የባህር በር – የማይሞት አጀንዳ!

አብዱራህማን አህመዲን

           ሁልጊዜም ግርም የሚለኝ ነገር አለ፡፡ የኢህአዴግ አባላት/ደጋፊዎች የባህር በር ጉዳይ ሲነሳ ያዙኝ ልቀቁኝ ከማለት አልፈው ፀጉራቸውን ለምን እንደሚነጩ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ሁሌም ግርም የሚለኝ ይሄ ነው፡፡ ግራኝ አህመድ ወረወረው እንደሚባለው ድንጋይ እንዴት አንድ ሰው 25 ዓመት ሙሉ አንድ ቦታ ላይ ይቸከላል?

              እኔ የዛሬ 25 ዓመት የነበርኩበት ቦታ ላይ አደለሁም፡፡ የዛሬ 25 ዓመት እቃወማቸው የነበሩ የኢህአዴግ አቋሞች፣ ዓላማዎች፣ መርሆዎች፣… በጊዜ ሂደት ስለገቡኝ ዛሬ ሽንጤን ገትሬ የምከራከርላቸው አጀንዳዎች ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ፤ የራስን እድል በራስ መወሰንን በሙሉ ልብ አልቀበልም ነበር፡፡ አሁን ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እቀበላለሁ፡፡ የቡድን መብት ከሚያጎናጽፋቸው የዴሞክራሲ መብቶች አንዱ ነውና!
የኤርትራን መገንጠል እቀበላለሁ፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ግን በወቅቱ በኢትዮጵያ በኩል ስህተቶች ስለተፈጸሙ ኤርትራ ነጻነትዋን ያገኘቺው በኢትዮጵያ ኪሳራ (with the expense of Ethiopia) ነው፤ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የባህር በሯን ስላጣች ሰላማዊና ሕጋዊ ድርድር፣ ውይይት፣… መደረግ አለበት እላለሁ፡፡ … የኢትዮጵያ ሕዝብ አዋጥቶ እየገነባው ያለው የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልገንጠል ቢል ዝም እንደማንለው ሁሉ ኤርትራ ስትገነጠል በኢትዮጵያ በኩል የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ መነሳት ነበረበት ነው የምለው!….
25 ዓመታት ሙሉ አንድ ቦታ ላይ ለተቸከሉት/ለቆሙት፣ የሀሳብ መነቃነቅ ላላደረጉት፣… ለኢህአዴግ አባላት/ደጋፊዎች ግን የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ እስከ አሁን ምንነቱ እንኳ የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ያኔ ይባል የነበረውን እየጠቀሱ አሁንም ሊከራከሩ ይዳዳቸዋል፡፡ አዳዲሶቹ አባላት ጭምር! አንዳንዶች እንዲያውም አንድ ኤርትራዊ ሊያደርገው በሚገባ ደረጃ ለኤርትራ ጠበቃ ሆነው ሲከራከሩ ሳይ እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉት ተግባር (ለኤርትራ ጠበቃ ሆነው ኢትዮጵያን መከራከራቸው) የሀገር ክህደት (national treason) መሆኑን አልተገነዘቡትም ማለት ነው? እላለሁ፡፡
በኔ እምነት የባህር በር ጉዳይ የፖለቲካም፣ የኢኮኖሚም ጉዳይ አደለም፡፡ ከኒዮ-ሊበራሊዝም ጋርም የሚገናኝ አደለም፡፡ የባህር በር ጉዳይ ዋነኛ የብሔራዊ ጥቅም (Core National Interest) ጉዳይ ነው፡፡ የብሔራዊ ጥቅም (Core National Interest) ጉዳይ ደግሞ ችላ የሚባል ተራ ጉዳይ አደለም፡፡ አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ … እየላከች የሕይወት ዋጋ ጭምር የምትከፍለው ለምንድነው ነው? የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ነው!
እኔ ጦርነትን በዓይኔ አይቼ አላውቅም፡፡ ባላይም ግን ጦርነት የሚባል ነገር አልወድም፡፡ ከጎረቤቶቻችንም ጋር ይሁን ከሌሎች ጋር ምንም ዓይነት ፀብ፣ ግጭት፣ … እንዲፈጠርም አልሻም፡፡ በኢህአዴግ ንዝህላልነት፣ በግፍ የተቀማነውን ለዘመናት ሃብታችን የነበረ የባህር በርም ቢሆን በድርድር፣ በውይይት፣… ማስመለስ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡
በአባይ የውሃ አጠቃቀም ጉዳይ ከግብጽ ጋር ለአስር ዓመታት ያልተቋረጠ ድርድር መደረጉን አቶ መለስ ነግረውናል፡፡ ታዲያ በባህር በር ጉዳይ ላይ ድርድር ቢጀመር ምናለ? በመቶ ዓመትም ይጠናቀቅ ግን ድርድሩ ይጀመር፡፡ ይህ ሃሳብ የኢህአዴግ አባላትን/ደጋፊዎችን ለምን ያናድዳቸዋል? ይህ ማለት እኮ በአንድ ወቅት ፓርቲያቸው/መሪዎቹና እነሱ ጭምር የሰሩትን ግድፈት ለማረም ይጠቅማል እንጂ ሌላ ጉዳት የለውም፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ ስናነሳ ጦርት እንደ ማወጅ ለምን ይቆጥሩብናል? እነሱ ያወጁትን ጦርነት (አሁንም በእነርሱ ስህተት) እኛ አብረናቸው ተዋግተን የለም እንዴ? ጦርነት እኮ በመፍራትና በመሸሽ የሚቀርልን ጉዳይ አደለም፡፡ እንደ ባድመው ዓይነት ጦርነት ከመጣ (ገና ለገና ሰው ይሞታል ብለን) እጃችንን አጣጥፈን ልንቀመጥ ነው? ፈረንጆቹ እንደሚሉት “war of necessity/just war” የሚባልም ነገር ስላለ በጦረኛነት አታስፈራሩን አቦ!
አሁን ይህንን ሃሳብ በዚህ ወቅት ለምን ጻፍከው? ምን አስበህ ነው?… የሚል ጥያቄ የምታነሱ ትኖራላችሁ፡፡ እኔ ምንም ያሰብኩት ነገር የለም፡፡ እናንተ ያሰባችሁልኝ ነገር ካለ ንገሩኝ፡፡ በሌላ ጉዳይ ላይ ስንወያይ እናንተው ጥያቄ ስላበዛችሁብኝ ነው ሰፋ አድርጌ ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡

አብዱራህማን አህመዲን

https://www.facebook.com/abdurahman.ahmedin.7?fref=nf

Leave a Reply