አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም.:- መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሥራ ረዳት ሚኒስትር ቶም ማሊኖውስኪ ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር በመሆን 6ኛውን የሁለቱን ሀገራት የዲሞክራሲ፣የመልካም አስተዳደር እና የሰብዓዊ መብቶች የጋራ የሥራ ቡድን ስብሰባ መርተዋል፡፡ ይህ የጋራ የሥራ ቡድን ስብሰባ የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ተወካዮች የመልካም አስተዳደርና ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በግልፅና በስፋት የሚወያዩበት መድረክ ነው፡፡
የጋራ ግብረ ኃይሉ ከተወያየባቸው ሰፋ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ከምርጫ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያለው ሁኔታ፣ዓመታዊው የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት፣መልካም አስተዳደርን በማጠናከር ረገድ የሲቪክ ማህበረሰብ ሚና ግንቦት 7፣ የመገናኛ ብዙኃን የተሳትፎና የሥልጠና ዕድሎች፤ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የማዕድን ሀብት አጠቃቀም ግልፅነት ኢኒሼቲቭ ይገኙባቸዋል፡፡
በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማጠናከርና የፖለቲካ ብዝሃነትን ለማስፋት እንደሚሠራ ያለውን ቁርጠኝነት የገለጸ ሲሆን፤የአሜሪካ መንግሥትም ግልጽነት በተሞላበት መንገድ የተደረገ ውይይትን የሚደግፍ መሆኑን ገልጾ፤የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለመፍታት ለሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡
በመጨረሻም የሁለቱ መንግሥታት ተወካዮች የሚያካሂዷቸው የውይይት ፎረሞች በቀጣይነት መጨመር እንደሚኖርባቸውና ይህም ጥልቅ ውይይቶችን ለማካሄድ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተስማምተዋል፡፡ … Download in PDF