የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሰሃሌ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የብሔራዊ ቡድኑ የአሰልጣኞች እና ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በሙሉ ከስራቸው እንዲሰናበቱ መወሠኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሪሽን ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑትን ኢንስትራክተር ዮሀንስ ሣህሌ ፣ ምክትል አሰልጣኝ የነበረው ፋሲል ተካልኝን ፣ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ የነበረው አሊ ረዲ ጨምሮ የብሔራዊ ቡድኑን እንቅስቃሴ የሚገመግመው የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሜቴ አባላት የነበሩት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እና እና ዶክተር ሲራክ ባጠቃላይ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን ኢትዮአዲስ ስፖርት ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ማረጋጋጥ ችላለች፡፡
ፌደሬሽኑ በአልጂሪያ ብሊዳ ላይ ብሔራዊ ቡድኑ ከደረሰበት የ7-1 አሸማቃቂ ሽንፈት በኃላ በሩን ዘግቶ በዝግ ሲመክር እንደነበር ሲዘገብ ቆይቷል፡፡
ኢንስትራክተር ዮሀንስ ሳህሌ ብሄራዊ ቡድኑን ከያዙ ከአስር ወራት በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑ 23 ጨዋታዎችን በእርሳቸው እየተመራ አድርጎ 11 ሽንፈት አስተናግዶ 5 አቻ ወጥቶ በ7ቱ ደግሞ ድል አድርጓል፡፡ 34 ጎሎች ሲቆጥሩበት ማስቆጠር የቻለው ደግሞ 25 ጎሎችን ነው፡፡