Wednesday, 12 November 2014 13:31

    አቶ አበባው መሐሪ
የቀድሞ የመኢአድ ሊቀመንበር

 መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥቅምት 29 እና 30 ቀን 2007 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔ ያካሄደ ሲሆን፤ በዚህም ጉባዔ ላይም ፓርቲው ያልተጠበቀ ሹም ሽር አድርጓል፡፡ በአቶ ሃይሉ ሻውል አመራር ዘመን ከፓርቲው የተባረሩት ቡድኖች የመኢአድን የፖለቲካ አመራር ቦታዎችን የተቆጣጠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አበባው መሐሪም ከኃላፊነታቸው ተነስተው በምትካቸው አቶ ማሙሸት አማረ በሊቀመንበርነት ተመርጠዋል። የጠቅላላ ጉባዔውን ሒደት በተመለከተ ከአቶ አበባው መሐሪ ጋር ባልደረባችን ፋኑኤል ክንፉ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሰንደቅ፡- ጠቅላላ ጉባኤው የተጠራው በማነው? በጥሪ ወረቀቱ ላይ ያረፈውስ ፊርማ የማነው?

አቶ አበባው፡-ጠቅላላ ጉባኤውን የጠሩት ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ናቸው። በጥሪ ወረቀቱም ላይ የእሳቸው ፊረማ ነው ያለበት።

ሰንደቅ፡- ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ከፓርቲው የዕለት ተዕለት ስራዎች እና ከፓርቲው ሊቀመንበርነት በመነሳት የበላይ ጠባቂ በሚል ስያሜ መቀመጣቸው ይታወቃል። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፣ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጥራት ሕጋዊ መሰረት ከየት ነው ያገኙት?

አቶ አበባው፡- ስብሰባውን ለመጥራት የተዘጋችሁት እኔ ነበርኩ። ኢንጅነሩ ግን የለም እኔ እንጂ አንተ አትጠራም አሉ። ስብሰባው መጠራቱን እንጂ ጉዳዩን ካለኝ የሊቀመንበርንነት ኃላፊነቴ ጋር አያይዤ ለማየት አልፈለኩም። ይህ በመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤውም በእሳቸው በኩል ተጠራ።

ሰንደቅ፡- በፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራው በሊቀመንበሩ አማካኝነት ነው። በምን የሕግ አግባብ ይህን ስልጣን አሳልፈው የሰጡት? የጠቅላላ ጉባኤ አባል ያልሆነ ሰውስ እንዴት ስብሰባ ሊጠራ ይችላል?

አቶ አበባው፡- ምክንያት ተብሎ በእሳቸው የቀረበውን ስንመለከተው፤ ምርጫ ቦርድ በ2005 ዓ.ም ፓርቲው ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አባላት የተሟሉበት ባለመሆኑ፣ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጉ የሚል አቅጣጫ ያስቀምጣል። ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ይህን ክፍተት ለራሳቸው ፍላጎት ማስፈጸሚያ ስለፈለጉት እኛን ሕጋዊ የፓርቲው ውክልና የላችሁም በማለት ራሳቸውን የፓርቲዊ ሕጋዊ ተጠሪ አድርገው ቀረቡ።

ሰንደቅ፡- ምርጫ ቦርድ የእርስዎን አመራር ሕጋዊ አይደለም የሚል መቃወሚያ አቅርቧል እንዴ?

አቶ አበባው፡- ምርጫ ቦርድ አመራሩ ሕጋዊ አይደለም አላለም። የተባለው የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ብዛት በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት አድርጋችሁ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ ይዛችሁ ቅረቡ ነው ያለው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ነው እኔ ሕጋዊ ነኝ የሚሉት። መቼም ኢንጅነር ኃይሉን ከመሰለ የእድሜ ባለጸጋ ጋር አትደባደብም፤ ወይም በጉልበት አታደርግም፤ ላድርግም ብል እድገቴም ይህን አይፈቅድም።

ሰንደቅ፡- የስብሰባውን መድረኩን በጋራ ነበር የመራችሁት?

አቶ አበባው፡- እስከተወሰነ ድረስ አብረን መርተናል። መቀጠል ግን አልቻልንም?

ሰንደቅ፡- ለምን?

አቶ አበባው፡- የዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ዋና አጀንዳ ተደርጎ የተወሰደው ከዚህ በፊት በኢንጅነር ኃይሉ ከፓርቲው የተባረሩት የእነማሙሸት አማረ ጉዳይ ነበር። በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ መሰረት ከእነማሙሸት አማረ ጋር የሚደረገው እርቅ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ ለአንድ አመት ከፓርቲው አመራርነት ርቀው እንዲቆዩ ጉባኤው ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በምን ምክንያት እንደሆነ ሳይታወቅ፣ አስመራጭ ኮሚቴ ወደመድረክ ኑ የሚል ትዕዛዝ በማስተላለፍ እኛን ከመድረክ እንድንወርድ አስደረጉ።

ሰንደቅ፡- በእሳቸው ፍላጎት ብቻ እንዴት መድረክ ትለቃላችሁ? ጉባኤተኛውስ ምን አለ?

አቶ አበባው፡- ከእሳቸው በማይጠበቅ መልኩ ልብሴን ይዘው እየጎተቱ ከመድረክ እንድወርድ ኃይል ለመጠቀም ሞከሩ። መቼም በእድሜ ገፋ ያሉ ናቸውና አክብረናቸው ከመድረክ ወረድን።

ሰንደቅ፡- ከመድረክ ከወረዳችሁ በኋላ በተራ ተሳታፊነት ጠቅላላ ጉባኤውን ተቀላቀላችሁ?

አቶ አበባው፡- እንዴት አድርገን እንሰበሰባለን። ፈጥኜ ነው፣ ራሴን ያገለልኩት። እኛ ህይወታችን ሸጠን ለፓርቲያችን እየሰራን ያለነው ለውጥ ይመጣል ከሚል ተስፋ ነው። ዴሞክራሲ በሀገራችን ይሰፍናል ከሚል ጠንካራ እምነት እንጂ በአንድ ሰው አምባገነንነት ፓርቲ የሚመራ ከሆኑ እንኳን ለሕዝባችን ለራሳችንም የሚበቃ ዴሞክራሲ አይኖረንም። ፈጽሞ የኢንጅነሩ አምባገነንነት የተንጸባረቀበት ስብሰባ ነበር። ይህ ከሆነ ለምን ፓርቲ ውስጥ እንሳተፋለን። ጠቅላላ ጉባኤው እነማሙሸት አማረን በተራ አባልነት በፓርቲው ውስጥ ያገልግሉ እያለ በአንድ አምባገነን ኢንጅነር ውሳኔ የጠቅላላ ጉባኤው ሃሳብ የሚጨፈለቅ ከሆነ ሁሉም ነገር ባዶ ነው የሚሆነው። ከጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ውጪ የፖለቲካ አመራር እንዲሆኑ ከተፈቀደ ዴሞክራሲ ትርጉሙ ለማንም ሊገባ አይችልም። በመኢአድ (በእኛ) ጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ የሆነው ይህ ነው።

ሰንደቅ፡- እርስዎ በሊቀመንበርነት ፓርቲው ሲያገለግሉ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ድጋፍ ነበራቸው። በተለይ በእነማሙሸት አማረ ጉዳይ ከእርስዎ ጎን ኢንጅነሩ መሰለፋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህን አቋማቸውን ያስቀየራቸው ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ አበባው፡- የሚገርመው እነዚህን 14 ሰዎች ያገዷቸው ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ናቸው። ጠባቸውም ከእኛ አመራር ጋር ሳይሆን ከኢንጅነር ኃይሉ ጋር ነበር። እንደአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የፓርቲውን ውሳኔ አዲስ አመረር ሲፈጠር ይዞ መቀጠል አለበት። እኛ ያደረግነው በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ቢባረሩም የፓርቲው ውሳኔ አድርገን ተቀብለን ነው የቀጠልነው። ይህ አካሄድ እንደተቋም የሰለጠነ አካሄድ ነው። የእሳቸውን ውሳኔ ለማስፈጸም በፓርቲው ውስጥ አባላት እርስ በእርስ ሲባሉ ነበር ላለፉት አራት ዓመታት የከረሙት።

የሚገርመው አስራ አራቱ ወደ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ይግቡ ሲባል መቶ ሃምሳ አንድ የጠቅላላው ጉባኤ አባላት ያልሆኑ ይዘው ገብተው ነው ምርጫው የተደረገው። እሳቸው አደራጅተው ካስገቡት ቡድን ውጪ የሆነ አባል ለመናገር ቢሞክር በጩኸት እና በፉጨት ሃሳቡን እንዳይገልጽ ተደርጓል።

ሰንደቅ፡- ለጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ የተጠራው የአባላት መጠን ስንት ነበር?

አቶ አበባው፡- መተዳደሪያ ደንባችን የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ብዛት ሶስት መቶ ሲደመር አንድ ነው የሚለው። ይህን መነሻ አድርገን ሶስት መቶ ሰማንያ አባላት ጠራን። ከጠራነው ውጪ አንድ መቶ ሃምሳ አባላት ይዘው የታገዱት የእነማሙሸት አማረ ቡድኖች ጠቅላላ ጉባኤውን ተቀላቀሉ። ከተለያዩ ክልሎች የመጡት አባሎቻችን ሃሳባቸውን ሳያቀርቡ ችግሮቻቸው ሳይሰማ በኢንጅነሩ ፈላጭ ቆራጭነት ስብሰባው ከታለመለት ዓላማ ውጪ ሆኖ ተጠናቋል።

ሰንደቅ፡- ለፓርቲው መልቀቂያ ያስገቡት በዚህ የስብሰባ ሂደት ደስተኛ ባለመሆንዎ ብቻ ነው? ወይንስ ሌላ የልዩነት ሃሳብ ከኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ጋር አላችሁ?

አቶ አበባው፡- እየጠየከኝ ያለኸው ስለጠቅላላ ጉባኤው በመሆኑ፣ የሰጠሁም ምላሽ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ስብሰባ ላይ በገጠመኝ ሁኔታም አኩርፌ አይደለም። ከዚህ ውጪ ከኢንጅነሩ ጋር በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች መግባባት አልቻልንም። እነሱም፣ ለጠቅላላ ጉባኤው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በትብብር ከተቻለም በውህደት እንድንሰራ ጥያቄው ቀርቦ እንዲጸድቅልን ፈልገን ነበር። ኢንጅነሩ ግን ሌሎች ፓርቲዎችን የሚፈልጉትን ቀለም እየቀቡ ከማንም ፓርቲ ጋር አብረን መስራት አንችልም አሉ። እኛ ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት ካልቻልን መኢአድ ብቻውን ምንም አያመጣም የሚል መከራከሪያ አቀረብን። ውድቅ ሆነ።

ሌላው፣ ምርጫ ነው። ምርጫ የሰላማዊ ትግል አንድ መሳሪያ ነው። ጠቅላላ ጉባኤው ስለምርጫው መወያየት አለበት። በምርጫው መሳተፍ፣ አለመሳተፋችን ግን በሂደት የምንወስነው ይሆናል የሚል መከራከሪያ አቀረብን። ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ግን፣ የምን ምርጫ ነው፤ ባለቀ ምርጫ አንሳተፍም የሚል መደምደሚያ አቅርበው ለውይይት እንዳይቀርብ አደረጉ። የተሰብሳቢው ድምጽ እንዳይሰማ በአደራጁት ቡድን አድርገው፣ ምርጫ አንሳተፍም በሚል አጀንዳው ተዘጋ። ስለዚህም ከዚህ መሰል አምባገነን አመራር ጋር ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መፍጠር ስለማይቻል መልቀቂያ አስገባሁ።

ሰንደቅ፡- ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ቤት በተደረገው ስብሰባ ተካፋይ ነበሩ?

አቶ አበባው፡- አዎ ሶስት ቀን ስብሰባ አድርገን ነበር። ከውጭ የመጡ የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ነበሩ። ያነሱት ነጥብ ለጠቅላላው ጉባኤ ስብሰባ ገንዘብ ለማውጣት ከእነማሙሸት አማረ ጋር መታረቅ በቅድሚያ ሁኔታ አስቀመጡ። እኔም በበኩሌ የሰጠሁት ምላሽ፣ ከእነማሙሸት አማረ ጋር በግሌ ጠብ የለኝም። ጠባቸው ከእርስዎ ጋር ነው። ከእኔ ጋር ታረቁ የሚባለው በመጀመሪያ መች ተጣላን እና ነው የምንታረቀው? አልኩ። በዚህ ጉዳይ አስገዳጅነት ለሶስት ቀን ኢንጅነሩ ቤት ተሰበሰብን። በመጨረሻ ተጣላን፣ አልተጣላንም እርቀ ሰላም ይውረድ ተብሎ እርቅ ወረደ። እርቁ ግን ስምምነት ነበረው። ይሄውም፣ አስራ አራቱም ሰዎች ጠፋ የተባለውን የፓርቲውን ንብረት ቀርበው እንዲያስረዱ። ሌላ ከእነሱ ውጪ በጠቅላላው ጉባኤ እንዳይሳተፍ ተስማማን። የሆነው ግን ስለጠፋው ንብረት አላስረዱም። ይባስ ብለው መቶ ሃምሳ አንድ ሰዎች ይዘው ወደ ጉባኤው ገቡ። ኢንጅነሩም ለምን የሚል ጥያቄ አላቀረቡም።

ሰንደቅ፡- እርስዎ ካነሷቸው ነጥቦች አንፃር የዚህን ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ምርጫ ቦርድ ሊቀበለው ይችላል? ቢቀበለውስ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል ብለው ይገምታሉ?

    አቶ አበባው፡- በምርጫ ቦርድ ውሳኔ አልገባም። ሆኖም ግን ምርጫ ቦርድ የነበረውን የጠቅላላ ጉባኤውን ስብሳባ ሁኔታ መረጃ ሰብስቦ ሚዛናዊ ውሳኔ ያስቀምጣል የሚል ግምት አለኝ። በቀጥታም ሳይፈትሸው የሚቀበለው ከሆነም፣ ውጤቱ ከአምባገነኖች ጋር አብሮ ለመሰለፍ ያለውን ፍጥነት የሚያሳይ ይሆናል።

****             ****           ****

ከጠቅላላ ጉባዔው ሒደት ጋር በተያያዘ

ቅሬታ ካቀረቡ አባላት በከፊል

አቶ በጋሻው ዳምጤ

በሰሜን ሸዋ ቆጥ ወረዳ የመኢአድ ሰብሳቢ

“የተጠራነው ለፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ነው። ከስብሰባው ውስጥ ግን በፊት ያለተነገረን አጀንዳ ቀረበ። እሱም ከእነማሙሸት አማራ ጋር እርቅ መደረጉን ተነገረን። የሚገርመው ማሙሸት አማራ በወረዳዎች ያዋቀረው መስመር መኢአድን ለመበታተን የተሰለፍ ናቸው። ምክንያቱም እሱ ያዋቀራቸው ቡድኖች በየወረዳው እየሄዱ በደጋም በቆላም ሽፍታ ተመድቧል እያሉ የመኢአድ አባላትን የሚያስፈራሩ ናቸው። እነዚህ ቡድኖች መታረቃቸው ችግር አይኖረው ይሆናል፣ ሆኖም ግን እርቅ ከሆነ ሌሎችም በ97 ዓ.ም ከፓርቲው የተገለሉ ሁሉም መጥተው እርቅ ቢፈጸም የሚል ጥያቄ ያቀረብን ቢሆንም ሰሚ አጣን።

ሌላው በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንድ ሰው ሶስት ወር ወርሃዊ ክፍያውን ካልከፈለ በምንም መልኩ አመራር ሆኖ ሊመረጥም አይችልም። አባል ሆኖም አይቀጥልም። ይህም ሆኖ እነዚህ ሰዎች በእርቅ የሚገቡ ከሆነ ከፖለቲካ አመራርነት ርቀው እንዲቀመጡ ጉባኤው ጥያቄ አቀረበ። ይህ ጉዳይ ብዙ ውይይት እንዳይደረግ በስብሰባው መካከል የሚረብሹ በርካታ ሰዎች ገብተዋል። ከሁሉ የሚገርመው ጉባኤውን መቀላቀላቸው ሳይሆን ወደ ምርጫ እንዲገቡ ተደርጎ በተደራጀ ቡድን እንዲመረጡ ተደረገ። ከፍተኛ ረብሻም በስብሰባው መካከል ተነስቶ ነበር።

ሌላው፤ የተመራጭ ቆጠራ ሲደረግ በአይናችን የወጡት እጆች ትንሽ ሆነው እያየን ወደ መድረኩ ሲነገር እጅግ የተጋነነ ውጤት ሆኖ ሲነገር ነበር። በእውነት እልሃለው ከሰሜን የመጣነው ከልባችን አዝነን ነው ከጉባኤው የወጣነው። አንድ መሆናችን ባልከፋ በዚህ መልኩ ሁኔታዎች መከናወናቸው ግን አሳዛኝ ተግባር ነው። እኔ ከፕሮፌሰር አስራት ጀምሮ አደራጅ ነበርኩ። ለምርጫም ቀርቤ ተወዳድሪያለሁ። በዚህ ፓርቲ ውስጥ ማን ምን እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን። በዚህ እድሜዬ ይህን ሕገወጥ ተግባር መመልከቴ ከልብ አዝናለሁ። በተለይ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ሁሉንም ነገር እያወቁ ይህን ማድረግ ለምን እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም።”

 

 

 

ወ/ሮ ደስታ ካሳ

ከደብረብርሃን ከቀይጥ ወረዳ፣

የባሶ አደራጅ እና በዞኑ የመኢአድ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ

“እኛ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ገብተን የታገልነው ነፃነት ፍለጋ ነው። ፓርቲያችንም ለሁሉም ዜጎች እኩልነት፣ መከባበር፣ እንደልባችን እንድንናገር እና በሰላም ወጥተን በሰላም ለመግባት እንድንችል ነው የተደራጀነው። እንኳን በፓርቲያችን ውስጥ ገዢውን ፓርቲ እየጠየቅን እየታገልን ያለው እኩልነት ለማስፈን ነው። ይህን አመለካከት ይዤ ነው ወደጉባኤው የገባሁት፣ በጉባኤው ያየሁት ግን እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነበር። እሱም፤ ኢንጅር ኃይሉ ሻውል የባላይ ጠባቂ መሆናቸውን ነው ከዚህ በፊት የምናውቀው። ስብሳበው ሲጀመር እሳቸው የፖርቲው መሪ ሆነው ተመለከትናቸው። ለጊዜው ምንም ማለት አልቻልንም።

ስብሳበው ሲጀመር የህዝብ መብት ወደጎን ተትቶ የቡድን ስራ ሆነ። ከብዙ ቦታዎች የመጣነው አባለት ብዙ የህዝብ ጥያቄዎችን ይዘን ነበር። ስለሕዝቡ የተነሳ ነገር የለም። መድረኩን የሚመሩት የሚያዙት ኢንጅነር ሃይሉ ሻውል ብቻ ሆኑ። በጉባኤው መካከል መድረኩን የሚመራ ከጉባኤው ውስጥ የተወጣጣ ይመረጥ። ብዙ የህዝብ ጥያቄዎች አሉ አለን። ምርጫው ከመከናወኑ በፊት ብዙ ውይይት የሚፈልጉ ነገሮች አሉ የሚሉ ጥያቄዎችን አነሳን፣ የሚሰማን አጣን። ጥያቄያችን ተቀባይነት አጣ። ይህን ሁሉ ያደረጉት ኢንጅነር ሃይሉ ሻውል ናቸው። የሚገርመው የበላይ ጠባቂ ታዛቢ እንጂ የጉባኤም አባል አይደለም። እሳቸው ፍላጎታቸውን ጭነው ስብሰባው ተጠናቀቀ፣ ይዘን የመጣነው የሕዝብ ጥያቄቆች ሳይቀርቡም ምላሽ ሳያገኙም ተበተንን። በተፈጠረው ሁሉ አዝናለሁ።”

 

 

አቶ ደምስ

ከሰሜን ሸዋ ባሰና ወራና የወረዳው አደራጅ

“ጉባኤው ላይ ልካፈል የመጠሁት ከአካባቢ የሚነሱትን ጥያቄዎች ለማቅረብ ነው። ስብሰባው ሲጀመር ግን የሁሉንም ጥያቄዎች መቀበል ስለማንችል የተወሰኑትን ብቻ ለመመለስ እንሞክራለን አሉ። ጥያቄ ለመጠየቅ እጅ ስናወጣ ግን እሳቸው አደራጅተው ላስገቡት ቡድኖች ብቻ እድል ይሰጡ ጀመር። ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም እድል ነፈጉን። የህዝብ ቅሬታን የማያዳምጥ እና የማይመልስ ጉባኤ እንዴት ጉባኤ ሊሆን ይችላል። እሳቸው የመጡት ላደራጁት ቡድን ስልጣን ለመስጠት ነው።

እሳቸው እርቅ ብሎ የሚናገር ቡድን አደራጅተው የመጠይቅ መብት ለእነሱ ብቻ ሲሰጡ ነበር። ርቁን የተቃወመ ጉባኤተኛ የለም። ጉባኤው ያለው እነማሙሸት አማረ ይመለሱ ግን ለአንድ አመት በተራ አባልነት ይቀጥሉ። ይህን የጉባኤውን ሃሳብ ማን ያዳምጥ። ረብሻው ፉጨቱ ማንችሎት። በጎሮ በር ጨርሰውት የመጡትን ስልጣን ፓርቲው ላገዳቸው ግለሰቦች አከፋፈሉት። ፈጽሞ ከእሳቸው የማይጠበቅ ተግባር አከናወኑ። ከፓርተው በላይ ሆነው ፉላጎታቸውን ፈጸሙብን። ትላንት በ800ሺ ብር ምዝበራ ክስ እሳቸው ራሳቸው መስርተው ዛሬ የወንጀሉ ጉዳዩ ሳይጣራ ለጠቅላላው ጉባኤ ሳይቀርብ ሁሉም ነገር በሽፍንፍን አለፈ። ኢንጅነሩ ለምን ፓርቲውን ማተራመስ እንደፈለጉ ግን አልገባንም። እርቅ ከእውነት የሚፈልጉ ከሆነ በምርጫ ዘጠና ሰባት ከእሳቸው ጋር በነበራቸው ልዩነት ፓርቲውን የሸሹትን ጠርተው እርቅ ማውረድ ነበረባቸው። ይህን ማድረግ ግን አልፈለጉም። ያደረጉት ጠቅላላ ጉባኤው ውስጥ የተሰገሱ የጠቅላላው ጉባኤ አባላት ያልሆኑ ድምፆችን በመጠቀም ትላንት በወንጀል ሲከሱት የነበረውን ማሙሸት አማረን የፓርቲው ፕሬዝደንት አድርገው ሰየሙት። ያሳዝናል። ፖለቲካ እንዲህ ከሆነ ፓርቲያችን አምነን እስካሁን የከፈልነው ዋጋ አፈር በላ ማለት ነው። ለኢንጅነሩ መጠቀሚያ መሆናችን ግን አሳዛኝ ነው”

 

 

አቶ ስለሺ ዳበሳ

ምዕራብ ሸዋ አመያ ወረዳ የወሊሶ ዞን ተጠሪ

“የዛሬ አራት ዓመት ከፓርተዊ የተገለሉት እነማሙሸት አማረ ፓርቲውን እንዲመሩ ኢንጅነሩ ውሳኔ አስተላልፈዋል። እኔ ከአካባቢዬ አባላት በብዛት መዝግቤ ለፓርቲው ሳመጣ ያለኝን ማሙሸት ያውቀዋል። በሱ ጠባብ አመለካከት መኢአድ ሲመራ ማየቴ በጣም ያስቆጣል። ኢንጅነሩም ለብዙ ነገሮች የሚበቁ መስለውኝ ነበር። ከጠባብ አመለካከት ጋር ሳገኛቸው ግን አዝኛለሁ።

 

 

መሐመድ ጋዳፊ

የላፍቶ ክፍለ ከተማ የፓርቲው ፀሐፊ

“የጠቅላላ ጉባኤ አባልም ነኝ። ጉባኤው ስብሰባ ሲጀመር ኢንጅነር ሃይሉ መሐመድ ከነባለቤቱ ከዚህ ጉባኤ ካልወጣ ስብሰባው አይካሄድም አሉ። ጉባኤውንም ረበሹት። ከስብሰባም እንድወጣ ተደረገ። የሚያሳዝነኝ እሳቸው የጉባኤው አባል ሳይሆኑ፣ ቲፎዞ ይዘው ወደ ጉባኤው በመግባት እኔን የጠቅላላ ጉባኤ አባል ከሕግ ውጪ ከስብሰባው እንድወጣ ተደረገ። ተምሯል ተብሎ ከሚጠበቅ አንድ ትልቅ ሰው ይህን ነውር ማየት አሳፋሪም፣ አሳዛኝም ነበር።

 

ኃይሉ ሻውል ከእምነቴም እሳቸው ላይ ካለኝ አመለካከቴ ጀምሮ ከበፊትም ጫናቸው ይበረታብኛል። በዚህ ጉባኤ ላይ ግን መሰብሰብ የእኔ መብት እንጂ የሳቸው አልነበረም። የበላይ ጠባቂ ታዛቢ እንጂ የፓርቲ ጉባኤ አይመራም። ምን አልባትም ሃይሉ ሻውል የመጀመሪያው ሰው ሳይሆኑ አይቀርም። ከፓርተው በሕግ አግባብ የተባረሩ ቡድኖችን ሰብስበው በውጭ ታርቀው ጉባኤውን ንቀው አምጥተው በፓርቲው ላይ አስቀመጧቸው። እኛም ይህን አሳዛኝ ታሪክ ተመለከትን። ለእሳቸው በጣም አዝናለሁ። አሳፋሪ ስራ መፈጸማቸውን ሊገነዘቡት ግን ይገባል”

Leave a Reply