Wednesday, 04 May 2016 12:50
በ ፀጋው መላኩ
በያዝነው አመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጣለ ባለውና በቀጣይም ይጥላል ተብሎ በሚጠበቀው የበልግና የክረምት ዝናብ በሚከሰተው ጎርፍ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ይፈናቀላል የሚል ስጋትን አሳድሯል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዕረቡ ሚያዚያ 25 የተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ውይይት ተካሂዷል። ምክር ቤቱ በተለይ መጪውን ክረምት ተከትሎ ሊከሰት ይችላል ተብሎ በሚጠበቀው የጎርፍ አደጋ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ በቀጣይ ለመከላከል በሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች ላይ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ላይ የብሄራዊ ሜትሪዮሎጂኤጀንሲ ቀጣዩ የዝናብ ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል የራሱን ትንታኔ ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከጎርፉ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ሊኖር ስለሚገባው ዝግጅትም ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። የጎርፍ አደጋ ይደርስባቸዋል ተብለው የተጠቀሱት ክልሎች አፋር፣ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ አማራ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ሐረሪ እና ድሬዳዋ ናቸው። ይከሰታል ተብሎ በሚጠበቀው ጎርፍም 485 ሺህ 610 ህዝብ ተጎጂ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ በእለቱ የቀረበው የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ትንበያ ያመለክታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ዜጎች በወሃ የመከበብ አደጋ ሊገጥማቸው ስለሚችል የሂሊኮፕተር እንደዚሁም የጀልባ እርዳታ መስጫ ያስፈልጋል ተብሏል። ከሚፈናቀሉ ዜጎች ጋር በተያያዘ ወረርሽኝ ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ የመከላከል ስራው ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል ተብሏል። የተፈናቀሉ ወገኖችንም ለማገዝ 188 ሚሊዮን 9 መቶ ሺህ ብር ያስፈልጋል ተብሏል። በአሁኑ ሰዓት አሊኒኖ ተፅዕኖ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሶ የመወረድ አዝማሚያ እየታየበት መሆኑን የብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ ሪፖርት አመልክቷል። በቀጣዩ ክረምት አሊኒኖ ሳይሆን ላልኒና የሚባል ክስተት የሚኖር መሆኑ በሜትሪዮሎጂ ሪፖርት ተመልክቷል። ሆኖም የክረምቱ ሁኔታ የተስተካከለ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን የትንበያው መረጃ አመልክቷል።
ዜጎች በውሃ የመከበብና የመዋጥ አደጋ ቢያጋጥማቸው አደጋውን ለመከላከል የሚያስችል ሄሊኮፕተር፣ ጀልባዎችና የመሣሠሉ ቴክኖሎጂዎች በቂ ዝግጅት ስለመኖሩ በስብሰባው ወቅት የተገለፀ ነገር የለም።
ስንደቅ