Written

      ካንሰር እያደገ የመጣ የጤና ችግር መሆኑንና በአገሪቱ በየአመቱ 44 ያህል ሺህ ሰዎች በካንሰር ሳቢያ ለሞት እንደሚዳረጉ፤ 77 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችም በካንሰር እንደሚጠቁ “አናዶሉ ኤጀንሲ” ዘገበ፡፡በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና ቁጥጥር ፕሮግራም የቴክኒክ አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የካንሰር ችግር በመስፋፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚከሰተው የሞት መጠን 5.8 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነውም በካንሰር በሽታ ሳቢያ የሚከሰት ሞት ነው፡፡ በአገሪቱ ለካንሰር ተጋላጭ በመሆን ረገድ ሴቶች ቅድሚያውን እንደሚይዙና ይህም እጅግ አሳሳቢእንደሆነ ለ“አናዶሉ ኤጀንሲ” የተናገሩት ዶክተር ኩኑዝ አብደላ፣ በካንሰር ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል በሚል ሪፖርት ከተደረጉት መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ በአዋቂ ሴቶች ላይ ከሚከሰቱት የካንሰር አይነቶች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የጡት ካንሰር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡መንግስት ካንሰርን ለመከላከልና ለማከም ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ በተመረጡ 118 ሆስፒታሎች የማህጸን በር ካንሰር ምርመራና ህክምናን ለማስፋፋት እየተሰራ እንደሚገኝ፤ የመድሃኒት አቅርቦትና ለካንሰር ህክምና የሰው ሃይል ማሟላትም ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ገልጿል፡፡

አዲስ አድማስ

Leave a Reply