Written by አለማየሁ አንበሴ
ጐርፍ በድሬደዋ ለሦስተኛ ጊዜ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ
የሦስት ሰዎች ህይወት አልፏል ከተማዋ አሁንም የጎርፍ አደጋ ያሰጋታል፤ ተባለ
በድሬደዋ ከትናንት በስቲያ ለሦስተኛ ጊዜ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በከተማዋ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ጠቆመ፡፡ ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ እስከ ንጋቱ 1 ሰዓት ድረስ በተከታታይ በድሬደዋና አካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ፤ ገንደጋራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ሰው ሲወስድ፣ ሃሉቡሳ በተባለ አካባቢም አንድ የ10 ዓመት ህፃን ልጅ በጎርፉ ተወስዶ ህይወቱ ማለፉ ታውቋል፤ በ“ሃርላ” አካባቢ በጎርፍ ምክንያት የኤሌክትሪክ ምሰሶ ወድቆ አንድ ሰው በኤሌክትሪክ አደጋ መሞቱንና 7 ያህሉ መቁሰላቸውን የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በእለቱ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በሰዎች ላይ ካስከተለው ጉዳት በተጨማሪ ድሬደዋን ከመልካ ጀብዱ የሚያገናኘው ድልድይ ሙሉ ለሙሉ መፍረሱንና የሁለቱ አካባቢዎች ግንኙነት መቋረጡን ኢንስፔክተሩ ጠቁመው፣ ከከተማዋ ወደ አዲስ አበባ የሚያስወጣው መንገድም በጎርፍ ክፉኛ በመቦርቦሩ አደጋው የሚቀጥል ከሆነ መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ሊዘጋ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የቤት እንስሳትና ተሽከርካሪዎች በጎርፍ መወሰዳቸውንና በየአሸዋው ውስጥ ተቀብረው መገኘታቸውን የጠቀሱት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ 13 ቤቶችና አንድ መስጊድ መፍረሳቸውንም ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል ጎርፍ በሚያጠቃቸው የከተማዋ አካባቢዎች ለጎርፍ መከላከያ የተገነቡ ግድቦች በየቦታው እየፈረሱ መሆኑን
የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ የሜትሮሎጂ መረጃ፣ ዝናቡም ጎርፉም ይቀጥላል ማለቱን ተከትሎ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል፤ ብለዋል፡፡ ፖሊስ ለህብረተሰቡ በጎርፍ ጉዳይ ላይ ተከታታይ ግንዛቤ እየሰጠ ነው፤ ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ በጎርፉ የተደፈኑ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን የመጠገንና ለጎርፍ መውረጃ ክፍት የማድረግ ሥራም ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት በደረሰ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉ የተዘገበ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማዋ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥም የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፤ ተብሏል፡፡ ከድሬደዋ ወጣ ባሉ አካባቢዎች የሚጥለው ከፍተኛ ዝናብ ከተማዋ በጎርፍ ለመጥለቅለቋ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩ ምንጮች ፤ ከትናንት በስቲያ ቀን ላይ በድሬዳዋ ምንም ዓይነት ዝናብ ሳይጥል ከአጎራባች አካባቢዎች የመጣ ጎርፍ ከተማዋን እንዳጥለቀለቃት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡