(ዳዊት ከበደ ወየሳ -አትላንታ)
በነ በቀለ ገርባ ላይ የተመሰረተው የክስ ሰነድ (ሙሉ ቃል)
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ተነስቶ የነበረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ፤ የኢህአዴግ አስተዳደር ብዙዎችን አስሯል። በጥቂቶችም ላይ የክስ መዝገብ ከፍቶባቸዋል። በልደታ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ከተመሰረተባቸው አብዛኞቹ በወጣት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ በራሱ በኢህአዴግ ዘመን ውስጥ ያደጉ ልጆች ናቸው። ይህም “አዲሱ ትውልድ የኔ ደጋፊ ነው” በሚል የትምክህት ቅዠት ውስጥ ለሚገኘው ኦህዴድ / ኢህአዴግ አዲስ የራስ ምታት መሆኑን ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ እንደከዚህ ቀደሙ፤ “የደርግ ስርአት ርዝራዦች” የሚል ፕሮፓጋንዳ ለመስራት ለኢህአዴግ ካድሬዎች አመቺ አልሆነም። የሚል ቅጽል ሊያሰጣቸው የሚችል አልሆነም። እንዲያው በደፈናው ግን “አሸባሪ” የሚል መጠሪያ ሰጥተው ለእስር አብቅተዋቸዋል።
የክስ መዝገቡ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ ተከሳሾቹ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የሚለውን የፖለቲካ ድርጅት እንደሽፋን በመጠቀም፤ ከኦነግ ጋር በመተባበር መንግስት በሃይል ለመጣል የአሸባሪነት ተግባር እንደፈጸሙ ይገልጻል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ለጠፋው ህይወት፣ የአካል ጉድለት እና የንብረት ጥፋት ተጠያቂ አድርጓቸዋል። ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ሰዎች አብዛኛዎቹ በሸዋ ዞን ወይም በአዲስ አበባ እና ዙሪያው የሚገኙ ከተሞች ነዋሪዎች ናቸው። የሚገርመው ግን የረብሻ እንቅስቃሴ ከነበረበት ለምሳሌ ከወለጋ ወይም ከኢሉአባቦር ወይም ከሀረር የኦሮሚያ ክልል ተይዞ የቀረበ ምንም ሰው አለመኖሩ ነው።
ከተከሳሾቹ ውስጥ እንደምሳሌ መምህር በቀለ ገርባን እንውሰድ። “አሸባሪ” ተብለው ከታሰሩና ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ከተፈቱ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ከእስር በኋላ… አሜሪካ መጥቶ በነበረበት ወቅት እዚሁ መቅረት ሲችል ተመልሶ ወደአገሩ ገብቶ፤ በናዝሬት ወይም አዳማ ከተማ ውስጥ ኑሮውን በሰላም ከቤተሰቡ ጋር ይመራ የነበረ ሰው ነው። አሁን የክስ መዝገቡ እንደሚያሳየው ከሆነ ግን፤ አሜሪካ ሄዶ ከኦነግ መመሪያ ተቀብሎ በመምጣት አብዛኛውን የኦሮሚያ ክልል የአመጽ እንቅስቃሴ ሲመራ እንደነበረ አቃቤ ህጉ ይተነትናል።
ይህንን የክስ ሰነድ ለህትመት ያበቃነው፤ በታሪካዊ መዝገብነቱ እንደመረጃ ሆኖ እንዲያገለግል እንጂ፤ ክሱ የሃሰት ለመሆኑ ህሊና ያለው ሰው የሚፈርደው ነው። ለማንኛውም እዚህ ላይ በመጫን ሙሉውን የክስ መዝገብ ማግኘት ይቻላል።