በደቡብ ኦሞ ዞን በኩራዝ አንድ ስኳር ልማት ሙስናው ቅጥ አጥቷል፣ በጀት ምዝበራው እየከፋ መጥቷል

በኩራዝ አንድ ስኳር ልማት ሙስናው ቅጥ አጥቷል፣ በጀት ምዝበራው እየከፋ መጥቷል // የፕሮጀክቱ ሠራተኞች– ፋሲካን በግማሽ ደመወዝ፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ እየተገነባ ያለው የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ያለ ዝርዝር ጥናትና ዕቅድ እየተከናወነ የመሆኑ ጉዳይ በአካባቢው አርብቶአደር ነባር ነዋሪዎች ላይ ካስከተለው ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተጨማሪ ለከፍተኛ የበጀት ምዝበራ ምክንያት ሆኖ በውጤቱ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች እየተጎዱ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡እነዚህ በአሁኑ ጊዜ በፕሮጀክቴ እየሰሩ ያሉና እየተፈጸመ ያለውን ሙስናና በሙያ ሥነምግባር ላይ እየደረሰ ያለውን ተጽዕኖ መቋቋም ባለመቻላቸው የለቀቁ ሰራተኞች እንደሚያስረዱት– በአሁኑ ጊዜ ፕሮጀክቱ በበጀት እጥረት ምክንያት እንቅስቃሴው የተገደበ መሆኑን ገልጸው ይህም በእስካሁኑ ትግበራ ለፕሮጀክቱ ለእርሻ ሥራ በሄክታር ከተመደበውና ለፋብሪካ ግንባታው ከተያዘው በጀት በላይ ወጪ ተደርጎ መመዝበሩ ይህም የሆነው ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ በፕሮጀክቱ አመራር ውስጥ ከትምህርት ዝግጅት፣ ከሙያና ልምድ ይልቅ ለፖለቲካ ታማኝነት ቅድሚያ በመሰጠቱ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ፕሮጀክቱን ከገጠመው የፋይናንስ እጥረት ጋር በተያያዘ ለሰራተኞች ደመወዝ የሚከፈል ገንዘብ በመጥፋቱ ሰራተኞቹ ግማሽ ደመወዝ እንደተከፈላቸውና ለፋሲካ በዓል ያቀዱትን ለመፈጸም ባለመቻላቸው ለችግር መዳረጋቸውንና የፕሮጄክቱ ቀጣይ ህልውናና የእነርሱም የስራ ዋስትና ጉዳይ ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ምንጮች እንደሚያስረዱት እነዚህ ከላይ እስከታች በኢህአዴግ አባልነታቸው በተለይም በህወኃት አባልነታቸውና ቀረቤታቸው የተቀመጡ አመራሮች በተለያየ ደረጃ ባሉ የፕሮጄክቱ አመራሮች መካከል ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየከፋ በመጣው የእርስ በርስ ያለመተማመን ከዚህ በፊት በአመራሮችና በባለሙያዎች መካከል ባለው አለመግባባት ላይ ተደምሮ የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ እግር ከወርች አስሮ ይዞታል፡፡ ለዚህ ችግር ከፍተኛ አመራሩ እንደመፍትሄ የወሰደው የፕሮጀክቱን ድክመት በሌለው እንቅስቃሴ የህዝብ ግንኙነት /ፕሮፖጋንዳ መሸፈን ነው ብለው በማመን በአሁኑ ጊዜ የፋብሪካ ግንባታው ከ65 ከመቶ /65%/ ባልበለጠበት እውነታ ውስጥ በየካቲት ወር ‹‹የሙከራ ምርት ጀመረ›› እያሉ በመንግስት ሬዲዮችና ቴሌቪዥን የሚያሰሙትንና የሚያሳዩትን ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህ የሚያቀርቡት ማስረጃና መረጃም ለፋብሪካው ግብዓትነት በሁለት ዙር ከተተከለው 14 ሺህ /14 000/ ሄክታር ሸንኮራ አገዳ ውስጥ በመጀመሪያ የተተከለው 7 ሺህ /7 000/ ሄክታር አገዳ ፋብሪካው ለማምረት ከመድረሱ በፊት ዕድሜው ስለገፋ/ ኦቨር ማቹርድ/ ለፋብሪካ ግብኣት ሊውል አይችልም በሚል ከብዙ ጭቅጭቅ በኃላ ተቆርጦ እንዲወገድ/እንዲጣል መወሰኑን ገልጸው ይህ በተራው በእርሻ ሥራውና የፋብሪካ ግንባታው መካከል ያለውን የዕቅድ ክፍተት/አለመጣጣም በግልጽ ያሳያል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ምንጮቹ የፋብሪካውን ለምርት መዘጋጀትና ስኬት እንዲያስረዱ የተጠየቁ ባለሙያዎችና የበታች አመራሮች የዚህ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ አካል አንሆንም፣ ያለውን ችግር እያየን- ያልሆነውን ሆነ ብለን አንመሰክርም በማለታቸው ከፕሮጀክቱ እንደተባረሩ፣ሌሎችም በፈቃዳቸውም ለቀው ወደ ዞኑ መንግስት መ/ቤቶች ተመልሰው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸው በአሁኑ ሰዓት ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ ቢፈለግ እንኳ የባለሙያ እጥረት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ እነዚህ በተደጋጋሚ ዓመታት እንደተያዘው ዕቅድና ለህዝብ እንደተገለታ ቢሆን ፋብሪካው ምርት በ2006 በጀት ኣመት ይጀምር እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ እውነታ ፋብሪካው በሚቀጥለው በጀት ዓመት አጋማሽ ማምረት ቢጀምር እንደ ከፍተኛ ውጤታማነት የሚቆጠር ሲሆን በዚህ የበጀት ዓመት የሙከራ ምርት ጀምሯል መባሉ ቀርቶ እስከ ቀጣይ ኣመት መጨረሻ ከፕሮጀክቱ ስኳር የሚታሰብ አይደለም ሲሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ከጅምሩ በዝርዝር የፕሮጄክት ጥናትና ዕቅድ ላይ ያልተመሰረተ፣ የአካባቢውን ህዝብ ያላሳተፈና ይሁንታቸውን ያላገኘ በፖለቲካ ውሳኔ የተገባበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ባለፈው ኣመት ባበቃው በመጀመሪያው የትራንስፎርሜሽን ዘመን ይጠናቀቃሉ ከተባሉት አስር የስኳር ልማት ፕሮጄክቶች አንዱም ወደ ምርት ለመግባት አለመቻሉ ይታወቃል፡፡ የኩራዝ አንድ ፕሮጀክት ትግበራ ያስከተለው ምዝበራና የአገር ሃብት ብክነት፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅልና በአካባቢው የተፈጥሮ ሥነ ምህዳርና ነዋሪዎች ህይወት ላይ የጋረጠው ፈተና የዚሁ አካል በመሆኑ ችግሩ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ በተለይም ከዚህ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከወራት በፊት በሱርማዎች ላይ የተፈጸመው ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ ያስቆጣው የባሪያ ሥርዓተ ማህበርን የሚያስታውስ ዘግናኝ ኢሰብዐዊ ድርጊት ለዚህ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ የአመራሩን ሁኔታ በሚመለከት መዋቅሩ ከልማት ዓላማው ይልቅ ሆን ተብሎ ለፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ የተዘጋጀና በህወኃት አባላት እንዲያዝ የተደረገ በመሆኑ ችግሩ ከዋና መስሪያ ቤት ጀምሮ በሁሉም አስሩ ፕሮጄክቶች በግልጽ የሚታይ እንዲያውም በዋና መስሪያ ቤቱ ከዚህም በከፋ ደረጃ እንደሚገኝና በአቶ አባይ ጸሃዬ አመራር ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የደረሰበት ሳይታወቅ አየር በአየር እንደባከነ ይህ በህወኃት የተዘረጋ የሙስናና የሃሳብ ማስቀየሻ እቅድ አቶ ሺፈራው ጃርሶን ሊያሰራ ባለመቻሉ በቆይታቸው ሲያማርሩ እንደነበር እነዚሁ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply