Wednesday, 12 November 2014 13:41

አቶ ግርማ ሰይፉ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ

ም/ፕሬዝደንት

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ጋር እያደረገ ባለው ውይይት ዙሪያ እና ከኢንጅነር ግዛቸው ስንበት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ከፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት እና ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉት ከተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ጋር ባልደረባችን ፋኑኤል ክንፍ ቃለ-ምልስ አድርጓል፡፡

 

ሰንደቅ፡- ኢንጅነር ግዛቸው ሺፈራው ከሊቀመንበርነቴ የለቀኩት በጫና ነው ብለዋል። እናንተ ደግሞ ኢንጅነሩ የአንድነት ፓርቲ ጀግና ናቸው ስትሉ በተደጋጋሚ ተደምጣችኋል። “ጫና” እና “ጀግና” የሚሉት ቃሎች እንዴት ይታረቃሉ?

አቶ ግርማ፡-በእኛ በኩል የኢንጅነር ግዛቸውን እርምጃ በጣም የሚከበር ነው። ምክንያቱም ከውጭም ከውስጥ በገጠመኝ ጫና ኃላፊነቴን ይዤ መቀጠል አልችልም ብለዋል። በተቃዋሚም ሆነ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ኃላፊነት ወይም ስልጣን ሞት ብቻ የሚገላግልበት ሁኔታ ባለበት እሳቸው ግን ኃላፊነታቸውን ለማስረከብ ወስነው፣ አድርገውታል። በአንፃሩ ከተመለከትነው፣ አንዳንዱ ሊመራውና ሊያስተዳድረው የማይችለውን ቦታ መሆኑን እያወቀ ቦታውን ብቻ ስለሚፈልገው ትንቅንቅ ውስጥ የሚገባበት ሁኔታዎች እናያለን። ለዚህም ነው፣ የኢንጅነሩ ውሳኔ በጣም የምናደንቀው። የምናከብረው። እንደሞዴል ማስተማር ነው የምንፈልገው።

ሰንደቅ፡- የእሳቸው ሃሳብ አግባብ፣ ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ፈልገው ሳይሆን በተደረገብኝ የፖለቲካ ሴራ መስራት አልቻልኩም፤ ስለዚህም ለመልቀቅ ተገድጃለሁ የሚል ነው። በእናንተ በኩል የሚቀርበው ምላሽ ግን፣ ስልጡን ሆኖም ግን የፖለቲካ ሴራ የተላወሰ ኢንጅነሩን ጀግና የማድረግ ምላሽ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ግርማ፡-ሴራ ነው ወይም ሌላ የተደረገ ነገር አለ የሚባለው ሰዎች ከራሳቸው አመለካከት በመነሳት ጉዳዩን የሚያዩበት መንገድ ነው ሊሆን የሚችለው። በኢንጅነሩ ላይ ከውጭም ከውስጥ ግፊት ተደርጓል። ይህ የሆነበት ምክንያት ፓርቲውን በምንፈልገው ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል አመራር አላገኘንም የምንል ሰዎች ግፊት አድርገናል። ይህን ሁኔታ አንዳንዱ አሻጥር ነው ሊለው ይችላል። ሌላው ደግሞ ትግል ነው ይላል። ይህ ግን የዲሞክራሲ አንዱ ሂደት ነው። ውጭ ሀገር ያለው የፓርቲው አባል ሀገር ውስጥ ካለው የፓርቲ አባል ጋር እኩል አባል ነው። ስለዚህም ውጪ ያለውም ሀገር ውስጥ ያለውም የእሳቸውን አመራር ካልደገፈ ይህን ተገንዝቦ ኃላፊነት መልቀቅ ትልቅነት ነው ብለን የምናምነው። ያደረጉትም ፓርቲውን ለመጥቀም ስለሆነም ነው።

ሰንደቅ፡-ኢንጅነሩ ችግራቸውን ሲያቀርቡ ውይይት ማድረግ ነበር የሚቀድመው ወይንስ በቀጥታ የስልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸውን ማስተናገድ? እኔ ካለኝ መረጃ፣ በቀጥታ ወደ ሊቀመንበር መተካት መሄድ አለብን ያሉት እርስዎ እንደሆኑ ነው።

አቶ ግርማ፡-ያልተደረገ ነገር አልተደረገም። የሆነው ነገር ግን፣ ኢንጅነሩ ችግር ገጥሞኛል እንዴት እንፍታው ብለው አልቀረቡም፤ አላሉምም። ቅዳሜ ካቢኔያቸውን በትነው እሁድ ኃላፊነታቸውን ለምክር ቤቱ ለማስረከብ ነበር የቀረቡት። ስለዚህም ችግር እንፍታ ባልተባለበት ሁኔታ ይህ ጥያቄ መቅረብ የለበትም። ኃላፊነታቸውን ለማስረከብ መጡ፤ ፓርቲው ያለመሪ አንድ ቀንም አያድርም ስለተባለ ምክር ቤቱ አዲስ ሊቀመንበር መረጠ። የሆነው ይህ ነው። ስልጣን ማስረከብ እንደሚፈልጉም ቀድሞ የተሰማ በመሆኑ ለምክር ቤቱ ይህን የኃላፊነት መልቀቂያ ሲያቀርቡም እንደአዲስ ነገር አልታየም። ምክር ቤቱ በተዘዋዋሪ ሰምቶት ስለነበረ።

ሰንደቅ፡- ሊቀመንበር የሰየማችሁበት አግባብ ደንብን ያልተከተለ መሆኑ በስፋት ተነግሯል። ለጠቅላላ ጉባኤው የተሰጠውን ስልጣን ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከሕግ ውጪ ተጠቅሞበታል የሚል ክስ የሚያቀርቡ አሉ። በዚህ ላይ ምን ምላሽ አልዎት?

አቶ ግርማ፡- በደንባችን መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ በሌለበት ምክር ቤቱ የጠቅላላ ጉባኤውን ሥራዎች ወክሎ ይሰራል ይላል። ይህ ማለት የድርጅቱን ፕሮግራም እና ደንብን ማሻሻል አይጨምርም። ከጠቅላላ ጉባኤ ስራዎች መካከል አንዱ የፓርቲውን ሊቀመንበር መሰየም ነው። ጠቅላላ ጉባኤው የሚጠራው በሶስት ዓመት አንዴ ነው። ስለዚህም ምክር ቤቱ የተፈጠረውን የኃላፊነት ክፍተት ጠቅላላ ጉባኤው በሰጠው ውክልና መሰረት ሊቀመንበር ለመምረጥ ችሏል። ይህን ሂደት በምንም መልኩ ሕገወጥ ሊያስብለው የሚችል መሰረት የለም። ስለዚህም ሊቀመንበሩ በደንቡ መሰረት የተመረጠ ነው። በነገራችን ላይ ይህን ሂደት የሚቃወሙ ሰዎች በዚህ ሂደት ለምርጫ ቀርበው ባገኙት አነስተኛ ድምጽ የተሸነፉ ናቸው። ሂደቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ቢኖረው፣ እነዚህ ውንጀላ የሚያቀርቡ ወገኖች ለሊቀመንበርነት መወዳደር ሳይሆን አካሄዱን በመቃወም በግልፅ መሟገት ነበረባቸው። እነሱ ግን፣ ምክር ቤቱ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ለአብላጫው ድምጽ መገዛት ሲገባቸው ወደ ውንጀላ አመሩ። ተገቢነት የሌለው ተግባር ላይም ተሰማሩ። ስለዚህም መከራከሪያቸው ውሃ የሚቋጥር አይደለም።

ሰንደቅ፡- ሕጋዊ ስርዓት መከተላችሁን እርስዎ ቢገልፁም፣ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ አመራር አይደለም ሲል መግለጫ ሰጥቷል። ይህን ጉዳይ እንዴት ነው የሚረዱት?

አቶ ግርማ፡-በመጀመሪያ ደረጃ መታረም ያለበት ፍሬ ነገር፣ ምርጫ ቦርድ ማብራሪያ እንጂ የሕግ ጥያቄ አላነሳም።

ሰንደቅ፡- ምን ማለት ነው?

አቶ ግርማ፡-ምርጫ ቦርድ ያለው፣ አሁን በእጃቹሁ ላይ የሚገኘው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ለምርጫ ቦርድ ቀርቦ የጸደቀ አይደለም። ይህም በመሆኑ አሁን ለምርጫ ቦርድ ፓርቲውን አስመልክተው ቅሬታቸውን ካቀረቡ ወገኖች ጋር የምዳኛችሁ በ2004 ዓ.ም ባጸደቃችሁት የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ እኛን በ2004 ዓ.ም መተዳደሪያ ደንብ ለመዳኘት ምርጫ ቦርድ የሚወስነው አይደለም። ምክንያቱም እያሉን ያለው፣ አንድነት አሁንም በዶክተር ነጋሶ እየተመራ ነው። ይህ ትክክል አይደለም። ምርጫ ቦርድ በታዛቢነት በተገኘበት ታህሳስ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዷል። በጉባኤው ፕሮግራም እና ደንብ አሻሽሏል። ስለዚህም በጉባኤው የተሻሻለውን ፕሮግራም እና ደንብ በፓርቲው ሲቀርብለት ተቀብሎ ማጽደቅ የምርጫ ቦርድ ኃላፊነት ነው። እኛ ሁሉንም ሰነዶች አጠናቀን ካስገባን በኋላ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ያቀረብነውን ሰነዶች መርምሮ ማፅደቅ የምርጫ ቦርድ ስራ ነው።

ሰንደቅ፡- ለምርጫ ቦርድ መቼ ነው ያስገባችሁት?

አቶ ግርማ፡- ቀኑን በትክክል አላስታውስም። ካስገባን በኋላ ግን ሐምሌ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ደንቡ ላይ ወደ ዘጠኝ ጥያቄዎች አንስተው ጠይቀውን ነበር። ለዘጠኙም ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተናቸዋል። እሱን ማብራሪያ ከሰጠናቸው በኋላ በሰላሳ ቀናት ምላሽ መስጠት ነበረባቸው። ግን አልሰጡንም። በሰላሳ ቀን ምላሽ ካልሰጡ ተቀብለውታል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- በ2004ቱ እና በ2006ቱ ደንቦች መካከል አሁን በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት ከመፍታት አንፃር እንዴት የሚታይ ነው?

አቶ ግርማ፡-የ2004ቱ ደንብ በጠቅላላ ጉባኤው ተሽሯል። ሆኖም የ2004ቱን ስንመለከተው ፕሬዝደንቱን በተመለከተ ቢታመም፣ ቢሞት፣ በፈቃዱ ቢለቅ፣ በስራ ቦታው ባይገኝ ምን መደረግ እንዳለበት ምንም የሚለው ነገር የለም። ጉባኤው ይህን ክፍተት በመመልከት በ2006ቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፕሬዝደንቱን በተመለከተ ማሻሻያ አድርጎበታል። ይህም ጠቅላላ ጉባኤው በሌለ ሰዓት ምክር ቤቱ የጠቅላላ ጉባኤውን ስራዎች በውክልና እንዲሰራ በደንቡ ውስጥ ተካቷል።

ሰንደቅ፡- ኢንጅነር ግዛቸው በ2006ቱ ደንብ መሰረት ነው የተመረጡት?

አቶ ግርማ፡- በ2006ቱ ደንብ ነው የተመረጡት። ወደ አስራ አምሰት ካቢኔያቸውንም አዋቅረው ለምርጫ ቦርድ አሳውቀው ስራም ሰርተዋል። ስለዚህም ይህ ደንብ ስራ ላይ የዋለ የተሰራበትም ነው። ከዚህ በፊት ላቀረቡት ዘጠኝ ጥያቄዎች መልስ መልሰናል። ምላሽ ከሰጠን ሰባ ቀናቶች አልፈዋል። አሁን ደግሞ ለሶሰት ነገሮች ማብራሪያ አቅርቡ ተብለን አቅርበናል።

ሰንደቅ፡- ምርጫ ቦርድ ግን በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል የ2006ቱን ደንብ በቦርድ የጸደቀ ባለመሆኑ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አዲሱ አመራር ሕጋዊነት እና ተቀባይነት የለውም ብሏል። እርስዎ ካቀረቡት መከራከሪያ አንፃር ምላሽዎ ምንድን ነው?

አቶ ግርማ፡-ምርጫ ቦርድ ይህን አላለም። ተቀባይነት የለውም ማለት ሕገወጥ ነው ማለት አይደለም። የትኛው ነው ተቀባይነት ያለው ደንብ በሚለው ተነጋግረናል። ምርጫ ቦርድም ቢሆን እኛ በምንሰጠው መተዳደሪያ ደንብ እንጂ እሱ በመረጠው ደንብ ሊዳኘን አይችልም። እኛም ጽ/ቤት ድረስ አስረድተናል፤ ተወያይተናል። ቦርዱም ያቀረብነውን ማብራሪያ መሰረት በማድረግ በቀጣይ ሳምንት ውሳኔውን ያሳውቃል። ከዚህ ውጪ የህግ መጣስ ጥያቄ የቀረበበት አግባብ የለም።

ሰንደቅ፡- የምርጫ ቦርድ ሕዝብ ግንኙነት በራሱ ተነሳሽነት ይህን ምላሽ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ መውሰድ ይቻላል?

          አቶ ግርማ፡-የቦርዱ ጽ/ቤቱ መንፈስ አይደለም። የተነሳው የሕግ ጥያቄ ሳይሆን፣ አሳታፊነት፣ የኮረም መጠን እና ለምን በጊዜ አላስገባችሁም ለተባሉት ጥያቄዎች ማብራሪያ እንድናቀርብ ነው የተጠየቅነው። ከዚህ ውጪ ሕግ ጥሳችኋል የሚል በምርጫ ቦርድ የቀረበ የለም። ይህ ባልሆነበት ሕገወጥ ወይም ሕጋዊ የሚል መጨቃጨቂያ ማንሳት ተገቢ አይደለም። ሕጋዊነት ካነሳን፣ ሕጋዊ ፓርቲ፣ ሕጋዊ ሥራ አስፈፃሚ፣ ሕጋዊ ምክር ቤት እና ሕጋዊ ጠቅላላ ጉባኤ አለን።

Leave a Reply