Wednesday, 04 May 2016 13:06
በይርጋ አበበ
የዓለም የፕሬስ ቀን እና የኢትዮጵያ መንግስት የፕሬስ ቅኝት
እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ስሌት ከሚያዝያ 21 እስከ ሚያዝያ 25 ቀን በ1991 የአፍሪካ ጋዜጠኞች በናሚቢያ ዊንድሆክ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ባጸደቁት ኮንቬንሽን መሰረት በየዓመቱ ሚያዝያ 25 ወይም ሜይ 3 ቀን የዓለም የፕሬስ ቀን ተብሎ ይከበራል። በዚህ ዕለት ስለ ፕሬስ ነጻነት ስለ መረጃ አሰባሰብ አሰረጫጨት እና አቀባበል ውይይት ይካሄዳል። በአምባገነን መንግስታት መዳፍ ስር በወደቁ አገሮች የሚሰሩና በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን በማሰብና ለጋዜጠኞቹ ድጋፍ በማድረግ ይከበራል። መንግስታትና ድርጅቶችም ለሙያውና ለባለሙያዎቹ ትኩረት እንዲሰጡ ይሰበካል።
በዓለም ለ24ኛ ጊዜ የተከበረው የዘንድሮው የፕሬስ ቀን “መረጃ የማግኘት መብት እና መሰረታዊ ነጻነት” ወይም (Access to Information and Fundamental Freedoms) በሚል መሪ ቃል በፊንላድ ዋና መዲና ሄልሲንኪ እየተከበረ ነው። የፕሬስ ቀን ዘግይቶም ቢሆን በኢትዮጵያ መከበር የጀመረ ቢሆንም ዕለቱ እየተከበረ የሚገኘው ግን በመንግስት አማካኝነት እንጂ በሙያው ባለቤቶች (የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ተቋማት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምር ተቋማት) አይደለም ተብሎ ይተቻል። እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነትና ባለቤትነት “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች አገር – ኢትዮጵያ” በሚል መሪቃል እለቱ ተከብሮ ውሏል።
የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር መንግስት “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች አገር” ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚዲያ ብዝሃነት ማለትስ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ምን ያህል የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ይገኛሉ? ከእነዚህ ውስጥስ የትኞቹ ከተጽእኖ ነጻ ሆነው ወገናዊ መረጃቸውን እየሰሩ ነው? ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞችን የምታስር አገር እየተባለች ትተቻለቸ ይህን መንግስት እንዴት ያየዋል እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችንና ሀሳቦችን ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል።
የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ እና ፕሬስ ለኢትዮጵያ መንግስት
የፕሬስ ቀን ትናንት በአዲስ አበባ ፍሬንድሺፕ ሆቴል ሲከበር በቦታው የተገኙት የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አያሌው ናቸው። ወይዘሮ ፍሬሂዎት “የፕሬስ መሰረታዊ ችግር ከመንግስት ለውጥ ጋር ተቀርፏል” ሲሉ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሬስ ነጻነት ማወጁን ተናገሩ። ሚኒስትር ዴኤታዋ አያየዘውም “ያለ ፕሬስ ነጻነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት አይታሰብም። አሁን ያለውን የፕሬስ ነጻነት ለመገንባተም ትልቅ መስዋዕትነት ተከፍሏል። ህገ መንግስታችንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ፍርሃትና ስጋት ሀሳቡን መለዋወጥ ይችላል” ሲሉ ደንግጓል ብለዋል።
በቅርቡ በወጣ አንድ ዓለም አቀፍ ሪፖርት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ከሚያፍኑ ጨቋኝ መንግስታት አንዷ መሆኗን ገልጾ ነበር። አገሪቱ በዚህ አይነት ስርዓት ውስጥ መሆኗን ጥናቶች እያረጋገጡ ሳለ መንግስት ግን የሚዲያ ብዝሃነትን ያረጋገጠች አገር መሆኗን ይናገራል። ለመሆኑ ይህን ጥናት እንዴት ያዩታል የሚል ጥያቄ ከተሰብሳቢዎች ተነስቶ ነበር። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት ወይዘሮ ፍሬህይወት “የአገራችንን ሁኔታ ውጭ ያሉ የሚዲያ ነጻነት ተሟጋች ነን ባዮች በሚያወጡት ሪፖርት ተነስተን ይህ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለት የለብንም። ፕሬስ ለአገሪቱ እድገት አዎንታዊ ትችቶችን ማቅረብ ይኖርበታል እንጂ አሉታዊ ትችት ሊያቀር አይገባውም” ሲሉ መልሰዋል።
በሌላ በኩል ወይዘሮ ፍሬህይወት የማህበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ ያለው ሚና አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ ጠቀሜታው ያነሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በ2015 ደቡብ አፍሪካዊ ምሁር በመሩት አንድ የጥናት ቡድን ውስጥ የ1050 ሰዎችን የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎችን የፌስ ቡክ መልዕክት (ፖስት የተደረገ) ከተመለከተ በኋላ በሰራው ጥናት ከአንድ በመቶ በታች የሆኑ መልዕክቶች የጥላቻ መልዕክት ያዘሉ መሆናቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። ይህ አኃዝ ደግሞ በኢትዮጵያ ፌስ ቡክን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በአፍራሽነት የሚሰሩት ስራ አነስተኛ መሆኑን ጥናቱ ገልጾ ነበር። ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው እና በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የሚዲያ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ታምራት ደጀኔ ግን ጥናቱ ትክክል አለመሆኑንና ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚበጁት የሚፈጁት እንደሚበልጥ ተናግረዋል።
የሚዲያ ብዝሃነት በኢትዮጵያ?
ኢህአዴግ የመሰረተው የኢትዮጵያ መንግስት ትናንት በተከበረው የፕሬስ ቀን ላይ “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች አገር” ሲል ኢትዮጵያን ገልጿታል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርናሽናል ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችና የፕሬስ መብት ተሟጋቾች የአገሪቱን መንግስት መገናኛ ብዙሃንን የሚያዳፍን ሲሉ ይገልጹታል። ተቋማቱ “ለአብነት ያህልም በአሁኑ ሰዓት ብቻ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ጋዜጠኞች (እስክንድር ነጋ ውብሸት ታዬ እና ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ) በሙያቸው ምክንያት እስር ላይ እንደሚማቅቁ ይገልጻሉ። ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላም እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የህትመት ውጤቶች ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል። አፋኝ የሆነው የፕሬስ አዋጅም የተረቀቀው ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ነው። ጋዜጠኞች በብዛት የሚሰደዱባት አገርም ሆናለች” ሲሉ ይወነጅሉታል።
የኢትዮጵያ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የሚዲያ ጥናት ዳይሬክተሩ አቶ ታምራት ደጄኔ ግን ውንጀላውን አይቀበሉትም። “የእነሱን ጥናት (ዓለም አቀፍ ተቋማቱ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን ያስራል የሚለውን) እንደወረደ መቀበል የለብንም። እነሱ ጥናቱን ሲያጠኑ ዓላማቸው ስለ ፕሬስ ተጨንቀው ሳይሆን የራሳቸውን ኒዮ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም ተቀብለን ስለማናቀነቅን ነው” ሲሉ ይናገራሉ። የአቶ ታምራትን አስተያየት የሚጋሩት ወይዘሮ ፍሬህይወትም የተቋማቱን ውንጀላ እንደማይቀበሉት አረጋግጠዋል።
የመንግስት ኮምዩኒኬሽን የስራ ኃላፊዎቹ የኒዮሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለምን የሚያቀነቅኑ መገናኛ ብዙሃንን እንደማይቀበሉ ሲናገሩ በሌላ በኩል ደግሞ የሚዲያ ብዝሃነትን ያረጋገጠች አገር ሲል ያሞካሻሉ።
ለመሆኑ እነዚህ ሁለት ነጥቦች እንዴት ይዛመዳሉ? የሚዲያ ብዝሃነት ማረጋገጥ እና የኒዮሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለምን የሚያቀነቅን መገናኛ ብዙሃንን አለመቀበል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ባይሆንም አቶ ታምራት በአሁኑ ወቅት 15 ጋዜጦችና 11 መጽሔቶች በግለሰብ ባለቤትነት እየታተሙ ለንባብ እንደሚበቁ ተናግረዋል።98 የመንግስትና የንግድ ኤፍ ኤም ሬዲዮዎችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በፌዴራልና በክልል ደረጃ እየሰሩ መሆኑን ተናግረው አስር ደግሞ ዝግጅታቸውን ጨርሰው ወደ ስራ የሚገቡ እንደሆነ ገልጸዋል።
የሚዲያ ብዝሃነትን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ድንጋጌው ምን ይላል ለሚለው ጥያቄ ሀሳቡ ዘርፈ ብዙ መሆኑንና አንድ ውስን ማብራሪያ እንደሌለው ይገልጻል። ሆኖም የሚዲያ ብዝሃነት ማለት ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ብዛት በዘለለ በይዘት ብዝሃነት ሲኖር መሆኑን ይናገራል። በአገሪቱ የፖለቲካ እና ማህበራዊ አስተሳሰቦች በምን ያህል ደረጃ ይስተናገዳሉ የሚለው ነጥብ መታየት አለበት ሲል ያትታል።
የፕሬስ ነጻነትን ቀን ማን ያከብረዋ
ትናንት በኢትዮጵያ ለሰባተኛ ጊዜ የተከበረውን የፕሬስ ነጻነት ቀንም ሆነ ከዚህ በፊት የተከበሩትን ቀናት በባለቤትነት ያከበረው መንግስት ነው። የፕሬስ ነጻነት ማለት የፕሬሱ ባለቤቶች ከማን ነው ነጻ ሊሆኑ የሚገባው? የሚለው ጥያቄ መልሱ የአገሪቱ መንግስት በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ከሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ አፈና እንደሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ ግን ቀኑን እያከበረ ያለው መንግስት ሲሆን ቀኑን ሲያከብርም በርካታ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የስራ ኃላፊዎችን እና በእሱ መነጽር ለክፉ አይሰጡኝም ብሎ ያሰባቸውን የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን ጥሪ በማድረግ ነው። ከዚህ ውጭ ከመንግስት ጋር ጠንከር ያለ ቅራኔ እና ልዩነት አላቸው ብሎ የሚያስባቸውን መገናኛ ብዙሃን ተቋማት በእለቱ እንዲገኙ ጥሪ አያቀርብላቸውም።
በመሰረቱ የፕሬስ ቀንን ማክበር ያለበት የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት (የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የጋዜጠኞች ማህበር የጋዜጠኝነት ትምህርት የሚሰጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ጋዜጠኞች) መሆን ይገባቸዋል። የፕሬስ ቀን ሲከበር መንግስት እንደ አንድ ባለ ድርሻ አካል ተሳታፊ ይሆናል እንጂ ባለቤት ሊሆን አይገባውም ነበር። መንግስት በባለቤትነት የፕሮግራሙ አዘጋጅ መሆኑ ግን የፕሬስ ነጻነትን ከማጎልበት ይልቅ የማግለል ሂደት እንዳይፈጠር ያሰጋል።
በእለቱ ውይይትን የመሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ግንኙነት ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ዶክተር ነገሬ ሌንጮ “የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ለጋዜጠኞች ህጋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል። ዶክተር ነገሬ አክለውም በቀጣዩ ዓመት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት የትምህርት ዘርፍ የሶስተኛ ድግሪ መርሃ ግብር እንደሚጀምር ተናግረዋል። ይህም በዘርፉ ላለው የጥናት ችግር ሊቀርፍ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።
በአገራችን ያለው የፕሬስ ታሪክ እና የመረጃ አቀባበል
የፕሬስ ነጻነት ቀን ሲከበር የውይይት መነሻ ጽሁፍ ካቀረቡት ባለሙያዎች መካከል አቶ አብዱ ጄራ “ከመንግስት የሚወጡ መረጃዎች ምስጢራዊነት ይበዛባቸዋል። ይህም ከመንግስት ክፉነት በመነጨ ምክንያት ሳይሆን ከአላዋቂነት የመነጨ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የህግ ባለሙያውን የጥናት ጽሁፍ አስመልክቶ “የመንግስት መረጃዎች ሁሉም ለምን ግልጽ እንዲሆኑ ይፈለጋል?” የሚል ጥያቄም ተጠይቀው ነበር።
አቶ አብዲ “በመጀመሪያ አንድ የአፋር ክልል አባባል ልጠቀምና ሀሳቤን ላቅርብ። አፋሮች ‘በአደባባይ የሚላጭ ጸጉር አለ በጓዳ የሚላጭም ጸጉርም አለ’ ይላሉ። እኔም ማለት የፈለኩት ሁሉም መረጃዎች ግልጽ ይሁኑ ሳይሆን ግልጽ መሆን የሚገባቸው የሚገባቸውን ያህል ግልጽ ይሁኑ ለምን ሁሉም ጸጉር ጓዳ ውስጥ ይላጫል ነው” ሲሉ መልሰዋል። አያይዘውም በመረጃ በኩል ከአያያዝ ጀምሮ እስከ አሰረጫጨት ድረስ ያለን ታሪክ ደካማ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየተከፈቱ ይገኛሉ። እነዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በህብረተሰቡ የተለያዩ ስሜቶችን እያስተናገዱ ይገኛሉ። አንዳንዶች ትውልድ በካይ ናቸው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ተገቢ መሆናቸውን አንስተው ይከራከራሉ። ዶክተር ነገሬ ለዚህ ጉዳይ መልስ መስጠት ያለበት መንግስት እንደሆነ ሲናገሩ “ትውልድን የሚበክሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየተስፋፉ ነው። እነዚህን መከታተልና የማስተካከያ ስራ መስራት ያለበት መንግስት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ነጻ ፕሬስ እና ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ተሟጋች ተቋም (ሲፒጄ) በዓለም ላይ አምባገነንና ጨቋኝ መንግስታት ባሉባቸው አገሮች የአምባገነኑን ቡጢ ተቋቁመው የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ለሰሩ ጋዜጠኞች ሽልማት ይሰጣል። ይህ ተቋም ከአምስት ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያዊው ዳዊት ከበደ (የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ባለቤት) ሰጥቶ ነበር። ድርጅቱ ዳዊትን ከመሸለሙ ሁለት ዓመታት በፊት የሸለመው ለሶማሊያ እና ለኤርትራ ጋዜጠኞች ነበር። የዳዊት ሽልማትም ለአገሪቱ መንግስት የስድብ ያህል የሚቆጠር ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የህትመት ውጤቶች ከህትመት ውጭ ሲሆኑ ጋዜጠኞቹም ለስደትና ለእስር መዳረጋቸው ይነገራል። በአሁኑ ወቅት ብቻ እስክንድር ነጋ ውብሸት ታዬ እና ተመስገን ደሳለኝ በእስር ላይ ይገኛሉ። ከአስር ወራት በፊት ደግሞ ዞን 9 የሚባሉ የብሎግ ጦማሪያንን መንግስት አስሮ እንደነበር አይዘነጋም።
ከሁለት ዓመታት በፊት ደግሞ በአንድ ወር ልዩነት አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣ ከህትመት ውጭ ሲሆን አዘጋጆቹ በስደት ላይ ይገኛሉ።
ስንደቅ