ረጅም ጊዜ መቀመጥ ከሲጋራ ማጨስ አይተናነስም
የስራ ግዴታ ሆኖባቸው ረጅሙን ጊዜያቸውን በቢሮ ውስጥ ተቀምጠው የሚያሳልፉ ሰዎች ለተለያዩ እና ውስብስብ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው። መቀመጥ ማለት በአጠቃላይ ራስን መግደል ነው ሲሉም ባለሙያዎች ይደመድሙታል። አንድ ሰው በ24 ሰዓት ውስጥ ከስድስት ሰዓት በላይ የሚሆነውን ጊዜ በማንኛውም ምክንያት ተቀምጦ የሚያሳልፍ ከሆነ ለልብ ህመም የመጋለጥ እድሉን በ64 በመቶ ይጨምራል። በአንፃሩ ደግሞ ጤናማ ህይወት የመኖሪያ ጊዜውን በሰባት ዓመት ይቀንሳል የሚሉት በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች፤ ከዚህ በተጨማሪም ለበርካታ የካንሰር አይነቶች የመጋለጥ እድሉም ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስቀመጡት።
በእንግሊዝ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የተደረገው እና ከወራት በፊት ይፋ የተደረገው የቡድን ጥናት ደግሞ እንደሚያመለክተው፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ መቀመጥ እየፈጠረ ያለው ችግር ሲጋራ ማጨስ እየፈጠረው ከሚገኘው ችግር ያልተናነሰ ነው። እንደ ጥናቱ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የሚቀመጡ ሰዎች ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ከሚቀመጡት ጋር ሲነፃፀሩ Type-2 የስኳር ህመም እና ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው በእጥፍ ከፍ ያለ ነው። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ለካንሰር የመጋለጥ እድላቸው 15 በመቶ፣ እንዲሁም ከእድሜያቸው ቀድሞ የመሞት እድላቸው 17 በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል።
በተለይ ለቢሮ ታስበው በተዘጋጁ ወንበሮች ላይ ለረጅም ጊዜ ተቀምጦ ማሳለፍ ደግሞ ለጀርባ ህመም የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ የሚሆንበት ምክንያትም አንድ ሰው ሲቀመጥ አብዛኛው የሰውነቱ ጫና በጀርባው፣ በትከሻው እና በእግሩ ላይ ስለሚሆን ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጫናው በአብዛኛው የሚያርፈው በጀርባ ጡንቻ እና የአከርካሪ ዲስክ ላይ መሆኑን ነው ስፓይን ሄልዝ የተባለው እና በጀርባ ህመም ላይ የሚያተኩረው ድረ-ገፅ የሚገልፀው።
ስራቸው ለረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ ተቀምጠው እንዲሰሩ የሚያስገድዳቸው ሰዎች ቢኖሩ ከእነዚህ ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሰዓታትን ቆመው ማሳለፈ እንዳለባቸው ነው የእንግሊዝ ተመራማሪዎች የገለፁት። ከተቻለ ይህን ጊዜ እጥፍ በማድረግ ለአራት ሰዓታት መቆም አሊያም ቀለል ያሉ እና በቁም የሚሰሩ ስራዎችን መስራትንም ነው ባለሙያዎቹ የጠቆሙት። ከዚህ ውጪ ግን ወንበር ላይ ቁጭ በሚባልበት ወቅት በተቻለ አቅም ወደ መገልገያ ጠረጴዛ ቀረብ በማለት እና እጅን በጠረጴዛ ላይ ለማሳረፍ እንዲያመች ሆኖ መቀመጥ ያስፈልጋል። በወንበር ላይ ወደ ፊት ሳያጋድሉ ወይም ወደኋላ ሳይለጠጡ መቀመጥም አስፈላጊ ነው። ይህን በማድረግም የአከርካሪ ጡንቻን ከአቅም በላይ ከመለጠጥ መታደግ ይቻላል።
ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ግዴታ ከሆነ በሁለተኛ ደረጃ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ የወንበርን ከፍታ እና ዝቅታ ማስተካከል ነው። የምንቀመጥበት ወንበር ከጠረጴዛ የሚኖረው ከፍታ እንዲሁም ከመሬት ያለው ርቀት መስተካከል ይኖርበታል። እንደየሰው አይነትና የሰውነት ቅርፅ የወንበርን ከፍታ እና ዝቅታ ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም በትክክለኛው ወይም በአመቺ ሁኔታ ላይ መኖር አለመኖሩን ግን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ወንበሩ ከመሬት በሚኖረው ርቀት ሳቢያ እግር መሬት ለመርገጥ የሚያስቸግር ሁኔታ ከተፈጠረም የእግር መርገጫዎችን መጠቀም ያስፈልጋል። ይሄን በማድረግም እግር ተንጠልጥሎ ከፍተኛ ጫና እንዳይፈጠርበት ያግዛል።
ስራቸውን በኮምፒውተር አማካይነት ለሚያከናውኑ የቢሮ ሰራተኞች ደግሞ ጤናማ አቀማመጥን መምረጫ ሌላው መንገድ አይናቸውና የኮምፒውተር ስክሪናቸው ትይዩ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ትክክለኛ የሚባለውም ቀጥ ብለው ከተቀመጡ በኋላ ቀጥታ ፊት ለፊት ሲመለከቱ አይናቸው በኮምፒውተር ስክሪናቸው መካከል ላይ ማረፍ ሲችል ነው።
ከዚህ ውጪ ደግሞ የወንበሩን እጅ ማሣረፊያ መጠቀም በጀርባ የላይኛው ክፍል ላይ የሚኖረውን ጫና ለመቀነስ ያግዛል። የተወሰነው የላይኛው የጀርባ ጫና በእጃችን ላይ ስለሚያርፍ በአከርካሪ እና የጀርባ አጥንት ላይ የሚፈጠረውን ጫናውን ከመቀነስ በተጨማሪም ወደፊት ላለማዘንበል ጠቃሚ ዘዴ ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ። በተጨማሪም የወንበር የኋላ መደገፊያዎችን በአግባቡ በመጠቀም፣ እግርን ሙሉ ለሙሉ በመሬት ላይ አሊያም በመርገጫ ላይ በማሳረፍ በአጠቃላይ የወገብን ህመም ለመከላከል እና የሰውነት ቅርፅ የተስተካከለ እንዲሆን ያግዛል።