Wednesday,

13 April 2016 12:06

በ 

ኢትዮጵያውያኑ ከ365 ሺህ ዶላር በላይ በቻይና ኤርፖርት ጥለው ተገኙ

ሁለት ቻይናውያን ወድቆ ያገኙትን የኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ነው የተባለ 356 ሺህ 246 የአሜሪካን ዶላር አግኝተው ለፖሊስ አስረከቡ። ቻይናውያኑ ገንዘቡን ያገኙት በደቡባዊ ቻይና ጉዋንግዡ ግዛት ባዩን በተባለ አለም አቀፍ ኤርፖርት ሲሆን ገንዘቡ የተገኘው በኢትዮጵያ አየር መንገድ የወረቀት ከረጢት (Paper Bag) ነው።

 ሁለቱ ቻይናውያን በአካባቢው በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የነበሩ ሲሆን ገንዘቡን እንዳገኙ ለፖሊስ አስረክበዋል። ከዚያ በኋላ“የገንዘቡ ባለቤት ነን” ያሉ ሶስት ኢትዮጵያውያን ተጓዦች ወዲያውኑ መቅረባቸውን ዘገባውን ያሰራጨው ቻይና ደይሌ አመልክቷል። ፖሊስ ሪፖርቱ እንደደረሰው ገንዘቡ ተረክቦ ቆጠራ አካሂዷል።

በዚሁ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የትምህርትና ኮሙኑኬሽን  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን የውጭ ጥሬ ገንዘብን ይዞ ከሀገር መውጣት ህጋዊም ሆነ ህገወጥ የሚሆንባቸው መንገዶች መኖራቸውን አብራርተዋል።

 እንደ አቶ ኤፍሬም ገለፃ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ከሆነ በጥሬ ገንዘብ የውጭ ምንዛሪን ይዞ ለመንቀሳቀስ የተጣለበት ምንም አይነት ገደብ የለም።

ሆኖም ገንዘቡን ይዞ ለመንቀሳቀስ ግን ጉዳዩ የሚመለከተው የባንክ ፋቃድ (Bank Permit) ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ የውጪ ሀገር ዜጋ ከሆነ እስከ 3 ሺ የአሜሪካ ዶላር ይዞ መውጣት የሚፈቀድለት መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ የኢትዮጵያን ብር በተመለከተ ግን 2 መቶ ብር ብቻ የሚፈቀድ መሆኑን ገልፀዋል።

ገንዘቡ በምን መልኩ እንደተንቀሳቀሰ የቻይና መንግስት ያለው ነገር ባይኖርም ከበርካታ ደሃ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ከባንክ አሰራርና ስርዓት ውጪ የሚወጣ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ከዚህ ቀደም ባሰራጨው ዘገባ ይሄንኑ ጉዳይ አመልክቷል።

 በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባት ያለችው አፍሪካ ስትሆን ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ በአፍሪካ ህብረት በኩል ውይይት እስከሚደረግበት ደረጃ ደርሷል። በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ኢምቤኪ የተመራውና በዚህ ዙሪያ የራሱን ጥናት ያደረገው የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ፓናል ደልጌሽን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በህገ ወጥ መንገድ ከሚወጣባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን በዘጠነኛ ደረጃ አስቀምጧታል።

እንደ ጥናቱ ከሆነ አፍሪካ በሃምሳ አመታት ውስጥ በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር አጥታለች። ኢትዮጵያ ብቻ እ.ኤ.አ ከ1970 እስከ 2008 ወደ 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ማጣቷን የአፍሪካ ህብረት ፓናል ያመለክታል። ብዙው በህገወጥ መልኩ የሚወጣው ገንዘብ የህግ ተጠያቂነትን እንዳያስከትልና ከክትትል ውጪ እንዲሆን ከባንክ ውጪ በሆነ የገንዘብ ዝውውር እንደሚከናወን ታውቋል።

ስንደቅ

Leave a Reply