ከአራት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ማክሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ምሽት፣ ታላቁንና ላቅ ባለው ሥራቸው ዓለም አቀፋዊ ክብርና ዝና ያገኙትን የሥነ ጥበብ ሰው፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ያጡበት ዕለት ነበር፡፡ እንደ አገር ትውፊት፣ እንደ አገር ልማድ፣ እንደ አገር ባህል በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መካነ መቃብራቸው ላይ የመታሰቢያ ሐውልት የቆመላቸው በ40ኛው ቀን፣ በ80ኛው ቀን፣ በመንፈቅ፣ ሻገር ሲል በሙት ዓመት አልነበረም፡፡ የአገር መነጋገሪያ ሆኖ ከቆየ በኋላ አራተኛው ዓመት ላይ በአንድ ኦሊምፒክ ዕድሜ (ኦሊምፒያድ)፣ እሑድ ሚያዝያ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ሐውልቱ ተጠናቆ ተመርቋል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱን ከንድፍ ጀምሮ የሐውልቱን ቅርጽ ሠርቶ ለማስጨረስ ወደ 150,000.00 ብር በሚጠጋ ወጪ ያሠራው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መሆኑን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በምረቃው ወቅት ተናግረዋል፡፡ የሐውልቱን ዲዛይን በማሠራቱ ሒደት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤትና የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ጉልህ ሚና መጫወታቸውን፣ በተለይም ሠዓሊ ግርማ ወልደ ሰማያት የሐውልቱን ዲዛይን በመሥራትና የሐውልቱን ሥራ በመከታተል ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸውም አውስተዋል፡፡ በዕለተ ሰንበት ረፋድ አራት ሰዓት ላይ በነበረው ጸሎተ ፍትሐትና የሐውልት ምረቃ ላይ ቁጥራቸው ከ50 የማያልፉ ሰዎች ብቻ መገኘታቸውና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንት፣ እንዲሁም ሌሎች አለመገኘታቸው በብዙኃኑ አለመወደዱ ተስተውሏል፡፡ ሐውልቱ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እንደሚቀሩት፣ አንዳንድ ያፈነገጡ መስመሮች ነቅሰው የተመለከቱ ሠዓሊያንም ድምፃቸው ቢሰማም፣ ለጥቅል ሥራው ግን አድናቆት ከመስጠት አልተቆጠቡም፡፡ የጥበቡ ሰው መጠሪያ ቅደም ተከተል መዛነፉን ‹‹እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሪየት ሜትር አርቲስት›› መባል ሲገባው ‹‹እጅግ የተከበሩ ሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬየት›› ተብሎ መቀመጡ፣ በተለይ በአማርኛው ጽሑፍ የሥርዓተ ነጥብ ጉድለት፣ በእንግሊዝኛው ፊደል ስማቸው በትክክል እሳቸው እንደሚጽፉት፣ ‹‹Afewerk›› (አፈወርቅ) መባሉ ቀርቶ ‹‹Afework›› (አፈዎርክ) መባሉ ምነው ቃፊር የለም ወይ አሰኝቷል፡፡ የራሳቸው መለያ የሆነው ዓርማቸው፣ በአውቶሞቢላቸውም ሆነ በቪላቸው ላይ ተለጥፎ የሚታየው ‹‹አፈወርቅ ወልደ ነጎድጓድ (Alpha Son of Thunder)፣ ከትውፊት የጠለፉት ሌላው መጠርያቸው ‹‹አባ መብረቅ››ስ እንዴት በሐውልቱ ላይ ሳይካተት ቀረ? እነዚህንና ሌላውንም ያስተዋሉት ቅርፀ ሐውልቱ፣ የኔታ አፈወርቅ ርእስ ጠበብት ለመሆናቸው ሜትር አርቲስት፣ የዓለም ሎሬት የሚለውን ከእጅግ የተከበሩ ጋር ያስቀጸለላቸው፣ የስኬታቸው ጫፍ የደረሱበትን ጉዞ በምልዓት አልገለጸውም ብለውታል፡፡ ለነገሩ ንድፍ ሥራውን ያከናወነው ሠዓሊና ቀራፂ ግርማ በሐውልቱ ምረቃ ላይ  የሰጠው፣  ‹‹ሎሬቱን አላወቅናቸውም፤ አልመረመርናቸውም፤›› የሚለው አስተያየቱ እውነታውን ያጎላዋል፡፡ አጥሩን ጨምሮ የሐውልቱ ማጠናቀቂያ ሥራ ክለሳ እንደሚደረግለት ይጠበቃል፡፡ የአፈወርቅ ወልደ ነጎድጓድ የጥበብ ሥራዎችና ንብረቶች እሳቸው በሕይወት እያሉ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ በገቡት ቃል መሠረት በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ሕጋዊ ሒደት ተከናውኖ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት መንግሥትን ወክሎ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቤትና ንብረታቸውን ተረክቦ በመጠበቅ፣ በማልማትና በማስተዳደር ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ እንዲያደርግ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም አስፈላጊውን የሕግ አግባብ በመከተል ውርሱና ሀብት ንብረቱ ከተጣራ በኋላ ባለሥልጣኑ ከታላቅ አደራ ጋር በይፋ ተረክቦ የሥዕል ጋለሪውን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ አውስተዋል፡፡ በመታሰቢያ ሐውልቱ ግንባታ ሒደትና በቪላ አልፋ ዕጣ ፈንታ ዙርያ ከጥበቡ ጎራ ታዋቂ ከሆኑት፣ በጸሎተ ፍትሐቱና በሐውልት ምረቃው ላይ ከተገኙት መካከል፣ የእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጓደኛ ከነበሩት ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔ አያልነህ ሙላቱ፣ ከሠዓሊት ደስታ ሐጎስ፣ እንዲሁም ከሙዚቃ ሰውና የኢትዮ ጃዝ ፈጣሪ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ሔኖክ ያሬድ አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

‹‹ቪላ አልፋን እንደገና እናደራጃለን ካሉ የአፈወርቅን መንፈስ ነው የሚያጠፉት››

ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ

ሪፖርተር፡- የእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የመቃብር ላይ ሐውልት ግንባታ አንድ ኦሊምፒያድ (አራት ዓመት) ወሰደ፤ እንዴት ነው ነገሩ?

ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ፡- ቢዘገይም መሠራቱ ጠቀሜታ አለው፡፡ በጣም ዘግይቷል፡፡ መዘግየቱ ለብዙ ሐሜታና ውዝግቦች የዳረገ ነው፡፡ በተለይ ቅርበት ላለን ሰዎች፣ በተለይ እሱ ለአገሪቱ የሰጠው ገፀ በረከትና ስጦታ የሥዕሉ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ካደረገው አስተዋጽዖ ጋራ ስታነፃፅረው እኔ ይሄን ያህል ጊዜ የሚፈጅ መስሎ አይታየኝም፡፡

አፈወርቅ ሐውልቱን መሥራት የሚችል ሰው ነው፡፡ በብዙ ነገሮች የተደራጀ ሰው ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ መጨረሻ ላይ የማይሆን ነገር ላይ ወድቆ፣ የሕይወት አመራር ውዝግብ ውስጥ ወድቆ፣ ራሱን እስከ መጨረሻው ሳያጠናቅቅ ተቀደመ እንጂ ሐውልቱንም ሠርቶ የሚሞት ሰው ነበረ፡፡ ያም ሆኖ ይሄ መደረጉ ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መኖሪያቸውንና ስቱዲያቸውን አጣምሮ የያዘው ቪላ አልፋስ ነገር እንዴት ነው?

ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ፡- ቪላ አልፋ መንግሥት ጋ ሄዶ መሸጎጡ አንዱ ትልቁ ችግር ይመስለኛል፡፡ ይህን ድርጅት ራሱን በቻለ መልኩ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ የመንግሥት ተቋማት ራሳቸውን መምራት በማይችሉበትና የተዝረከረከ ነገር እያለ፣ አሁን እንደገና ሌላ ነገር እንጨምር ብሎ ማለት ግዛትን ከማስፋት ውጪ ጠቀሜታው ብዙ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ለምን እንደዚህ ያለ ነገር ላይ ሲሆን፣ ልዩ የሆነ መስፈርት ያለው ልዩ ኮሚቴ ወይም ስፔሻል ፈንድ ተቋቁሞ እንዲመራው ቢደረግ በጣም ከፍተኛ ውጤት ያለው ሥራ ሊሠራ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ቪላ አልፋን እናደራጃለን እያሉ ነው፤

ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ፡- አፈወርቅ የቪላ አልፋ ሙዚየሙን አዘጋጅቶት ነው የሞተው፡፡ እያንዳንዷን ዕቃ ለይቶ፣ ምን እንደሆነች በደንብ አድርጎ ከውጭ አገር ኤክስፖርቶች ጋራ እየተመራ አዘጋጅቶት ነው የሞተው፡፡ ከፍቶ ማስጎብኘት ነው እንጂ ይህንን ቪላ አልፋን እንደገና እናደራጀዋለን ብለው ከተነሡ ያበላሹታል፡፡ ቪላ አልፋን እንደገና እናደራጃለን ካሉ የእሱን የአፈወርቅን መንፈስ ነው የሚያጠፉት፡፡ ሙዚየሙን ለመምራት ልዩ ኮሚቴ መቋቋም አለበት፡፡ ዝም ብሎ የሙያ ባለቤት ነኝ ወይም ደግሞ የመሥሪያ ቤቱ [ባለሟሎች] ነን በሚል ብቻ ተነሥቶ እናደራጅ ተብሎ ቢባል፣ የአፈወርቅ መንፈስ እዚያ ውስጥ አይኖርም፡፡ መንፈሱን ያዘጋጀው ሰው በሕይወት እያለ ራሱ ያዘጋጀው፣ ደግሞ ትክክለኛ ነው ብለን የምናምነው እያለን ዛሬ ወደ ሌላ መልክ ለውጠን ‹‹ዘመናዊ›› እናድርገው፣ ምናምን እናድርገው ተብሎ ቢጀመር እኔ ትልቅ ችግር የሚፈጠር ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው?

ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ፡- ሁለት ነገሮች ይታዩኛል፡፡ አንዱ በተለይ በልዩ ኮሚቴ ወይም ፈንድ ወይም ሌላ ስም ተሰጥቶት አመራሩ በዚያ ቢካሄድ እዚያ ውስጥ ትልልቅ ሰዎች ይኖሩበታል፡፡ እንደ ሪታ ፓንክረስትና አሉላ ፓንክረስት እንዲሁም ሌሎች የጥበብ ሰዎች ይሳተፉበታል፡፡ የዓለምን ታላላቅ ሰዎች ሊስብ በሚችል መልኩ መመራት አለበት፡፡ ልዩ የፕሮፖጋንዳ ሥራና ማስታወቂያዎችም እየተደረጉ ተግባሩ መከናወን አለበት፡፡ ተቋሙ ግማሽ ነፃ ሆኖ መንግሥት ቁጥጥሩንና ገንዘቡንም ማድረግ ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ባይሸጎጥና በራሱ ቢካሄድ ለአገሪቱ ገጽታ መለወጥ፣ ለሥራውም እንቅስቃሴ ጠቀሜታ ያለው ይመስለኛል፡፡ አሁን እዚያ ውስጥ [ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን] ወስዶ መሸጎጡ ትልቅ ችግር ነው፡፡ መንግሥት ሁሉም ነገር ላይ እጁን ካስገባበት ለአሠራር ችግር ይሆናል፡፡ የተለየ ዕውቀትና አመራር፣ ፍቅርንም ይጠይቃል፡፡ በየቦታው በየቀኑም ማበልፀግንም ይሻል፡፡ ለምሳሌ ኮምፒተራይዝድ ልታደርገው ብትነሳ ሥራውን የሚሠራው ይኸው ልዩ ኮሚቴ ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ከተመለከትከው ብሔራዊ ሙዚየም ነው የሚሆነው፡፡ ብሔራዊ ሙዚየም አሁን ያለበትን ደረጃ ታውቀዋለህ፡፡ አንዳንድ ነገሮች እንኳን ተሻሽለው ተገለባብጠው እንኳን አታያቸውም፡፡ በገባህበትና በወጣህበት ነው የምትመላለሰው፡፡ ያ ያንን መድገም እኔ አይታየኝም፡፡ ያ እንዳይደገም ከተፈለገ ልዩ ተቋም ማቋቋሙ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቤተ ክርስቲያኑ አፀድ ባሻገር አደባባይ ላይ መታሰቢያ አያስፈልግም?

ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ፡- ይገባል፡፡ እኛ ይህን ሁሉ አቅርበናል፡፡ እኔ የውርስ አጣሪ ኮሚቴ ውስጥ በፍርድ ቤት በኩል ወዳጅ ተብዬ በተወከልኩበት ጊዜ የአደባባይ መታሰቢያን በተመለከተ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ያሁኑን ሐውልት ለመሥራት አራት ዓመት ነው የወሰደው፡፡ የርሱን አደባባይ ለማስገኘት በዚህ መልኩ ከቀጠለ ሌላ አርባ ዓመት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው የተለየ ኮሚቴ ከተቋቋመ፣ የእኔ ሥራ ነው ብሎ ስለሚለው በተለያዩ ነገሮች የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ውጤታማ ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡ ከዚያ ውስጥ ከተገባ ግን ያንኑ የሐውልቱን ያህል ዕድሜ፣ ከዚያም የበለጠ ዕድሜ ሊጨርስ የሚችል ሥራ ይሠራል ብዬ ነው፡፡ የማስበው፡፡ እና ይኸንን ነገር ቢለቁት ምናለ፣ ሕዝቡም ነፃ ሆኖ ቢመለከተው፡፡

ስለዚህ አንድ ቦርድ ተቋቁሞ ቢሠራ ነገ ከነገ ወዲያ እንደዚህ ዓይነት ተግባር ለሚሠራላቸው ደራስያን ለነ ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ ለነ መንግሥቱ ለማ ለመሳሰሉ፣ ሠዓልያንም ሌሎች ጠቢባን አርአያ ይሆናል፡፡ ጠቢባኑ የት እንደወደቁ አናውቃቸውም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ኮሚቴ ቢቋቋም ግን ጉዳዩን እየተመለከተ የደራስያን መጻሕፍታቸውን፣ የሠዓሊዎችን ሥዕላቸውን በየመልኩ ሊያደራጅና ትልቅ ሥራ ሊሠራ ስለሚችል ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ይመስለኛል፡፡ ቪላ አልፋ መንግሥት ውስጥ መወተፉ ግን አሁንም ቢሆን አይታየኝም፡፡ መንግሥት የበላይነቱን ትክክል ነው መውሰድ አለበት፤ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ነውና፡፡

*******************************

‹‹ዕውቀቱ መውደዱ አድናቆቱ ያለው ሰው ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት››

ሠዓሊት ደስታ ሐጎስ

ሪፖርተር፡- ሥነ በዓሉን እንዴት አየሽው?

ሠዓሊት ደስታ ሐጎስ፡- የዛሬው ተግባር ትልቅ ተስፋ ነው የሰጠኝ፡፡ አገራችን መሠረቷ የጥበብ አገር ናት፡፡ አፈወርቅ ቀደምት ሆኖ የኢትዮጵያን ስም በጥበብ ያስነሳ ሰው ነው፡፡ አፈወርቅ ዘመድ የለውም፣ ልጅ የለውም ተብሎ ዝም አለመባሉ፤ መንግሥት በትልቅ ደረጃ አስቦበት፣ ለጥበብም ትኩረት ሰጥቶበት ይህንን ሥራ መሥራቱ ለእኔ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ ለጠቢባኑም ተስፋ ይሰጣል፡፡ ጥበቡንም ያሳድጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሐውልቱን ለመሥራት ዓመታትን ወስዷል፤

ሠዓሊት ደስታ ሐጎስ፡- እውነት ለመናገር ዘግይቷል፡፡ እኛም ብዙ ሰውም ጠይቋል፡፡ ነገር ግን በንብረቱ ጉዳይ ሲከራከሩ ነበረ፡፡ ሁለተኛ እኛ ጠቢባኑ አልጎበዝንም፣ መጎትጎት መሥራት ነበረብን፡፡ ይኼ አይካድም፡፡ ሆኖም በመጨረሻም እንደዚህ ዓይነት ሥራ መሠራቱ በጣም ደስ ብሎናል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ቪላ አልፋ››ን በተመለከተ ምን መደረግ አለበት?

ሠዓሊት ደስታ ሐጎስ፡- ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ በእውነት አንዲት ስንጥር ሳትቀር ተመዝግባለች፡፡ በቅርስነት በታሪክነት መጠበቅ ስላለበት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ቪላ አልፋን ለማስተዳደር ልዩ ዕውቀትን ስለሚጠይቅ፣ በሙያው በተካኑ (ስፔሻላይዝ ባደረጉ) መመራት አለበትና የአፈወርቅን ልዕልና እያየን እነማንስ ናቸው ሊመሩት የሚችሉት? የሚያሳስበው እሱ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ቀናነት ሊኖር ይችላል ግን ዕውቀት ያስፈልጋል፡፡

ሠዓሊት ደስታ ሐጎስ፡- ግልፅ ለመናገር፣ መቼም አለመታደል ሆኖ ከመሠረታችን ስለ ጥበብ ስንማር አልኖርንም፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች እንደ ሌሎች የሚያደንቁ ሕዝቦች እያደነቅን አልነበረም፡፡ አሁን እንዳልከው ዕውቀቱ፣ መውደዱ፣ አድናቆቱ ያለው ሰው ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ ሁሉም ቦታ ችሎታ ኖሮት አይደለም፣ ሰው የሚመደበው ወይም ተወክሎ የሚቀመጠው፡፡ በዚህ ምክንያትም ብዙ ብልሽት ይካሄዳል፡፡ ግን አሁን ታስቦበት፣ ትኩረት ሰጥቶ ትልቅ ንብረት ነው፣ ትልቅ ታሪክ ነው ብሎ ቪላ አልፋን የሚጠብቀው ሰው ያስፈልጋል፡፡ መቼም አሁን ያለን ባህል ሚኒስቴር ይመስለኛል፡፡ ባህል ሚኒስቴርም በጠሩ ሰዎች አጠናክሮ ዕውቀትና አድናቆት ያለው፣ ታሪክን የሚያውቅ፣ በታሪካችን እንደ አክሱም ሐውልት ያሉትን የሠሩ ነበሩንና ይህን በጉልህ ሊናገሩ፣ ሊጠብቁ የሚችሉ ሰዎች በቦታው መመደብ አለባቸው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

*****************************

‹‹ዋናው ነገር ሁኖ ማየታችን ነው››

የሙዚቃ ሰው ሙላቱ አስታጥቄ

ሪፖርተር፡- የዛሬውን ሐውልት ምረቃ እንዴት አገኘኸው?

የሙዚቃ ሰው ሙላቱ፡- መቼም ትልቅ ታሪክ ነው ብዬ የማምነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ክብር መስጠት ራሱ ላሉትና አዲስ ለሚፈጠሩት መልካም ነው፡፡ ታላላቅ ሠዓሊዎች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ለእነርሱ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ የወደፊታቸውን እንዲያዩ፣ የበለጠ እንዲሠሩ፣ እነሱ ካለፉ በኋላ እንደዚህ መከበር ሊኖር እንደሚችል የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ሐውልት ላቆሙት ከልብ ነው የማመሰግናቸው፡፡ ብሩህ ተስፋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሐውልቱን ማቆሙ አራት ዓመት ወሰደ’ኮ፤

የሙዚቃ ሰው ሙላቱ፡- የጊዜው ጉዳይ ሳይሆን መሠራቱ ነው የሚታየው፤ ምናልባት ጊዜ የወሰደው ሲጠና ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ዋናው ነገር ሁኖ ማየታችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደፊትስ ምን መደረግ አለበት?

የሙዚቃ ሰው ሙላቱ፡- አፈወርቅ በእውነት የሚደንቅ ሰው ነው፡፡ አልፎ አልፎ እንገናኝ ነበር፡፡ ቤቱን (ቪላ አልፋ) ለመጎብኘት ሄጄ ያየኋቸው ሽልማቶች ስመለከት፣ ለአንድ አፍሪካዊ ሠዓሊ በዓለም ዙርያ ይህ ሁሉ ክብር ተሰጥቶት ሳይ በጣም ነው ያኮራኝ፡፡ ወጣቶቹ በተለይ ቪላ አልፋ በሚከፈትበት ሰዓት ላይ እነዚያን ሽልማቶች መመልከትና መመራመር ከቻሉ እነርሱም እንደሱ መሆን እንዲችሉ ያነሳሳቸዋል፡፡

ሪፖርተር