04 May, 2016
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ላይ ያመረቀዘ ሥጋት
በምርጫው ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ድምፅ እንዲያገኙና ሕዝቡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ካደረጉት መካከል የግል ሚዲያው፣ ሲቪል ማኅበራትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ምርጫው በከፍተኛ ውዝግብ ሲጠናቀቅም ለእስር ከተዳረጉት መካከል የእነዚህ ዘርፎች አባላት ይገኙበታል፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ዘረኛ ቅስቀሳ ሳይቀር ያራምዳሉ ተብሎ የሚታመንባቸውን የግል ሚዲያዎች በመታገስ በአንዳንዶች ሲመሰገን የነበረ ሲሆን፣ ከ97 በኋላ ግን ያንን ሁኔታ ወደኋላ የሚመልስ ዕርምጃዎች ወስዷል ተብሎ ይተቻል፡፡ ከእነዚህም ዕርምጃዎች መካከል፤ በምርጫው ማግስት የፀደቁት የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በተለይ ደግሞ ከአሜሪካ መንግሥትና ከአውሮፓ ኅብረት፣ በአገር ውስጥም ከዋና ተቃዋሚዎችና ከምሁራን ትችት የተሰነዘረባቸው እነዚህ አዋጆች፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲታፈን አድርገዋል በሚል ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርባቸው ነበር፡፡
በተለይ ደግሞ ፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ በውስጡ በያዛቸው አንዳንድ አስፈሪ አንቀጾች፤ ተቃዋሚ ኃይሎችን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ፀጥ ለማስደረግ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ተብሎ ከፍተኛ ሥጋት ሲቀርብበት ነበር፡፡ በተግባርም እነዚህ አካላትን አዋጅ ተጠቂ እንዳደረገ ጉዳዮችን በመተንተን የሚሞግቱት በርካቶች ናቸው፡፡ መንግሥት እስካሁን እንደ ሥጋት የታዩት ዋና አንቀጾችን ለማሻሻል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
በተግባርም አንዳንድ የተቃዋሚዎች አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ተሟጋቾች በአዋጁ ክስ የተመሠረተባቸው ሲሆን፣ ከጥቂቶች ውጪ አብዛኞቹ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እነዚህን ፍርደኞች የፖለቲካ (የህሊና) እስረኞች ይሏቸዋል፡፡
በአዋጁ ክስ ከተመሠረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት የአንድነቱ አቶ ሀብታሙ አያሌውና የዓረና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ይገኙባቸዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አቶ በቀለ ገርባም ለተወሰኑት ዓመታት በእስር ቆይተው ከተፈቱት መካከል ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የነበሩትና መንግሥትን በመተቸት የሚታወቁት አቶ በቀለ ገርባ፣ ለተወሰነ ጊዜ ከእስር ቤት ወጥተው ከቆዩ በኋላ በድጋሚ በዚህ ዓመት ለእስር መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡
አቶ በቀለ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲታሰሩ ምክንያት የሆናቸው በቅርቡ በኦሮሚያ ውስጥ የተነሳው መጠነ ሰፊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው፡፡ መንግሥት ‹‹ሕዝቡን ለአመፅ አነሳስተዋል፣ በተቃውሞውም ሌላ የውጭ ዓላማ ለማራመድ ሞክረዋል፤›› ያላቸውን በርከት ያሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በቅርቡ አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች 22 የሚደርሱ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን በመጎብኘት የመጀመርያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ የተቃዋሚ አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አባላት እንዲፈቱ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽም የሰላ ትችት መሰንዘራቸው አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የማናቸውም የውጭ መንግሥትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተፅዕኖ እንደማይቀበል ደጋግሞ የሚገልጽ ቢሆንም፣ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት በተቃረበበት ወቅት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን በከፊል ከእስር በነፃ መለቀቃቸው ግን በአሜሪካ ጫና የመጣ ነበር፡፡
በእርግጥ የአሜሪካ መንግሥት ከ97ቱ ምርጫ ውዝግብ በኋላ መግለጫ ከማውጣት ባሻገር ይኼ ነው የሚባል ዕርምጃ ሲወሰድ አልታየም፡፡ ይሁንና የተቃውሞ መግለጫዎችና ሥጋቶች ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡
ባለፈው ሳምንትም የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫው ‹‹በኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ለእስር በተዳረጉት አቶ በቀለ ገርባና በሌሎች ላይ የሽብር ክስ ለመመሥረት በወሰነው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአሜሪካ መንግሥት እጅግ ከፍተኛ ሥጋት አድሮበታል፤›› ይላል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በመቀጠልም፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ላይ በመንጠልጠል ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ፀጥ ለማድረግ መንቀሳቀሱን እንዲያቆም ለማሳሰብ እንወዳለን፤›› ይላል፡፡ ዕርምጃው የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ዕድገት የሚያጨልም እንጂ የሚያለመልም አይደለም በማለትም አክሏል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በዚሁ ማሳሰቢያው የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ለተፈጠረው ተቃውሞ ዜጎች ላነሱት ጥያቄ በቂ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቋል፡፡ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁከትም የፀጥታ ኃይሎች እጅ እንዳለበት አውቀው ዕርምጃ እንዲወስዱ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አሳስቧል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ መንግሥት እየወሰደው ያለው ዕርምጃ የመጨረሻ መፍትሔ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት የሚያዳክምና እምነትን የሚያሳጣ መሆኑን በመግለጫው አካቷል፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካ መንግሥት በሕግ ቁጥጥር ሥር ያሉ እስረኞች አያያዝም ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግን እንዲከተልና ያለአግባብ ከማሰቃየት እንዲታቀብ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ክስ በቀረበባቸው ግለሰቦች ላይም ግልጽ የሆነ ማስረጃ እንዲያቀርብ፣ በተቃውሞ ፖለቲካ መንቀሳቀስና ሁከት በማስነሳት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲመለከት፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ የተካተቱት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ መከበራቸውን እንዲያረጋግጥና መብታቸው ተጠቅመው በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት ለእስር የዳረጋቸውንም እንዲፈታ ጥሪ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ ቃል በቃል የተቀዳ ነው በማለት የሚቀርብበትን ትችት ያስተባብላል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ መንግሥት ግን በአዋጁ ለተለያዩ አሻሚና አምታች ትርጉም ክፍት የሆኑ አንቀጾች በመኖራቸው፣ አዋጁ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ወይም ከናካቴው እንዲቀር በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ፡፡ የሕግ ሒደቱን በገለልተኝነት የሚዳኝ የፍርድ ቤት ተቋማት አለመኖራቸውም ላይ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በዚህ መግለጫው አማካይነት የአሜሪካ መንግሥት በቅርብ ጊዜ እንዲህ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ የያዘ መግለጫ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሲያወጣ የመጀመርያው ሲሆን፣ ሁለቱ አገሮች ካላቸው ግንኙነት በመነሳት መንግሥት ማሳሰቢያውን ባይቀበል ሊወሰድ የሚችለውን ዕርምጃ መገመት ግን አይቻልም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ባለፈው ወር የስድስት ወራት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ባቀረቡበት ወቅት፣ በኦሮሚያ ስለተከሰተው ተቃውሞ መንግሥት ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ የተናገሩ ሲሆን፣ መንግሥታቸውንም ወክለው ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ እንዳስቀመጠው፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የኦሮሞ ተወላጅ ወጣቶች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በአቶ በቀለና ሌሎች 22 ግለሰቦች ላይ የሽብርተኝነት ክስ መመሥረቱ መንግሥት የጠየቀውን ይቅርታና ሙሉ ኃላፊነት ስለመውሰዱ ብዙዎቹ ጥርጣሬ ገብቷቸዋል፡፡
- የማነ ናግሽ’s blog
- 125 reads