ፡-ማዕከላዊ በነበርኩበት ጊዜ በተደጋጋሚ የምጠየቀው “የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን አወቃቀር ንገረን እና አማራ ክልል የሚገኙ መምህራንን ስታደራጅ ነበር ይህንን እመን” የሚሉ ሁለት ውንጀላዎችን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን የግንቦት ሰባት አባል ነህ ብሎ የጠየቀኝም ሆነ የመረመረኝ አካል የለም።
አቃቢ ህግ ያቀረበብህ የሰነድም ሆነ የድምጽ ማስረጃ የለም ወይ ላልከኝ አቃቢ ህግ ያቀረበው የድምጽ ማስረጃ ከመኢኣድ አባላት ጋር ያደረኩትን የስልክ ውይይት ነው። በስልክ ያደረኩት ውይይት “አይዟችሁ በርቱ ድሉ የእኛ ነው፤ ቢመቱንም ቢገድሉንም ትግሉን ከዳር ማድረስ አለብን ወደኋላ እንዳትሉ” የሚል እና “የመኢአድ አባላት እየታሰሩ እየተደበደቡ እና እየተገደሉ ነው። ስርዓቱ ጨቋኝ ነው” ብዬ ከኢሳት ሬዲዮ ጋር ያደረኩትን የስልክ ቃለ ምልልስ ነው። ይህንም ሆነ የመጀመሪያውን የአቃቢ ህግ ማስረጃ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
ሰንደቅ፡-ቀደም ሲል ለመታሰሬ በፓርቲያችን ውስጥ የገዥው ፓርቲ ቅጥረኛ ሰላዮች ያደረጉብኝ የሀሰት ውንጀላ ነው ሲሉ ነግረውን ነበር። በፍርድ ቤትም ምስክር ሆኖ የቀረበ የደህንነት አባል እንደነበረ ይነገራል። ይህን በተመለከተ እስቲ በግልጽ ይንገሩን?
አቶ ዘመነ፡-የቀረበብኝ ምስክር ለሶስት ዓመታት በመኢአድ ውስጥ ገብቶ የፓርቲውን ገበና ሲመረምር የቆየ መሆኑን በአራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ተናግሯል። ያንተን ጉዳይ (የአቶ ዘመነን) እንድከታተል የተመደብኩ ሰው ነኝ ብሎ ነው የተናገረው።
ሰንደቅ፡-በእስር ቤት በቆዩበት ጊዜ በእርሰዎ ላይ የደረሰበዎት የአካልም ሆነ የስነ ልቦና ጥቃት ነበረ? የእስረኞችን አያያዝስ እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ዘመነ፡-ከሌሎች የተለየ ጫና እና በደል አልደረሰብኝም። ነገር ግን በማዕከላዊ ያለው ጥቃት ግለሰብን ለይቶ የሚደረግ ሳይሆን ዘርን (ብሔርን) መሰረት አድርጎ የሚደረግ መሆኑን አይቻለሁ። ከአማራ ክልል፣ ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ የመጡ ተጠርጣሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ይፈጸማል። በተለይ በአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃቱ ያየለ ነው። ይህን ሁሉ ሳይ ለእኔ ከእስር ቤት ይዤ የወጣሁት “በዚህ መንግስት የስልጣን ዘመን አማራ ሆኖ መወለድ ወንጄል መሆኑን ነው”። ምክንያቱም በተደጋጋሚ ጊዜ የሚደረግብን ምርመራ “የአማራን የበላይነት ለመመለስ የምትሞክሩ” ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል። ይህ አጠያያቃቸውን ስታየው “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጎደለው” ነው፤ የሚፈጽሙት ጥቃት ሰውነታችንን አውልቀው የሚገርፉ እና የፍትህ ስርዓቱ የተበላሸ ነው። በአጠቃላይ የእሰረኞችን አያያዝ በተመለከተ የምነግርህ እውነታ “ፋሽስት እንኳ ያላደረገውን ቶርቸር” የሚፈጽሙ መሆናቸውን ነው።
ሰንደቅ፡-ከእስር ከተፈቱ በኋላ የሚኖረዎ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ሊሆን ይችላል? ከቀድሞ ፓርቲዎ (መኢአድ) ጋር ይቀጥላሉ ወይስ ሌላ አማራጭ ይፈልጋሉ?
አቶ ዘመነ፡- እውነት ለመናገር አሁን ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጨለማ ሆኖ ነው የሚታየኝ። የፖለቲካ እንቅስቃሴው በጨለማ የተከበበ ቢሆንም ጨለማውን ለማብራት የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ እንንቀሳቀሳለን። በአሁኑ ሰዓት በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመኢአድ አባላት በተለይም በክልል ያሉ የፓርቲው አባላት በእስር ላይ ይገኛሉ እነሱን ለማስፈታት እንታገላለን።
በግልህ ያለህ አቋም ምን ሊሆን ይችላል ላልከኝ በግሌ ከትግሉ የምሸሽ አይደለሁም። ምክንያቱም መኢአድ ማለት የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ህይዎት የተከፈለበት የህዝብ ፓርቲ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ አሁን በፓርቲያችን ያለው ሁኔታ ግን የክልል መዋቅር እና የማዕከላዊ ጽ/ቤት መዋቅር የተገናኘ ሳይሆን የተለያየ ሆኗል። ይህንን ለማስተካከል ከጓደኞቼ ጋር በመሆን እንሰራለን። ምክንያቱም በአሁነኑ ሰዓት አባላትና ደጋፊዎች ከእኛ ጋር ናቸው እነሱን ይዘን መኢአድን ወደ ነበረበት እንመልሰዋለን።n