ከመነሻችን ገበያው በየት አቅጣጫ እንደሆነ ከመጠየቃችን ውጭ ገበያውን ማግኘት ከባድ ስላልነበረ መንገድ ከጀመርን በኋላ በድጋሚ ማንንም መጠየቅ አላስፈለገንም ነበር፡፡
16 NOVEMBER 2014 ተጻፈ በ ምሕረት አስቻለው
ብዙ ጀሪካኖችን የጫኑ ጋሪዎችንና በተመሳሳይ መልኩ ብዙ ጀሪካኖች ታስረው የተጫኑባቸውን ሽኩኔታዎች የሚገፉ ሰዎችን መከተል ብቻ ነበር የነበረብን፡፡ እነሱን እየተከተልን ከደቂቃዎች በኋላ በእንጨት ከታጠረ ሰፊ ሜዳ (ካሬ) ደረስን፡፡ ሜዳው ላይ በብዙ ረድፍ የተሰለፉ እጅግ በርካታ ጀሪካኖች ይታያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሸርተት እንደማለት ብለው ጀሪካኖቹ ላይ ሲቀመጡ ሌሎቹ ደግሞ ቢቆሙም የጀሪካኖቹ ባለቤቶች የሆኑት ሴቶች የተሠለፉት በጀሪካኖቹ ረድፍ መሠረት ነው፡፡
የአርሲው አረቄ ተራ ብዙ ዓይነት ትዕይንት የሚታይበት ነው፡፡ መውጫና መግቢያ ሁለት በር ባለው በአረቄ ተራው ሃያ አምስት ሊትር የሚይዝ ሦስትና አራት ጀሪካን አረቄ ይዘው የመጡ ሻጮች፣ በርካታ የአረቄ ጥራት ቀማሾች (ሳቢ ተብለው ይጠራሉ)፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ አረቄ ገዢ ነጋዴዎች፣ ከጀሪካን ጀሪካን አረቄ ገልባጮችና ጫኞች ሥራቸውን ለመከወን በየፊናቸው ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡
ባዶ ጀሪካኖችን የጫኑ አይሱዙዎች ሲገቡ አረቄ የጫኑት በሌላው በር ይወጣሉ፡፡ ጋሪዎችም እንደዚያው፡፡ ለቦታው እንግዳ የሆነ ሰው ዓይኑ ሊያርፍ አይችልም፡፡ የሚታየው ነገር ግራ የሚያጋባ ትርምስ ቢመስልም የአረቄው ተራ የራሱ ሥርዓት አለው፡፡ የነጋዴዎች ባዶ ጀሪካኖች የትም ሳይሆን የሚደረደሩት ደንበኛ ከሆኑ ሻጮች ቡድን ጀሪካኖች ፊት ለፊት ነው፡፡ አረቄ የያዙ ጀሪካኖች ሠልፍም እንዲሁ ሳይሆን አረፋ የሚባለው አንደኛ ደረጃ አረቄ፣ በታኝ፣ መልክ፣ መለስተኛና ቦጭ እየተባሉ በጥራት ደረጃቸው ነው የሚሰለፉት፡፡ እያንዳንዱ ነጋዴ የራሱ አረቄ ቀማሽ ያለው ሲሆን፣ በ80 ሊትር ጀሪካን ለቀማሽ አምስት ብር ያስባል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ገልባጮችም ጫኞችም ክፍያቸው ይታሰባል፡፡
አረቄ ጭነው ከአረቄ ተራው የሚወጡ አይሱዙዎችም ሆኑ ጋሪዎች በ80 ሊትር ጀሪካን 20 ብር ታክስ ከፍለው ነው የሚወጡት፡፡ ይህ የአርሲ ነገሌ የአረቄ ኢንዲስትሪ የብዙዎች የኑሮ መሠረትና የገንዘብ ምንጭ ነው፡፡ ተዘዋውረን እንደተመለከትነውና ብዙዎች እንደገለጹልንም በአርሲ ነገሌ ሀብታም፣ ደሀ፣ ነጋዴ የመንግሥት ተቀጣሪ ሳይባል በየቤቱ አረቄ ይወጣል የአረቄው የጥራት ደረጃ ሊለያይ ይችላል እንጂ፡፡ አረቄውም በመላ አገሪቱ ተሰራጭቶ ኬንያ ጠረፍ ይደርሳል፡፡ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አርሲ ዞን አርሲ ነገሌ ወረዳም ከቤት ውስጥ የአረቄ ኢንዱስትሪ በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ይሰበስባል፡፡ ነገር ግን ኢንዱስትሪው በአካባቢው የጥቅም ምንጭ ብቻ ሳይሆን እየደረሰ ላለ ከባድ ጥፋትም ምክንያት ሆኗል፡፡
አካባቢዋን ያጠፋች ከተማ
በፊት በውስጡ ለማለፍ አንገታቸውን አጎንብሰው ያልፉባቸው የነበሩ ጥቅጥቅ ጫካዎች ዛሬ ላይ ጉቶ እንኳ የማይታይባቸው አውላላ ሜዳ መሆናቸውን ይናገራሉ ወይዘሮ አሰገደች አለሙ፡፡ ለሃያ ሰባት ዓመታት በቤታቸው አረቄ ወጥቷል ዛሬም ሥራው እየተሠራ ነው፡፡ ነገሌ ላይ አረቄ የማይወጣበት ቤት አለ ማለት ይከብዳል የሚሉት ወይዘሮ አሰገደች አብዛኛው ሰው የሚጠቀመው የማገዶ እንጨት በደን ልማት ለሽያጭ የሚቀርበውን ሳይሆን ደን እየተጨፈጨፈ በነጋዴ የሚቀርበውን እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በአርሲ ነገሌ በአረቄ ከፍተኛ የማገዶ ፍጆታ ምክንያት በወረዳው ያሉ ደኖች ተጨፍጭፈው በዙሪያ ወዳሉ ሌሎች አካባቢዎች መገባቱን ‹‹የራሳችንን ጨፍጭፈን በመጨረሳችን አሁን እንጨት በገበሬና በነጋዴ እየመጣልን ያለው ከሌሎች አካባቢዎች ነው›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ በጋራ ዱሮ፣ መረሮ አውሎ፣ መታአርባ፣ ጎንዴ ጉራዴና ጐዴ ባሉ ቦታዎች የነበረ ጥቅጥቅ ጫካ ዛሬ ላይ ትዝታ ብቻ ሆኖ መቅረቱ ያሳዝናቸዋል፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ከጠቀሱት ጥቅጥቅ ጫካ ከነበረው አንዱ ቦታ ላይ ተገኝተው የተሰማቸውን ‹‹ያ ቦታ መላ አካባቢውን አሻግረው የሚያዩበት ዓይነተኛ ቦታ መሆኑ ቀድሞ ለሚያውቀው ልብ የሚሰብር ነው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡
አንድ ጥዶሽ (እንስራ) ለሁለት ሰዓት ያህል እሳት ላይ መቆየት ይኖርበታል፡፡ በየቤቱ አረቄ የሚወጣው ደግሞ በ15 እና በ20 ጥዶሽ መሆኑን ተዘዋውረን ተመልክተናል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ደን እየተጨፈጨፈ በነጋዴ ይቀርብላቸው በነበር እንጨት አረቄ ሲያወጡ የኖሩት ወይዘሮ አሰገደች ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን አማራጭ ኃይል መጠቀም መጀመራቸውን ነግረውናል፡፡
ከተለያዩ ሰዎች ገለጻ በማየትም እንደተረዳነው አብዛኛው ቤት ከአረቄ ማውጣት ጎን ለጎን ከብት ማድለብና ላሞ ማርባት ይሠራል፡፡ ይህ የሆነው የአረቄ ተረፈ ምርት ለከብት መኖ መዋሉ ነው፡፡ ብዙዎች ተረፈ ምርቱን ተከትለው ወደ ከብት ማደለብ ቢገቡም በቀዳሚነት አረቄ ለመነገድ ሳይሆን ለተረፈ ምርቱ ሲሉ አረቄ ማውጣት ላይ የተሰማሩም አሉ፡፡
ነገሌ ውስጥ የአረቄ ንግድ ምን ይመስላል? የሚለውን ለማየት ከተዘዋወርንባቸው ቤቶች የታወቁ ባለሀብት ቤት አንዱ ነበር፡፡ ባለሀብቱ ከተማ ውስጥ ትልቅ ሆቴል ያላቸው ናቸው፡፡ እሳቸው ቤት አረቄ የሚወጣው ከትልቁ መኖሪያ ቤታቸው አጠገብ ባለ ሌላ ትልቅ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ የግቢውን ትንሽ በር አልፈን ዘለቅን፡፡ በተንጣለለው ግቢ አንድ ጥግ ላይ ከተሠራው ኩሽና ውጭ ምንም ነገር የለም፡፡ የተፈለጠ እንጨት ክምር ሰፊ መሬት ይዞ ይታያል፡፡ በአንድ በኩል አሥራ አምስት እንሥራ ጥዳ በሌላ በኩል ለቀጣዩ ቀን የሚሆን እንኩሮ በማንኮር ላይ የነበረችው አስናቀች ወደ ነገሌ ለሥራ የሔደችው ከወላይታ ነው፡፡ በጠዋት ገብታ በአሥር ጥዶሽ ለምታወጣው አረቄ በቀን የሚከፈላት ሰላሳ ብር ነው፡፡ በቤቱ በሁለት ሠራተኛ ሃያ ጥዶሽ አረቄ በቀን በቀን የሚወጣ ቢሆንም ባልደረባዋ እረፍት ላይ በመሆኗ ነበር አሥራ አምስት እንስራ ጥዳ ያገኘናት፡፡
ግቢው ውስጥ ያገኘነው እንጨት ፈላጭ የቀን ሠራተኛ እንደሆነ ብንጠረጥርም የወር ደመወዝተኛ ቋሚ ተቀጣሪ እንደሆነ ነገረን፡፡ እንጨት የሚገዙት የማገዶ እንጨት ከሚያቀርበው ደን ልማት እንደሆነ በማለት ጠየቅነው፡፡ ‹‹አንድም ቀን ከዚያ ገዝተን አናውቅም፡፡ ከነጋዴዎች ላይ ነው የምንወስደው›› በማለት ለየቤቱ ከሚያመጡ ገበሬዎችና በየገበያው ከሚሸጡ ሴቶች እንደሚገዙ አስረዳን፡፡ ሌሎች ቤቶች እንዳየነው ሁሉ ባለሀብቱ ቤትም ከብት ይደልባል፡፡ ዋናው ትኩረት ግን አረቄው ላይ ይመስላል፡፡
ለማገዶ የሚጠቀሙበት እንጨት ከየትም ይምጣ ከየት ዋናው ነገር ገዝተው መጠቀማቸው ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት የአራት ልጆች እናት ወይዘሮ አበራሽ ዘንባባ ናቸው፡፡ የቤተሰባቸው አባላት ቁጥር ዘጠኝ መኑንና ሕጻኑም አዋቂውም እንደ አቅሙ በአረቄ ማውጣት ሥራ እንደሚሳተፉ ይናገራሉ፡፡ በቤታቸው አረቄ ለሃያ ዓመታት መውጣቱን የሚናገሩት ወይዘሮ አበራሽ አንደኛ የሆነው አረቄ 650 ብር ሲሸጥ ተከታዮቹ 450፣ 350 እያለ እንደሚቀጥል ገልጸውልናል፡፡
‹‹ማገዶ የምንገዛው የለት የለት ነው፡፡ እቤት ድረስ የሚያመጡልን ነጋዴዎች አሉ፡፡ እኛም አጣና ተራ ሔደን እንገዛለን›› በማለት አረቄ እንጀራቸው በመሆኑ ከፍለው ከመግዛት በዘለለ የማገዶ ነገር ብዙ እንደማያሳስባቸው፤ ቢያስቡም ምንም ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳ እየሠሩበት ባይሆንም ከተጣዱት የአረቄ እንስራዎች ፊት ለፊት ከሠጋቱራና ከቡና ገለፈት የተሠራ ማገዶን የሚጠቀሙ ምድጃዎች ተቀምጠው በማየታችን ጠየቅናቸው፡፡ አካባቢው ላይ በሚንቀሳቀስ ድርጅት ምድጃዎቹን በአማራጭነት እንዲሞክሯቸው ከጥቂት ወራት በፊት እንደሰጣቸው ገለጹልን፡፡ ‹‹በሰዓት ደረጃ በእንጨት ከምንጠቀመው እኩል ሁለት ሰዓት ነው የሚወስደው ግን በጥቅሉ የተሻለ ከሆነ እያየነው ነው፡፡ እንግዲህ እንደ አየሩ ፀባይ የሚያዋጣንን ዓይተን ወደ አንዱ እናዘነብላለን›› አሉን፡፡
የአረቄው ትርፍና ኪሣራ
በአርሲ ዞን ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ደን አለ፡፡ ከሰው ሠራሽ ደን ዛፎች አድገው ሲደርሱ ተቆርጠው በሽያጭ ለማገዶም ለእንጨት ሥራም በሽያጭ ይቀርባሉ፡፡ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት አርሲ ቅርንጫፍ በደን ጥበቃና ልማት ከአራት አሠርት በላይ ሲሠራ መቆየቱን ሥራ አስኪያጁ አቶ ከድር ኒኖ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ የደን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይም መሥራት ከጀመረ ቆይቷል፡፡
የደን ሀብት በተለየ መልኩ አካባቢውን በዓለም ደረጃ ብርቅዬ በሆኑ የዱር እንስሳት፣ ፏፏቴና ወንዞች የታደለ ማድረጉን የሚናገሩት አቶ ከድር ይህ ደግሞ በአካባቢው በቱሪዝምና በሆቴል ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምክንያት በመሆን ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ቢሆንም የአርሲ ዞን ደን ላይ እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋ ትልቅ አደጋ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ላንጋኖ፣ ዝዋይና አቢጃታ ሻላ ሐይቆች ከየትም የመጡ ሳይሆን ከደን አካባቢ የተነሱ ምንጮች ውጤት ነው›› የሚሉት አቶ ከድር ሻሸመኔ ላይ የታሸገ ውኃ ለማምረት እየተንቀሳቀሰ ያለ ኩባንያ መኖሩን፣ ቢራ ላይም ኢንቨስት ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት መኖሩን በመጥቀስ የአካባቢው ደን በአካባቢው ኢኮኖሚ፣ የንጹሕ ውኃ አቅርቦትና በሌላም መልክ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ አንድምታ አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር የአየር ንብረቱ እንደተጠበቀ እንዲኖር የደኑ ሚና ዋጋ ከግምት በላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እሳቸውም የአካባቢው የደን ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያረጋግጣሉ፡፡ በደን ልማትና ጥበቃ ጥሩ ሥራ እየተሠራ ቢሆንም እየደረሰ ያለው ጥፋት ከፍተኛ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ የእርሻ መሬትን ማስፋፋት፣ ማገዶና የእንጨት (ጣውላ) ሥራ የአካባቢው ደን ጭፍጨፋ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
አረቄ ማውጣትን በመጥቀስ አርሲ ነገሌ በማገዶ ፍጆታ በመጀመሪያ ደረጃ የምትጠቀስ ከተማ ነች የሚሉት አቶ ከድር ኢላማ እየሆነ ያለው ደግሞ ተፈጥሯዊ ደኑ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲሁም በደን ልማት በማሳተፍ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን እየሠሩ ቢሆንም ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ሠፊ ሥራ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በወረዳው የአካካቢ ጥበቃ የመሬት አጠቃቀም ሥራ ፈጻሚ የሆኑት አቶ በለጠ ወርቅነህ ምንም እንኳ እየተሠሩ ያሉ አዎንታዊ ሥራዎች ቢኖሩም የደን ጭፍጨፋ በአካባቢው ችግር መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አስርና ሃያ ሔክታር መሬት መንጥረው ሰዎች የእርሻ መሬት ያደርጋሉ፡፡ ይህ መሬት መንግሥት የማያውቀው ግብርም የማይከፈልበት ነው፡፡ አርሲ ነገሌና ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ‹‹እንደ አሸን ፈልተዋል›› የሚሏቸው የጣውላ መሰንጠቂያና የእንጨት ሥራ ቤቶች ሌላ የደን ጭፍጨፋ ምክንያት ሆነዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ቀድሞ ያሳስብ የነበረው የመሬት ወረራ አቅጣጫውን ለውጦ ወደ ደን ጭፍጨፋ ዞሯል፡፡ ጭፍጨፋውም እንደቀድሞ በቀላሉ ሳይሆን በተደራጀና በረቀቀ ዘዴ እየተፈጸመ መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አደገኛ ያደርገዋል፡፡ አቶ ከድር የድርጅታቸው ሁለት የደን ጥበቃዎች ባለፈው ዓመት፣ ዘንድሮ ደግሞ አንድ ጥበቃ በደን ጨፍጫፊዎች መገደላቸውን ገልጸውልናል፡፡ ‹‹ከሚታየው ነገር የደን ሀብት በዚህ አካባቢ ብሎ ብሎ ከመንግሥት እጅ ውጭ እንዳይሆን እፈራለሁኝ›› ይላሉ፡፡ በአካባቢው ስመጥር የሆኑ ወንዞች ደክመው አንዳንዶቹም መድረቃቸው የደን ሀብት ጭፍጨፋ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ ውጤቶች መሆናቸውን፤ በዚህ መልኩ ሁኔታዎች ከቀጠሉ የከፋ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ይሠጋሉ፡፡
በአርሲ ነገሌ ከተማ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዋሪ በአረቄ ንግድ ላይ የተሰማራ መሆኑን የከተማው ገቢዎች ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ መኢሶ ዱላ ይናገራሉ፡፡ አረቄው በመላ አገሪቱ የሚሰራጭ መሆኑን፤ በቀን አሥራ አምስት የሚሆኑ አረቄ የጫኑ አይሱዙዎች ከከተማው እንደሚወጡም ይገልጻሉ፡፡
ቀደም ሲል ይሰበሰብ የበረው በንጽጽር ያነሰ እንደነበር በማስታወስ በ2006 ዓ.ም. በአርሲ ነገሌ ከአረቄ 5.5 ሚሊዮን ብር ቀረጥ መሰብሰቡን፤ በተያዘው ዓመት ደግሞ ይህን ቁጥር ወደ ሰባት ሚሊዮን ብር ከፍ የሚያደርግ ዕቅድ መያዙን አመልክተዋል፡፡ በችግሩ አሳሳቢነት ደረጃ ከለሎቹ የተወሰነ ልዩነት ቢኖራቸውም ከአረቄ ከሚገኘው ጥቅም ጀርባ የደን ጭፍጨፋ መኖሩን፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍም አካባቢው ላይ ከሚንቀሳቀስ አንሲዳ ከተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አማራጭ ኃይል መጠቀምን በሚመለከት የተጀመረ ሥራ ቢኖርም ወደ ተግባር አለመገባቱንም ገልጸውልናል፡፡
የአረቄው ምርት ሌላ ገጽታ የታያቸው
ከረዥም ዓመታት በፊት ጥቅጥቅ ደን የነበሩ የአርሲ ነገሌ ወረዳ ቦታዎች ለማወቅ እስከሚያዳግት ድረስ በደን ጭፍጨፋ መቀየራቸውን የሚገልጹት የአርሲ ኔቸር ኮንሰርቬሽንና ኢንቫይሮሜንታል ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን (አንሲዳ) ዳይሬክተር አቶ ደቀቦ ደሌ የአካባቢው የደን ጭፍጨፋ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ጉዳቱ ዛሬ ላይ እየታየ መሆኑን፤ ለወደፊቱም የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከባድ ስለሚሆን የአርሲ ነገሌ አረቄ ምርት እያስገኘ ያለውን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የምርቱን ሌላ ገፅታ በማየት አካባቢ ሳይራቆት ምርቱን ማስቀጠል የሚቻልበት መንገድን ማፈላለግ የሁሉም ኃላፊነት ነው ይላሉ፡፡
በቤታቸው የሚወጣው አረቄ ለደን ጭፍጨፋ ምክንያት መሆኑ ያሳሰበው የተለያዩ ፈጠራ ሥራዎች ባለቤት የሆነው የአሥራ ስምንት ዓመቱ ወጣት ዋሲሁን ተፈራም መፍትሔ ይሆናል ያለውን ኮንክሪት ምድጃ ሠርቷል፡፡ በአቅም ውስንነት በስፋት ምድጃውን አምርቶ የማሠራጨት ውጥኑ ለጊዜ ዕውን ባይሆንም እናቱ ለአንድ ዓመት ያህል ለዘጠኝ ጥዶሽ እየተጠቀሙ ያሉት እሱ የሠራቸውን የኮንክሪት ምድጃዎች እንደሆነ ገልጾልናል፡፡ የማገዶ ፍጆታንና ጭስን ከመቀነስ አንጻር የምድጃው ጥቅም ወሳኝ እንደሆነ፤ ምድጃው በሙቀት እንዳይፈነዳም የራሱን ምስጢራዊ የኬሚካል ውህድ እንደተጠቀመ ያስረዳል፡፡
አቶ ደቀቦና ወጣት ዋሲሁን ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎች የአርሲ ነገሌ ወረዳና የአካባቢው ደን ጭፍጨፋ መሬት መሸርሸርን፣ ወንዞችና ምንጮች መድረቅን በማስተካከል፤ የእፅዋትና እንስሳት ብዝሃነትን በማጥፋት እያደረሰ ያለው ጥፋት ከፍተኛ በመሆኑ፤ ይህ በቀጣይ በአገር ደረጃ ተፅዕኖ ከባድ ስለሚሆን ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ፡፡