Wednesday, 20 April 2016 13:23

 በይርጋ አበበ

 

በጋምቤላ ስላለቁት ዜጎች ምሁራን፣ ፓርቲዎችና መንግስት ምን አሉ?

በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለው የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአገሪቱን መንግስት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር እና የፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩን አቅርቦ በጋምቤላ ክልል በተፈጠረው ጭፍጨፋ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ አደረገ። ከከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናቱ በተጨማሪ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት በክልላቸው የደረሰውን አደጋ አብረው ሲያወግዙ አሳዬ። ከኢህአዴግ እና ከጋምቤላው ፕሬዚዳንት ጎን ለጎን ደግሞ የድህነት ቀንበር በሚገባ የገረፋቸው መሆኑን የሚያሳብቁ፣ ልብሳቸው ከገላቸው ላይ ያለቀ አዛውንቶች ቀርበው የደረሰባቸውን ጉዳት እንዲያስረዱ እድል ስላገኙ የደረሰባቸውን በደል በቋንቋቸው አቀረቡ።

ከላይ የተጠቀሰው ማብራሪያ ባሳለፍነው ዓርብ በጋምቤላ ክልል አኝዋክ እና ኑዌር ዞኖች በሚገኙ የአምስት ወረዳዎችን ነዋሪዎች ከደቡብ ሱዳን የተነሳውና የሽፍቶች ስብስብ የሆነው ቡድን ያደረሰው ግድያ፣ ዝርፊያ እና አፈናን አስመልክቶ ለተፈጠረው ቀውስ የተሰጠ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ከ500 በላይ ሰዎችን አሳፍረው በሜዲትራኒያን ባህር አቋርጠው ጣሊያን ለመግባት ጉዞ የጀመሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያንና ሶማሌያዊያን ዜጎች ጀልባዎቹ በመገልበጣቸው ሁሉም ሊባል በሚችል መጠን ህይወታቸው አለፈ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ኢትዮጵያዊያኑ ቁጥራቸው የሚበዛ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ። ከአንድ ዓመት በፊት በሊቢያ ዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን አይ ኤስ በግፍ የቀላቸው 31 ኢትዮጵያዊያን ሀዘን ሳይረሳ በድጋሚ ይህን ያህል ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ለስደት በሚጓዙበት ባህር ሰጥመው ለሞት ተዳርገዋል።

እነዚህ ከላይ የተቀመጡት ሁለት አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተቶች ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሱ ሰቆቃዎች ናቸው። ሰቆቃዎቹን በተመለከተ መንግስት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ምሁራን ምን አሉ? ለሚለው ጥያቄ የሚመለከታቸውን ግለሰቦች ሰንደቅ ጋዜጣ አነጋግሮ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት

የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከደቡብ ሱዳን መንግስትም እንዲሁም ከታጣቂ ቡድኑ ውጭ የሆነ ነው ባሉት ታጣቂ ቡድን ባደረሰው ጥቃት 208 ሰዎች መሞታቸውን፣ 75 ሰዎች መቁሰላቸውን እና 108 ህጻናት ታፍነው መወሰዳቸውን ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የሞት በትር በህጻናትና በሴቶች ላይ የበረታ መሆኑን ተናግረው ጉዳቱን ያደረሰው ደግሞ ከመሬሌ ጎሳ የተነሳው ከብት ዘራፊ ቡድን ነው ሲሉ ነበር የተናገሩት። አቶ ኃይለማሪያም ጥቃቱ በተፈጸመ በሶስተኛው ቀን በቴሌቪዥን ቀርበው በተናገሩት መግለጫቸው ላይ “ከዚህ በፊት በተለምዶ ይሄ የመሪሌ ጎሳ የሚባል የጎሳ አባላት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ጋምቤላ ክልል በመግባት በባህላዊ መንገድና በተለያዩ ኋላ ቀር አስተሳሰቦች ምክንያት በህጻናት፣ በከብቶች ዘረፋና ግድያ እየፈጸሙ መሄዳቸው ይታወቃል። ከዚህ በፊት የነበሩ ጥቃቶች በመጠናቸው ትንሽ እና በአርብቶ አደር አካባቢ እና በድንበር አካባቢ ይከሰታሉ ተብለው የሚወሰድ ቢሆንም ነገር ግን የዛሬውን ለየት የሚያደርገው አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት ወደ 208 የሚሆኑ በርካታ ህጻናትንና እናቶችን  በመጨፍጨፍና ወደ 108 የሚሆኑ ህጻናትን ደግሞ በንጥቂያ ይዞ በመሄድ በደል አድርሰዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ኃይለማሪያም ጨምረውም “መንግስት በአሁኑ ሰዓት እነዚህን የታጠቁ ሀይሎች መከላከያ ሰራዊታችን ቦታው በመድረስ ከገቡበት ገብተው የተነጠቁ ልጆቻችንን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲመልሱ ለማድረግ ከዛም በላይ እነዚህ የታጠቁ ሀይሎች ከገቡበት ገብተው እርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ያለው። እስካሁንም በርካታ ታጣቂዎችን ገድሏል ቁጥሩን ወደፊት የሚገለጽ ይሆናል። የኢፌዴሪ መንግስት ከደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ መንግስት ጋር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየት ጀምሯል” ብለው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም “ጥቃቱን ያደረሰው ከደቡብ ሱዳኑ መንግስትም ሆነ ከኣማጺው ጦር ውጭ ነው” ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ኃይለማሪያም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ባደረሰው የመልስ ምት ቁጥሩ ያልታወቀ የታጣቂ ሀይል መሞቱን ቢናገሩም የመንግስታቸው የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ጌታቸው ረዳ ግን ለአሶሼትድ ፕሬስ እና ለሮይተርስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የመንግስት ሰራዊት 60 ታጣቂዎችን መግደሉን ተናግረዋል።

የተቃዋሚዎች አስተያየት

“በጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በኑዌር ብሔረሰብ አባላት ላይ በተፈጸመው ግድያ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን” ሲሉ በጋራ መግለጫ ያወጡት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና ሰማያዊ ፓርቲዎች  ናቸው። ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው “ዜጎቻችን ለዚህን ያህል ጥቃት የተዳረጉት ቀደም ሲል ጥቃት ሲፈጸምባቸው እንደቆየ እየታወቀ የኢህአዴግ መንግስት ግን ራሳቸውን የሚከላከሉበትን ትጥቅ በማስፈታቱ የመከላከያ መሳሪያ እንዳይኖራቸው በመደረጉና ባዶ እጃቸውን በቀሩበት ሁኔታ ለደህንነታቸው ተገቢው ጥበቃ ስላልተደረገላቸው መሆኑን መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባሉ” ብለዋል።

ፓርቲዎቹ አያይዘውም “ቀደም ባሉት መንግስታት በየጠረፍ አካባቢዎች ይመደብ የነበረው ጠረፍ ጠባቂ ሀይል እንዳይኖር በመደረጉ የውጭ ሀገር ታጣቂዎች እንደፈለጉ ድንበር ጥሰው የሚገቡበትና ወገኖቻችን ጥቃት የሚደርሱበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል” ሲሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የምሁራኑ ሀሳብ

ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት ከአቶ ኃይለማሪያም መግለጫ ላይ በመነሳት ነበር። አቶ ኃይለማሪያም ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ ከተቃዋሚው የሪክ ማቻር ቡድን ውጭ መሆኑን በቴሌቪዥን መናገራቸውን እንዴት ያዩታል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ “ዜጎቹ የእኔ ናቸው አይደሉም ወይም እኔን አይመለከተኝም ወንበዴዎች ናቸው ማለት የነበረበት የደቡብ ሱዳን መንግስት ነው። የእኛ መንግስት ትኩረቱ መሆን ያለበት በዜጎቻችን ላይ ስለደረሰው ጥፋት እንጂ ጥቃት ስላደረሰው ቡድን ማንነት ላይ አልነበረም” ሲሉ ይናገራሉ።

ዶክተር በድሉ አያይዘውም “አንድ ሉዓላዊ አገር ክልል ውስጥ ለሚፈጸም ጥፋት ጥቃት ያደረሰው አገር መንግስት ተጠያቂ መሆኑ ግልጽ ነው። ጥቃቱን ያደረሰው ቡድን አባላት ሱዳናዊ በመሆናቸው የደቡብ ሱዳን መንግስት ለጥፋቱ ተጠያቂ ነው” በማለት ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። ዶክተር በድሉ “ሌላው አሳዛኙ ነገር እኮ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ (ቃለ ምልልሱን ያደረግነው ትናንት ማክሰኞ ረፋዱ ላይ ነው) የደቡብ ሱዳን መንግስት ኦፊሻላዊ መግለጫ አልሰጠም። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ማብራሪያ መጠየቅ ነበረበት። ሌላው ቀርቶ ሀዘናቸውን እንኳን አልገለጹም። ይህ የሚያመለክተው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ንቀት ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ውድቀት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ጦርነት ቢከፈት እኮ በአንድ ቀን መቶ ሰው አይሞትም” የሚሉት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፤ “ጥቃት አድራሾቹ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ወይም ከተቃዋሚው ወገን አለመሆናቸውን ከደቡብ ሱዳን መንግስት በደረሰን መረጃ ለማወቅ ችለናል” ሲሉ አቶ ኃይለማሪያም የተናገሩትን አይቀበሉም። “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልክ ወይም በሌላ መንገድ ነግረዋቸው ሊሆን ይችላል ነገር ግን እኔ እያልኩህ ያለሁት የደቡብ ሱዳን መንግስት በግልጽ በሚዲያ የሰጠው መግለጫ የለም ነው። በውጭ ወራሪ አንድ አገር ላይ ባደረሰው ጥቃት ይህን ያህል ሰው ሞቶ፣ ቆስሎ እና ታፍኖ ተወስዶ የሀዘን ቀን የማይታወጅበት ምክንያትስ ምንድን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኮ ችግሩ ሲፈጠር በጣና ፎረም ስብሰባ ላይ ተቀምጠው ነበር። ነገር ግን ስብሰባውን እንኳን አቋርጠው መግለጫ ለመስጠት አልፈለጉም። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ግን የፖሊስ ጣቢያ ህንጻ እና መኪና ተቃጠለ ብለው በየቴሌቪዥኑ ሲናገሩ አይተናቸዋል። እውነት ለመናገር እንኳን ይህን ያህል ዜጋ ሞቶ ይቅርና አንድ ሰውስ ቢሆን የሞተው ከፖሊስ ጣቢያ ህንጻ እና ከመኪና የቱ ይበልጣል?” ሲሉ መንግስት በጋምቤላው ጥቃት ላይ የወሰደውን የተለሳለሰ አቋም በመተቸት ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው “ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት በዚህ መልኩ ማለፉ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዜጋ እጅግ አሳዛኝ ነው” ሲሉ መናገር ይጀምራሉ። አቶ ሙሼ “የደረሰው ጉዳት መጠኑ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ባይቀርብም የደረሰውን ጉዳት ስመለከት ግን ቦኮሃራም ናይጄሪያ ላይ ካደረሰው በምንም የሚተናነስ ሆኖ አላገኘሁትም” ይላሉ።

የደቡብ ሱዳን መንግስት በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ኦፊሻላዊ መግለጫ አለመስጠቱን እንዴት ያዩታል ተብለው የተጠየቁት አቶ ሙሼ “በመጀመሪያ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን የያዘበትን መንገድ ማየት ይኖርብናል። የኢትዮጵያ መንግስት ጥቃቱን የተመለከተው ቀለል አድርጎ እና ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጎ ነው። ስለዚህ የአገሪቱ መንግስት ቀለል አድርጎ በተመለከተው ጉዳይ ላይ የደቡብ ሱዳን መንግስት ከመሬት ተነስቶ ኃላፊነቱን በመውሰድ መግለጫ ሊሰጥ አይችልም። ከደቡብ ሱዳን የምንጠብቀው መግለጫ ከእኛ መንግስት በሚመነጭ አቋም ላይ ተነስተን ነው” ብለዋል።

አካባቢው ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸም እንደነበር በተደጋጋሚ ሲዘገብ የቆየ መሆኑን አቶ ኃይለማሪያምም ተናግረዋል። ቀጠናው ለውጭ ጥቃት ተጋላጭ መሆኑ ከታወቀ ሰራዊት ማሰማራት አግባብ አልነበረም ይላሉ? ለሚለው የሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ ደግሞ “ልክ ነህ አካባቢው ላይ ጦር ማስቀመጥ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጦር ማስቀመጡ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ከተቀመጠው ጦር የበለጠ ቁጥር ያለው ታጣቂ ይዘው ቢመጡ ጥቃቱ መፈጸሙ አይቀርም።  ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ማድረግ የነበረበት ለዜጎቹ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ነው። ይህ ማለት በአካባቢው በደቡብ ሱዳን ዜጎች ለሚፈጠር ጥቃት የደቡብ ሱዳን መንግስት ተጠያቂ እንደሚሆን ቀደም ብሎ ውይይትና ስምምነት መደረግ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ባህላቸው እንደዛ አይነት ከሆነ (በጦር መሳሪያ ታጥቀው ሌላውን መውረር) ጦር እንዲፈቱ ማስደረግ ይገባ ነበር” ብለዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply