Monday, 04 April 2016 07:35
ህገ ወጥ ደላሎች በአደገኛ ስልት እየተንቀሳቀሱ ነው
Written by አለማየሁ አንበሴ
• ያለምንም ወጪ ሊቢያ ድረስ አስኮብልለው በእገታ ገንዘብ ይቀበላሉ
• ወላጆች የታገቱ ልጆቻቸውን ለማስለቀቅ ንብረታቸውን እየሸጡ ነው
ህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪ ደላሎች፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በአዲስ የማታለያ ስልት ከሀገር በማስወጣት ለእንግልት እየዳረጓቸው ሲሆን በተለይ ሊቢያ ከደረሱ በኋላ ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው እንዲያስልኩ እገታ እየተፈጸመባቸው ነው ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች የጉዞ ወጪያቸው በደላሎች ሙሉ ለሙሉ ተሸፍኖላቸው ከሀገራቸው ከወጡ በኋላ ሊቢያ ሲደርሱ እንደሚታገቱና ለቤተሰቦቻቸው ስልክ ደውለው እስከ 2 መቶ ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ እንዲያስልኩ እንደሚገደዱ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከምስራቅ ኢትዮጵያ በተለይም ከጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ፣በአዲስ አበባ ጎንደር መተማ አድርገው በሊቢያ በኩል አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ታዳጊዎችና ወጣቶች የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በጅግጅጋ የሚገኙ ምንጮቻችን ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፤ደላላዎቹ ወጣቶቹን አውሮፓ እስኪደርሱ ለጉዞ የሚያስፈልገውን ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍኑላቸውና ቤተሰብ ሳያስቸግሩ አውሮፓ መግባት እንደሚችሉ፣ከዚያ በኋላ ሰርተው እንደሚከፍሏቸው በማግባባት ከሀገር ያስኮበልሏቸዋል፡፡ ሊቢያ ሲደርሱ ግን አግተው በመያዝ፣ በፍጥነት ከሀገር ቤት ገንዘብ ካላስላኩ ወዴትም መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ያስፈራሯቸዋል ተብሏል፡፡ ስደተኞቹም ወደየቤተሰቦቻቸው እየደወሉ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን በመግለጽ ገንዘብ እንዲላክላቸው ይጠይቃሉ፤ቤተሰብም ልጆቹን ከሞት ለማትረፍ መሬቱንና ያለውን ሃብት በመሸጥ ገንዘብ ይልካል ብለዋል፤ምንጮቻችን፡፡ ቤተሰቦች ገንዘቡን ለመላክ ሶማሌ ላንድ ድረስ ለመጓዝ የሚገደዱ ሲሆን ይህም የገንዘቡ ዝውውር በኢትዮጵያ መንግስት እንዳይደረስበት ታልሞ የሚደረግ ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው የካቲት 4 ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ከመጀመሪያ ልጃቸው አብዱል መጅድ አድናን ጋር ፀጉራቸውን አብረው መስተካከላቸውን የሚናገሩት አባቱ አብዱል መጅድ አድናን፤ እሳቸው ወደሚሰሩበት ጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሲሄዱ ልጃቸው ግን ከ5 የእድሜ እኩዮቹ ጋር ድንገት መሰወሩን ማታ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ማረጋገጣቸውን ይገልፃሉ፡፡
ወደ ስደት ሳይወጡ እንዳልቀረ በመጠራጠር ከጅግጅጋ እስከ አዲስ አበባ ባሉ መስመሮች ሁሉ ልጃቸውን ማፈላለጋቸውን የሚገልፁት ወላጅ አባት፤ “በመጨረሻ ከ15 ቀን በኋላ ልጄ ሊቢያ ገብቻለሁ ብሎ ደወለልኝ” ይላሉ፡፡ በሀገሪቱ ያሉትን ኬላዎች እንዴት እንዳለፉት ተአምር ሆኖብኛል የሚሉት አባት፤ “እኔ የመንግስት ደሞዝተኛ፣ ምንም የግል ንብረት የሌለኝ ሰው ነኝ፤ ገና ገንዘብ ከሰው ለምኜ ነው ልጄን ለማስለቀቅ እየሞከርኩ ያለሁት” ብለዋል፡፡
ከ17 ዓመቱ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው ጋር የጠፉት የአካባቢው ልጆች፡- አህመድ ኡመር የ7ኛ ክፍል ተማሪና እድሜው 14፣ አሚን ፈይሰል የ8ኛ ክፍል ተማሪና እድሜው 15ኛ የ8ኛ ክፍል ተማሪ እንዲሁም የ17 ዓመቱ ሃምዜ ሃሰን፣ የ9ኛ ክፍል ተማሪና የ8ኛ ክፍሉ ተማሪ አያሌ አብዱ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ኢድናን አህመድ፤ የልጃቸው ሁኔታ እረፍት እንደነሳቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በጅግጅጋና አካባቢው ያሉ በአብዛኛው ከ14 ዓመት እስከ 17 ዓመት እድሜ ያላቸው ታዳጊዎች፤ ቤተሰቦቻቸውን “ባጃጅ ግዙልን ካልሆነ ወደ ስደት እወጣለሁ” እያሉ እንደሚያስጨንቁም ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ከሰሞኑ ብቻ ከ20 በላይ እድሜያቸው በአስራዎቹ የሚገመት ታዳጊዎች በዚሁ መንገድ ወደ ሊቢያ መጓዛቸውን የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ ቤተሰቦችም ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መነሻቸውን ከምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች (ድሬደዋ፣ ሃረር፣ ጅግጅጋ)፣ መዳረሻቸውን አውሮፓ ያደረጉ ስደተኞች፤ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች አቆራርጠው ከሀገር እየወጡ መሆኑን የገለጹልን ምንጮች፤ በአንጻሩ ጅግጅጋን ጨምሮ ሃረርና ድሬደዋን የስደት መተላለፊያ ኮሪደር ያደረጉት በአብዛኛው ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከትግራይና ከወሎ አካባቢ የሚጓዙ ስደተኞች መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
አዲስ አድማስ