Monday, 02 May 2016 15:55
ኦፌኮ
በይርጋ አበበ
“የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ፕሮግራም ለኦሮሞ ወጣቶች አደጋ ያዘለ ነው”
ከሳምንታት በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ እና የመሰናዶ መግቢያ ፈተና ፕሮግራም ለኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች አደጋ ያንዣበበ ነው ሲል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አስታወቀ። የኢህአዴግ የትምህርት ፖሊሲው አሳሳቢ እና አስፈሪ ነው ሲልም ገልጿል።
ኦፌኮ ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው “ከፍተኛ አደጋ እየሆነ ያለው የአገር አቀፍ ፈተና ፕሮግራም በኦሮሞ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ አደጋ ሆኖ በማንዣበብ ላይ ይገኛል። ይኸውም አብዛኛው የኦሮሞ ወጣቶች ክፍል ገብተው ባልተማሩበት ሁኔታ አገር አቀፍ ፈተናዎች (የ10ኛ ክፍልና የ12ኛ ክፍል) ሊሰጡ ቀናት ብቻ ቀርተውታል። የኦሮሞ ወጣቶች ትምህታቸውን በበቂ ሁኔታ አልተከታተሉም” ያለው ፓርቲው መፍትሔ ያለውን ሲያስቀምጥም የታሰሩ ፖለቲከኞች ተማሪዎችና አስተማሪዎች ከእስር ተፈትተው የተስተጓጎለው የትምህርት ጊዜ ቢያንስ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ድረስ እንዲሰጥ መደረግ አለበት ብሏል።
ኦፌኮ በመግለጫው አያይዞም በኦሮሚያ የተነሳውን ተቃውሞ የመልካም አስተዳደር መጓደል የፈጠረው ነው የሚለውን እንደማይቀበል ገልጾ “ያም ሆኖ ግን መልካም አስተዳደር ማስፈን ያቃተው ኢህአዴግ ሆኖ ሳለ በሰላም ለመታገል የተደራጁ የፓርቲያችንን አባላትና ሰላማዊ ህዝብ ላይ ተኩሶ መግደል፣ ማሰር፣ ማፈናቀልና ማወክ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። ስለሆነም ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ አጥብቀን እናሳስባለን” ሲል አስታውቋል።
“ህዝባዊ የመብት ጥያቄን በአዘናጊ መልሶች ማለፍ አይቻለም” ሲል መግለጫ ያወጣው ኦፌኮ፤ “በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ውስጥ ያለውን ህዝባዊ መነሳሳት ለማዘናጋትና ለማዳፈን ሲል በሚቆጣጠራቸው የዜና ማሰራጫዎች ተጎጂ የሆነውን ህዝባችንን በይበልጥ ለመጉዳት ታስቦ በሚመስል መልኩ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ድርጊትም ህዝባችንን የሚጎዳ ስለሆነ መንግስት የሚጠበቅበትን አገልግሎት ከመስጠትና በራሱ አባላት ላይ ከሚወስደው እርምጃ በስተቀር ህዝብን ከሚጎዱ እርምጃዎቹ እንዲታቀብ እናሳስባለን” ብሏል።
በቅርቡ የመልካም አስተዳደርን አጓድለዋል ብሎ በ1163 ባለስልጣናት ላይ የወሰደው የማሰናበት እርምጃም ለኦሮሞ ህዝብ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ኦፌኮ ገልጿል። ፓርቲው “ህዝብን እየጎዳ ያለውና ከዚህ በፊትም የጎዳው አብዮታዊ ዴሞክራሲ/ልማታዊ ዴሞክራሲ የተባለው የኢህአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና እንጂ የግለሰቦች ከስልጣን መውረድና መውጣት አይደለም” ብሏል። በአገሪቱ ብሔራዊ እርቅ እንዲሰፍንና ዜጎችም በአገራቸው ጉዳይ በነጻነት የሚሳተፉበት ዴሞክራሲ እንዲመቻችም አሳስቧል።
ኦፌኮ በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ “በኦሮሚያ ክልል የሚታዩ ችግሮችን መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ መፍታት እንዳለበት አጥብቀን እናሳስባለን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመላው አገሪቱ ለሚከሰት መመሰቃቀል ኃላፊነቱ የኢህአዴግ መንግስት መሆኑን ደግመን ግልጽ እናደርጋለን” ሲል አጠቃሏል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አባል ፓርቲ ነው።