ህወሓት በኢትዮጵያና ህዝቦችዋ ላይ ብዙ ታሪካዊ ስህተቶች የፈፀመ ቢሆንም ዋናው ግን በድርጅቱ የነበሩ( አሁንም ብዙዎች አሉ) አድራጊ ፈጣሪ ባለስልጣናት ‹‹ኤርትራውያን ናቸው›› ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ችላ በማለት ለኤርትራ ፍላጎቶችን ሽንጣቸው ገትረው በመከራከር ኢትዮጵያችን ያለባህር በር ማስቀረታቸው ነበር፡፡አንዳንዶቹ ‹‹ኢትዮጵያን ያለ ወደብ ያስቀረናት ታሪካዊ ህግጋቶችን ባለማወቃችን ነበር›› በማለት ፀፀታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ስህተቶች መስራታቸውን አምነው፣ እነዝያ ስህተቶች ለመድገም ባለፈለጋቸውም የነበራቸው ስልጣንም ሆነ ድርጅቱ በፍቃዳቸው ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ከእነዚህ አንጋፋ የድርጅቱ መሪዎች አንዱ ገብሩ አስራት ነው፡፡ገብሩ ከ1971 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ የህወሓት ማእከላይ ኮምቴና ፖሊት ቢሮ አባል እንዲሁም የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን መስራቱ ይታወቃል፡፡በተጨማሪም ከደርግ ውድቀት በኋላ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1993 ዓ.ም ህወሓት ለሁለት እስኪሰንጠቅ ድረስ የትግራይ ክልል ፕረዚደንት ሆኖ አገልግሏል፡፡አሁን በትግራይ የሚገኙት የትእምት ፋብሪካዎችም ሆነ ድርጅቶች(አልመዳ፣ዓዲ ግራት መድሐኒት ፋብሪካ፣መስፍን እንዳስትርያል እንጂኔሪንግ፣ መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ…)፣መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ የተቋቋሙት ገብሩ የትግራይ ክልል ፕረዚደንት በነበረበት ወቅት ነው፡፡ከ93ቱ የድርጅቱ መከፋፈል በኋላ ግን ‹‹የጎልጎል ራያ ፕሮጀክትን›› ጨምሮ በጅምር የቀሩ ብዙ ፕሮጀክቶች ዛሬም ድረስ ብዙ የትግራይ ተወላጆች የሚቆጩባቸው ናቸው፡፡

ከክፍፍሉ በፊት ከህወሓት ቁልፍ ሰዎች ጋር እኩል ይጠቀሱ የነበሩት እነ ተወልደ ተወልደማርያም፣አበበ ተክለሃይማኖት፣ፃድቃን ገብረትንሳኤ፣አለምሰገድ ገብረአምላክ ወዘተ በመገናኛ ብዙሓን የተረሱ ይመስላሉ፡፡በተለይ ተወልደና አለምሰገድ የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ምናልባት ግን ከክፍፍሉ ጋር ተያይዞ ህወሓት ስማቸውን ለማጥፋት ባደረገው ዘመቻ ተስፋ ሳይቆርጡ አልቀሩም ባይ ነኝ፡፡ገብሩ፣አረጋሽና ስየ ግን ከፖለቲካው ዓለም ሙሉ በሙሉ አልጠፉም፡፡ከሁሉም ግን ዛሬም ድረስ አንጋፋነቱ ያልደበዘዘው ገብሩ አስራት ነው፡፡ዓረና ትግራይን መስርቶ በመምራት አሁን ላለችበት ደረጃ ካደረሱ ሰዎች ግንባር ቀደም ነው፣ አቶ ገብሩ፡፡ሰሞኑን ደሞ ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› የሚባል 524 ገፅ ያለው መፅሐፍ ለአንባብያን በማበርከት እውነተኛ ታጋይነቱን አስመስክሯል፡፡
በግሌ ከእነዚህ አንጋፋ ታጋዮች፣ህወሓት ጭራቁ ደርግን አስወግዶ መላው ኢትዮጵያ እንዲቆጣጠር የረዱት ቁልፍ የትግራይ ልጆች የምጠብቀው ብዙ አስተማሪ መፅሐፎች እንዲፅፉ ነበር፡፡የህወሓት አሰራር በደምብ የሚያውቁት እነሱ በመሆናቸው ከእነሱ ብዙ እጠብቅ ነበር፡፡እንዳውም ያለፈው ታሪካችን ደካማና ጠንካራ ጎኖች ሳናውቅ ዓረና ትግራይ ፓርቲ መመስረታቸው የህወሓት ሌላው ገፅታ ናቸው የሚል እምነት አሳድሮብኝ ነበር፡፡ህወሓትን የሚቃወሙት በ93ቱ ክፍፍል በመለስ ብልጠት በመሸነፋቸው ለመበቀል እንደሆነ ነበር እማስበው፡፡አሁን ግን እውነታው ሌላ መሆኑን እየተገለፀልኝ ነው፡፡ገብሩ አስራት የፃፈው መፅሐፍ እኔን ጨምሮ የብዙ ተጋሩ አስተሳሰብ የሚቀይር ይመስለኛል፡፡በዚሁ አጋጣሚም በሃገር ወስጥ ታትሞ እንዲደረሰን በዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ማስታወስ የምፈልገው፡፡ዓረና ትግራይ መፅሐፉ ለአንባብያ እንዲደርስ መስራት የሚጠበቅባት ይመስለኛል፡፡

ከዋሽንግተን ዲሲ የሚሰራጨው የቬይስ ኦፍ አመሪካ የትግርኛው ክፍለ ጊዜ ከመፅሐፉ ጋር በማያያዝ አቶ ገብሩ አስራትን በሁለት ክፍል ያደረጋቸው ቃለ መጠይቅ ማድመጥ ችያለሁ፡፡ቃለ መጠይቁ የመፅሐፉ አጠቃላይ ይዘት በግርድፉ የሚያስቃኝ ከመሆኑም ባሻገር የገብሩ አስራት ማብራርያዎችም ለመከታትል አስችሎኛል፡፡ይህን መጣጥፍ ለመከተብ ያነሳሳኝም ቃለ መጠይቁ ሲሆን በአማርኛ ለመፃፍ የወሰንኩበት ምክንያትም ትግርኛ ማዳመጥ ለማይችሉ አንባቢዎቼን የቃለ መጠይቁ ጭብጥ የቻልኩትን ያህል ለማስቃኘትና የራሴ እይታዎችን ለመጨመር ነው፡፡በፅሑፉ የገብሩም ሆነ ሌሎች ታጋዮች ስም ስጠቅስ አቶ ወይም አንቱታን ያልተጠቀምኩበት ምክንያት ክብራቸውን ዝቅ ለማድረግ አስቤ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡

እነዚህ አንጋፋ ታጋዮችን አቶ ወይም አንቱ እያልኩ መጥራቱ ያራቅኳቸው መስሎ ስለሚሰማኝ ብቻ ነው፡፡እህትና ወንድም፣አባትና እናት አንቱ እያሉ መጥራት አይመቸኝም፡፡የልጅነቴ ታጋዮች በልቤ ልዩ ቦታ አላቸው፤አሁን የተሰማኝን በመፃፌና በመናገሬ ብቻ እንደ ደርግ ሊያስሩኝ ሊያሰቃዩኝ፣ህይወቴን ሊያመሰቃቅሉት፣ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቼን ሊነጥቁኝ፣ህተኩሰውም ሊገድሉኝ ይችላሉ ሆኖም ግን በልጅነቴ ሰርፆብኝ አብሮኝ ያደገው ፍቅር ከመቃበር በቀር ማንም ሊፍቅው አይችልም፡፡አሞራና ቀሺ ገብሩ በደርግ እጅ የወደቁ ጊዜ ምን ዓይነት ግርፋትና ስቅያት ደርሶባቸው እንደሚሆን መገመቱ አያዳግትም፡፡ሆኖም ግን እስትንፋሳቸው እስክታልፍ ድረስ ፈራሽ ገላቸውን ለማትረፍ ብለው እውነትን አልካዱም፡፡የእነሱና ጓዶቻቸው ድንቅ ታሪኮች እየሰማሁና እያነበብኩ ነው ያደግኩት፣ እንደ እነሱ ለእውነት እሞታለሁ፡፡እነሱ ለእውነት፣ለፍትህና ርትእ የተሰው የእውነት ሻማዎች ናቸው…ታድያ እንዴት አንቱ ልበላቸው?

የገብሩ አስራት መፅሐፍ የህወሓት የ40 ዓመታት የትግል ጉዞና በሂደቱ የተፈፀሙት ታሪካዊ ስህተቶችን በመዘርዘር እንዴት መታረም እንዳለባቸው የሚተነትን መሆኑን ከቃለ መጠይቁ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ህወሓት ከመነሻው ጀምሮ ፖለቲካዊ ብያኔዎችና አቋሞች የሚወስደው በጥናትና ምርምር ሳይሆን በስሜት እንደነበርም ተገንዝብያለሁ፡፡ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ሲነሳ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ምክንያት አልነበረውም፡፡የያኔው ወጣቶች መለስና አባይ ፀሐየ የ68ቱን ማኒፌስቶ አርቅቀው ሲያሰራጩት ጠንካራ ተቃውሞ ስለገጠማቸው ከስድስት ወር በኋላ ሐሳባቸውን ለመቀየር የተገደዱትም የሚከራከሩበት መርገጫ ስላልነበራቸው ነበር፤ ከማርክሲዝም-ለሊንዚም ርእዮተ ዓለም በስተቀር፡፡እንደ ገብሩ አገላለፅ የህወሓት ታሪካዊ ስህተቶች‹‹ከእውቀት ማነስና ወጣትነት ከሚያስከትለው ችኩልነት›› የተፈፀሙ ነበሩ፡፡

ሌላው ስህተት ‹‹የኤርትራ ጥያቄ የቀኝ ግዛት ጥያቄ ነው›› የሚለው አጉል መረገጫቸው ነበር፡፡‹‹የቀኝ ግዛት ጥያቄ ነው›› ብለው ስላመኑም ነበር የኤርትራ መገንጠልን ያለማቅማማት የተቀበሉትና ለተግባራዊነቱም ከሻዕብያ በላይ የታገሉት፡፡‹‹ያኔ የወሰድናቸው አቋሞች ዛሬ ላይ ሁኜ ሳሰላስላቸው›› ይላል ገብሩ አስራት ‹‹ምንም ዓይነት ታሪካዊና ስነ አመክንዮዊ መነሻ አልነራቸውም፡፡በአዋጅ እንጂ በምክክርና በክርክር የተወሰኑም አልነበሩም›› ነው የሚለው፡፡ በመቀጠልም ‹‹የ1952ቱ የኤርትራ ፌደሬሽን መፍረስ ለመገንጠል መክንያት ሊሆን ባይችልም እንደ አንዱ መነሻ ግን ሊሆን ይችላል›› ባይ ነው፡፡ምክንያቱን ሲገልፅም ያ የፈረሰው ህጋዊ ፌደሬሽን መመለስ እንጂ መገንጠል አዋጪ መፍትሔም ህጋዊ አካሄድም ስላልሆነ ነው ይላል፡፡አፄ ሚኒሊክ ከጣልያን ጋር በ1889ና በ1900 ዓ.ም.ፈ የተፈራረሙባቸው ውሎች‹‹ጣልያን በማንኛውም ምክንያት ኤርትራን ለቃ ስትወጣ ኤርትራን ለኢትዮጵያ ማስረከብ አለባት›› ነው የሚሉት፡፡ በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት በ1952 ዓ.ም.ፈ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት እንዲከበር ወስኗል፡፡በመሆኑም ኤርትራ ብትገነጠልም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ማንም ሊሽረው አይገባም ነበር፡፡

የኢርትራ ፌደሬሽን ለምን ፈረሰ?

ኤርትራ በፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ጋረ እንድትቀላቀል የወሰነው የተባበሩት መንግስታት ነበር፡፡ፌደሬሽኑ እውን እንዲሆን ትግርኛ ተናጋሪዎቹ(ደገኞቹ ክርስትያኖች) ኤርትራውያንና የአፄ ሃይለስላሴ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ቢሆንም ግን ፌደሬሽኑ ብዙ ሳይቆይ ነበር የፈረሰው፡፡በእርግጥ የፌደሬሽኑ መፍረስ የሚጠበቅ ነበር፡፡በአንዲት ሃገር ሁለት እርሰበርሳቸው የሚቃረኑ ህጎች ከቶም ሊኖሩ አይችሉምና፡፡ ምክንያቱን በትክክል ተረድቶ በደንብ የተነተነው ኤርትራዊ ምሁሩ ዮሴፍ ገብረሂወት ነው…‹‹Eritrea: The Federal ArrangementFarce›(ኤርትራ፡የፌደራል መዋቅሩ ቀልድ) በሚለው መጣጥፉ፡፡እንደ የሴፍ አገላለፅ በወቅቱ በንጉሳዊ አገዛዝ ስር የነበረችው ኢትዮጵያ ኤርትራ ዲሞክራሲያዊት( ነፃ ፕረስ፣ ራሳቸው የቻሉ የመንግስት አካላት…ህግ አውጪ፣ህግ ተርጓሚና ስራ አስፈፃሚ) ግዛት ሆና እንድትቀጥል ሁኔታው አይፈቅድም ነበር፡፡

ምክንያቱም ሌሎቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶችም እንደ ኤርትራ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ሊያነሱ ስለሚችሉ ነው፡፡ይህ ደሞ ለአፄ ሃይለስላሴ አገዛዝ አደገኛና በቀላሉ የማይዋጥለት ነበር፡፡ንጉሳዊ አገዛዝና ዲሞክራሲ አብሮው ሊሄዱ አይችሉም…የያኔዋ ኢትዮጵያ ከንጉሳዊው አገዛዝ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራትም፡፡

እናም ለራሷ ዲሞክራሲ ያለነበራት ኢትዮጵያ ከየት አምጥታ ነበር ለኤርትራ መስጠት የነበረባት፣ የሌለህን ነገር እንዴት ለሌሎች መስጠት ይቻላል? ‹‹የተባበሩት መንግስታት የኤርትራ ጉዳይ ከራሱ ለማውረድ ብሎ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትወሃድ አደረገ እንጂ በፍፁም ሊሆን የማይችል ነበር›› ባይ ነው የሴፍ ገብረሂወት፡፡በአንዲት በፍፅማዊ አገዛዝ ስር የወደቀች ሃገር ከፊሉ ግዛቷ ዴሞክራሲያዊ ከፊሉ ደሞ ኢዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡እናም ፌደሬሽኑ የግድ መፍረስ ስለነበረበት ነበር የፈረሰው፡፡መፍትሔው ግን ኤርትራን መገንጠል ሳይሆን ኢትዮጵያን እንዳለ ዲሞክራሲያዊት ሃገር ማድረግ ነበር፡፡ያኔ ኤርትራም በፌደሬሽን ተዋህዳ ትቀጥል ነበር፡፡

የዮሴፍ ገብረሂወት ሌላኛው ጥልቅ ትንታኔ የኤርትራ ጥያቄ የቀኝ ግዛት ጥያቄ ሊሆን እንደማይችል ያስረዳበት መንገድ ነው፡፡ምዕራባውያን ቀኝ ገዢዎች በሃገራቸው የሚኖሩ ህዝቦች በዲሞክራሲ እያስተዳደሩ በቀኝ ግዛቶቻቸው የሚኖሩት ህዝቦች ግን እንደ ባሮች ነበር የሚቆጥሯቸው፡፡እንዳውም ወደ ቀኝ ግዛቶቻቸው የሚወስዱዋቸው ነጮች የጥቁሮቹ ጌቶች አድርገው ነበር የሚስቀምጧቸው፡፡በቀኝ ግዛቶቻቸው የሚኖረው ማንኛውም ነገር እንደ ንብረት እንጂ እንደ ሰው አይቆጥሩም ነበር፡፡

አሜሪካን በቀኝ ግዛት ሲገዙ የነበሩት አውሮፓውያን ‹‹ቀይ ህንዳውያን›› የሚባሉት የሃገሪትዋ ባላባቶችን ስረ መሰረታቸውን በማጥፋት ነበር በአውሮፓውያን የተኳቸው፡፡ደቡብ አፍሪካና ዝምብባዌም ዛሬም ድረስ በነጮች እጅ ያሉ ሃገሮች ናቸው – የሮቦርት ሙጋቤው ነጮች የያዙት መሬት ለጥቁሮች የመመለስ ውሳኔ በምእራባውያን ምን ያህል እንደሚብጠለጠል የሚታወቅ ነው፡፡በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግን ይህ ክስተት አልነበረም፡፡ይልቁንስ በኢትዮጵያ የነበሩት ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን ባልተናነሰ መልኩ ከፍተኛ ባለስልጣኖችና ባለሃብቶች እንደነበሩ ነው ታሪክ የሚያወሳው፡፡ኢትዮጵያ የኤርትራ እንጡራ ሃብት ለመዝረፍ የተንቀሳቀሰችበት ወቅት አልነበረም፡፡

ዋናው ጉዳይ ጉዳይ ግን ምዕራባውያን አፍሪካን በቀኝ ግዛት ሲቀራመቱ ምክንያታቸው ‹‹አፍሪካን ከኋላ ቀርነት ለማናገፍ›› ነበር፡፡‹‹ኋላቀሮቹ አፍሪካውያንን በማሰልጠን ጨለማዋን አህጉር ለማዘመን ነበር በቀኝ ግዛት የያዝናት›› ነው የሚሉት፡፡ የአስተሳሰብ ልሂቃኖቹ አውሮፓውያን ‹‹ዓለምን የማዘመን ግዴታ አለብን›› ብለው ነበር የሚያስቡት፡፡ኢትዮጵያውያን ግን በኤርትራውያን ላይ ተመሳሳይ አመለካከት አልነበራቸውም፡፡ ይልቁንስ በአንፃሩ ኤርትራውያን(በተለይ ሞስሊም ሊሂቃን) ኢትዮጵያውያንን ‹‹ኋላ ቀር፣ፊውዳል፣ያልተማሩ፣ያልዘመኑ …›› እያሉ ይሰድቧቸው እንደነበር ነው የሴፍ የሚሞግተው፡፡እዚ ጋ የዮሴፍ ቃላት እንዳለ መዋስ ይኖርብኛል፡

‹‹If one takes a cursory look at the Muslim League’s literature in that era, it is rather astounding to see how this argument was used ad nausea. Reference to Ethiopia as “backward”, “feudal”, “medieval”, “uneducated”, “uncivilized”, “ignorant”, “primitive”, “archaic”, “inferior”, etc was frequent not only in its newsletter, but also in its correspondence with UN authorities. ››

እውነታው ይህ ከሆነ ታድያ በምን ምክንያት ነው ‹‹ኢትዮጵያ የኤርትራ ቀኝ ገዢ ነበረች›› ማለት የሚቻለው?

የህወሓት ሕንፍሽፍሽ

በ1969 ዓ.ም የተከሰተው የህወሓት(ያኔው ትሓሕት) ሕንፍሽፍሽ(ብጥብጥ) መንስኤ አውራጃውነት አልነበረም፡፡ መነሰኤው የአመራር ስልጣን በዴሞክራስያዊ ምርጫ ይሁን የመሳሰሉ የፍትሕ ጥያቄዎች እንደነበሩ ነው አቶ ገብሩ የሚገልፀው፡፡ ህወሓት ያኔ የጀመረው፣አሁንም እየሰራበት ያለው ማንኛውም ጥያቄ ሲቀርብበት በጅምላ የመፈረጅና የተለመደ ጥቀርሻ የመቀባት ባህል ‹‹አውራጃውነት›› በማለት ፈርጆት ነበር፡፡ይህ አካሄዱ አሁንም ቀጥሎበት ተቀናቃኞቹን ‹‹ትምክህተኛ፣የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣የኒዮ ሊበራሎች አቀንቃኝ፣ጦረኛ፣አሸባሪ፣ጥቂት አክራሪ ሓይሎች(ዋህብያና ሰለፊ) ወዘተ›› እያለ ይፈርጃል እንጂ ለዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ሲሰጥ አይታይም፡፡ዶክተር አረጋዊ በርሀና ገብሩ አስራት‹‹ሕንፍሽፍሹን ተከትሎ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ታጋዮች መገደላቸው በፅሑፎቻቸው ቢያሰፍሩም›› በድርጅቱ ስፖንሰርነት የታተሙና እየታተሙ ያሉት ውዳሴ ህወሓት መፃሕፍት ግን በዴሞክራስያዊ አገባብ መፈታቱን ነው የሚያወሱት፡፡ለካስ ሁሉም ታጋዮች ከጠላት በተተኮሱ ጥያቶች አልነበረም የተሰውት?

ውህደት ትሓህትና ግገሓት

ትሓህትና ግገሓት ልዩነታቸውን በመፍታት ለመዋሃድ ተስማምተው በምስራቅ ትግራይ ተገናኝቷል፡፡ሆኖም ግን ግገሓቶች እርሰበርሳቸው ይገዳደሉ ስለነበሩ ብቻ ትሓህትም ‹‹በመግደል ከማንም እንደማታንስ ለማሳየት›› የግገሓት መሪዎችን ገደለች፣አቆሰለች…ያመለጡም አምልጧል፡፡ለእርቅ ከተስማሙ በኋላ መገዳደል የትግራይ ገበሬም አድርጎት አያውቅም፡፡ውግዘት ነው! ትሓህቶች ግን ጭቆና አስመርሯቸው በረሃ የወጡትን ወንድሞቻቸውን ለእርቅ ጠርተው ፈጇቸው…ትጥቃቸውን ከሳፈቱ በኋላ፡፡አየ ወላድ ትግራይ!

የሻዕብያ ወራርና መለስ

ኤርትራ ያለተቀናቃኝ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ የኢትዮጵያ ሃብት ተጠቅማ የአፍሪካ ሲንጋፖር የመሆን ዓላማ ነበራት፡፡ይህን ዓላማዋን ለማሳካትም በድብቅም ሆነ በሚስጢር የኢትዮጵያ ሃብት ስተዘርፍ ነበር፡፡ኢምባሴዋ ሳይቀር በኢትዮጵያ ግዛት እንዳሻው ኮንትሮ ባንድ ይነግድ ነበር፣ የስለላ መረቧን በመዘርጋት ለዓላማዋን እንቅፋት ናቸው ብላ የጠረጠረቻቸውን ትገድል ነበር፣በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚጎዱ ተግባራት ተከናውን ነበር፡፡

ይኋላ ኋላ ይህንኑ ተግባሯ በትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች ተቃውሞ ገጠመው፡፡አይነኬው ሻዕብያ እሳት ጎርሶ እሳት መትፋት ጀመረ ‹‹በሬድዮ ሳይቅር የትግራይ አስተዳደር ጎሮሯችን መጥቶብናል›› በማለት አወጀ፡፡በኢትዮጵያ ድንበር የሚያካሄደው ወታደራዊ ልምምድ ቀጠለበት፡፡ይህን የታዘቡት የትግራይ አመራሮች ‹‹ሻዕብያ ሊወረን እየተዘጋጀ ነውና እኛም ሉዓላውነታችንን ለማስጠበቅ እንዘጋጅ›› የሚለው ተማፅኗቸውን ለህወሓት ፖሊት ቢሮ አቀረቡ፡፡መለስ ግን‹‹ሻዕብያ እብድ አይደለም፣ አይወረንም››በማለት አምርሮ የተከራከረ፡፡‹‹ሻዕብያ ሊወረን ነው፣ አይወረንም›› የሚለው ክርክር በድምፅ ለመወሰን ተስማሙ፡፡ተወልደ ወልደማርያ፣ አለምሰገድ ገብረአምላክ፣አባይ ፀሓየና ገብሩ አስራት ይወረናል ብለው ሲወስኑ፣ ሌሎች አራት የፖሊት ቢሮ አባላትና(ስዩም፣ስብሓት፣ስየና ፃድቃን?) መለስ አይወረንም በማለት ወሰኑ፡፡‹‹ሻዕብያ አይወረንም›› የሚለው ቡድን በአንድ ድምፅ ብቻ አሸነፈ፡፡ከስድስት ወራት በኋላ ግን ሻዕብያ ኢትዮጵያን ወረረ፡፡

‹‹ሻዕብያ የወረረን መዳከማችን አይቶ ነበር፣ብንዘጋጅ ንሮ ግን ደፍሮ አይወረንም ነበር፡፡ቢወረንም እንኳ ጥፋቱ መቀነስ በቻልን›› አንጋፋው ታጋይ ገብሩ አስራት፡፡‹‹ህወሓት ሁሌም ሚስጥራዊ ነው፡፡ፓርቲዎች ግን አቋማቸውንና ሃገራቸው ያለችበት ሁኔታ ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ለባቸው›› የሚለው ገብሩ ‹‹ህወሓት ታሞ እያለ ምንም እንዳልነበር ለማሳመን ይያደርግ ነበር፡፡ሌላው ቀርቶ የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮምቴም በህወሓት ውስጥ የነበረው ፍጭትና የሻዕብያ አዝማምያ አያውቅም ነበር ይህ ደሞ በወቅቱ የፈፀምነው ስህተት ነው፡፡››በማለት ቁጭቱን ይገልፃል፡፡

ሻዕብያ የኢትዮጵያ ግዛት በሃይል ወሮ እያለ መለስ ግን‹‹አትንኳቸው፣ ዝም በሏቸው›› ይልነበር፡፡ኤርትራ የያዘችውን ይዛ የፈለገችውን በምታደርግበት ወቅትና ኢትዮጵያ ራሷን መከላከል አንዳለበት ተወስኖ ለጦርነት እወጃ ትንሽ ቀናት ሲቀረው ዓሊ አላሙዲን ለሽምግልና ወደ መቐለ ልኮ ‹‹ጦርት ማካሄድ የለባችሁም፣ ምዕራባውያን(አሜሪካ) አይፈልጉትም እና›› የሚለው ተማፅኖ ይሁን ማስጠንቀቅያ ውሉ ያልታወቀው መልእክቱን አድርሷል፡፡በወቅቱ ‹‹ቀኝ አክራሪዎች›› ተብለው የተፈረጁት ገብሩና አባይ‹‹ኤርትራ ግዛታችንን ለቃ ትውጣ እንጂ እኛ ጦርነት አንፈልግም፣ ካልሆነ ግን መሬታችንን ለመመለስ እንዋጋለን›› ሲሉ መልስ እደሰጡ ገበሩ አስራት ይናገራል፡፡ይህን መሳዩ የመለስ አቋም የታዘቡት አቶ ዮሴፍ ረታ ‹‹መለስ፣ስዩምና ካሱ ኢላላ በዚሁ አቋማቸው ጦርነቱን መምራት ስለማይችሉ ከስልጣናቸው ይውረዱ›› ብለው ነበር፡፡ ገብሩ ግን ጥያቄው‹‹ የነበረው የፖለቲካ ግለት ግምት ውስጥ ያላስገባ ሃንደበታዊ ጥያቄ ስለነበር አልተቀበልነውም፡፡ሃገራችን ራሷን መከላከል ባማትችልበት ደረጃ ሊያደርስ የሚችል አደጋ ስለነበረው›› ይላል፡፡

መለስ በድምፅ ብላጫ ተሸንፈዋል፣ደም አፋሳሹ ጦርነት ተካሂዷል፡፡‹‹ከባድሜ መውጣን ማለት በቃ፣ ከእንግዲህ ፀሐይ አትወጣም ማለት ነው›› በማለት የፈከረው ሻዕብያ አቀጡት ተቀጥቶ የኢትዮጵያ መሬት ብቻም ሳይሆን ግዛቱን ለቆ መሸሹን ተያያዘው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሰራዊት በሁሉም ግንባሮች እየገፋ ነበር፣እስከ ተሰኔ ሁለቴ ተመላልሷል…የሚከለክለው አልነበረም…ሻዕብያ ያኔ የመዋጋት አቅሙ ደቆ ነበር…››ይላል ገብሩ አስራት፡፡

መለስ ግን አላስቻለውም የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮምቴ ውሳኔን ሽሮ‹‹ጦርነቱ በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲቆም›› የሚል ትእዛዝ በግሉ ፍቃድ በማስተላለፍ አስቆመው፡፡ በኋላም ‹‹ባድሜን ለቀን እንውጣና በዓዲ ሃገራይ መሽገንእንከላከል የሚል ሃሳብ አቀርበው ነበር›› ዳሩ ግን ‹‹የሻዕብያ መዳከም ግምት ያላስገባ ነበርና አልተሳካላቸውም›› በማለትም ያክላል፡፡‹‹የሉዓላዊነታችን አደጋ የነበረው የሻዕብያ ሰራዊት በገባበት ገብተን መልሶ በማያንሰራራበት መልኩ እንምታው ሲባልም ተቃውሞታል፡፡››

በሻዕብያ የተያዘው የኢትዮጵያ ግዛት የማያስከብር በአፍሪካ ህብረት የቀረበው ‹‹ተክኒካዊ ማስተካከያ››የሚባል አስታራቂ ሰነድ መለስና ካሱ ኢላላ ብቻ ሲቀበሉት…‹‹መሬታችን ተወረን እያለ አንፈርመም›› በማለት አልተቀበልነውም፡፡ ‹‹ለመከፋፈላች ምክንያትም እሱ ይመስለኛል…አትተንኩሷቸው፣ አትትንኳቸው ሲል ቆይቶ እንዲህ ማለቱ›› ማንም አልተቀበለውም፡፡ ስየ አብርሃ የአልጀርስና የሄግ ስምምነት አንፈርም ብሎ ነበር፡፡አሁን መለስ ብየ ሳየው መፈረማችን ስህተት ነበር›› ብሏል ገብሩ አስራት፡፡

የሻዕብያ ተላላኪዎች መፅሐፉን እንዳይገዛ እየሰሩ ይገኛሉ…ቤተ መፃሕፍቶች እንዲዘጉ እያዘዙ መሆኑም ገብሩ አስራት በምሬት እየተናገረ ነው…

የዓረና መስራችና የአመራር አባል የሆነው ገብሩ አስራት ‹‹ለወደፊትም እፅፋለሁ አቅሜ እስከፈቀደው ድረስ›› እያለ ነው፡፡የልቡን ያስምርለት!!!

Leave a Reply