ዳዊት ሰለሞን

Wednesday, 30 Mar 2016 12:27 PM
ለአቦይ አስገደ ገ/ስላሴ የማይነጥፍ አክብሮት አለኝ፡፡አንጋፋው የፖለቲካ ሰው ሰሞኑን በወልቃይት ጉዳይ ስሜት ኮርኳሪ ጽሁፉችን እያስነበቡን ይገኛሉ፡፡ አስገደ ጉዳዩ የብሄር ግጭት ከማንሳቱም በፊት በግራም በቀኝም ያሉ ኃይሎች በዋናነት ምሁራን፣የሐይማኖት አባቶች፣ተማሪዎችና ሁሉም ወገን ለመነጋገር ዕድል እንዲመቻችና የወልቃይት ጉዳይ በተቀመጠው የህገ መንግስት ድንጋጌ መሰረት የፌደሬሽን ምክር ቤት እልባት እንዲያበጅለት ጫና እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል፡፡

አስገደ በተከታታይ ባስነበቡንና ገና እንደሚቀጥል ተስፋ በገቡበት ጽሁፋቸው በወልቃይት የማንነት ጥያቄን በማንሳት ረገድ ተጠያቂ የሚያደርጉት የቀድሞ የብአዴን አንጋፋ አመራሮችን በመተካት ወደ ስልጣን የመጡትን አዳዲሶቹን መሪዎች ነው፡፡አስገደ በዋናነትም የአማራ ክልል ፕሬዘዳንት የሆኑትን ገዱ አንዳርጋቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

‹‹በሕወሓትና ብአዴን መካከል የነበረውን የጌታና የሎሌ ግኑኝነት አዲሶቹ የብአዴን አመራሮች ባለመቀበላቸው የተነሳ በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ይህ የወልቃይት ጉዳይ እንዲቀጣጠል ተደርጓል››ብለዋል አስገደ፡፡

አስገደ ለመፍትሄ አብዝተው የጮሁትን ያህል የችግሩን ሰበዝ ከስሩ ለመምዘዝ አለመድፈራቸው ለማንም ግልጽ ለሆነው የወልቃይት ጥያቄ ስውር የማቀጣጠያ ምክንያት እንዲባዝኑ አድርጓቸዋል፡፡እንደ አስገደ በቅርበት ሁኔታውን ሲከታተልና ሲጎነጎን የነበረውን ከመነሻው የሚያውቅ ሰው ጥያቄውን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የነጠረ አቋም ማራመድ ሲገባው ‹‹ጉዳዩን የፈጠረው ብአዴንና ሕወሓት ግጭት ውስጥ መግባታቸው ነው ››ማለት ቋጠሮውን ለመፍታት የሚደረገውን መነሳሳት ያወሳስበው ይሆናል እንጂ ፍለጋውን አያቀለውም፡፡

አስገደ ደገፉትም ተቃወሙትም በወልቃይት ጉዳይ የማንነት ጥያቄ መነሳት የጀመረው ገዱ ፕሬዘዳንት ከመሆኑ በፊት ገና በአነስተኛ ስልጣን ወሎ ውስጥ እንኳን ከመመደቡ በፊት ነው፡፡ ወልቃይት ያለ ህዝቡ ፈቃድ ወደ ትግራይ ክልል መካለሉን የተቃወሙ ወልቃይቴዎች ተገድለዋል፣ታፍነው ተወስደው እስካሁን ይኑሩም ይሙቱም አይታወቁም፡፡የወልቃይት ህዝብ ኮሚቴም እንዳረጋገጠው ከ300 የሚበልጡ ወልቃይቴዎች ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ባለፉት 25 ዓመታት መገደላቸውን ቁጥራቸው የማይታወቁ ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን መግለጹ አይዘነጋም፡፡

ልጆቻችን በኃይል በትግርኛ ቋንቋ እንዲማሩ ተደርገዋል በማለትም ወላጆች ጥያቄ ማንሳት የጀመሩት አዲሶቹ የብአዴን አመራሮች ስልጣን በመያዛቸው አይደለም፡፡በወልቃይቴዎች እምነት አሁንም ሆነ ከዚህ ቀደም የአማራ ክልል መንግስት ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር ሲያስራቸው፣ሲያሳድዳቸው፣ሲገድላቸውና ሲያፈናቅላቸው ቆይቷል፡፡

አስገደ ‹‹ ጥያቄው የተነሳው በብአዴን አመራሮች ነው›› ማለታቸውም ለእኔ ህዝብን እንደ በግ መሪዎቹ የሚነዱት አድርገው እንደሚነዱት መቁጠራቸውን ያሳየኛል፡፡አልያም ብአዴን የአማራን ህዝብ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ማሰባሰብ ከቻለም ጥያቄው አልያም ብአዴን ቀድሞውኑ የህዝብ ተቀባይነት ነበራቸው ማለት ነው፡፡

የወልቃይትን ህዝብና የብአዴን አመራሮችን ጥያቄ ለይተን መመልከት ይገባናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ህወሓት ሁልግዜም በኢህአዴግ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘ ሊቀጥል አይችልም፡፡ነገር ግን ይህ ጥያቄ በቀጥታ እንደተነሳበት ለማስረዳት የወልቃይትን ጉዳይ በተባባሪነት ማንሳት ተገቢ አይሆንም፡፡ህዝቡ ብአዴንን ቀድሞ በወልቃይት ጉዳይ ጥያቄና ተቃውሞውን ማንሳት ከጀመረ ሁለት አስርት ዓመታት ነጉደዋል፡፡

የወልቃይትን ህዝብ መሰረታዊና ህገ መንግስታዊ ጥያቄ መፍታት የሚቻለውም ህወሓትንና ብአዴንን የኢንተር ሐሙዌ አይነት ስብከታችሁን አቁሙ በማለት ሳይሆን ከመነሻው የጥያቄውንና የጠያቂውን ምንነት በመገንዘብ የመፍትሄ አቅጣጫ በማኖር ነው፡፡

አስገደ ድፍር ብለው እንዲህ አይነት የማንነት ጥያቄ ህዝቡ አንስቶ እንደማያውቅና የሚፈልገው በአንዲት ኢትዮጵያ ጥላ ውስጥ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡እውነቱን ለመናገር ‹‹ትግሬ ወይም አማራ አይደለሁም››የሚልን ማህበረሰብ በግድ አይደለሁም የሚለውን ማንነት በመጫን በአንድ ጥላ ውስጥ እንዲጠለል አናደርገውም፡፡ማንነቴ ነው የሚለውን ስናከብርለትና ያንን መገለጫውን ስንጠብቅለት ኢትዮጵያዊ አንድነቱን የጋራ መገለጫው ያደርገዋል፡፡

አንጋፋው ፖለቲከኛ ይህንን ባይስቱትም ሌላ አስቂኝ ነገርም ለብአዴንና ለህወሓት ለማካፈል ሞክረዋል፡፡‹‹የብአዴን ሰዎችም ከትግራይ ክልል ትግሬ ነን የሚሉ ሰዎችን አፍነው ወስደዋል››ይላሉ፡፡ይህንን አበው ‹‹የአብዬን ወደ እምዬ …››የሚለትን ተረት ያስታውሰኛል፡፡እርግጥ ነው በአማራ ክልል በጎንደር ጭምር የሚገኙ ወልቃይቶችና የህዝቡን ጥያቄ እንደግፋለን የሚሉ ሰዎች እየታፈኑ ተወስደው ማስፈራሪያ ደርሶባቸው አንዳንዶቹ መለቀቃቸውን ሌሎቹም ለእስር መዳረጋቸውን ደጋግመን ሰምተናል፡፡በቅርቡ አቶ ሊለን ሲሳይ የተባለ የወልቃይት ህዝብ ኮሚቴም መታፈኑ መነገሩ አይዘነጋም፡፡

የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄ የፌደራል መንግስቱ በህገ መንግስቱ መሰረት እንዲፈታለት የሚፈልግ አካል ግን በምን መነሻነት ‹‹እኛ ትግሬ እንጂ አማራ አይደለንም››የሚሉትን ለማሰር ይከጅላል? አስገደ ግን ከሁለቱም ወገን አለመሆናቸውን ሲሉ ህወሓት ሲሰራ የቆየውን ብአዴንም ይህንኑ አድረጓል ይሉናል፡፡

የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ከብዙ አመታት እስራት፣ጋሬጣ፣አፈና እና ግድያ በኋላ የብዙዎችን ትኩረት ማግኘት በመቻሉ ‹‹ይህ የሆነው ብአዴን ስለደገፈው ነው››ማለት ጥያቄውን ያነሳውን ህዝብ መናቅ ነው፡፡አስገደም ሆኑ ሌሎች በዚህ ጉዳይ መካሪ ሆነው መቅረቡ ከፈለጉ ነገሩን ከስሩ ቢመረምሩት መልሱን ቀላል ያደርግልናል ለማለት እወዳለሁ፡፡

አክባሪዎ ዳዊት ሰለሞን

ምንች    ሳተናወ

Leave a Reply