Wednesday, 06 April 2016 12:10

በይርጋ አበበ

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝና ውብሸት ታዬ ለምስክርነት ተጠሩ

በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝና ውብሸት ታዬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት “ግዙፍ ያልሆነ አመጽ የማነሳሳት ተግባር በመፈጸም” ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ባሉት በእነ ኤልያስ ገብሩ ጉዳይ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ።

ጋዜጠኛ ኤልያስ “በአቃቤ ህግ በኩል አምስት ምስክሮችን አስቆጥሮ ሁለት ብቻ አስመስክሯል” ሲል የትናንቱን የፍርድ ቤት ውሎ የገለጸ ሲሆን አያይዞም “እኛ አራት ምስክሮችን አቅርበናል። ከቀረቡት ምስክሮች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበባው መላኩ ቀርበው ከጽሁፉ ታሪክ ጋር በተገናኘ ሙያዊ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል” ሲል ተናግሯል። ከአቶ አበባው መላኩ በተጨማሪ ሌሎች ሶስት ምስክሮች አቅርበው ቃላቸውን መስጠታቸውን ገልጿል።

የአራቱን ምስክሮች ቃል ያደመጠው ፍርድ ቤቱም አውራምባ ታይምስ የቀድሞው ዋና አዘጋጅ ለመከላከያ ምስክር ሊመሰክር ችሎት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም እስር ላይ ካሉት ሶስቱ ጋዜጠኞች (እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝና ውብሸት ታዬ) የመከላከያ ምስክር ሆነው ከቀረቡት በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ እንዲመሰክሩ ከእስር ቤት እንዲመጡ ድጋሚ መጥሪያ እንዲጻፍላቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ ለግንቦት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ተናግሯል።

የክሱን መነሻ የገለጸው አንደኛ ተከሳሽ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በ2006 ዓ.ም አሁን ህትመት ላይ በሌለው “ዕንቁ መጽሔት” ላይ አምሳሉ ገብረ ኪዳን የተባሉ ጸሃፊ “እየተገነቡ ያሉ ሀውልቶች በማን እና ለማን” በሚል ርዕስ በጻፉት አርቲክል ምክንያት መሆኑን ተናግሯል። የአቶ አምሳሉ ገብረኪዳን መጣጥፍ ብሔርን ከብሔር ጋር የሚያጋጭ ነው ተብሎ በአቃቤ ህግ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደቻለ ነው የገለጸው።

ስንደቅ

Leave a Reply