ስፔይን በዓለም ላይ ምርጥ ከሚባሉት መካከል አንዷ በመሆን ሕገ መንግሥት ያላት አገር ነች፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት በተሻለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ከተጓዙት የአውሮፓ አገሮችም መካከል ትጠቀሳለች፡፡ ለስፔይን የዴሞክራሲ ሒደት መሠረት የጣለው እ.ኤ.አ. በ1978 የተረቀቀውና በሕዝበ ውሳኔ ዕውቅና ያገኘው ሕገ መንግሥቷ ሲሆን፣ ከአርቃቂዎቹ ሰባት የሕግ ምሁራን መካከል ግሪጎሪዮ ፒሰስ-ባርባ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በአገሪቱ በወቅቱ ለተከሰቱት ግጭቶች እልባት አስገኘ ተብሎ የሚታመንበት ይኼው ሕገ መንግሥት፣ የተለያዩ ቡድኖችንና ማንነቶችን ተቃራኒ ፍላጎቶች እንዲያስታርቅ ተደርጎ የተቀረፀ ነው፡፡ ፒሰስ-ባርባ የዚህ አብነታዊ ሕገ መንግሥት አባት ተደርጎ ዛሬም ድረስ ይንቆለጳጰሳል፡፡

ዳኛና ፖለቲካኛ ፒሰስ-ባርባ የአንድ አገር ፖለቲካ በጤነኛ መንገድ ይጓዝ ዘንድ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የግድ ይላል የሚል እምነት አለው፡፡

ፒስስ-ባርባ ብሔራዊ መግባባት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ እንዲሀ በማለት ይገልጻል፡፡ ‹‹ከተፋላሚ ወገኖች አንዱ ሙሉ ለሙሉ የማይደሰትበት፣ እንዲሁም ሁሉንም ወገኖች የማያስቀይም›› ይለዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች በሚካሄዱ ጦርነቶች፣ ግጭቶችና አለመግባባቶች እንደ ዋነኛ መፍትሔ ተደርጎ የሚታየው ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ሲሆን፣ የፒስስ-ባርባን መርህና ጽንሰ ሐሳብ ብዙዎች ጥቅም ላይ ያውላሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ

በኢትዮጵያ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ላይ በተካሄደው ሕዝባዊ አመፅ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣ፣ 60 የቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናትን ያለ ሕግ በመግደል ነበር ‹‹አብዮቱን›› የቀለበሰው፡፡ በሌላ መንገድ የደርግን ሥርዓት ከጠዋቱ ከተቃወሙት መካከል ሕወሓት (በኋላ ኢሕአዴግ) በተራዘመና ብዙ ሕይወት የቀጠፈ የትጥቅ ትግል ደርግ ሲሸነፍ ሲገድሉና ሲያስገድሉ የነበሩት የደርግ ባለሥልጣናት በሕግ እንዲዳኙ በማድረግ ለ20 ዓመታት እስር ላይ ቆይተው ምሕረት ተደርጎላቸው ከእስር ቤት ወጥተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተከፋፍሎ የሚገኘውና ህልውናው እምብዛም እንደሆነ የሚነገርለት ኦነግን ጨምሮ የተለያዩ በአመፅ ላይ የነበሩ ድርጅቶችን ያካተተ ብሔራዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን፣ በዚሁ ሒደትም የተለያዩ ሕዝባዊ ኮንፈረንሶች ተካሂደው በሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን የተዘጋጀው አሁን ሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ሊፀድቅ ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በመርህ ደረጃ ከምሁራን እምብዛም ተቃውሞ የማይሰማበት ቢሆንም፣ በኢሕአዴግ ዋነኛ ተቃዋሚዎች ዘንድ ግን የጎሳ ፖለቲካ አከፋፋይና ገንጣይ የሚሉ ቅጽሎች ይሰጡበታል፡፡ አንዳንዶቹም ‹‹የአራዊት ሕግ›› ይሉታል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአብዛኛው በብሔር ብሔረሰቦች መብቶች የተቃኘና በየትኛውም አገር የማይደፈረውን የ‹‹እስከ መገንጠል›› አንቀጽ ያሰፈረ ቢሆንም፣ በተለይ የቀድሞው መንግሥት ሥርዓት ደጋፊ የሆኑ የአሃዳዊ አስተሳሰብ አራማጆችን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የፌዴራል ሥርዓት አቀንቃኞች ግን ሰፊ ድጋፍ ይቸሩታል፡፡

የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም በሽግግሩ ዘመን በቂ ሕዝባዊ ውይይት ተደርጎ የፀደቀ ሕገ መንግሥት በማለት ተቺዎችን ይሞግታል፡፡ ተቃዋሚዎችንም እንደ በፊቱ ሥርዓቶች ባያጠፋቸውም፣ ሐሳባቸውን ግን ለማካተት ፈቃደኛ አልነበረም ተብሎ ይተቻል፡፡ ኦነግን ጨምሮ በርከት ያሉ ተቃዋሚዎች የተሰጣቸውን ወንበር ይዘው እምብዛም ሳይቆዩ አፈንግጠው መውጣታቸውም ይታወሳል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ጥንካሬያቸው እየቀነሰና እየተከፋፈሉ የመጡ ቢመስልም ዛሬም ድረስ በተለይ ፌዴራሊዝምን በተመለከተ፣ የቡድንና የግለሰብ መብትን በተመለከተ፣ የኤርትራን መገንጠልና የባህር በር እንዲሁም የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ በተቃራኒ ጫፍ ላይ ሆነው ሲከራከሩ ይስተዋላሉ፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በ1987 ዓ.ም. ከተካሄደው የመጀመሪያ ምርጫ አንስቶ አምና እስከተከናወነው አምስተኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ እነዚህ ጉዳዮች ዋና የልዩነት ነጥብ ሆነው የቀጠሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ መቀራረብ መፈጠር ባለመቻሉ፣ የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት ዕጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በሰላማዊ መንገድ የመንግሥት ለውጥ ተካሂዶ እስካሁን የተገነባው የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ሒደት ይቀጥላል ብሎ የሚያምነው ጥቂት ይመስላል፡፡ ደርግና ኢሕአዴግ የነበረውን በሙሉ አፍርሰው ከዜሮ እንደጀመሩ ሁሉ፣ ወደፊት የሚመጣው መንግሥትም በተጀመረው ላይ እንደሚቀጥል የሚያስተማምን ነገር የለም የሚሉ አሉ፡፡ በየአምስት ዓመቱ በሚካሄዱት ብዙዎች የ‹‹ይምሰል›› በሚሉዋቸው የምርጫ ሒደቶች ተስፋ የቆረጡ ነፍጥ አንግበው ጫካ መውጣታቸውን ያወጁ ሲሆን፣ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ አድርገው የነበሩት አገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚዎችም ጠቅልለው ከሕዝባዊ ውክልና ወጥተዋል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹አውራ›› ፓርቲ የሚል ስያሜ ቢሰጡትም የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት በኢትዮጵያ ዕውን ሆኗል፡፡ የተለያዩ አስተሳሰብ ያላቸው ተቃዋሚ ኃይሎች የሚወክሉትን ሕዝብ ጨምረው ከፖለቲካ ጨዋታው ውጪ ሆነዋል፡፡ የመድበለ (የብዙኃን) ፓርቲ ሥርዓት አደጋ ላይ መውደቁ የሚያሳስባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡

ነገስ?

ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ‹‹ሞኖፖሊ›› ተጠያቂው ኢሕአዴግ ብቻ ባይሆንም፣ ዛሬ ባለበት ከቀጠለ ‹‹ምን ይከሰታል?›› በማለት የሚጨነቁ ጥቂት አይመስሉም፡፡

በአንዳንድ ገለልተኛ ታዛቢዎች እንደሚባለው በ1997 ዓ.ም. እንደታየው ከተቻለ በምርጫ፣ ካልሆነ በምድር አንቀጥቅጥ አመፅ ኢሕአዴግን ለመጣል የተነሳን ኃይል ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ የተወሰደው ዕርምጃና የፀደቁ አዋጆች አከራካሪነታቸው የቀጠለ ቢሆንም፣ ዛሬም ተስፋ ቆርጠው እጅና እግራቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳች ነገር የሚጠብቁ መስለው ይታያሉ፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የተያዩ አካባቢዎች የተነሳው አመፅ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ብቅ ጥልቅ የሚሉት ግጭቶች ለተለያዩ ወገኖች የተለያዩ ትርጉሞች እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአስተዳደር ችግር መከሰቱን አምነው ሙሉ በሙሉ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ግን የአስተዳደር ቀውሱን ለይቶ መፍታት እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡ የዴሞክራሲ ‹‹ቅልበሳ›› ውጤት መሆኑን በመሞገት፡፡

ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የኦሮሚያ ችግር ከመከሰቱ በፊት የመልካም አስተዳደር ችግሩን ለመፍታት በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠና ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከተለያዩ ወገኖች (ከምሁራንና ከፖለቲካ ፓርቲዎች) ጋር የሚያደርጉዋቸው ውይይቶች የመፍትሔው አካል ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ የሚሉ አሉ፡፡ በውይይቶቹ በተለይ ከምሁራን ጋር በተደረገው ውይይት የተነሳው አንድ ቁም ነገር ግን የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ይመስላል፡፡ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር፡፡

ቀደም ሲል ብሔራዊ እርቅ እንዲደረግ ከተቃዋሚዎች ይቀርብ ለነበረው ጥያቄ፣ ‹‹ማንና ማን ተጣልተው?›› በማለት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተሰጠው ምላሽ ጥያቄውን አዳፍኖት የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬም የሥርዓቱ ደጋፊ እንደሆኑ ከሚታመንባቸው ምሁራን የተነሳው ጥያቄ በይደር የሰነበተው የመቻቻልና እርቅ የመፍጠር ፖለቲካ ፊቱን ቀይሮ የመጣ ይመስላል፡፡

በአሜሪካ የሚኖሩት ዶ/ር ገላውዲዮስ አርዓያ የተባሉ ምሁር፣ ‹‹National Reconsilation and National Development›› በሚል ርዕስ በ2002 ዓ.ም. ባስነበቡት መጣጥፍ፣ ‹‹ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ በአገሪቱ ፖለቲካ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸውን አምነው መቀበል አለባቸው፤›› በማለት የደመደሙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና ተቃዋሚዎች በውል ያልተሳተፉበት የፈለገው ዓይነት ልማት ቢመጣ ነገ ፈራሽ መሆኑን አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለወደፊቱ በሚከሰት ችግር ተጠያቂነቱ ከፍ ያለ እንደሆነ በማመላከት፣ ‹‹ከኦነግ ጋር መደራደር የቻለ መንግሥት ከመድረክ ጋር መደራደር የማይችልበት ምክንያት የለም፤›› በማለት ሞግተዋል፡፡ ኢሕአዴግ፣ እጅግ አክራሪና ዘረኛ የሆነ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ያሉዋቸውን አንዳንድ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ፖለቲካ ስለሌላቸው እነርሱን (ጥቂቶችን) አግልሎ ከተቀረው ከሰፊው ዳያስፖራና አገር ውስጥ ካለው ተቃዋሚ ጋር ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ካልቻለ፣ የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አመላክተው ነበር፡፡

‹‹ብሔራዊ እርቅ የሚፈለገው ቁርሾና በቀል ለማብረድ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ አቋሞች ያሉዋቸው ተፈላሚ ወገኖች አንዱን ሌላውን ሳያጠፉ የአስተሳሰብ ልዩነቶቻቸው እንደታቀበ ለአገር እንዲጠቅም ይረዳል›› ብለዋል፡፡

እንዲሁም ኢሕአዴግን ክፉኛ በመተቸት የሚታወቁት ዶ/ር መሳይ ከበደ በበኩላቸው፣ ‹‹Democracy and its Trade off: Ethiopia’s path to national reconciliation›› በሚለውና በተለያዩ መጣጥፋቸው ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የዕርቅ መንግሥት መፍጠር አስፈላጊነትን ያሳውቁ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሀቀኛ የእርቅ መንግሥት መፍጠር ቢችሉ ኖሮ ኢትዮጵያዊ ኔልሰን ማንዴላ በሆኑ ነበር፤›› በማለት ኢሕአዴግን በነፍጥ መጣል ለኢትዮጵያ የተሻለ ዴሞክራሲ ያመጣል ብለው የማይቀበሉት የኢሕአዴግ ተቺ የሆኑት ዶ/ር መሳይ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጭቆናውን በመቀነስ ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ማስተንፈሻ ይሰጡታል የሚል ግምታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

‹‹እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ይመስላል፡፡ እልባት አልባ፡፡ አገሪቱ አሁን ወደ ፊትም ወደ ኋላም እየተጓዘች አይደለችም፡፡ ሕዝቡ እየታፈነና እየተቆጣ ይመጣል፡፡ በወቅቱ መንግሥት ሊቀለብሰው የማይችለው ደረጃ ይደርሳል፡፡ ሕዝባዊ አመፅም ይከሰታል፤›› ይላሉ፡፡ በሕዝባዊ አመፅ ለውጥ እንደማይመጣ በመቃወም፡፡ ሊሆን የሚችለው በመንግሥት ላይ በሚከሰት አመፅ የእርስ በርስ ግጭትና የብቀላ ዕርምጃዎች መውሰድ መሆኑን ገልጸው፣ የኢሕአዴግ መንግሥትም ከሥልጣን ከወረደ ሌላ የባሰ አምባገነንና በቀለኛ መንግሥት ሥልጣን ላይ ወጥቶ ማለቂያ ወደሌለው ደም መፋሰስ ሊገባ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

‹‹ደርግን ለመጣል ሕወሓት የከፈለው መስዋዕትነት ሕዝቡን ከማመፅና ከመገንፈል አያግደውም፤›› የሚሉት ዶ/ር መሳይ፣ በትግራይም ሆነ ከዚያ ውጪ ሕዝባዊ ተቀባይነቱን የሚያገኘው ሥልጣኑ ላይ የወጣበት መንገድ ሳይሆን ሥልጣኑን ከኃይል ውጪ ለመግዛት የተጠቀመበት መንገድ ነው ይላሉ፡፡

ቱኒዚያና ግብፅን እንደ ምሳሌነት በመውሰድ በሕዝባዊ አመፅ መንግሥት መጣል የዴሞክራሲ ምንጭ እንደማይሆን ይከራከራሉ፡፡ በዚህ ብሔራዊ የእርቅ መንግሥት ሊካተቱ የሚችሉ አባላትን ለይቶ ባልተድበሰበሰና ግልጽ በሆነ መንገድ ወደ ዴሞክራሲ ሊያመራ የሚችል፣ በጠረጴዛ ዙርያ ድርድር ማድረግን እንደ የመጨረሻ እልባት አድርገው አስቀምጠዋል፡፡

ዛሬ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከምሁራን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ መንግሥታቸው ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆነ ቢገልጹም፣ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል የሚለው አጠያያቂ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይወሳል፡፡

የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ‹‹ቀደም ሲል ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረግ ውይይት  ነበር፡፡ ሜዳው ባዶ አልነበረም፡፡ አሁን የፖለቲካ መልኩ እየተቀየረ መጥቷል፡፡ የሕዝቡን ይሁንታ ማግኘት ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡ ምርጫውን አሸንፎ መንግሥት ከመሠረተ ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ መከሰቱ ለኢሕአዴግ አስደንጋጭ እንደሆነ በመጠቆም፣ ኢሕአዴግ የተመረጠበት ምክንያት አማራጭ ማጣት፣ የህልውና ሥጋትና የኢኮኖሚ ጥገኝነት የወለደው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ ‹‹አሁን መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተበላሽቷል፡፡ ይኼ ደግሞ የመንግሥታዊ ተቋማት ችግር ውጤት ነው፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ያሉት ችግሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከገለጹት በላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አስከፊውን ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የመታፈን ስሜትና የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ካልተፈጠረ ኢሕአዴግ ብቻውን ችግሮቹን ሊፈታቸው አይችልም ይላሉ፡፡ ‹‹በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ሳይፈጠር ዘላቂ እርቅ አይኖርም፡፡ ያለ ፍትሕም እርቅ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡

የሕዝቡን ጩኸት ለማዳመጥና ችግሩን ለመፍታት ጠቅላይ ማኒስትሩ የጀመሩትን ጥረት ያደነቁት ፕሮፌሰር ገብሩ፣ የውይይቱ አድማስ ወደ ታች ወደ ወጣቱና ወደ ዕድሮችም ሳይቀር እንዲወርድ ይጠይቃሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ዕርቅ የሚያስፈልጋቸው በዋናነት ሕዝብና መንግሥት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ቀደም ሲል በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት በግንቦት 20 የድል መድፎች እየተኮሱ የሌላውን ቁስል ከመቆስቆስ ይልቅ ቀኑ የዕርቅ፣ የመወያያና የምክክር ቢሆን የሚል ሐሳብም ያቀርባሉ፡፡ ‹‹በታሪክ አጋጣሚ በየሜዳው በሁለቱም ወገኖች የተዋደቁ፣ አፈር ለብሰው አፈር ሆነው የቀሩትን የምናስታውስበት ይሁን፡፡ የአንዱን ጭፈራ የሌላውን ቁስል ይጎዳል፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ኢሕአዴግ የእርቋን ነገር ይፈራል፤›› የሚሉት ደግሞ ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን መጋራት እንደማይፈልግ የሚናገሩት ዶ/ር መረራ፣ በደቡብ ሱዳንና በሩዋንዳ ዕርቅ ለመፍጠር ይዋትታል በማለት ‹‹የራሷ አሮባት …›› መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው የሚሉት ዶ/ር መረራ፣ መሠረታዊ ባሉዋቸው ጉዳዮች ማለትም በሕግ የበላይነት፣ ሀቀኛ የራስ አስተዳደር፣ ነፃ የመንግሥት ተቋማትን የመገንባትና የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነትና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

‹‹ፓርላማ ትክክለኛ የአገሪቱ ውክልና እንዳለው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤›› በማለት ብሔራዊ መግባባት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዋነኛ ድልድይ መሆኑን ይደመድማሉ፡፡