09 NOVEMBER 2014 ተጻፈ በ 

በቴሌቪዥን ከምንሰማው ወቅታዊ የጤና ጉዳዮች አንዱ የእናትና የሕፃናት ግንኙነትን የሚመለከት ነው፡፡

እናቶች ከወለዱ በኋላ ልጅን የመንከባከብ ተፈጥሯዊ ጸጋ (ግዴታ) የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሳይንሱ እንዳረጋገጠውም ያለምንም ተጨማሪ ምግብ ለተከታታይ ስድስት ወራት የእናት ጡት የጠባ ሕፃን ጤናማ ይሆናል፡፡ ጤናማ ሕፃን ደግሞ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለአገሩ ጠቃሚ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ይህንን መልዕክት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በየቤታችን አድርሰውናል፤ እኛም ሰምተናል፡፡ ይህንን ምክር እውን እንዲሆን የሚያስችሉ ነገሮች ስለመኖራቸው ግን በተግባር አንመለከትም፡፡ በተለይ ነፍሰጡሯ ሠራተኛ በሆነች ጊዜ የሚነሱት የሕግ ጭብጦች፣ የሴቷ መብትና የአሠሪው ግዴታዎች ብዙ ባይባልላቸውም ሰፊና አንገብጋቢ ናቸው፡፡ የሚቀረው ብዙ ቢሆንም ያለውም መብት በአግባቡ አይታወቅም፡፡

ሰው በመሆናቸው ብቻ ከሚከበሩላቸው መብቶች እኩል፣ ሴቶች በሴትነታቸው ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መብቶች ውስጥ አንዱና ዋናው በተፈጥሮ ከታደሉት የእናትነት ፀጋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሴቶች ነፍሰ ጡር ሲሆኑ ለእነሱና ለሕፃኑ ጤንነትና መልካም ኑሮ ኅብረተሰቡና መንግሥት አዎንታዊ ድጋፍ ማድረጋቸው ግድ ነው፡፡ ይህ ድጋፍ በአግባቡ መሰጠቱ ጤናማ ቤተሰብ ለመመሥረት፣ ብቁ ተተኪ ትውልድ ለማፍራትና በአጠቃላይ የኅብረተሰብን ህልውና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ያለው ሚና አሌ አይባልም፡፡ ሴቶች በዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች፣ በአገሮች ሕገ መንግሥቶች እንዲሁም በብሔራዊ ሕጎች የተረጋገጡ ልዩ ልዩ መብቶች ያሏቸው ሲሆን፣ በዚህ ጽሑፍ ሠራተኛ የሆነች ሴት ልጅ ከመፀነሷ ጀምሮ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ ያላትን ሕጋዊ መብቶች ለመተንተን ተሞክሯል፡፡ የጽሑፉ ዓላማ ሴቶች መብቶቻቸውን አውቀው እንዲጠይቁ መርዳትና ግዴታ ፈጻሚ ባለድርሻ አካላትም መብቶቹን ለማክበር እንዲያስችላቸው ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ ነው፡፡

ነፍሰጡርን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሴቶች መብት ዙሪያ የተፈረመው ቀዳሚና ገዥ ስምምነት በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት አድሎአዊነትን ለማስወገድ የተፈረመው ስምምነት (Convention On the Elimination of All Forms of Discrimination Against Women) ነው፡፡ ይህ ሰነድ ዓላማው የሴቶችን እኩልነት በተለያዩ መስኮች ማረጋገጥ ሲሆን ከፀደቀበት እ.ኤ.አ. ከ1977 ጀምሮ አገራችንን ጨምሮ በርካታ አገሮች ፈርመውታል፡፡ በዚህ ስምምነት ሴቶች በጋብቻ ወይም በወሊድ ምክንያት አድሎአዊ ልዩነት እንዳይደረግባቸውና የመሥራት መብታቸውን ለማረጋገጥ አገሮች ተገቢ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ግዴታ ገብተዋል፡፡

በዚህ መሠረት አገሮች በእርግዝና ወይም በወሊድ ምክንያት ሴቶች ከሥራ እንዳይባረሩ የወሊድ ፈቃድ ከክፍያ ጋር እንዲሰጣቸውና ከወሊድ ሲመለሱም የነበራቸውን ጥቅምና የሥራ ልምድ ሳያጡ እንዲቀጥሉ፤ ወላጆች የቤተሰብ ኃላፊነትን ከሥራ ግዴታና ከማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ ጋር አጣምረው እንዲይዙ ለማበረታታት አስፈላጊ ድጋፍ ሰጪ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በተለይም የሕፃናት መንከባከቢያዎች በየቦታው እንዲቋቋሙና እንዲደራጁ ለማድረግ፣ በእርግዝና ጊዜ ለጤንነታቸው አደገኛ መሆናቸው የተረጋገጡ የሥራ ዓይነቶችን ለይቶ በመቆጣጠር ለሴቶች ልዩ ጥንቃቄ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

አገሮች የሴቷን መብቶች ለማረጋገጥ ሕግ የማውጣት፣ አድሎአዊነት ያላቸውን ሕጎች የማሻሻል እንዲሁም ሕጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1989 የፀደቀውና አገራችን የፈረመችው የሕፃናት መብቶች ስምምነት (UN convention on the rights of the child)፣ ከሕፃናት መጠበቅ ጋር የእናቲቱ መብቶችም እንዲጠበቁ ይደነግጋል፡፡ ይህ የሕግ ሰነድ በመግቢያው  ላይ ሕፃናት በቅድመ ወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት በቂ እንክብካቤ እንዲሰጣቸው የሚያስገድድ ሲሆን፣ በዝርዝር ድንጋጌዎቹም ለነፍሰጡሮችና ለአጥቢ እናቶች ተገቢ አገልግሎት መስጠቱን የማረጋገጥ ግዴታ በፈራሚ አገሮች ላይ ጥሏል፡፡ ተመሳሳይ ጥበቃዎች በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተዘጋጅተው ከተፈረሙት መካከል የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች ቻርተርና የአፍሪካ የሴቶች ፕሮቶኮል ቀርጸዋል፡፡

ነፍሰጡር ሴቶች በሥራ ላይ ያሏቸውን መብቶች በግልጽ በመደንገግ ዘርዘር ያሉ ጥበቃዎችን የያዙት የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነቶች (International Labour organization Conventions) ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስምምነቶች ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1952 በዓለም የሥራ ድርጅት የወጣውን ስምምነት ያሻሻለው የ2000ው (Maternity Protection Convention (Revised)) ቀዳሚ ነው፡፡ ስምምነቱ ሴት ሠራተኞች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ኃላፊነት ለሆነው እርግዝና በቂ ጥበቃ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ስምምነቱ እርጉዝ ሴቶች ለራሳቸው ወይም ለልጆቻቸው ጤንነት በማይመቹ የሥራ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳይሠሩ ይከለከላል፡፡ ነፍሰጡር ሴቶች የሕክምና ማስረጃ ባቀረቡ ጊዜ ይወልዳሉ ተብሎ ከተገመተበት ጊዜ ጀምሮ ከ14 ሳምንት የማያንስ የወሊድ ፈቃድ የማግኘት መብት እንዳላቸው፣ ከወለዱ በኋላም በግዴታ ቢያንስ የ6 ሳምንታት ዕረፍት፣ ከመውለዳቸው በፊትም ተገቢ ዕረፍት እንዲያገኙ ይደነግጋል፡፡ ስምምነቱ ነፍሰጡር ሠራተኞች ሲታመሙ፣ ከእርግዝና ወይም ከወሊድ ጋር የተያያዙ ሕመሞች ሲሰማቸው ሁሉ በአገሮች ብሔራዊ ሕግ የሚወሰን የሕመም ፈቃድ እንዲያገኙ ደንግጓል፡፡ እንደየአገሮቹ ልምድ በእርግዝና ጊዜ የሚከፈል የገንዘብ ጥቅሞች ለነፍሰጡሮች እንዲሰጡ ይደነግጋል፡፡ ይህን መሰሉ ግዴታ ግን ባላደጉ አገሮች ውስጥ በተለየ ሁኔታ እንዲፈጸም ስምምነቱ ያመለክታል፡፡ ይኸውም ነፍሰጡሮች ሊያገኙ በሚገባው የሕክምና ወጪ መጠን ብቻ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ስምምነቱ ሴት ሠራተኞች በእርግዝናቸው ወቅት ከሥራ እንዳይሰናበቱ የወሊድ ፈቃዳቸውን ጨርሰው ሲመለሱም በተመሳሳይ የሥራ ቦታቸው ላይ እንዲመለሱ፣ ለእነርሱ ካልጠቀማቸው በስተቀር በቅጥር ወቅት የእርግዝና ምርመራ እንዳይጠየቁ በመከልከል አሠሪዎች ላይ ግዴታ ይጥላል፡፡

የነፍሰጡር መብቶች በኢትዮጵያ ሕግ

አገራችን ቀደም ሲል የተገለጹትን ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነትን የፈረመች በመሆኗ የነፍሰ ጡር ሠራተኞችን ልዩ ልዩ መብቶች የማክበር ግዴታ አለባት፡፡ በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥታችን በአንቀጽ 35 ላይ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የማግኘት መብት እንዳላቸው በመግለጽ፣ የወሊድ ፈቃድ ጊዜ ሴቷ የምትሠራውን የሥራ ሁኔታ፣ የሴቷን ጤንነት፣ የሕፃኑንና የቤተሰቡን ደህንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕግ እንደሚወሰን ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ የወሊድ ፈቃድና ሌሎች የነፍሰጡሯ መብቶች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ስለተሰጣቸው፣ ዝርዝር ሕጎች መብቶቹን ሊያጠናክሩ እንጂ ሊሸረሽሩ እንደማይገባ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን የሚገዙ ሕጎች የነፍስጡር ሠራተኞችን መብቶች በዝርዝር ደንግገዋል፡፡ በዚህ ረገድ በተለያየ ጊዜ ቢሻሻልም በሴቶች መብቶች ረገድ ተመሳሳይ የሥራ ሁኔታዎችን የደነገገው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ቀዳሚው ነው፡፡ ይህ አዋጅ በክፍል ስድስት የሴቶችና የወጣት ሠራተኞችን የሥራ ሁኔታ የሚደነግግ ሲሆን፣ አንቀፅ 87 እና 88 የነፍሰጡር ሠራተኞችን የተለያዩ መብቶች ይዘረዝራል፡፡ በዚህ ሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸውን መብቶች  በቀጣዮቹ ክፍሎች ለማብራራት እንሞክር፡፡

ለሴቶች ከባድ ወይም ለጤናቸው ወይም ለእርግዝናቸው ጎጅ በሆኑ ሥራዎች ላይ ያለመሥራት መብት

የሴቶች የሥነ ተዋልዶ መብቶች ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በሥራ ቦታ የተለየ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያጠይቁ ናቸው፡፡ ነፍሰጡሮች መቆፈር፣ መቁረጥ፣ ዛፍ መቁረጥና የመሳሰለውን ተግባር  በሚጠይቅ የኮንስትራክሸን ሥራ፣ ማሞቂያ ላይ፣ ባትሪ መሙላት፣ መበየድ፣ የውኃ ጉድጉድ ማፅዳት፣ ለረዥም ሰዓት መቆም በሚጠይቁ ሥራዎችና ከፍ ያለ ሙቀት የሚያመነጩ ሥራዎችን እንዳይሠሩ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ ከልክሏል፡፡ እነዚህ ጥበቃዎች ለነፍሰጡሯ የተለየ ጥበቃ ለማድረግ ታስቦ ብቻ ሳይሆን፣ የነገ አገር ተረካቢ ግን ያልተወለዱ ሕፃናትንም ለመጠበቅ በማሰብ ነው፡፡ ይህ ጥበቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡

የሌሊትና የትርፍ ሰዓት ሥራዎችን ያለመሥራት መብት

አንዲት ነፍሰጡር ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ እንዲሁም የትርፍ ሰዓት ሥራ ያለመሥራት መብት አላት፡፡ እንደሚታወቀው የትርፍ ሰዓት ሥራ አሠሪው ከመደበኛ ሥራ ወይም ድርጅቱ ያጋጠመውን ችግር ወይም የአስቸኳይ ጊዜ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በተለየ ክፍያ ሠራተኞችን የሚያሠራበት አግባብ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ነፍሰጡሯ የተለየ ጥበቃ ተደርጎላታል፡፡

ነፍሰጡሯ የምትሠራው ሥራ አደገኛ ከሆነ በሌላ ሥራ ላይ ተመድባ የመሥራት መብት

አንዳንድ ጊዜ ሴቶች ከመፀነሳቸው በፊት ወንዶች የሚሠሯቸውን ከባድ ሥራዎች የሚሠሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ በማምረቻ ድርጅት (ፋብሪካ) ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች በዚህ በኩል ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሴቶች ከፀነሱ በኋላ ቀድሞ ይሰሩበት በነበረው የሥራ ቦታ እንዲሠሩ ማድረግ ለጤንነታቸውም ሆነ ላልተወለደው ልጅ ሕይወት ጎጅ ነው፡፡ ስለዚህ ሕጉ ሴቶች በፀነሱ ጊዜ ቀድሞ ይሠሩበት የነበረው ሥራ አደገኛ ከሆነ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሠሩ መብት ይሰጣቸዋል፡፡ ሆኖም ነፍሰጡሯ የምትሠራው ሥራ ለራሷ ጤንነትም ሆነ ለጽንሱ አደገኛ መሆኑ በሐኪም መረጋገጥ ይገባዋል፡፡

ነፍሰጡር ከሥራ ያለመሰናበት መብት

የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ ሴት ሠራተኛ ነፍሰጡር በሆነችበት ጊዜና ከወለደችበት ቀን ጀምሮ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ አሠሪው ከሥራ ሊያሰናብታት እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ ይሄ የሴቷን የሥራ ዋስትና በአግባቡ ያረጋግጣል፡፡ አሠሪው ሴት ሠራተኛውን በማጣቱ ምክንያት ለመስራት ቢቸገር እንኳ ለማሰናበት ሕግ አይፈቅድለትም፡፡ ያለው አማራጭ በእርሷ ቦታ ለተወሰነ ጊዜ ሌላ ሠራተኛ ቀጥሮ ወይም ተክቶ ማሠራት ነው፡፡ ሕጉ ሴቶች በእርግዝና ምክንያት እንዳይሰናበቱ ክልከላ ያደርጋል እንጂ ከዚህ ውጭ ባሉ ከእርግዝና ጋር ተያይዥነት በሌላቸው ምክንያቶች ስንብት እንዳይፈጸም አይከለክልም፡፡ ነፍሰጡር ሠራተኛ በፈቃዷ ሥራ ብታቋርጥ፣ ያለማስጠንቀቂያ ሊያሰናብቱ የሚያስችሉ ጥፋቶችን ብትፈጽም እንዲሁም በሥራ መቀዝቀዝ ወይም መክሰር ምክንያት የሠራተኛ ቅነሳ በሚደረግበት ጊዜ ነፍሰጡሯ የሆነችው ሠራተኛ ተቀናሽ ከተደረገች የአሠሪው ድርጊት ሕገ ወጥ ላይሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ሕጉ በሠራተኛ ቅነሳ ወቅት ነፍሰ ጡር ሴቶች ከሁሉም ሠራተኛ መጨረሻ ረድፍ ላይ ሲደርሱ እንዲቀነሱ በመደንገግ ልዩ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡

የነፍሰጡር የወሊድ ፈቃድ የማግኘት መብት

ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ከእርግዝናዋ ጋር የተያያዘ ምርመራ ለማድረግ እንድትችል አሠሪው ከደመወዝ ጋር ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ሠራተኛዋ ከምርመራ በኋላ የሐኪም ማስረጃ ማቅረብ አለባት፡፡ በተጨማሪም ከመውሉዷ በፊት ሐኪም እንድታርፍ ካዘዘ፣ ከክፍያ ጋር እረፍት ይሰጣታል፡፡ ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት መውለጃዋ ሲደርስ ተከታታይ የ30 ቀናት የወሊድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ ተከታታይ 60 ቀናት የወሊድ ፈቃድ ከክፍያ ጋር ይሰጣታል፡፡ ሠራተኛዋ ከመውለዷ በፊት የወሰደችው የ30 ቀን ፈቃድ ሲያልቅ ካልወለደች እስከምትወልድበት ቀን ድረስ ዕረፍት ልታገኝ ትችላለች፡፡ የ30 ቀን ፈቃድ ሳያልቅ ከወለደች ከወሊድ በኋላ የምትወስደው የወሊድ ፈቃድ ይጀምራል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወሊድ ፈቃድ እስከ 6 ወር ሊራዘም ይችላል የሚል ወሬ ቢናፈስም በተግባር ሕጉ ተሻሽሎ አልተመለከትንም፡፡ሕጉ የወሊድ ፈቃድን እስከ ስድስት ወር ካራዘመ እናቶች ሳይንሱ ከሕፃኑ መጥባት ጋር በተያያዘ ለጤንነቱ ያረጋገጣቸውን መብቶች ለመተግበር ያስችላቸዋል፡፡ ሆኖም ከድርጅቱ ትርፋማነት አንፃር አከራካሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ሕግ አውጭው ግራ ቀኙን ተመልክቶ ሕጉን በማሻሻል የሚጨምረውን የወሊድ ፈቃድ ወደፊት የምንመለከተው ይሆናል፡፡

ሕጉ የወሊድ ፈቃድ መጠንን የደነገገው አነስተኛ የሥራ ሁኔታውን በመንተራስ ስለሆነ፣ አሠሪውና ሠራተኛው በሚያደርጉት የሥራ ውል፣ የኅብረት ስምምነት፣ አሊያም በሠራተኛ ጥቅም  ፖሊሲ ነፍሰጡሮች በሕጉ ከተቀመጠው በላይ የወሊድ ፈቃድ መጠን ሊያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ የወሊድ ፈቃድ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡

ከወሊድ ፈቃድ ጋር በተያያዘ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ በአብዛኛው ከላይ ከተገለጸው ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም የተወሰኑ ልዩነቶች አሉት፡፡ በጎ ነገሩ የመንግሥት ሠራተኛ የተሰጣት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከማለቁ በፊት ከወለደች ያልተጠቀመችበትን ቀሪ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወለደች በኋላ እንድትጠቀምበት ይፈቅዳል፡፡ ይህ ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የተሻለ መብት ለመንግስት ሠራተኛ ይሰጣል፡፡ ምክንያቱም ቅድመ ወሊድ ፈቃድ ወደ ድህረ ወሊድ ፈቀድ የሚተላለፍበትን ሁኔታ ስለሚያስቀምጥ፡፡

በሌላ በኩል ግን ከአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ ባነሰ መልኩ ‹‹ሠራተኛዋ የወሰደችው የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ሲያልቅ ያልወለደች እንደሆነ እስከምትወልድበት ቀን ድረስ ባሉት የሥራ ቀናት የምትቆይበት ዕረፍት በበጀት ዓመቱ ካሉት የዓመት እረፍት ፈቃድ ወይም በበጀት ዓመቱ የዓመት ዕረፍት ፈቃድ የሌላት እንደሆነ ከሚቀጥለው የበጀት ዓመት የዕረፍት ፈቃዷ ይተካል›› በማለት አመልክቷል፡፡ የዓመት ዕረፍት ፈቃድና የወሊድ ፈቃድ የተለያየ ዓላማ ያላቸው በመሆኑ፣ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ የሁለቱን ዓላማ ያቀላቀለ ይመስላል፡፡ ቅድመ ወሊድ ዕረፍት ካለቀ በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት ተጨማሪ ፈቃድ ሊሰጥ ይገባል እንጂ ለሌላ ዓላማ የተሰጠ የዓመት ዕረፍት ፈቃድ መብት ለመጠቀም ማስገደድ ተገቢ አይሆንም፡፡ የዓመት ዕረፍት ፈቃድ የሚያስፈልገው በሥራ ድካም የቀነሰ የሠራተኛውን ምርታማነት ለመጨመር መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ሊደነቅ የሚገባው ከወሊድ ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶች የባልና የሚስት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ዕውቅና መስጠቱ ነው፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 41/6/ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛው የትዳር ጓደኛ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ቤተሰቡንና ባለቤቱን ለመንከባከብ ደመወዝ የሚከፈልበት አምስት የሥራ ቀን ፈቃድ ይሰጠዋል›› በማለት ደስ የሚል ድንጋጌ አስፍሯል፡፡ አግብተው ለወለዱ ባሎች ይሄ የምሥራች ነው፡፡ ሳያገቡ ለወለዱ ባሎች መብቱ አለመሰጠቱ የሕጉ ጋብቻን የማበረታታት ዓላማውን ያሳብቃል፡፡

በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮች

ማንኛውም መብት በሕግ በተቀመጠው መልኩ ሲፈጸም ችግር እንደሚገጥመው ሁሉ የነፍሰ ጡር ሠራተኞችም መብቶቻቸውን በተመለከተ የተወሰኑ ችግሮች በተግባር ይስተዋላሉ፡፡ አሠሪዎች ሠራተኛ ሲቀጥሩ የእርግዝና ሁኔታን የመጠየቅ አዝማሚያ ባያሳዩም በአንዳንድ ጥናቶች እንደታየው ሴት ሠራተኛ መቅጠር ትርፋማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ያምናሉ፡፡ ይህ የሴቷን ሰብዓዊ መብትና መውለድ ለኅብረተሰቡ ሊኖረው የሚችለውን ሁለንተናዊ ጥቅም ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ አንዳንድ አሠሪዎች ደግሞ ለሕክምና ምርመራና ለወሊድ ክትትል ሴቷ የምታጠፋውን ጊዜ ከሕመም ፈቃድ በተለየ መልኩ ዕውቅና ያለመስጠት አዝማሚያ ይታያል፡፡

ሴቶችም ቢሆኑ መብታቸውን ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን ጊዜና በሕጉ የተቀመጠውን መብት ባለመረዳት ሦስት ወር የወሊድ ፈቃድ ከወለዱ በኋላ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ለሴቷ የሚጠቅም ሆኖ አሠሪው ከፈቀደ ተፈፃሚ የሚሆን እንጂ ሕጉ የወሊድ ፈቃድ ከመውለድ በፊት አንድ ወር ከወለደች በኋላ ሁለት ወራት የሚል በመሆኑ፣ በዚሁ መልኩ መፈጸሙ አግባብ ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ድርጅቶች ከወሊድ በፊት የተወሰደ የወሊድ ፈቃድ ሴቷ ከወለደች በኋላ ያላትን ፈቃድ እንድትጠቀም የሚያስገድዱበት ሁኔታ መታየቱ ሕገ ወጥ ነው፡፡ ከትርጉሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ከወሊድ በኋላ የሚወሰድ ፈቃድ በማንኛውም ሁኔታ ሊጀምር የሚገባው በወሊድ ጊዜ ነው፡፡ ዓላማውም የወለደችውን ሴትና ልጅ እንዲጠነክሩ ለማድረግ ነው፡፡

ሌላው ችግር ነፍሰጡሯ ያላትን የወሊድ ፈቃድ ይመለከታል፡፡ ለእንዲህ ያሉ ሴቶች ተፈፃሚ የሚሆነው የፍትሐብሔር ሕጉ አነስተኛ የወሊድ ፈቃድ ከግማሽ ክፍያ ጋር የሚደነግግ በመሆኑ፣ ለሴቶች ጠቃሚ አይደሉም፡፡ ስለዚህ አሠሪዎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተጣጣመ አሠራር ሊከተሉ ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ነፍሰ ጡር ሴት ከክፍያ ጋር የወሊድ ፈቃድ እንደሚሰጣት ስለሚደነግግ ይህን መሠረታዊ መብት የሚሸረሽር ሕግም አሠራርም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

የሠራተኛ ሕክምናን በተመለከተ በአሠሪዎች የሚገቡ ኢንሹራንሶች እርግዝናን የማይጨምሩ /Policy excluding pregnancy/ መሆናቸውም ይስተዋላል፡፡ በዚህ ረገድ የንግድ ሕጉ እርግዝና መድን እንዳይገባለት የሚከለክል ካለመሆኑም ሌላ ድርጅቶችም የእርግዝና ሕክምና ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ የጤና ዋስትና መሆኑ ቸል ሊባል አይገባም፡፡ እርግዝና መምጣቱ የታወቀ ‹‹ችግር›› /High likelihood risk/ ነው ቢባልም፣ የአረቦን ክፍያውን ከፍ በማድረግ አሠሪዎች ለሴት ሠራተኞቻቸው የሚሰጡትን ጥቅም ሊያሰፉ ይገባል፡፡ በአብዛኛው ድርጅቶች ዘንድ የእርግዝና ሕክምና በድርጅቶቹ የሚሸፈን ቢሆንም አልፎ አልፎ ዘመናዊነትንና ሰብዓዊነትን በአግባቡ ባልተረዱ የድርጅት መሪዎች ምክንያት ይህን ጥቅም ለሴቷ የማይሰጡ ድርጅቶች እንዳሉ በዕለት ተዕለት የሕይወት ተሞክሮ የምናስተውለው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች አመለካከታቸውን ሊቀይሩ ይገባል፡፡

መብቶቻቸው በተሻለ እንዲከበሩ

መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሕዝቤ ባለማወቅ ጠፍቷልና›› እንዲል የመብት አለመፈጸም ዋናው መነሻ ምክንያቱ ባለመብቶቹ መብታቸውን አለማወቃቸው ነው፡፡ መብቱን ያላወቀ መጣሱን አያውቅም፤ መፍትሔም ለመፈለግ አይተጋም፡፡ ስለዚህ ሴቶች ነፍሰ ጡር በሆኑ ጊዜ ያላቸውን መብቶች ማወቅ የሚገባቸው ሲሆን፣ የማያውቁ ከሆነ ደግሞ እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል፡፡ ካወቁ ደግሞ መብቶቻቸው ተጥሰው በተገኙ ጊዜ ለበላይ አስተዳደር አካላት፣ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወይም ለፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረብ መብታቸውን ሊጠይቁ ይገባል፡፡ መብት መጠየቅ የዘመናዊነት መገለጫ ነው፡፡ አሠሪዎችም ቢሆኑ ነፍሰ ጡር ሴት ያላት መብት እናታቸው ወይም እህታቸው ወይም ሚስታቸው ወይም ልጃቸው ሊኖራት የሚገባት ሰብዓዊ መብት መሆኑን በማመን መብት አክባሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ያለሴቶች ተሳትፎ አብዮቱ ግብ አይመታም አይደል የሚባለው፡፡ መንግሥት ‘ሕፃናት 6 ወር የእናታቸውን ጡት ቢጠቡ ጤናማ ይሆናሉ’ ከማለት ጎን ለጎን ሕጉ ያስቀመጠውን የወሊድ ፈቃድ መጠንን በመጨመር እናት ልጇን የምታጠባበትን ጊዜ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

Leave a Reply