መድረክ የአንድነትን እገዳ አስቀጠለ፤ አንድነት ሰማንያውን ቀደደ
Wednesday, 12 November 2014 13:24
መድረክ እና የአንድነት አሰጥ አገባ እንዲህ ተጀመረ። የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም ከአምስት ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴምክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) 9ነኛ ጠቅላላ ጉባዔ አባል ድርጅቱ የነበረውን የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) በይፋ አገደ። አንድነት ለእገዳ የበቃበት ዋንኛ ምክንያት የመድረክን ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ አክብሮ ባለመንቀሳቀሱ ሲሆን አንድነት በመድረክ ላይ አፍራሽ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ማሰራጨት ሥራዬ ብሎ መያዙ ደግሞ ተጨማሪ ምክንያቶች ነበሩ። አንድነት እነዚህን ችግሮቹን ፈትቶ ሲመጣ በመድረክ አባልነቱ ሊቀጥል እንደሚችል ተስፋ ተሰጥቶትም ነበር። ነገር ግን ላለፉት ስምንት ወራት ጊዜያት ያህል በአንድነት በኩል የአቋም ለውጥ ስለመደረጉ ምንም ዓይነት የደረሰው መረጃ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን የተካሄደው የመድረክ ጠቅላላ ጉባዔ በአንድነት ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ እንዲቀጥል ሲል ውሳኔ በማሳለፍ ተጠናቋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ስለጉዳዩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ መድረክ የአንድነት እገዳ እንዲቀጥል የወሰነው ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት ለምርጫ ቦርድ እስከሚያስገቡበት ጊዜ ድረስ (በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከህዳር 15 እስከ 30/2007 ዓ.ም) መሆኑን ጠቅሰው ከዚያ በኋላ የአንድነት አቋም ተገምግሞ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሚኖር ተናግረዋል። «መድረክ ይህን ውሳኔ ሊያሳልፍ የቻለው አዲሱ የአንድነት አመራር በምርጫ ቦርድ በመታገዱ ምክንያት ከዚህ ጋር ተያይዞ የምርጫ ተሳትፎአችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል ከሚል መነሻ ይሆን ወይ» በሚል ዶ/ር መረራ ተጠይቀው ችግሩ የቆየ መሆኑን በማስታወስ ውሳኔው ከመጪው ምርጫ ጋር ግንኙነት የለውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“አንድነት ከመድረክ ከታገደ በኋላ በጉዳዩ ላይ ሁለታችሁም ተቀራርባችሁ ለመነጋገር ሞክራችሃል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ዶ/ር መረራ ሲመልሱ ለስድስት ወራት በአሜሪካን ሀገር ለሥራ ጉዳይ በመቆየታቸው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ስለመኖሩ አለመከታተላቸውን፣ ነገር ግን ወደሀገር ከተመለሱ በኋላ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል። ዋናው ነገር የአንድነት አመራር ከመድረክ ከታገደ በኋላ በይፋ የአቋም ለውጥ ስለማሳየቱ የገለጸው ነገር አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ሰይፉ አንድነት ከመድረክ ሊታገድ የቻለበትን ምክንያት ያስረዳሉ። አንድነት መድረክ የኢትዮጵያ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን በመገምገሙ እና የፀረሽብር ሕጉን በመቃወም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያካሄድነው የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ከመድረክ እውቅና ውጪ ነው በሚል ነው ያገደን። በዚህ በምርጫ ወቅት የአጋጅ ታጋጅ እሰጥ አገባ ውስጥ ባለመግባት ራሱን ከመድረክ ለማግለል መወሰኑን አስረድተዋል።
የአንድነት አዲሱ አመራር የጠራው የፓርቲው ብሔራዊ ምክርቤት ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም መድረክ የአንድነትን እገዳ ማራዘሙን በተመለከተ ተወያይቶ እስከነአካቴው ከመድረክ ለመውጣት መወሰኑን በኦፊሻል ድረገጹ አስታውቋል። የአንድነት መግለጫ እነሆ።
“አንድነት ከመድረክ ተገፍቶ እንዲወጣ ሆኗል”
“አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ መድረክ የተሻለ ስብስብ ሆኖ እንዲወጣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲሠራ እንደነበረ የሚታወቅ ነው። ከዚህም ባሻገር መድረክ የአሠራርና የአወቃቀር ለውጥ እንዲያደርግ፣ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ህዝብ ለለውጥ ከሚታገሉ ኃይሎች የሚጠብቀው ቅርፅና ቁመና እንዲኖረው ብዙ ጥረት አድርገዋል። የጥናት ኮሚቴ በማቋቋም በጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ ኀሳብም አቅርቦ ነበር። ነገር ግን በመድረክ ውስጥ ባሉ የተወሰኑ አመራሮች በአንድነት በኩል እየቀረበ የነበረው ማሻሻያ ወደ ጎን በመተው አንድነትን ከመድረክ እንዲታገድ መደረጉ የሚታወስ ነው።
አንድነት ምንም ዓይነት የፈፀመው ስህተት እንደሌለ ቢያውቅም፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ባለው ፅኑ አቋም ምክንያት እግዱ አግባብ ስላልሆነ እንዲነሳለት፤ መድረክ በትክክለኛ ሁኔታ ግንባር እንዲሆን የህገ ደንብና የአወቃቀር ማሻሻያ እንዲያደርግ በደብዳቤ ቢጠይቅም በመድረክ በኩል ለዚህ ጥያቄው መልስ ሳይሰጠው ለበርካታ ወራት ቆይቷል። አንድነት ይህ ሁኔታ የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ መፍትሄ ይሰጠው ይሆናል በማለት እስካሁን በትዕግስት ቢጠብቅም፤ በጥቅምት 29/2007 ዓ.ም. በተካሄደው የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ በአንድነት ላይ የተጣለውን እግድ እንዲቀጥል በመደረጉ ምክንያት አንድነት በአጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ወቅቱ የምርጫ ወቅት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሰዓት እግዱ እንዲቀጥል መደረጉ አንድነት በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ ቢፈልግ በእግድ ላይ ሆኖ መሳተፍ ስለማይችል፤ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 30/2007 ዓ.ም. ብሄራዊ ምክር ቤቱ ተስብስቦ ከመድረክ የነበረ ግንባር ያበቃለት መሆኑ ተገንዝቦ ከግንባሩ ራሱን በይፋ እንዲወጣ በከፍተኛ ድምፅ ወስኗል። በዚህ አጋጣሚ አንድነት አሁንም ቢሆን ከመድረክና ከሌሎች እውነተኛ ተቃዋሚዎች ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለው አቋም ፅኑ መሆኑ እንዲታወቅለት ይፈልጋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ሰፊ ጋዜጣዊ መግለጫ የምንሰጥ መሆኑ ተረድታችሁ በትዕግስት እንድትጠብቁን በአክብሮት እንጠይቃለን።»
**** *** ***
የአራት ፓርቲዎች ማለትም የደቡብ ኅብረትና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ (ኢሶዴፓ) ተዋህደው የፈጠሩት የኢትዮጵያ ማህበረ ዴሞክራሲ- ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ (ኢማዴደአፓ) ፣ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ)፣ የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዐላዊነት (አረና)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ግንባር የሆነው የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና አንድነት ከመድረክ ወጥቻለሁ ሲል ያሳለፈው ውሳኔ ይህ ጹሑፍ እስከተጠናቀረበት ሰኞ ዕለት ቀትር ድረስ አለመስማታቸውን ጠቁመው እውነትም ውሳኔ አሳልፎ ከሆነ ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል። “እኛም ያልነው በይፋ አቋማችሁን አሳውቁ ነው። ወይ አቋማችሁን አስተካክላችሁ የመድረኩን ፕሮግራምና ደንብ አክብረን አብረን ልንሰራ እንችላለን በሉ ወይንም አብረን ልንሰራ አንችልም በሉ በሚል ግልጽ ምርጫ ቀርቦላቸዋል። ዝም ከማለት አቋምን በግልጽ ማሳወቅ ጥሩ ነገር ነው” ካሉ በኃላ ከመድረክ መውጣትን ከመረጡ መብታቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ዶ/ር መረራ የተቃዋሚዎች አንድነት የማጣት ጉዳይ ለሠላማዊ ትግሉ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ተጠይቀው “ይህ ምን ጥርጥር አለው። ተቃዋሚዎች ተባብረው ቢሰሩ ውጤታማ ይሆኑ ነበር። አለመተባበራቸው ለኢህአዴግ የማርያም መንገድ ሰጥቶታል” ሲሉ ተናግረዋል።
መጪውን ምርጫም በተመለከተ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ለውይይት በሩን ክፍት እንዲያደርግ፣ ያጣበበውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲያሰፋ የመድረክ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ማሳለፉን ጠቅሰው በምርጫ የመሳተፍና ያለመሳተፍ ጉዳይ ወደፊት ሁኔታው ተገምግሞ የሚወሰን መሆኑን አስታውቀዋል።