Wednesday, 30 March 2016 12:01
- በ ፍሬው አበበ
- ጥቂት ነጥቦች ስለ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ወጥነት ያለው፣ ውጤታማና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥ፣ የህዝብንና የመንግሥትን ጥቅም በተሟላ ሁኔታ የሚያስጠብቅ አንድ ጠንካራ ሕግ አስከባሪ ጠቅላይ የአቃቤ ሕግ ተቋም ለማቋቋም የሚያችለውን ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሳምንት ተወያይቶበት ለሚመለከተው ቋሚ ኮምቴ መርቶታል። ይህ ረቂቅ አዋጅ ቀደም ሲል በሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በንግድ ውድድርና ሸማቶች ጥበቃ ባለስልጣን የነበሩትን የአቃቤ ሕግ ሥራዎች በመውሰድ በአንድ የሚያጠቃልል ነው። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሰረት የወንጀል ጉዳይ በተጨማሪ በፍትሐብሔር ጉዳይም መንግስትን ወክሎ የመከራከር ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ከላይ የተዘረዘሩት ተቋማት ራሳቸው ከሳሽ፣ ራሳቸው መርማሪ እና ፈራጅ የሆኑበትን አሰራር ከመሰረቱ ይንደዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይ ከሕዝብ በሚመጡ ጥቆማዎች ላይ መደራደር መሰረታዊ ይዘታቸውን መቀየር እንዲሁም በምርመራ በተገኙ ሰነዶች ላይ ድርድር በመፈጸም ራሳቸውን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት ሥርዓትን ይቀጨዋል ተብሎ በስፋት ታምኖበታል፡፡ የሥርዓቱ ትልልቅ ሌቦች ያገኙት የነበረውን ሕገወጥ ከለላ ከመግፈፉም በላይ ሁሉም ዜጎች እኩል ዳኝነት የሚያገኙበትን አሰራር ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ረቂቅ ሕጉ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ጡንቻ ሰጥቶታል። ፖሊስ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የመጨረሻ ውሳኔ የማክበር ግዴታ ተጥሎበታል። የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮምሽንም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንዲሆን ተደንግጓል። ይህ በተለይ በማረሚያ ቤቶች ላይ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቅሬታዎችን በወቅቱ ለማረም ዕድል እንደሚሰጥ ይገመታል። የአዋጁ አንኳር ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
*** *** ***
የሕግ ማስከበር ተግባር በዐቃቤ ሕግ ተቋም የሚከናወን ሲሆን፤ ይህ የዐቃቤ ሕግነት ስራ በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ መሰራቱ፣ የሕግ ማስከበር ስራውን ውጤታማና ቀልጣፋ እንዳይሆን ያደረገው በመሆኑ ሕግን በማስፈፀም ረገድ ሕገ መንግስቱ የሚጠይቀውን የህዝብና የመንግስት ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ካለመቻሉም በላይ፣ ተቋማቱ በራሳቸው የተለያ ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። በዚሁ መሰረት እነዚህን ተቋማት የተበተነውን ስራ በመሰብሰብ አንድ ጠንካራ እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ተግባር መፈፀም የሚችል ተቋም መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን መንግስት ስላመነበት
አስፈላጊው የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
ሕጎች በተጣጣመና ወጥነት ባለው መልኩ መዘርጋታቸውን በማዕከል ደረጃ የሚረጋገጥበት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። በዚህም መሰረት አፈፃፀሙን የሚከታተል የፌዴራል ተቋም ማደራጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በሕግ የበላይነት መከበሩን እና ዘለቄታዊነቱን የሚያረጋግጥ እንዲሁም በሚዘረጉት ሕጎች መሰረት የመንግስት ስራዎች በአግባቡ መከናወንና መመራታቸውን የሚያረጋግጥ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚሰራ ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ነው።
በተጨማሪም የሚቋቋመው ተቋም የሕግ ማስከበሩ ስራ በሙሉ ሙያዊ ነፃነት እንዲሁም በተቋማዊና ሙያዊ ተጠያቂነት የሚሰራ ሆኖ ማደራጀት ያስፈልጋል። ይህን ሁኔታ የሚፈጥር የሕግ መዋቅር መፍጠር በማስፈለጉ ይህ አዋጅ ሊዘጋጅ ችሏል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ በአራት ዋና ዋና ክፍሎችና በ28 አንቀጾች ተዋቅሮ የተረቀቀ ሲሆን፤ እነዚህ አራት ክፈሎች በቅደም ተከተላቸው ጥቅላላ ድንጋጌዎች፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር፣ ነፃነትና ተጠያቂነት እና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች፣ የሚሉ ናቸው። በጠቅላላ ድንጋጌዎች ስር የአዋጁ አጭር ርዕስ እና በረቂቅ ሕጉ ውስጥ ተርጉም የሚያሰፍልጋቸውን ቃላት ትርጉም የተሰጠበት ክፍል ነው። በክፍል ሁለት አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባርን በተመለከተ፣ ስለ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መቋቋም፣ ዋና መስሪያ ቤት የት እንደሚሆን፣ ስለተቋሙ ዓላማዎች፣ ስለሚኖረው ስልጣንና ተግባራት፣ ስለ ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቋም፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የምክትል ጠቅላይ ዐቃብያነ ሕግ ስልጣንና ተግባር፣ ስለ ስራ ዘመናቸው፣ ዐቃቤያነ ሕግ ስለሚተዳደሩበት ሁኔታ፣ ስለ ፌዴራል ዐቃብያነ ሕግ አስተደደር ጉባኤ እንዲሁም ስለ ጠቅላይ ዐቃቤያነ ሕግ ምክር ቤትና የህዝብ ተጠያቂነትን በተመለከተ የተደነገገበት ክፍል ሲሆን፤ የተቋሙን በጀት በተመለከተ እና የስራ እንቅስቃሴና የሂሳብ መዛግብት ቁጥጥርን አስመልክቶ በዚህ ክፍል ተደንግጓል።
ክፍል ሦስት ነፃነትና ተጠያቂነትን በተመለከተ የተደነገገበት ክፍል ሲሆን፤ ስለ ዐቃቢያነ ሕግ የሙያ ነፃነት፣ ተጠሪነትና ተጠያቂነት በተመለከተ እንዲሁም የይግባኝ አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ ጥቆማና አስተያየት የማቅረብ መብትን አስመልክቶ በዚሁ ክፍል ተመልክቷል። ክፍል አራት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ስለ ደንብና መመሪያ የማውጣት ስልጣን፣ መብትና ግዴታን ስለማስተላለፍ፣ የመተባበር ግዴታ፣ የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች፣ የተሻሩና ተፈፃሚነት የማይኖራቸው ሕጎችን በተመለከተ እና አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ በተመለከተ ተካቷል።
የረቂቅ አዋጁ አላማና አስፈላጊነት
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴራል ስርዓት ተደራጅቷል። ይህ ሰርዓት በሕግ መሰረት መዋቀርና በሕግ የበላይነት የሚመራ መሆን ይኖርበታል። ይህን የሕግ ስርዓት በሕገ መንግስቱ መሰረት በተሟላ መልኩ መዘርጋቱንና በሕግ የበላይነት መፈፀሙን የሚከታተልና የሚያረጋግጥ ተቋም ማደራጀት ያስፈልጋል። ከዚህ ከቀደም በነበረው ሁኔታ የዐቃቤ ሕግ ተግባር በተለያዩ ተቋማት ሲከናወን የነበረ በመሆኑ ይህም በስርዓት ሳይደራጅ ወጥነት በሌለው መልኩ ሲፈፀም ቆይቷል። በዚህ ረቂቅ አዋጅ ግን በአንድ ማዕከል በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር በአንድ ስርዓት ረቂቅ ሕጎች ከሕገመንግስቱ እና ከሌሎች ሕጎች ጋር የተጣጣሙ መሆኑን በወጥነት ለማረጋገጥ የሚቻልበት ስርዓት ተዘርግቷል። በዚህም ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን የሚያገለግል እና ዘለቄታዊነቱን የሚያረጋግጥ የሕግ ስርዓት ይኖራል ተብሎ ይታመናል።
በሕግ ሰርዓቱ የሚዘረዘሩ ተግባራት በአግባሙ መፈፀማቸውን በባለቤትነት የሚከታተል ተቋም ማደራጀት ያስፈልጋል። ከላይ በተመለከተው መሰረት የሚወጡ ሕጎች በሙሉ የአስፈፃሚ አካላቱን ስራ ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል። አስፈፃሚ አካላትም የመንግስትን ስራዎች ሲያከናውኑ በሕግ መሰረት መመራታቸውን የሚያረጋግጥ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም በረቂቅ አዋጁ ተደራጅቷል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የመንግስት አካላት ተግባራትን ከሕገመንግስቱ እና ከሕግ አንፃር በአግባቡ መፈፀሙን ይከታተላል። መፈፀም ያለባቸው ነገር ግን ያልተፈፀሙ ተግባራት ሲኖሩም መፈፀም የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም በሕግ አፈፃፀም ወቅት የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ሲያገኝ እንዲታረሙ በማድረግ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የፀና የመልካም አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል። ከዚህ አልፎ የሕግ ጥሰቶች ሲኖሩም በረቂቅ አዋጁ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል።
በአጠቃላይ ሕጎች በሕገ መንግስቱ መሰረት እና ከሌሎች ሕጎች ጋር ተጣጥመው እና ተሟልተው መውጣታቸው የሚያረጋግጥ፣ የወጣው ሕግም በአግባቡ መተግበሩን በባለቤትነት የሚከታተል፣ ጉድለቶች ሲገኙም እንዲታረሙ ማድረግ የሚያስችል እና የሕግ ጥሰቶች ሲኖሩም የሕግ እርምጃ መውሰድ የሚችል ተቋም ማደራጀት በማስፈለጉ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም በረቂቅ አዋጁ ተደራጅቷል።
በሌላ በኩል የኅብረሰቡን ሰላም፣ ደህንነት እና መብት ለማስጠበቅ፣ ወንጀልን መከላከልና ተፈፅሞ ሲገኝም የመመርመርና የመክሰስ ኃላፊነት የመንግስት ነው። እስካሁን ባለው አፈፃፀም ይህ ተግባር በተለያዩ የፌዴራል ተቋማት /ፍትህ ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሸማቾች ዐቃቤ ሕግ እና በክልሎች/ ሲከናወን ቆይቷል። ይህ አፈፃፀም ወጥነት በሌለው እና የሀዝብን ጥቅም በአግባቡ ሳያስከብር መቆየቱን ከተደረጉ ጥናቶች መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ይህን ተግባር በአንድ ተቋም በማሰባሰብ በወጥነትና የህዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ መፈፀም እንዲያስችል የመመርመር ስራ ወደ ፌዴራል ፖሊስ እንዲሰባሰብ ማድረግና የመክሰስ ስልጣን የሚኖረው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም ማደራጀት አስፈልጓል። በዚህም በተለያዩ ተቀማት ተበታትኖ ሲከናወን የቆየው የሕግ ማስከበር ተግባር ውጤታማና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም የህዝብንና የመንግስትን ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ የሚችል አንድ ጠንካራ ተቋም ማደራጀት አስፈልጓል።
የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ እና የሕግ ማስከበር ስራ መሉ ሙያዊ እና ተቋማዊ ነፃነትን ይጠይቃል። በዚህም ውሳኔ ሰጪ አካላት /የሕግ አስከባሪ አካላት/ ስራቸውን በሕግ አግባብና በሙያቸው መሰረት ሲፈፅሙ ከማናቸውም ወገን ከሚመጣ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጓዳኝም ይህ ትልቅ የህዝብ አመኔታና ኃላፊነት በአግባቡ መፈፀሙን በውስጣዊና ውጫዊ የተጠያቂነት ሥርዓት ለማረጋገጥ ተቋማዊ፣ ሙያዊ እና ህዝባዊ የተጠያቂነት ሥርዓት በአግባቡ መዘርጋት ያስፈልጋል። ረቂቅ አዋጁ ይህን ለማድረግ የተለያዩ ሥርዓቶችን ዘርግቷል።
ይህን አዋጅ ለማዘጋጀት ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ እና ሀገራችንን መሰል ፌዴራል ስርዓት ካለቸው ሀገራት ልምድና ተሞክሮ ለማየት ተሞክሯል። በዚህም መሰረት ከአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ተወስዷል። በእነዚህ ሀገራት የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር፣ የሕግ ስርዓቱን የሚያስጠብቅ፣ የወንጀል ሕግ የሚያስከብር፣ የመንግስትንና የህዝብን የፍትሐብሔር ጥቅምን የሚስጠብቅ አንድ ጠንካራ ተቋም አደራጅተው ስራዎችን ይመራሉ። በእነዚህ ሀገራት የተደራጀው ተቋም ኃላፊነቱን በሚወጣበት ወቅት በተለይም የየትኛውም አካል ጥቅም አስፈፃሚ እንዳይሆን የሚያደርጉ ተገቢ ስርዓቶች ተደራጅተው የመንግስትንና የህዝብን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅበት በተለይም ለፖለቲካል ስርዓቱ አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ወንጀሎችን ያለማንም ውጫዊና ውስጣዊ ተፅዕኖ በባለቤትነት የሚከላከልበትና የሚቆጣጠርበት አቅምና ነፃነት እንዲኖረው ሆኖ ተደራጅቷል።