ጠ/ሚሩ በመኢአድ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ ተጠየቁ
Written by አለማየሁ አንበሴ
ምርጫ ቦርድ ከግማሽ በላይ የሆኑ የፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት አባላት የወሰኑትን ውሣኔ ባለመቀበልና ለፕሬዚዳንቱ ለአቶ አበባው መሃሪ በማድላት ጫና ፈጥሮብናል ብለዋል ቅሬታ አቅራቢዎቹ በደብዳቤያቸው። ከፕሬዚዳንቱ አቶ አበባው መሃሪ ጋር በማህተም ጉዳይ በፍ/ቤት ሲከራከሩ፣ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ህጋዊ አመራሮችና የም/ቤት አባላት በዝርዝር እንዲያሳውቅ ተጠይቆ፣ በተገቢው መንገድ ሳያቀርብ ቀርቷል ሲሉም ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ አመራሮችን ስለ ጉዳዩ አነጋገግረዋቸው እንደነበር የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሆኖም በጎ ምላሽ አላገኘንም ብለዋል፡ “እኛ የምናውቀው የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አበባው መሃሪ ነው፤ እሳቸው የሌሉበትን ስብሰባ አናይም፣ በማህተም የተደገፈ ደብዳቤ ስላመጣችሁ ብቻ አናነጋግራችሁም” ተብለናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ውዝግብም ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርቲው ጣልቃ ገብተው መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡
በፓርቲው ተ/ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ እንድሪያስ ኤሮ የሚመሩት እኒሁ አቤቱታ አቅራቢዎች፤ ባለፈው ጥር 15 ከግማሽ በላይ የሆኑ የማዕከላዊ ም/ቤት አባላት በተገኙበት ከፓርቲው ፅ/ቤት ውጪ ስብሰባ አድርገው፣ አቶ አበባውን ከሊቀመንበርነት በማገድ በምትካቸው አቶ እንድሪያስን መሾማቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
የፓርቲው አመራር አባል አቶ ሙሉጌታ አበበ ጉዳዩን በተመለከተ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ ጥያቄውን ያነሱት አካላት ከፓርቲው በተለያየ መንገድ የታገዱና ራሳቸውን ያገለሉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ በፓርቲው ስም እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት እንደሌለውና በዚህ እንቅስቃሴ ከቀጠሉ ፓርቲው በህግ ሊጠይቃቸው እንደሚገደድ አስጠንቅቀዋል፡፡
“ከማህተም ጉዳይ ጋር በተያያዘ እነሱ በከሰሱበት መዝገብ ነው የተሸነፉት” ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ሰዎቹ ህጋዊ እንዳልሆኑ ማስረጃ በማቅረብ መከራከራቸውንና ፍ/ቤቱም ፓርቲው በማን እንደሚመራ ከምርጫ ቦርድ ማረጋገጫ ጠይቆ፣ በአቶ አበባው መሃሪ እንደሚመራ አረጋግጧል ብለዋል፡፡
አዲስ አድማስ