በይርጋ አበበ
Wednesday, 06 April 2016

ኢህአዴግ ከብሔራዊ መግባባት ይልቅ ብሔራዊ መምታታት እየሰራ ነው

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንደነት መድረክ (መድረክ) “አገሪቱ በዚህ መንግስት የአገዛዝ ስርዓት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች” በማለት በጽ/ቤቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር መገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በሚያስብል መልኩ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ፓርቲው“በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከዳር እስከ ዳር እየተስፋፉ ያሉት የሕዝብ ምሬቶችና ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መንስኤ ፀረ ዴሞክራሲያዊው የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ የፈጠረው ብልሹ አስተዳደር መሆኑን ምልአተ-ሕዝቡ ከመራር የሕይወት ልምዱ እና ተሞክሮዎቹ የተገነዘበው ጉዳይ ነው። የሕዝቡን ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከፋሽስታዊ ጭካኔ ባልተናነሰ ሁኔታ የመጨፍለቅ እርምጃ እየወሰደ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት፣ የሀገራችንን ችግሮች በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ብቻ በማሳበብ የሽንገላ መግለጫዎችን እየሰጠ መሆኑን መድረክ በትዝብት እየተከታተለ ውይገኛል” ሲል ነው የገለጸው።

ፓርቲው አያይዞም “ኢህአዴግ መሠረቱ ሕዝባዊ ውክልና የሌለው አምባገነን መንግሥት በመሆኑ የሕዝቡን ምሬትና የተቃውሞ እንቅስቃሴን ከዚህ በላይ እንደተገለጸው በአገዛዙ በሰፈነው ብልሹ አስተዳደር ላይ ብቻ ለማሳበብ ይሞክራል። በሌላ አንጻር ደግሞ የሕዝቡን ሕገመንግሥታዊ፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጣስና በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በሰላማዊ አግባብ በዚሁ ብልሹ አስተዳደሩ ላይ ተቃውሞአቸውን የገለጹትን ዜጎች በገፍ እያፈሰ ማሰሩንና ማሰቃየቱን እያባባሰው ይገኛል። በሀገሪቱ ለሚካሄደው ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተግባር እየሰጠ ያለው ምላሽም በተቃውሞ እንቅስቃሴው ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ዜጎች ሁሉ ከየመኖሪያ ቤታቸውና ከየሥራ ቦታቸው እያፈሰ ከማሰርና ከማሰቃየት አልፎ፣ እንደ ደርግ መንግሥት ዘመን እየገደሉ በየቦታው አስከሬን መጣል ድረስ የደረሰ ሆኗል” ያለ ሲሆን በተለይ የመድረኩ አባል በሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላትና አመራሮች ላይ እየተወሰደ ያለውን እስር በተመለከተም “አገዛዙ በብልሹ አስተዳደሩ ላይ በሰላማዊ አግባብ ተቃውሞ በማሰማታቸው የታሰሩትንና በተለያዩ እስር ቤቶች ታጉረው የሚገኙትን የኦፌኮ/መድረክ የአመራር አባላት፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም በአገዛዙ ላይ ምሬታቸውንና ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የተንቀሳቀሱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን ከእስር በመፍታት ረገድ አንዳችም ተጨባጭ እርምጃ ሳይወስድና በአገዛዙ በግፍ ለተገደሉ ዜጎችም ኃላፊነት ወስዶ ተጠያቂዎችን ለሕግ ሳያቀርብ፣ አሁንም ተቃውሞ አሰምታችኋል ባላቸው ዜጎች ላይ ሕገ ወጥ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ የሕግ የበላይነት የሌለበት ሥርዓተ መንግሥት መሆኑን ግልጽ ያደርገዋል” ሲል ገልጿል።

የፓርቲው አመራሮች በጽ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የፓርቲውን መግለጫ ተመርኩዘው ወቅታዊ ጥየቄዎችን አቅርበው ነበር። የመድረክ አመራሮችም ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ጥያቄ፡-በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። በሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ከገዥው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው መድረክ በውይይቱ ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው? የፓርቲዎቹንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውይይትስ መድረክ እንዴት ያየዋል?

መልስ፡- አንደኛ የጋራ ምክር ቤት የተባለው መነሻ መሰረቱ ከኢህአዴግ ጋር መሰረታዊ የአቋም ልዩነት የሌላቸውን ጥቂት በምርጫ ቦርድ በፓርቲነት የተመዘገቡትን ፓርቲዎች በአባልነት አሰባስቦ የያዛቸውን ነው ኢህአዴግ “የጋራ ምክር ቤት” እያለ የሚጠራው። በዚህ ምክር ቤት ውስጥ እኛ (መድረክ) መግባት ያልቻልንበትን ምክንያት ደጋግመን የገለጽነው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አንድ የምርጫ ስነ ምግባር የተባለ ሰነድ ፈርሙ ተብለን እኛ ደግሞ የህግ አግባብ የሌለው ሰነድ ነው ፈርሙ የምትሉን ብለን አቋም የወሰድንበት ሰነድ ነው ፈርሙ የምትሉን ብለን ነው የቀረነው።

ነገር ግን እነዚህ ግድ የሌላቸው በፓርቲ ስም የተቋቋሙ የሚጠሩ ወገኖች ከኢህአዴግ ጋር መሰረታዊ የመርህ ልዩነት ማንጸባረቅ ዓላማቸውም ሆነ ያንን ለማድረግ ብቃቱ የሌላቸው ስለሆኑ ሂደው ፈረሙና ተሰባሰቡ። ኢህአዴግ እነዚህ ፓርቲዎች ለህዝብ ግንኙነት ፍጆታ ነው የሚጠቀምባቸው። በተለይ ለጋሽ አገራት ለምንድን ነው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብራችሁ የማትሰሩት ሲባል ይሄው አብረን እየሰራን ነው ለማለት ነው የሚጠቀምባቸው።

የፓርቲዎቹ ዓላማም የጥቅም ፍላጎት ነው። ለምሳሌ በፓርቲዎች ህግ ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ባላቸው ወንበር ልክ የመንግስት ገንዘብ ድጎማ ይደረግላቸዋል ይላል። እነዚህ ፓርቲዎች ግን እንኳን ፓርላማ ገብተው ወንበር ሊይዙ ቀርቶ ምን ያህል ድምጽ እንዳገኙ እንኳን የተገለጸ አይደለም። እነዚህን ስብስቦች ነው ኢህአዴግ በችሮታ ከመንግስት ካዝና ለመንቀሳቀሻ ሳንቲም የሚሰጣቸው።

መድረክ ለምን በውይይቱ አልተገኘም ለተባለውም መልሳችን መድረክ ከእነዚህ አይነት ፓርቲዎች እኩል ለመሰለፍ የፓርቲያችን ተክለ ሰውነትም ሆነ ክብራችን አይፈቅድም። ምክንያቱም መድረክ አገራዊና ህዝባዊ ዓላማ ያለው ፓርቲ ስለሆነ ከዚህ አይነት ርካሽ ጥቅምና መሞዳሞድ አልፎ ለህዝባችን ነጻነትና ክብር የሚታገል ፓርቲ ነው። ያ ስብስብ (የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱን) ከቆምንበት ዓላማ ተነስተን ስናየው ተገቢ መድረክ (ምክር ቤት) አደለም።

 ከዚህ ሌላ ደግሞ በውይይቱ ተሳታፊነት ሳይሆን በታዛቢነትም ባይሆን ተገኙ ተብለን አልተጠራንም። ይህን ያደረጉት ደግም (ኢህአዴጎችን) እኛን ጠርቶ ለመወያየት ድፍረቱ ስለሌላቸው ነው። በእውነቱ ይህ ብሔራዊ መግባባት ሳይሆን ኢህአዴግ እየፈጠረ ያለው ብሔራዊ ማምታታት ለመፍጠር ነው። ይህ ብሔራዊ ማምታታት ውሎ አድሮ የት ያደርሰናል የሚለውን ደምረን ቀንሰን የምንሰራው ይሆናል።

ጥያቄ፡-ጋዜጣዊ መግለጫ ስትጠሩ “በወቅታዊ የአገራችን ጉዳዮች ላይ” ብላችሁ ነበር። አሁን መግለጫችሁን ስንመለከተው ግን በተወሰኑ ክልሎች ላይ ብቻ (የመድረክ አባል ፓርቲዎች ባሉባቸው ክልሎች) ያተኮረ መረጃ ነው ያቀረባችሁት። በሌሎቹ የአገራችን ክፍሎች ችግሮቹ የሉም ማለት ነው ወይስ እናንተን ስለማይመለከታችሁ ነው ያላቀረባችሁት?

መልስ፡- በእውነቱ ይህ ጥያቄህ የመድረክን ዓላማም ሆነ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ገላጭ አይደለም። መግለጫችንን በደንብ ካየኸው ብሶቱና ምሬቱ በመላው አገሪቱ ሰፍኗል ነው ያልነው። እነዚህን አካባቢዎች የጠቀስነው “ለአብነት” ያህል እያልን ነው የጠቀስነው። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ አርሶ አደር ተቸግሮ እያለ “የማዳበሪያ እዳ ክፈል” ተብሎ ያልተገደደበት ክልል የለም። እኛ ግን አንድ ነገር ስንናገር እስቲ መረጃ አምጡ ብንባል ማቅረብ የምንችለውን ማስረጃ ይዘን “ለመድረክ ጽ/ቤት” የደረሱ መረጃዎች ብለን ነው የምንናገረው። ይህ ደግሞ ጥንቃቄን ያሳያል። አሉባልታ ማውራት አልፈለግንም። አሉባልታ ማውራት የመድረክንም ሆነ የእኛን ክብር አይመጥንም እንጂ መጀመሪያ ስንነሳ “አገራዊ ችግር” ብለን ነው የተነሳነው።

አቅማችን በፈቀደ መጠን ችግር ያለበትን ሁሉ መረጃ እንዳገኘን የህዝቡን ብሶት ለማስተጋባት አቅማችንን እና ብቃታችንን የምንቆጥብ አይሆንም። ይህንም አስረግጠን ለመግለጽ እንወዳለን። መግለጫው ማንንም የለየ አይደለም።

ጥያቄ፡- ዶክተር መረራ በቅርቡ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲሄዱ ፓስፖርተዎን ሲስተሙ ሊያነበው ባለመቻሉ ከጉዞ እንዲቀሩ ተደርገዋል። ወደ አሜሪካ ሊሄዱ የነበረው በምን ምክንያት ነው? አሁንስ ችግረዎ መልስ አግኝቷል?

መልስ፡- ከ30 ዓመታት ላላነሱ ጊዜያት ነው ሲስተሙ ፓስፖርቱን ሊያነብ አይችልም ተብሎ ሲመለስ። እኔን እንደዛ ብሎ የመለሰኝ የክፍሉ ኃላፊ ስሜን ያውቃል የቪዛ ቁጥሩ በግልጽ ይታያል። በዚህ አይነት መልኩ (ሲስተም አያነብም ተብሎ) ተጓዥ ከኤርፖርት የሚመለስበት ሁኔታ የለም ነበር። ለሚመለከተው የኢሚግሬሽን ባለስልጣን ጠይቄያለሁ። አጣርቼ እነግርሃለሁ ስልክ ቁጥር ይዘህ ሂድ ቢለኝም ጸሃፊዎቹ ግን ደውለን እንነግርሃለን ብለው ቢያሰናብቱኝም ይሄው እስከዛሬ (እስከ ዓርብ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም) የተነገረኝ ነገር የለም።

ይህንን ሳይ በእኔ ላይ የተለየ ነገር እየተደረገብኝ እንደሆነ ነው ለማወቅ የቻልኩት። ምክንያቱም በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት እኔን ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያስተማሩኝ አሁንም በማስተማር ስራቸው ላይ ቢሆኑም እኔን ግን ‘ጡረታ ውጣ’ ብለው አስወጥተውኛል። ምናልባት የኦሮሞ ወጣቶች ውስጥ ችግር ይፈጠራል ብሎ ኢህአዴግ ሰግቶ ይሆናል እንደዛ የሚያደርግብኝ። ነገር ግን በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ኢህአዴግ ይህን በማድረጉ አላተረፈም። ምክንያቱም የኦሮሞ ወጣቶች ከእኔ ጋር ባልተገናኘ መንገድ መብታቸውን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት።

ወደ አሜሪካ የሚሄዱበት ምክንያት ምን ነበር ላላችሁኝ የምሄደው አሜሪካን አገር ያሉ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ያቋቋሙት ራዕይ ኢትዮጵያ የተባለ የምሁራን ስብስብ ያለበት ተቋም ነው የጋበዘኝ። በዚያ ቦታ ሂጄ ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳቀርብ ነበር የተጋበዝኩት። መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላቀርበው የነበረውን ጽሁፍ ኮፒ ልታዩት ትችላላችሁ።

ጥያቄ፡- በጋዜጣዊ መግለጫችሁ ላይ ካቀረባችሁት መረጃ ውስጥ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን የገለጻችሁበት ይገኛል። ለመሆኑ በዚህን ያህል መጠን ዜጎች ለእስር የተዳረጉት በምን ምክንያት ነው?

መልስ፡- ምክንያቱን የሚያውቀው ኢህአዴግ ነው። ይህንን ጥያቄ ለምን እነሱን (ኢህአዴጎችን) አትጠይቋቸውም። በእኛ በኩል ግን እስራቱን የምናየው ለመቀጣጫ ለመጠቀም ነው። “እሱን ያየህ ተቀጣ” እያሉ ሌሎች ክልልችን አስፈራርቶ ቤቱ እንዲቀመጥና ኢህአዴግና ስርዓቱ እንዳፈቀደው እንዲፈነጭ ለማድረግ ነው።

ሌላው የእስሩ ምክንያት ኢህአዴግ አፍኖ ለመግዛት ሰለሚፈልግ ነው። በሰለጠነው ዓለም ሰው የሚታሰረው በሰራው ወንጄል ነው። እኛ ጋ እየተደረገ ያለው ግን ገና ወንጀል ሊሰራ ይችላል (Preventive Detention) ብሎ በግምት ታስቦ ነው እያሰረ ኢህአዴግ ያለው።  ይህ አይነት አሰራር ደግሞ በጥቂት የአፍሪካ አገራትም ይታያል። አሁን አሁን ደግሞ እየከፋ ያለው ማሰሩ ሳይሆን የታሰሩበትን ቦታ በመሰወር ቤተሰባቸው እንዳይጠይቃቸው ማድረግ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጸመ ያለው ሌላው ከባድ ወንጀል ደግሞ “ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማይማሩት በእናንተ ምክንያት ነው” እየተባሉ መምህራንን እያሰሩ እና አይቀጡ ቅጣት እየፈጸሙባቸው ይገኛል። በክልሉ (በኦሮሚያ) አብዛኛው ትምህርት ቤቶች ስራ አቁመዋል። ብጥብጡን ተቆጣጥረናል ቢሉም የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ እየተጠበቁ ነው የሚወጡትና የሚገቡት። ግድያውና እስራቱም አልቆመም ጨመረ እንጂ። እንዲያውም በቅርቡ በደረሱን መረጃዎች እንደ “ጦላይ” ያሉ የመከላከያ ማሰልጠኛዎች ሳይቀሩ ለማሰሪያነት እያገለገሉ መሆኑን ነው።

በአጠቃላይ ስንመለከተው ኦሮሚያ ውስጥ ኦህዴድ ከሞላ ጎደል እየሰራ አይደለም። ስራም አቁሟል። ክልልን እያስተዳደረ ያለውም ሰራዊቱ ነው። በክልሉ አሁን አሁን ግብር እየተሰበሰበ ያለው እንደ ድሮው በኦህዴድ ባለስልጣናት ሳይሆን በሰራዊቱ ሆኗል።

ጥያቄ፡- በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች የአገራችን ክፍሎች የማንነት ጥያቄ በጣም ገንኖ እየወጣ እና የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ። ጥያቄዎቹን ተከትሎም ችግሮች ይፈጸማሉ። ይህ የማንነት ጥያቄ በመድረክ አመለካከት በአሁኑ ጊዜ ከርሮ የተነሳበት ምክንያት ምንድን ነው? መፍትሔው መሆን ያለበትስ ምንድን ነው?

መልስ፡- ማንነት ማለት ህዝቦች ወይም ቡድኖች ‘በዚህ መልክ እንታወቅ’ ወይም ‘የአስተዳደር ክልል ይኑረን’ ብለው ሲጠይቁ ነው።በዚህ መልክ እንታወቅ ብለው ሲነሱ የህዝቡ መጠሪያ ስም ይህ ነው ብለው ሲነሱ ነው። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸውን የማረጋገጥ መብት አላቸው ይላል። ይህን ተመልክቶም ከመንግስት ለውጥ በኋላ ብዙ መነሳሳቶች ነበሩ። ከዚህ በፊት የምጠራበት አባባል ሌሎች ወገኖች ካላግባብ የሰጡን ነው የሚሉ ጥያቄዎች ባለፉት 25 ዓመታት ሲነሱ የነበረ ነው።

ይህ እንግዲህ ህጋዊና ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ ‘በዚህ መልኩ እንታወቅ’ የሚሉ ጥያቄዎችን አታንሱ ብሎ መድረክ አይቃረንም። ነገር ግን ጥያቄዎቹ መነሳት ያለባቸው ራስን አሳውቆ ሌላውን ለማግለልና ለመበደል ወይም በአገሪቷ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ጥያቄ የሚጭር መልክ ይዞ መቅረብ የለበትም ነው የምንለው። ለምን በዚህ ጊዜ ሆነ ለሚለው ጥያቄ ግን ከጠያቂው ጋር አንስማማም። ምክንያቱም ጥያቄዎቹ ሲነሱ የነበሩት አሁን ብቻ ሳይሆን ላለፉት 25 ዓመታት በተለያዩ መልኩ ሲነሱ ነው የቆዩት። ፊትና ኋላ የመሆን ጉዳይ አለ እንጂ ጥያቄው ሲነሳ አሁን አይደለም። ወደፊትም ይነሳሉ።

እነዚህ ጥያቄዎች በሰላማዊ አግባብና ህገ መንግሰቱ በሚፈቅደው መሰረት ከተነሱና በሰላማዊ አግባብ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት እስከተደረገ ድረስ ክፋቱ እና ለእኛም ለቀረነውም ስጋት የሚሆንበት ምክንያት አይኖርም። ግን ዋናው ነገር ለሚነሱ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍትሔ ለማግኘት እንቅስቃሴ ከማድረግ የሚድነው ይህን አገር በዴሞክራሲያዊ አግባብ ሁሉንም ግለሰቦችና ቡድኖች ያለ አድልዎ የሚያስተዳድር ስርዓት ሲፈጠር ብቻ ነው።

ነገር ግን ኢህአዴግ እንዳሻው እንደፈለገ ‘ለእኔ ድጋፍ ይሰጠኛል’ የሚለውን ወገን እየደገፈ ሌላውን ደግሞ እያፈነ ብዙ በደሎች እየደረሱ እንዳለ እናውቃለን። ይህ ደግሞ የጠቅላላው ችግራችን አካል ነው።

አሁን ያለውን የማንነት ጥያቄ የኢህአዴግ ደጋፊዎች አቅልለው ሊያዩት ይችላሉ። እውነታው ግን እጅግ በጣም አደገኛ በሆነ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው አገሪቱ የምትገኘው። ይህ የመጣው ደግሞ ላለፉት 25 ዓመታት ኢህአዴግ ብሔራዊ መግባባት ከመፍጠር ይልቅ ብሔራዊ ማምታታትን በመስራቱ ህዝቦች ራሳቸውን ያስተዳድራሉ እያለ መሬት ላይ ያለው ግን የሞግዚት አስተዳደር ነው የዘረጋው።  እርግጠኛ መሆን የማልችለው የትግራይ ክልልን ነው እንጂ አሁን የትም ቦታ ሂዳችሁ ብታዩ ምናልባት ማን ማንን ያስተዳድራል የሚባለው ግልጽ ነው። የሞግዚት አስተዳደርን ነው የጫነው። ከሶቭየት ህብረትና ዩጎዝላቪያ የምንማረው አገርን የሚያፈርሰው ሀሰተኛ ምርጫ እና እንደዚህ አይነት የሞግዚት አስተዳደር ነው።

ጥያቄ፡- የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በቅርቡ ባካሄደው ግምገማ ከ300 በላይ አመራሮቹንና አባሎቹን እርምጃ እንደወሰደባቸው ተናግሯል። እርምጃ የወሰደባቸው አባሎቹ ድግሞ ከታችኛው ርከን ላይ ያሉ አመራሮቹን እንጂ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን አይደለም እየተባለ ይነገራል። ይህ ውሳኔ ፖለቲካዊም ሆነ ህጋዊ አንድምታው ምንድን ነው?

መልስ፡- ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሰርቶ የመኖር መብት አለው። ሰርቶ የሚኖረው ደግሞ በብቃቱ እና በትምህርት ዝግጅቱ ነው መሆን የሚገባው። ምናልባት አሁን የጠየቃችሁት የኦህዴድ አባላት የተባሉት የፖለቲካ ሹመኞች ሊሆኑ ስለሚችሉ እና የፖለቲካ ሹመኛን ደግሞ ሲፈልጉ የሚሹሙና ሲፈልጉ የሚሽሩ ስለሆነ ምንም ማለት አይቻልም። ለዚህ ደግሞ በአንደ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው” ብለው መናገራቸው ይታወሳል። ሹመኞቻቸውም በዚህ መመሪያቸው መሰረት ማለትም በአለቆቻቸው ትዕዛዝ መሰረት የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ባላቸው ችሎታ ተነስተው መብት ኑሯቸው ሳይሆን እንዲሁ ዝም ብለው ያስቀመጧቸው በመሆኑ እነዚያን ወዲህና ወዲያ ቢያንከረባብቱ ምን ይደንቃል።

በመጀመሪያ አሰናባቹ አካልም ቢሆን ህገ ወጥ ነው። አባራሪው ራሱም ብቃት ኖሮት ተወዳድሮ የተቀመጠ አይደለም። የህግ የበላይነት መስፈን አለበት። እያንዳንዱ ሰራተኛ መብቱ ሊከበር ይገባል በህግ አግባብ። ያለ ችሎታው መቀመጥም የለበትም። ያለ ችሎታው ከተቀመጠ የሚመለከተው አካል እርምጃ መውሰዱ አይቀርም በየትኛውም ዓለምም የተለመደ ነው።

እንዳላችሁት የላይኞቹ አልተነኩም። ኢህአዴግ ብዙ ጊዜ የሚነካቸው ለእሱ መላክ ያልፈለጉትን ወይም ያቃታቸውን  ሲሆነ ነው የምናየው። ለእኛ ግን ዋናው ነገር መሆን አለበት የምንለው በሽታው ካልታወቀ በስተቀር ሀኪም ያንን በሽተኛ ማከም አይችልም ነው። ይህ ስርዓት ታሟል የኢህአዴግ ስርዓት ኦህዴድም ይገለጽ በየትኛውም ይሁን ስርዓቱ ህክምና የሚያስፈልገው መሆኑን ነው የምናየው። አንዳንድ ባለስልጣናትን በማፈናቀልና በማሸጋሸግ የሚፈታው ሳይሆን ኢህአዴግ የፈጠረው ስርዓት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ሳይሆን አንድን ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጫነ ስርዓት ነው።

ኢህአዴግን ከበሽታው ለማዳን የሚበጀው ሊሆን የሚችለው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲፈልግ የሚሽረው ሲፈልግ የሚያነግሰው ስርዓት ሲኖር ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ካየን ግን ኢህአዴግ ከበሽታው የሚድን አይመስልም።

ስንደቅ

Leave a Reply