Wednesday, 13 April 2016 11:53
በ ፀጋው መላኩ
ሙስሊም ብራዘርሁድ ከስልጣን ተወግዶ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ ግብፅን በገንዘብ ጡንቻዋ ቁጥጥር ስር እያስገባቻት ነው።ሳዑዲ አረቢያ ለግብፅ በእርዳታና በብድር መልክ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ቢሊዮን ዶላር ስታፈስ የቆየች ሲሆን ከሰሞኑም የሳዑዲው ንጉስ የግብፅ ጉብኝትን ተከትሎ ይሄው ለግብፅ የሚፈሰው ቢሊዮን ዶላር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
እንደ ኢጂብት ዴይሊ ኒውስ ዘገባ ከሆነሳዑዲ የሲናይ በረሃን ዘመናዊ ግብርና ልማት እንዲኖረው፣የግብፅ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲሻሻል፣ ግብፅ ያላት የነዳጅ አቅርቦት የተረጋጋ እንዲሆንና ሁለቱ ሀገራትም በመሰረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ከፍተኛ ስራዎችን እየሰራች ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የሳዑዲ ባለሀብቶችም በግብፅ ምድር ከፍተኛ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ የግብፅን ኢኮኖሚ እንዲያነቃቁየሳዑዲ መንግስት ፕሮጀክት ቀርፆ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በልዩ ልዩ ማበረታቻዎች በመቀስቀስ ላይ ነው። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የሳዑዲ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋይ በግብፅ ምድር ይፈሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህም በተጨማሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል አፍሪካንና መካከለኛው ምስራቅን በሚለየው ቀይ ባህር ላይ ረዥም ድልድይ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል። ይህንን ድልድይ በመገንባት ሁለቱን ሀገራት ለማገናኘት ከታሰበ በርካታ አመታት የተቆጠሩ ሲሆን በአሁኑ የንጉስ ሳልማን ጉብኝት ግን ጠንከር ያለ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በዚሁ ዙሪያ አጠር ያለ ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዝዳንት አልሲሲ የድልድዩ መገንባት አፍሪካንና እስያን የሚያገናኝ ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀው፤ በተለይ በሳዑዲና በግብፅ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክረው መሆኑን ገልፀዋል።ድልድዩን ለመገንባት ከ 3 እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ሊጠይቅ ይችላል ተብሎ ተገምቷል። ድልድዩም በሳዑዲው ንጉስ በሳልማን ቢን አብዱል አዚዝ ስም የሚሰየም መሆኑን ፕሬዝዳንት አልሲሲ ተናግረዋል። ባለፈው ሃሙስ ለአምስት ቀናት ኦፊሴል ጉብኝት ካይሮ የገቡት የ80 ዓመቱ ንጉስ ሳልማን ጉብኝታቸውን በማጠናቀቅ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ከዚህ ቀደም በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ያደረጉ ሲሆን የንጉሱን ጉብኝት ተከትሎም ከሰሞኑ ብቻ 17 የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነቶች መፈረማቸውን ኤኤፍፒ በዘገባው አመልክቷል። የአብዛሃኞቹ ስምምነቶች የገንዘብ ምንጭ ሳዑዲ አረቢያ ስትሆን በርካቶች ሳዑዲ ግብፅን በገንዘብ ጡንቻዋ እያሰረቻት ነው የሚል አስተያትን እየሰጡ ነው።
ከመንግስታቱ የትብብር ስምምነት በተጨማሪ በርካታ ግብፃውያን በሳዑዲ አረቢያ ተቀጥረው በመስራት የስራ እድልን ከማግኘታቸውም በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጪ ምንዛሬን ወደ ግብፅ በመላክ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ይደግፋሉ።
ዘገባዎች ሳዑዲ ግብፅን በዚህ ደረጃ ስትደግፍ የኢኮኖሚ ስበት ተፅዕኖዋን በሀገሪቱ ላይ በማሳረፍ በማናቸውም የሳዑዲ የውጪ ፖለቲካ አቋም ግብፅን ተከታይ ለማድረግ በማሰብ ነው። ሳዑዲ አረቢያ በየመን እና በሶርያ በምታራምደው አቋም ግብፅ ከጎኗ እንድትሆን ትፈልጋለች።
ሩስያ በሶርያ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሳዑዲ አረቢያ በጥብቅ የምትቃወም ሲሆን፤ የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር የፈጠሩት የቅርብ ግንኙነት እንዲቀዛቀዝ ሳዑዲ በፅኑ የምትፈልግ መሆኑ ታውቋል።ፕሬዝዳንት አልሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሩስያና የግብፅ ግንኙነት የተጠናከረ ሲሆን በተለይ በወታደራዊው መስክ የቀደመውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለመመለስ ፕሬዝዳንቱ እየጣሩ ነው የሚሉ ግምቶች አሉ።
አልሲሲ በሞስኮ ከአራት ጊዜ ያላነሰ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከሩስያ ጋር በኢኮኖሚና በወታደራዊ ዘርፍ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸውን ተከታታይ ስምምነቶች ተፈራርመዋል። ግብፅ እየገጠማት ያለውን የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ለመቋቋም በሩስያ ሙያዊ እገዛ የኑኩሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት እንቅስቃሴ የጀመረች ከመሆኗም በላይ፤ ግብፅ ከሩስያ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያን ግዢ እንድትፈፅም የሚያስችላትን ስምምነት ማድረጓ ይታወሳል። ሳዑዲ አረቢያ ሩስያ በሶርያ በምታካሂደው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና ከኢራን ጋር ባላት ጥብቅ ግንኙነት ብዙም ደስተኛ አለመሆኗን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ የመጣውን የግብፅ ሩስያ ግንኙነት ለማቀዛቀዝ ፍላጎት ያላት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዚህምየሳዑዲ መጠነ ሰፊ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት፤ ሳዑዲ ከኢራን ጋር ባላት ባላንጣነትና በሶርያና የመንም ባላት አቋም ግብፅን ከኋላ ለማሰለፍ የሚደረግ የኢኮኖሚ ማሰሪያ ገመድ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።