Saturday, 09 April 2016 09:01
Written by አለማየሁ አንበሴ
በሱማሌ ክልል በድጋሚ በደረሰ ጐርፍ፣ የ8 ሰዎች ህይወት ተቀጠፈ
በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በተከሰተ የጐርፍ አደጋ የ8 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን በመጀመሪያው የጐርፍ አደጋ 23 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ ባለፈው ሰኞ ሌሊት ከጅግጅጋ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው “ጭናቅሰን” በተባለ ስፍራ የዘነበው ከፍተኛ ዝናብ ጐርፍ አስከትሎ የ23 ሰዎች ህይወት መጥፋትና ከ80 በላይ በሚሆኑት የአካል ጉዳት ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ረቡዕ እለት በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ ድንበር ላይ በምትገኘው የቶጐ ጫሌ ከተማ ላይ የተከሰተው ጐርፍ ከከተማዋ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ 8 ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡ እስከ ትናንት ድረስ ምንም አይነት እርዳታ እንዳልደረሳቸው የጠቆሙት ተጎጂዎቹ፤ ያለመጠለያ መቅረታቸውንና ውጪ ለማደር መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡በቶጐ ጫሌ ከተማ ጉዳት ያስከተለው ጐርፍ ከአካባቢው ገጠራማ አካባቢዎች በዘነበ ዝናብ የተፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ረቡዕ ማታ 3 ሰዓት ላይ በከተማዋ ከፍተኛ መጥለቅለቅ ፈጥሮ ወደ በርካቶች መኖሪያ ቤት በመግባት፣ ከቀጠፈው የሰው ህይወት በተጨማሪ ንብረት ማውደሙንም ጠቅሰዋል፡፡ በአካባቢው በሚገኙ የጉምሩክና ኢምግሬሽን መስሪያ ቤቶች ላይም ጉዳት ማድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ “ጐርፉ ቤታችንንና የቤት እቃችንን በማውደሙ ማህበራዊ ኑሮአችንን አናግቶታል” ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ይህን መሰል ጐርፍ ከዚህ በፊት አጋጥሞን አያውቅም ብለዋል፡፡ በሳምንቱ መጀመሪያ በጅግጅጋ ከተማ ተከስቶ ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነው የጐርፍ አደጋ በባለሀብቶች ንብረት ላይ ውድመት ማድረሱም ታውቋል፡፡ ከ400 በላይ ቤቶችም በጎርፉ ወድመዋል፡፡ የንብረት ውድመት ከደረሰባቸው የግል ሃብቶች መካከል “ዘ ፓርክ” የተሰኘው የ1ኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አንዱ ሲሆን 15 ኮምፒውተሮችና ከ800 በላይ የሚሆኑ መማሪያ መጽሐፍት እንዲሁም የተማሪዎች ዶክመንቶች መውደማቸውን የትምህርት ቤቱ ባለቤት ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ ጐርፉ እንደሚከሰትና ጥንቃቄ እንዲደረግ በትነበያው ማስታወቁን የሚጠቅሰው ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ፤ በአካባቢው የዘነበው ዝናብ 55 ሚሊ ሜትር የተመዘገበ ከባድ ዝናብ እንደነበር ገልጿል፡፡ በቀጣይም የዝናቡ ሁኔታ በደቡብ አጋማሽና የሱማሌ ክልል በሚገኝበት የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ከብዶና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሜቲዎሮሎጂ መ/ቤት የረጅም ጊዜ የአየር ትንበያ ባለሙያ አቶ ነገደ መንግስቱ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በጅግጅጋ ከተማ የጐርፍ አደጋው ከማጋጠሙ በፊት በወንዞች አካባቢ ጥንቃቄ እንዲደረግ በተደጋጋሚ ሲገለፅ እንደነበር ያስታወሱት ምንጮች፤ ለጐርፉ መከላከያ ተሠርቶለት ቢሆን ኖሮ የአደጋው መጠን በቀነሰ ነበር ይላሉ፡፡ አደጋውን ተከትሎ በከተማዋ ያሉ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች ወደ 13 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰባቸውንና ለተጐጂዎች መከፋፈሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንዲከፋፈል መደረጉ ተጠቁሟል፡፡