Monday, 02 May 2016 16:11
· በሰማሊያና በሶማሌላንድ የአየር ኃይል ጦርሰፈሮችን ለመጠቀም፣
· የበርበራ ወደብን ለባሕር ኃይል የስምሪት ማዕከል ለማድረግ፣
· የሶማሊያና የሶማሊላንድ ወታደራዊ ተቋሞችን ለማደስና የጦር ሰፈር ለማግኘት ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።
ወታደራዊ ሴራው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ተደማሪ ጫናዎችን ለማሳረፍ ያነጣጠረ ነበር።
ግብፅ ኢትዮጵያን በወታደራዊ የከበባ ቀለበት ውስጥ ለማስገባት የነደፈችው ስትራቴጂ መክሸፉ አነጋገረ
የግብፅ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያና የደህንንት ከፍተኛ ኃላፊዎች ልዑካን ከሚያዚያ 03 እስከ 08 ቀን 2016 በሶማሌ ሞቃዲሾ ከተማ እና በሶማሌላንድ ሐርጌሳና በርበራ ወደቦችን ጎብኝተዋል። ይህን አስራ አራት አባላት ያለው የባህር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የወታደራዊ ደህንነት እና የመረጃ ተቋም ከፍተኛ ባለስልጣናት ያካተተውን ልዑካን የመሩት በኢትዮጵያ የቀድሞ የግብፅ አምባሳደር የነበሩና አሁን በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስቴር በመሆን የተሾሙት ሞሃመድ እድሪስ ናቸው።
የግብፅ የልዑካን ቡድን በሶማሊያና በሶማሌላንድ ያደረገው ጉብኝት ዓላማ የግብፅ መንግስት በአፍሪካ ቀንድና በኤደን የባህር ሰላጤ አካባቢ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጥቅሞችና ትስስሮችን በማጠናከርና በማጎልበት በአካባቢው የበላይነት ለማረጋገጥ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የልዑካኑ ቡድን በሞቋዲሾና በሐርጌሳ ካደረገው ግልፅና ሚስጥራዊ ውይይቶች መረዳት የቻልነው፣ በዋናነት ከዓባይ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ያለመ መሆኑን ነው። በሁለተኛ አጀንዳነት የተቀረጸው፣ የግብፅ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በሆነው የሲዊዝ ካናል ላይ ችግሮች እንዳይጋረጡ የመከላከል እርምጃዎች መውሰድ ነው። ይኽውም፣ በየመን ላይ እየተፈጸመ ባለው ጦርነት መነሻነት ወደ ሲውዝ ካናል የሚወስዱ የባህር መንገዶችን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር በሶማሌና በሶማሌላንድ ግዛት ውስጥ የሚገኙ የአየር ኃይል ማዕከላትና ጦርሰፈሮችን በኪራይ መልክ መያዝ እንዲሁም የሶማሌላንድን የበርበራ ወደብንም በተመሳሳይ መልኩ የግብፅ የባህር ኃይል የግዳጅ ማዘዣ ማዕከል አድርጎ መጠቀምን ይጨምራል። በተለይ ሁለተኛው አጀንዳ ወደ ሲዊዝ ካናል የመርከቦች ፍሰት እንዳይስተጓጎል ለመከላከል የሚለው አጀንዳ ለሽፋንነት የቀረበ ሲሆን ዋነኛው ዓላማ ግን የኢትዮጵያን ሁኔታዎች በቅርብ ርቀት ለመቆጣጠር የሁለቱ መንግስታትን ይሁንታ ለመጠየቅ የታለመ እንደነበር የዝግጅት ክፍላችን ምንጮች አረጋግጠዋል።
በተለይ በ1990ዎቹ በሶማሊያ ውስጥ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻ በማድረግ እ.ኤ.አ. በግንቦት 18 ቀን 1991 ራሷን ነፃ ሀገር አድርጋ ያወጀችውን ሶማሌላንድን ከሶማሌ ግዛት ጋር መልሶ ለማዋሃድ በቱርክ አስተባባሪነት የተጀመረው ድርድር ቆሞ፣ በግብፅ መንግስት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ሁለቱን የሶማሌ መንግስታትን ለማግባባት የግብፅ ልዑካን ፍላጎት እንደነበር ከዝግጅት ክፍላችን ምንጮች ደርሶናል። ግብፅ አዲስ አደራዳሪ ሆና ለመቅረብ በምክንያትነት ያነሳችው፣ ከሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ጠንካራ የሶማሌ መንግስትና ተቋም ለመፍጠር አለመቻሉ የግብፅ ብሔራዊ ጥቅም የተጎዳ በመሆኑ የሶማሌን የፀጥታ ተቋማት ዳግም ለማጠናከር እና ስልጠናዎችንና የማሰልጠኛ ተቋሞችን ለማደስና ብቃታቸውን ከፍ ለማድረግ ካላት ፍላጎት መሆኑን ትገልጻለች። ይህ ሲሆን በሶማሌ ሕዝቦች ያለው መበታተን በማስቀረት የተዋሃደች ሶማሊያ ለመፍጠር ያስችላል የሚል የአዛኝ ቅቤ አንጓች አቋም ታራምዳለች።
ግብፅ ስትራቴጂክ ጫና የማሳደርና የትርምስ ፖሊሲዋን ተግባራዊ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎቿ በተናጠልና በጋራ ከሶማሊያና ከሶማሊላንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው መረጃዎች እያሉ፣ በሽፋንነት ከሶማሊያና ከሶማሌላንድ መንግስታት ጋር በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በጤና፣ በትምህርት እና በግብርና ስምምነቶችን ብቻ መፈጸማቸውን የግብፅ የልዑካን ቡድን ለሚዲያ አካላት ባሳለፍናቸው አስራ አምስት ቀናቶች ገለፃ አድርጓል።
የሞቋዲሾው ሚስጥራዊ ውይይት ምን ይመስላል?
የግብፅ ልዑካን ቡድን በመጀመሪያ ከሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ማሀሙድ ጋር በመገናኘት ሚስጥራዊ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ በዝግ ከልዑካኑ ቡድን መሪ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። የዝግጅት ክፍላችን ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት፣ በዚህ ሚስጥራዊ ስብሰባ ላይ በቀንዱ አካባቢ ስላለው ሁኔታ በተለይ ከናይል ወንዝ ውሃ ጋር በተያያዘ የናይል ውሃ አጠቃቀምና የኢትዮጵያ “ያልተመጣጠነ” ያሉትን ፍላጎት አንስተው መክረዋል።
ከናይል ውሃ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ላይ የተፈጠረውን ቀውስ ለመቆጣጠር በግብፅ በኩል የቀረበው የማግባቢያ ሃሳብ፣ ከግብፅ ብሔራዊ ጥቅሞች ጋር በማስተሳሰር የሶማሊያ የፀጥታ ተቋማት በተለይ የመከላከያና የፖሊስ ሃይሎችን በማጠናከርና አቅማቸውን ማብቃት፤ የሁለቱን ተቋማት የማሰልጠኛ አካዳሚዎችን ማደስ፣ ማስፋፋትና በቁልፍ አቅሞች ዙሪያ የግብፅ ባለሙያዎች በአሰልጣኝነት እንዲሳተፉ ማድረግ እንዲሁም በአጠቃላይ የሃገሪቷ የፀጥታ ተቋማት ለማጠናከርና ያለውን ድጋፍ ለማስቀጠል የቅድመ ጥናትና ዳሰሳ የሚሰሩ የግብፅ ባለሙያዎች ወደ ሶማሊያ ለመላክ የልዑካኑ ቡድን ከፍተኛ የማግባባት ሥራዎች አድርጎ ነበር።
ከዚህ ፍላጎታቸው በተጨማሪ በሳዑዲ ዓረቢያ በሚመራውና በየመን ሕዝቦች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጦርነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የግብፅ አየር ኃይል የተወሰነ ክፍል ከሶማሊያ እየተነሳ ጥቃት እንዲፈጽም የቀድሞ የሶማሊያ አየር ኃይል ዋና ማዕከል የነበረውን የበለዶግሌ ኤርፖርት በማደስ በኪራይ መልክ ለመጠቀም የልዑካኑ ቡድን ፍላጎቱን አቅርቧል። እንዲሁም ለሁለቱም ተቋማት የሚያገለግሉ ወታደራዊ አልበሳት፣ የቴክኒክና የጦር መሳሪያዎች ድጋፍም ለማቅረብ የልዑካኑ ቡድን በሚስጥራዊ ስብሰባው ላይ ለሶማሊያ ፕሬዝደንት እንዳነሱላቸው አረጋግጠናል። የልዑካኑ ቡድን መሪ ሶማሊያ ለግብፅ ፍላጎቶች ለምታደርግላቸው ትብብር 7ሺ ለሚሆኑ የሶማሊያ ዜጎች ግብፅ የትምህርት እድል መሰጠቷን አስታውሰው በቀጣይም በኢኮኖሚው ዘርፍም የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ ግብፅ ዝግጁ መሆኗን ለፕሬዝደንቱ መግለፃቸው የዝግጅት ክፍላችን ምንጮች አስታውቀዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ማሀሙድ የግብፆችን ፍላጎቶች ካደመጡ በኋላ ያልተጠበቀ ምላሽ መሰንዘራቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል። የሶማሊያ ፕሬዝደንት በልዑካኑ የቀረበውን የአቅም ግንባታ፣ የማሰልጠኛ ተቋማት እድሳት፣ የወታደራዊ ባለሙያዎች ጉብኝትና ጥናት እና ለግብፅ አየር ኃይል የሚውል የጦር ሰፈር ጥያቄዎችን በተመለከተ እንደማይቀበሉትና ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ፕሬዝደንቱ አያይዘውም ሶማሊያ ከግብፅ ጋር ከወታደራዊ ጉዳዮች በመለስ ባሉ የተለያዩ ዘርፎች ብቻ በትብብር ለመስራት ፈቃደኛ መሆኗን ማስታወቃቸውን ከሶማሊያ ቤተመንግስት ምንጮቻችን ገልጸውልናል።
በሶማሊያው ፕሬዝደንት ምላሽ ያልረኩት የግብፅ ልዑካን ቡድን መሪ የተላኩበት ተልዕኮ እንዳልተሳካ ቢያውቁም ዲፕሎማሲያዊ ክስረታቸውን ለመሸፈን ከፕሬዝደንቱ ጋር የነበራቸው ውይይት መገባደዱን ተከትሎ፣ የልዑካኑ ቡድን አባላት ከተለያዩ የሶማሊያ ተቋማት መሪዎች ጋር ውይይት እንዲያደርጉ በማድረግ ውይይቶቹ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጣቸውና ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራቸውን ለመሸፈን አውለውታል።
የግብፅ ልዑካን ቡድን ከላይ የሰፈሩትን ጥያቄዎች በርግጠኛነት ለፕሬዝደንቱ ያቀረቡት የሶማሊያ የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ጀነራል መሃመድ አሊ አደን በሰጧቸው የመግባቢያ ሰነድ በመተማመን ነበር። ይኽውም በግብፅ ለአንድ ሀገር መሪ የሚደረግ አቀባበል የጠበቃቸው የሶማሊያ የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ጀነራል መሃመድ ከግብፅ መከላከያ አመራሮች ጋር በካይሮ ባደረጓቸው ስብሰባዎች ላይ የግብፅ መንግስት የሶማሊያን መከላከያ ማሰልጠኛዎችና ሌሎች ተቋማትን ማደስና መጎብኘት፣ የተለያዩ ስልጠናዎች መስጠት እና የግብፅ መከላከያ ለሶማሊያ አቻው የሚያደርገውን ድጋፍ የሚያጠኑ የግብፅ ወታደራዊ ባለሙያዎች ወደ ሶማሊያ መላክን በተመለከተ በካይሮ ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትለው ነው።
ነገር ግን ግብፅን የጎበኙት የሶማሊያ የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ጀነራል መሃመድ አሊ አደን ወደሀገራቸው ሶማሊያ ተመልሰው ስለጉብኝታቸው በተመለከተ ለፕሬዝደንቱ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የፕሬዝደንቱ ምላሽ ምን እንደነበረ ግብፆች መረጃ አልነበራቸውም። የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ማሀሙድ የቀረበላቸውን ማብራሪያ ካደመጡ በኋላ፣ ኤታማዦር ሹም ጀነራል መሃመድ ከእሳቸው ፈቃድ ውጪ የግብፅ መንግስት ፍላጎቶችና የተስማሙባቸውን ጉዳዮች እንዳልወደዱትና እንዳልተቀበሉት አቋማቸውን በግልፅ አስቀምጠው ነበር። እንዲሁም ግብፅ በወታደራዊ መስክ ትብብር የፈለገችው ከኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የራሷን ፍላጎት ለማራመድ መግቢያ ቀዳዳ ለመፍጠር እንጂ ለሶማሊያ ብሔራዊ ጥቅም አስባ አለመሆኗን ፕሬዝደንቱ አፅንዖት ሰጥተው ከገለጹ በኋላ፣ በካይሮ በኤታማዦር ሹም ጀነራል መሃመድ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ተፈፃሚ እንዳይሆን ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
የሶማሊላንድ ሚስጥራዊ ስብሰባ ምን የተለየ ገጽታ ነበረው?
የግብፅ ልዑካን ቡድን በሞቋድሾ የነበራቸውን የሁለት ቀናት ጉብኝት ካገባደዱ በኋላ ለተመሳሳይ ተልዕኮ እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 05 እስከ 08 ቀን 2016 ወደ ሶማሌላንድ ነበር ያቀኑት። በዚህ አራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ሀርጌሳና የበርበራን ወደብን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችን ከሶማሊላንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በሶማሌላንድ ዋና ከተማ በሐርጌሳ ከሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ጋር በዝግ ስብሰባ ለመነጋገር እንደሚፈልጉ የግብፅ ልዑካን መሪ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ከፕሬዝደንቱ ጋር ዝግ ስብሰባ አድርገዋል። በዚህ ሚስጥራዊ ስብሰባ በግብፅ በኩል የቀረቡ የውይይት አጀንዳዎች፣ በንግድና በትምህርት ትብብር ማጠናከር፤ የግብፅ መንግስት ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በመቀናጀት በየመን ላይ እያካሄዱት የሚገኘውን ወታደራዊ ዘመቻ ለማጠናከር የበርበራ ኤርፖርት ለግብፅ አየር ኃይል የስምሪት ማዕከል እንዲሆን መፍቀድና ለስምሪቱ ማዕከል የሚሆን የመሬት ጥያቄ፤ የኤርፖርቱን አጠቃቀም ውልና ፈቃድ፤ በግብፅ መንግስት ድጋፍና በግብፅ ባለሙያዎች የበርበራ ወደብን ለማስፋፋትና ለማደስ፤ በበርበራ ወደብ ለግብፅ አየር ኃይል ማዕከል እንዲሰጣቸው፤ ጠንካራ የተዋሃደች ሶማሊያ በቱርክ መንግስት አስተባባሪነት ለመፍጠር በሶማሊያ ፌደራል መንግስትና በሶማሌላንድ መካከል ይካሄድ የነበረው የድርድር ሃላፊነቱን ካይሮ እንድትወስደው እና ሁለቱም ወገኖች በቅርብ ቀን በካይሮ ውስጥ ድርድር እንዲጀምሩ፤ በሶማሊያ ውስጥ “ህቡዕ አጀንዳ” ካላቸው እንደኢትዮጵያ ከመሳሰሉ ሀገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነቶችና ትብብሮችን ዳግም እንዲያጤኑት፤ ግብፅ በሁሉም ዘርፍ ሶማሌላንድ ለመደገፍ ያላትን ፍላጎትና ዝግጅኑት በተመለከተም በአጀንዳነት መነሳቱን ምንጮቻችን ገልጸዋል። የልዑካኑ ቡድን የሶማሌላንድ ባለስልጣናትን የበለጠ ለማግባባት የውጭ የትምህርት ዕድል መስጠት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሕክምና ዶክተሮችን ለመላክም እንደሚፈልጉ ያላቸውን ሃሳብ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የግብፅ ልዑካንን አጀንዳዎች ያዳመጡት የሶማሊላንድ ፕሬዝደነት ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል ሕዝባዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳሉ መግለፃቸው ታውቋል። ፕሬዝደንቱ የግብፅ አየር ኃይል እና ባህር ኃይል በበርበራ ወደብ ላይ የስምሪት ማዕከል እንዲኖራቸው መፍቀድን በሚመለከት የሕዝብ ንብረት መሆናቸውን ጠቆም አድርገው እሳቸው ብቻቸውን የመወሰን ስልጣንና ኃላፊነት እንደሌላቸው ለልዑካኑ ቡድን በግልጽ ማሳወቃቸውን የምንጮቻችን መረጃዎች ያሳያሉ። አያይዘውም በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ዘርፎች ለመተባበር ግን ፈቃደኛ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።
ሌላው በግብፅ ልዑካን ቡድን በኩል የሶማሊያ ፌደራል መንግስትን ከሶማሌላንድ ጋር ለማዋሃድ የቀረበውን ጥያቄ ፕሬዝደንቱ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። ፕሬዝደንቱ የግብፅን ጥያቄ ላለመቀበል ያቀረቡት ምክንያት፣ በአሁን ወቅት ሶማሊያ ራሷን ለማረጋጋት ባልቻለችበትና እርስ በእርስ ግጭት በነገሰበትና መተማመን በጠፋበት ሁኔታ ውስጥ እያለች ስለውህደት ለመነጋገርና ለማሰብ እንደማይፈልጉ አቋማቸውን ገልጸውላቸዋል። አያይዘውም የግብፅ መንግስት ያቀረበውን ጥያቄ በማክበር ግን በካይሮ ለመገናኘት ፈቃደኛ መሆናቸውን ቢገልጹም፤ ከሶማሊያ ባለስልጣናት ጋር ከመገናኘታቸው በፊት በቅድሚያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የግብፅ ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት እንደቅደመ ሁኔታ ማቅረባቸውን ምንጮቻችን ጠቆም አድርገዋል።
ከሞቋድሾ በተለየ መልኩ ግን የግብፅ ልዑካን ቡድን ሐርጌሳ ሲገባ የሶማሌላንድ ከፍተኛ ኃላፊዎች በሆነ ባልሆነ ምክንያቶች በጋራ ስብሰባው ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው በልዑካኑ ቡድን ላይ ቅሬታ ማሳደሩ ታውቋል። የልዑካኑ ቡድን ግን ባለስልጣናቱ በጋራ ስብሰባው ላይ እንዳይካፈሉ በኢትዮጵያ በኩል የተደረገ ተፅዕኖ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የግብፅ መንግስት የበርበራ ኤርፖርትን ለመጠቀም ቀደም ያለ ፍላጎት የነበረው እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ጉዳዩን በይደር አስቀምጦት ቆይቶ ነበር። ሆኖም ግን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በጅቡቲ ወደብ ያጋጠመውን መጨናነቅ ለመፍታት የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ከሶማሌላንድ ጋር የወደብ አጠቃቀም አገልግሎት ስምምነት መፈራረሙን ተከትሎ ፍላጎታቸው እንደአዲስ እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ግብፅ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ከሶማሌላንድ ጋር ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ትስስሮችን ለመመስረት በአሁኑ ጊዜ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማት እና ዴሞክራሲያዊ ሂደቶችን ለማጨናገፍ እንዲሁም ወታደራዊ ከበባ ውስጥ በመክተት በሕዳሴ ኃይል ማንጫ ግድብ ላይ አሉታዊ ጫናዎችን ለማሳረፍ መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው። በተለይ የግብፅ ልዑካን ቡድን በሞቋድሾና በሐርጌሳ ያደረጉት ጉብኝቶች የዓላማቸው ይዘት በኢትዮጵያና በሶማሊያ ሕዝቦች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነቶች ለማደፍረስ ከተቻለ ለመናድ የተቀመረ መሆኑን ከላይ ከሚስጥራዊ ውይይቶች አጀንዳዎች ለመረዳት የተለየ እውቀት አይፈልግም። ይህንን የግብፅ መንግስት እኩይ የከበባ የትርምስ ፍላጎቶችን በጥንቃቄ የመረመሩትና የተረዱት የሶማሊያ እና የሶማሌላንድ ባለስልጣናት፣ በኢትዮጵያ የቀድሞ የግብፅ አምባሳደር የነበሩና አሁን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስቴር በመሆን በተሾሙት ሞሃመድ እድሪስ የተመራውን የግብፅ ልዑካን ተልዕኮ ውድቅ በማድረግ ለቀጠናው ሰላም ያላቸውን ታማኝነት አረጋግጠዋል።
እንደመውጫ፣ ገልፍ ካንትሪስ ካውንስል (GCC) እየተባሉ የሚጠሩት ሀገሮች በየመን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ውስጣዊ የፖለቲካዊ ትግል የፕሬዝደነት አበዱ ራቡሃ ማንሱር ሃዲን የፖለቲካ ክንፍ በመደገፍ በጦርነቱ ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሀገሮች ባህሪን፣ ኩዌት፣ኦማን፣ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬት እንዲሁም ግብፅ እና ሱዳን ናቸው፡፡ ይህን የየመን ውስጣዊ የፖለቲካ ትግል ሽፋን በማድረግ እንዲሁም ወደ የመን የሚገቡትን ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለመቆጣጠር በሚል ሽፋን የኤርትራን አገዛዝ የትግላቸው አጋር አድርገው ቀላቅለውታል፡፡ ከዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ የተነጠለው የኤርትራ አገዛዝም የቀረበለትን ጥያቄ በመልካም አጋጣሚ በመውሰድ የጥፋት ፈረሱ ላይ ተሳፍሯል፡፡
እንዲሁም በየመን ውስጣዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያለውን የሁቲ አማጺያን የአደባባይ ስማቸው አንሳር አላህ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት በመፈጸም ስልጣን ጨብጧል ሲሉ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመሩት የሱኒ እስልምና እምነት ተከታይ ሀገሮች ይከሳሉ፡፡ እነዚህ ሀገሮች ተፈጽሟል ብለው የሚያምኑትን መፈንቅለ መንግስት፣ በማስተባበርና ከጀርባ ሆና የፈጸመው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግስት መሆኑን በይፋ ከመናገር አልፈው፣ ኢራንን በተለያዩ መድረኮች ይከሳሉ፡፡ ውዝግቡን ተከትሎም የየመን ውስጣዊ የፖለቲካ ትግል ነስሩን ስቶ በሱኒ እና በሺዓ የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል እየተደረገ ያለ ጦርነት ተደርጎ ዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ እየተቀበለው ይገኛል፡፡
አጠቃላይ የየመንን ውስጣዊ የፖለቲካ ትግል ሽፋን በማድረግ የዓረቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ከበባውን አጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል፡፡ ይህን የየመን ቀውስ በተለይ ግብፅ ኢትዮጵያን ከበባ ውስጥ ለመክተት አመቺ የጦር ሰፈሮችን ለማግኘት እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን ለመጠቅም የሚስችላት ጊዚያዊ ፖለቲካዊ ምክንያትም አግኝታለች፡፡ ከእነዚህ ወደቦች ጋር በተያያዘ በቀጣይ በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጠሩ በሚችሉ ትንኮሳዎች መነሻ የአስመራ አገዛዝ እድሜው ሊያጥር የሚችልበት እድል ከፍተኛ መሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
sendeknewspaper