Friday, 01 Apr 2016 12:42 PM
ይህ ጽሁፍ ዳንኤል ክብረት በቅርቡ ‘“ሃገር ማለት ሰው ነው”! እስቲ ሙት በለኝ!’ ሲል ለለቀቀው ጽሁፍ መልስ ነው።… እስካሁን ድረስ “ሃገር ማለት ሰው ነው” የሚባል ዘፈን መኖሩን ሰምቼም አይቼም አላውቅም። በዚህ ስም የሚጠራ ዘፈን ኖሮ እኔ ያላወቅሁ እንኳን ቢሆንም፣ “አገር ማለት ሰው መሆኑን” ሊያስክድ የሚችል አንዳችም ነገር ያለ አይመስለኝም። በዚህ ስም የሚጠራ ዘፈን ጨርሶ ሳይኖር፣ የበድሉ ዋቅጅራን “አገር ማለት የኔ ልጅ…ሰው ነው…” በሚል ርዕስ የሚታወቀውን ታላቅ ግጥም እንዲሁ “ዘፈን” በማለት ለመተቸት ወይም ለማውረድ ከሆነ ደግሞ፣ ዲያቆኑን የባሰ የታሪክ፣ የሃይማኖት እና ከሁሉም በላይ የስነ-ጽሁፍ ድህነቱን ይናገርበት ይመስለኛል። ምክንያቱም አገር ማለት ሰው ነው! ላስረዳ።
“ሃገር ማለት ሰው ነው”። ካለ ሰው፣ አገርማ’ ያው ግኡዝ’ኮ ነው፣ እስራኤውላዊያን የሆኑት ሰዎች ናቸው እስራኤል የሚባልን አገርን የሰሩት፣ አገሩ አይደለም ሰዎቹን የሰራቸው። አብደሃል እንዴ! ያለ ሰው አገር ብቻውን ምንድነው? እናም “ሃገር ማለት ሰው ማለት መሆኑን” እስካሁን ካላወቅህ፣ እውነትም እንደምኞትህ መሞት ይሻልሃል–ዳንኤል ሙት! ከጁላይ 4/1776 በፊት አሜሪካ የሚባል አገር የለም ነበር። ከዚህም ከዚያም የመጡ እና የተሰባሰቡ እንግሊዞች እና ሌሎቹም ሰዎች ፣ ናቸው አሜሪካ የሚባለውን አዲስ አገር የሰሩት። አየህ አገር ማለት ሰው እንደሆነ?
አገር ማለት ሰው ነው፣ ዳንኤል ሙት! ህወሃት የሚባል የሰዎች ስብስብ/ቡድን አዲስ “ትግራይ” የሚባል ትልቅ አገር ሲሰራ እያየህ? ዳንኤል ሙት! ራያና ቆቦ የሚባል የትግራይ ግዛት የለም ነበር፣ አገው/ሰቆጣ የሚባል የትግራይ ምድር የለም ነበር። አሁን እነዚህን ጨምሮ ትልቅ ትግራይ የሚባል አዲስ አገር ህወሃት በሚባሉ ሰዎች እየተሰራልህ ነው። በሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ፣ ራያን እና ሰቆጣን፣ በሰሜን እና በሰሜን ምዕራብ ደግሞ ወልቃይት እና ጠቀዴን ከቦ ይዞ፣ እየገደለ እና እያስገደለ፣ ህወሃት የሚባል ሰዎች ስብስብ፣ ትግራይ የምትባል ትልቅ አገር ለመስራት፣ “ኢትዮጵያ” የምትባለዋን አገር እየገደሉ መሆኑን እያየህ፣ “አገር ማለት ሰው ማለት መሆኑ” ካልገባህ፣ እውነትም እንዳልከው ብትሞት ይሻልሃል፣ ዳንኤል ሙት!
ደግሞስ “ ባድሜ ለምትባል ከጦርነቱ በፊት ብዙው ህዝብ ስምቷት ለማያውቅ መሬት የተደረገውን ጦርነት የረሳ ሰው ነው ‘ሃገር ማለት ሰው ነው’ የሚል… በሄግ ፍርድ ቤት የነበረው ክርክርስ የመሬት ክርክር እንጂ የሰው ክርክር ነበር እንዴ? ..” ነው ያልከው? አየህ የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ “አገር ማለት ሰው ነው” የሚገባህ፣ ባድሜን ሳይሆን፣ በባድሜ ስበብ ያለቀው ያ ሁሉ ወጣት የሚታይህ ቢሆን ነበር።
እነዚያን ሱርማዎች አየሃቸው? እንዳንተና እንደኔ ሰዎች የሆኑት ሰዎች፣ እንደ እንሰሳ በገመድ፣ አንገታቸውን እና እጃቸውን፣ እግር ተወርች ታስረው ገጽታቸውን አይተኸዋል? ያ ደሙን በግንባሩ ላይ እያዘራ … ያለውን የሱርማ ጎረምሳ፣ ፊቱ ላይ ያለውን ተስፋ መቁረጥ አስተውለሃል? “ምነው አንድ መስመር ነፈግሃቸው?” የሚል አጉል ክርክር አልገጥምም እዚህ አሁን። ግንሳ አንተም እኔም እነሱም አንድ ላይ ሆነን፣ በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የ“አገር ማለት ሰው ነው” የግጥም ይዘት እና ቅኝት፣ ሰብዓዊነትን አስቀድመን፣ ለሁሉም እኩል የሆነች አገርን መስራት እና ለትውልድ ማቆየትም ግን እንችላለን። ምክንያቱም “አገር ማለት ሰው ነው”፣ ዲያቆን ሙት!
የጥንቶቹን ኢትዮጵያዊያን የባህረ-ነጋሽ ኗሪዎችን፣ ጣሊያን እና እንግሊዝ የሚባሉ የሰዎች ስብስብ፣ “ኤርትራ” የሚባል ስም ሰጥተው፤ ከዚያም “ህወሃት” በሚባሉ ሌሎች የሰዎች ስብስብ አስፈጻሚነት፣ የአሁኗን “ኤርትራ” ሲሰሩ እያየህ? እናም መለስ ዜናዊ ይሉ ገልቱ ሰው “አይናቸው አላማረኛም ብዬ ካገር ማስወጣት እችላለሁ” በሚል ኢሰብዓዊነት፣ ህጻን አሮጊት ሳይቀር ከገዛ አገራቸው ላይ አስነስቶ በግፍ በረሃ ላይ ወስዶ ሲጥላቸው፣ እና “ሲፈልጉ ግመላቸውን ያጠጡበት” በሚል የመሃይም ፈሊጥ፣ አገሪቱን ወደብ አልባ አድርጓት (ለመሆኑ ለረሃብተኛው ህዝብ የተላከው ስንዴ የት ደረሰ አሁን?) እያየህ? እናም “ኤርትራ” የምትባል አንዲት አዲስ አገር ተሰርታ፣ እንደገና እኒሁ ሰዎች አገራቸው በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የገዛ አገራቸው “ስደተኞች” ተብለው ሲጠሩ እያየህ “አገር ማለት ሰው … መሆኑ” ካልገባህ፣ ዳንኤል ሙት! ብትሞት ይሻልሃል–እንደተመኘኸው። ምክንያቱም አገር ማለት ምን እንደሆነ ገና አልገባህም። አገር ማለት ሰው ነው፣ ዳንኤል ሙት!
ሰዎች የሆኑት አባት፣ አያት ቅማያቶችህ ናቸው ከአድዋ እስከ መተማ ዘምተው፣ ሰዎቹ አርበኞች የጥንቶችህ ናቸው ቆስለው፣ ደምተው፣ ሞተው እና ገድለው “ኢትዮጵያ” የምትባለውን አገር ያስረከቡህ፣ ሰዎች የሆኑት አያት ቅማያቶችህ ናቸው። አገርማ’ ግኡዝ ነው። በነጻነት ይህን ያህል ዘመናት የኖርክበትን አገር ‘አገር” አድርገው ያቆዩልህ ሰዎች ናቸው፣ ዳንኤል ሙት! ስለዚህ አገር ማለት ሰው ነው፣ የእንቁላል እና የጫጩቷን አይነት የ“ማን ቀደመ” እንቆቅልሽ እንኳን የለበትም። የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የስነ-ጽሁፍም ድህነት አለበት ይኼ ጽሁፍህ ዳንኤል፤ እናም ብትሞት ይሻልሃል፣ ዳንኤል ሙት!
የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ “አገር ማለት የኔ ልጅ… ሰው ነው” ግጥም፣ ምናልባትም የአንድነታችን መሰረት የሚሆን፣ ከዚያም ባለፈ የ“አለም አቀፍ ሰብዓዊነት” ይዘት ያለው ግጥም ይመስለኛል። እንዲህ “ዘፈን” ብለህ እንደ ባዶ ጩኸት የምታየው እና በደረጃም የምታወርደው ግጥም አልነበረም። በውነት አንድን ስነ-ጽሁፍ ተችተህ ከመጻፍህ በፊት አንብብ፣ አለዚያ እንደተመኘኸው መሞት ይሻልሃል፣ ዲያቆን ሙት!
አሊ ጓንጉል
ምንች ሳተናዉ