Wednesday, 06 April 2016 12:23

  • በ  ፋኑኤል ክንፉ

ከ118 ዓመታት በኋላ በርበራ ወደብን ለመጠቀም፣ በደብረዘይት ፊረማ ኖረ

 

በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የወደብ አገልግሎት አጠቃቀም ስምምነት ማርች 31 ቀን 2016 በቢሾፍቱ ከተማ ተፈርሟል። በዚህ የስምምነት ፊርማ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት እና በአዲስ አበባ የሶማሌ ላንድ ሚሲዮን በታዛቢነት ታድመው ነበር። እንዲሁም ሌሎች ዲፕሎማቶች በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የፊርማው ስነስርዓት የተደረገው በኤጀንሲዎች ደረጃ ነው። ከኢትዮጵያ በኩል የማሪታይም ባለስልጣን ጉዳዮች ሲሆን በሶማሌ ላንድ በኩል የበርበራ ወደብ አስተዳዳሪ ባለስልጣን ናቸው። በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ እንተገለጸው፣ ስምምነቱ ዓለም ዓቀፍ ቅርጽ እንዲኖረው እና ከሶማሌላንድ እውቅና ጋር በተያያዘ የሚንጸባረቁ ነገሮች እንዳይኖሩት በከፍተኛ ጥንቃቄ በዓለም ዓቀፍ ሕግ መሰረት እንደሚሰራ ማረጋገጫ ቀርቧል። እንዲሁም ስምምነቱ አስፈላጊውን ዓላማ ማሳካት በሚችል መልኩ ይደረጋል ተብሏል።

ታረካዊ ዳራው

በኢትዮጵያ በኩል የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ፍላጎት የነበረው በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ነበር። በዚያን ወቅት ሶማሌ ላንድ በቅኝ ግዛት ሲያስተዳድር የነበረው የእንግሊዝ መንግስት በርበራ ወደብን ከአዲስ አበባ ጋር በባቡር መንገድ ለማስተሳሰር ከአፄ ሚኒልክ ጋር በትብብር ለመገንባት እቅድ እንደነበረው ማጣቀሻዎች ያሳያሉ።

ሆኖም ግን በወቅቱ በተፈጠረ ፖለቲካዊ ምክንያት ዝርጋታው ተቋርጧል። የታሪክ ድርሳናት ያስቀመጡት ፖለቲካዊ ምክንያት በእንግሊዝና በፈረንሳይ መካከል በተነሳ ግጭት የእንግሊዝና የአፄ ሚኒልክ ስምምነት መፍረሱን ነው። ይኽውም፣ ፈረንሳዮች ከዳካር እስከ ጅቡቲ (ከምዕራብ ወደ ምስራቅ) እንግሊዞች ደግሞ … ካይሮ (ከደቡብ ወደ ሰሜን) በዘረጉት የማስፋፋት ዕቅድ ተከትሎ በሱዳን ውስጥ ፋሾዳ በተባለ ቦታ ላይ እ.ኤ.አ. 1898 የእቅዳቸው አማካኝ ስፍራ ሆና በመገኘቷ ማን ያስተዳድረው በሚል ግጭት ውስጥ መግባታቸው ነበር። በታሪክ “The Fashoda Crisis” ተብሎ ይታወቃል፡፡

በወቅቱ እንግሊዝ በቅኝ ግዛት ከምታስተዳድራቸው ሀገሮች በቂ የጦር ሰራዊት የነበራት በመሆኑ ወደ ጦርነት ውስጥ ለመግባት የማንም እገዛ አላስፈለጋትም። በአንፃሩ ፈረንሳይ የያዘችው ጦር ሠራዊት እንግሊዝን ለመግጠም የሚያስችላት ባለመሆኑ አፄ ሚኒሊክን እገዛ ጠይቃለች። በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በዓድዋ ተራሮች ላይ በፈጸመው ታሪካዊ ገድል በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ስሙ የናኘ ሃይለኛ ሃይል ነበር። አፄ ሚኒሊክም ፈረንሳይን ለማገዝ ፈቃዳቸውን በማሳየታቸው፣ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር መቃቃራቸው ድርሳናት ይናገራሉ። የእንግሊዝ እና የአፄ ሚኒሊክ ስምምነት ቢፈርስም፣ በምትኩ ግን በፈረንሳይ መንግስትና በአፄ ሚኒሊክ በተደረሰው ስምምነት ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የባቡር መንገድ ዝርጋታ ተከናውኗል። ዛሬ ላይ  በአፄ ሚኒልክ የተጀመረው አዲስ አበባ ከበርበራ ጋር ለማገናኘት በተግባር ተፈጽሟል።

በርበራን ለመጠቀም ለምን?

ኢትዮጵያ የገቢ እቃዎቿ መጠንና አይነት በየዓመቱ እየጨመር መጥቷል። አሁን ላይ በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ቶን እቃዎች በጅቡቲ ወደብ በኩል ታስገባለች። የጅቡቲ ወደብ በአንፃሩ ይህን መጠን ያህል እቃዎች ለማስተናገድ ከአቅሙ በላይ ነው። የጅቡቲ ወደብ ካለው የሰው ኃይል፣ አደረጃጀት እና ፋሲሊቲ አንፃር ይህን ያህል መጠን ሊያስተናግድ አይችልም። በተለይ ዘንድሮ ከድርቅ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ግዢ በመፈጸማቸው የገቢውን እቃ መጠን ከፍ አድርጎታል። እንዲሁም የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ በመዝነቡ የማዳበሪያ አቅርቦት ፍላጎትን በመጨመሩ ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ሁኔታ የማዳበሪያ ግዢ ተፈጽሟል፣ ግዢውንም የተፋጠነ አድርጎታል። ከሚገባው የእርዳታ እህል በተጨማሪ በእህል ንግድ ድርጅት በኩል ለተጠቃሚዎች የሚደርስ ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴ ግዢም ተከናውኗል።

ይህ ጽሁፍ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ አስራ ስድስት የጭነት መርከቦች በባሕር ላይ ቆመዋል። አንድ ማዳበሪያ የጫነ መርከብ እና አስራ አምስት ስንዴ የጫኑ መርከቦች ማራገፍ ባለመቻላቸው ባሕር ላይ መቆየት ግድ ሆኖባቸዋል። እንዲሁም ሰባት ጭነት የተሸከሙ መርከቦች ወደብ ተጠግተው እያራገፉ ይገኛሉ። ይህ ከተለመደው አሰራር ውጪ ሲሆን በተለምዶ ሶስት መርከቦች ብቻ ናቸው ወደብ ተጠግተው የሚያራግፉት።

ይህን ችግር በመረዳት የጅቡቲ መንግስት  ከሶስት ወደ ስድስት ሰባት መርከቦች ወደብ ተጠግተው እንዲያራግፉ ተባብሯል። ሆኖም ግን ከሁለት ወር በላይ ወረፋ የሚጠብቁ መርከቦች በመኖራቸው አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ምርጫ አልባ ሆኗል። ከዚህም በላይ በእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ እቃዎች አስር በመቶ የሚሆነው ጭነት በሱዳን ወደብ ለመጠቀም፤ እንዲሁም ሰላሳ በመቶ የሚሆነውን በበርበራ ወደብ ለመጠቀም በእቅድ ሰፍሮ ተቀምጧል። ቀሪውን ስልሳ በመቶ ጭነት በጅቡቲ ለማስገባት የታቀደ ነው።

ከዚህ አንፃር አስገዳጅ ሁኔታዎች መፈጠራቸው ብቻ ሳይሆን ቀጣዩን የኢኮኖሚ መጠን በመገመት በርበራን ወደብ ለመጠቀም ቀድሞ የሰፈረ እቅድ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በርበራ ወደብን ለመጠቀም ብዙ ሙከራዎች ከዚህ በፊት ተደርገዋል። ለውጤት የበቃ ወደ ኦፕሬሽን የተገባበት አግባብ ግን አልነበረም። ምንአልባት ሊጠቀስ የሚችለው እ.ኤ.አ. በ2005 በተደረገ ስምምነት የመብራት ኃይል ንብረት የሆኑ 900 ኮንቴነሮች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸው ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ የተደረገ አንድም አይነት ኦፕሬሽን የለም።

የበርበራ ወደብን እና ፖለቲካዊ አንደምታዎቹ

ሶማሌላንድ የቀድሞ የሶማሌ ጠቅላይ ግዛት አንድ አካል እንደነበረች የሚታወቅ ነው። በዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ እውቅና ባይሰጣትም በራሷ ጊዜ ነፃ ሀገር መሆኗን ማወጇ የሚታወቅ ነው። በተለይ የአፍሪካ ሕብረት ለሶማሌላንድ እውቅና ያልሰጠ ተቋም በመሆኑ፣ ኢትዮጵያም ለአፍሪካ ሕብረት ቻርተሮች ፈራሚና ተገዢ በመሆኗ እውቅና የሰጠችበት አግባብ እስካሁን የለም።

ሆኖም ኢትዮጵያ የበርበራ ወደቦችን ለመጠቀም አያስችላትም ተብለው ከሚሰጡት ምክንያቶች መካከል ፖለቲካ አንደምታቸው ከፍ ያሉት ይበዛሉ። እውነተኛው ምክንያት ግን በበርበራ ወደብ ያለው ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የፋሲሊቲ አቅርቦቶች እና የኢትዮጵያ መንግስት ወደቡን ለመጠቀም የነበረው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው። ምክንያቱም ከሶማሌላንድ ጋር የተለያዩ የንግድ አገልግሎቶችን የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕዝብ ያከናውናሉ። በተመሳሳይም ከበርበራ ወደብ የሚገኘው አገልግሎት እንጂ የተለየ አንዳች ነገር የለም። ለዛውም ተራ የወደብ አገልግሎት። ይህ የወደብ አገልግሎት ለሶማሌላንድ ፖለቲካዊ እውቅናን ከመስጠት ጋር አንዳችም ተዛምዶ የለውም። ምክንያቱም በሌሎች የንግድ ዘርፎች ተመሳሳይ አገልግሎቶች እየተለዋወጡ ያሉ አካሎች የወደብ አገልግሎት ላይ ሲደርሱ ፖለቲካዊ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።

ከውጭ ግንኙነት ፖሊስ አንፃር

ከኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንፃርም ቢታይም ተገቢነቱ ከፍ ያለ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በተለይ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ኢኮኖሚያዊ ትስስር መፍጠር የፖሊሲው የማዕዘን ድንጋይ ነው። በአጠቃላይ አገላለጽም፣ በቀንዱ ሀገሮች መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር፣ በአስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ላይ የቆመች፤ ሰላሟ የተረጋጋ ምስራቅ አፍሪካን መፍጠር ትልቁ ስዕሉ አድረጎ የሚንቀሳቀስ መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው። ለዚህ ራዕይ ማሳያ የሚሆነው ከጅቡቲ የተደረገው የሃይል፣ የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የውሃ፣ የባቡር እና የወደብ አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ነው። በሁለቱ መንግስታት የተፈጠረው ግንኙነት ከሁለትዮሽ ትብብር ባለፈ ለአህጉራዊ ትብብሮች ማሳያ ተደርጎ ቢወሰድ የተጋነነ አይሆንም።

እቅዷንም ለማሳካት ኢትዮጵያ ከአጎራባች ሀገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመዘርጋት የሚጠቅባትን ኃላፊነቶች ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ቀድማ አሳክታለች። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ እስከ በርበራ ባለው የመንገድ ርዝመት ውስጥ ከአዲስ አበባ እስከ ቶጎ ጫሌ ድረስ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ መንገድ ተዘርግቷል። በሶማሌ ላንድ በኩል ከቶጎ ውጫሌ እስከ በርበራ ድረስ የ241 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን በአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ ከፊሉን ደግሞ በራሳቸው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መንገዱን ዘርግተዋል። የመንገዱ ደረጃ ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ጥገና የሚያስፈልገው ቢሆንም ኦፕሬሽን ለመጀመር በሚያስችል ደረጃ ዝግጁ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

ከጂኦ ፖለቲካ አቀማመጥ አንፃር

ከጂኦ ፖለቲካ አቀማመጥ አንፃር ሲታይ፣ የጅቡቲ ወደብ ለምስራቁና ለመካከለኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አመቺነቱ ከፍተኛ ነው። የኬኒያ ወደቦች ለደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በጣም ቅርብና አመቺ ናቸው። የሱዳን ወደቦች ለሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል አመቺዎች ናቸው። የበርበራ ወደብ ለምስራቁ የሀገራችን ክፍል ቅርብና አመቺ ወደብ ነው። ከላይ ከሰፈረው አንፃር ለወደብ አጠቃቀም ቁልፍ መለኪያው ቅርበት እና የፋሲሊቲ አቅርቦት መሆኑ አሻሚ አይደለም። እነዚህ ሁለት ነገሮች ከተሟሉ አቅራቢያ የሚገኙ ወደቦችን መጠቀም ብልጠት ነው። ይህም በመሆኑ የትኛውም የኢትዮጵያ አጎራባች ሀገሮች የወደብ አጠቃቀሟን ሊጠራጠሩ አይችሉም፣ አይገባምም።

በተለይ ወደብ አልባ ሀገሮች ዓለም ዓቀፍ እውቅና ያለው “right of transit” መሰረታዊ መብታቸው ነው፡ የዓለም ዓቀፍ ንግድ ዘጠና በመቶ የሚሆነው የሚስተናገደው በባሕር አገልግሎት ዘርፍ ነው። ከዚህ አንፃር የአገልግሎት መለኪያው ወደብ አልባ ሀገሮች የመጠቀም አለመጠቀማቸው ነው እንጂ፣ የወደብ ባለቤት የሆኑ ሀገራት ከሚያገኙት ጥቅም አንፃር የሚመዘን አይደለም።

ስጋቶች

በኢትዮጵያ በኩል ከኤርትራ ወደ ጅቡቲ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣ የጅቡቲን ወደ ለማልማት የዱባይ ባለሃብቶች ጠይቀው ወደስራ የገቡበት ሁኔታዎች ናቸው ያለው። አሁን ላይ ደግሞ የጅቡቲን ትልቁን ወደብ እና የአሮጌ ተርሚናል ቦታዎችን ከቻይናዎች ጋር በሽርክና ለመስራት የጅቡቲ መንግስት ተስማምቷል። በሌላ በኩል ለጊዜው ባንጠቀምበትም የኤርትራ ወደቦች በአረብ ሀገሮች ሊዝ ተደርገው ተይዘዋል።

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በኩል የጅቡቲን ወደብ በጋራ ለማልማት የቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው። አሁን ላይ ደግም በርበራን ለመጠቀም የተደረሰው ስምምነት በጋራ ማልማት ላይ ያተኮረ ካልሆነ ለሌላ ሶስተኛ ወገን ከሶማሌላንድ ጋር በጋራ ለማልማት ሊስማሙ ይችላሉ። መብታቸው ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የምታቀርበውን በጋራ ወደብን የማልማት ጥያቄዎች ውድቅ እያደረጉ ዙሪያዋን ከሶስተኛ ሀገሮች ጋር በመሆን የሚሰሩ ከበባዎች አንድምታቸውን መፈተሸ ተገቢ ነው የሚሆነው። በተለይ ከኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጥቅሞች ጋር በተቃርኖ ከሚቆሙ ሀገሮች ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች የወደፊት የስጋት ምንጭ እንደሚሆኑ ታውቆ ዛሬ ላይ መስራት ብልህነት ነው።

ኢትዮጵያት በጣም ትልቅ ሀገር ነች። በዓለም ከሕዝብ ቁጥር አንፃር አንደኛው ወደብ አልባ ሀገር ናት።

ስንደቅ

Leave a Reply