Saturday, 07 May 2016 13:52
Written by  አንተነህ ይግዛው

                                                                                       የ20 አመት እስር የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን – በሱዳን ኡምዱርማን እስር ቤት

(የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ በቦታው ተገኝቶ አነጋግሯቸዋል)

ደነገጥሁ!…
ኑር ሁሴን በቫይበር የላከልኝን የመጨረሻውን መልዕክት እንዳነበብኩ፣ በድንጋጤ ክው አልሁ!… ያነበብኩትን ለማመን ቸግሮኝ፣ ደጋግሜ አነበብሁት!…መልዕክቱ ግን ያው ነው – ተስፋዬንም፣ ደስታዬንም የሚገድል መርዶ!…
ደስ ብሎኝ ነበር…
በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም እውን ላደርገው ያሰብኩትን ውጥን፣ ለማሳካት የምችልበት ዕድል ስለተፈጠረልኝ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ በተስፋ ተሞልቼ ነበር፡፡ ወደ ህልሜ የሚያደርሰኝ ጠባብ መንገድ እንደተከፈተልኝ ሲሰማኝ፣ ከካርቱም ሰማይ ስር በደስታ ፈንጥዤ ነበር…
ተስፋና ደስታዬ ግን ብዙ አልቆየም!… የኑር ሁሴንን የመጨረሻ መልዕክት ሳነብ፣ ደስታዬ ድንገት ከሰመ – ጠባቡ መንገድ የበለጠ ጠበበ!…ደጋግሜ አነበብኩት… እያነበብኩት ግራ ተጋባሁ!… ምን እያለኝ ነው ኑር ሁሴን?!…
ከጥቂት ሳምንታት በፊት…
በዚሁ ጋዜጣ ላይ አንድ አሳዛኝ ዜና አነበብሁ…
“በጫት መቃም ወንጀል እስከ 20 አመት የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን በሱዳን” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ዘገባ፣ ድንበር አቋርጠው ወደ ሊቢያ ለመግባት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት እየማቀቁ መሆናቸውን ያትታል፡፡ ስደተኞቹ የኢትዮጵያ መንግስት ከዚያ አሰቃቂ እስር ቤት አስወጥቶ ወደ አገራቸው እንዲያስመልሳቸው ያቀረቡትን ተማጽኖም ያሳያል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት…
ከዚህ ዘገባ የተመዘዘ ሃሳብ ይዤ፣ በሱዳን መዲና ካርቱም ተገኘሁ…ጫት በመቃምና በመነገድ እንዲሁም፣ አደንዛዥ ዕጽ በመጠቀምና በማዟዟር ተከስሰው እስከ 20 አመት የሚደርስ እስር ተፈርዶባቸው፣ በሱዳን እስር ቤት ውስጥ የሚማቅቁትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ በስፋት ለመዘገብ ነው ሃሳቤ፡፡ ይሄን ሃሳቤን ያጋራኋት የአዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ሊሰጠኝ የሚችል አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ እንዳለ ጠቆመቺኝ፡፡ ኑር ሁሴን እንደሚባል ነግራኝ፣ ስልክ ቁጥሩን ሰጠቺኝ፡፡
የጸሎተ ሃሙስ ዕለት ማለዳ…
ካርቱም ውስጥ ባረፍኩበት ሆቴል ጋደም ብዬ፣ የቫይበር መስመሬን ከፈትኩ፡፡ ከጋዜጠኛዋ በተሰጠኝ ስልክ ቁጥር፣ ለኑር ሁሴን የሰላምታ መልዕክት ላክሁለት፡፡ ምላሹን ፈጥኖ አልሰጠኝም፡፡ ለአንድ ብርቱ ጉዳይ እንደምፈልገው የሚገልጽ መልዕክት ደግሜ ላክሁለት፡፡ አሁንም አልመለሰልኝም፡፡ ግማሽ ቀን ሙሉ በጉጉት ብጠብቀውም ምላሹን አላገኘሁም፡፡ ብርቱ ያልኩትን ጉዳይ ገልጬ መንገር እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ ስለታሰሩት ኢትዮጵያውያን ሰፋ ያለ ዘገባ ለመስራት እንዳሰብኩ ገለጽኩለት፡፡ ለዚህ እቅዴ መሳካት የሚያግዘኝን መረጃ በመስጠት ይተባበረኝ እንደሆን የሚጠይቅ መልዕክት ላክሁለት፡፡
በተስፋ ተሞልቼ ስጠብቅ ብውልም፣ የኑር ሁሴንን ምላሽ አላገኘሁም፡፡ እሱ በቫይበር ለላክሁለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠኝም ብዬ፣ አርፌ አልተቀመጥኩም፡፡ ስለ ስደተኞቹ ጉዳይ መረጃ የማገኝበትን ሌላ አማራጭ መፈለግ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ በካርቱም በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ስለሰማሁ፣ ካረፍኩበት ሆቴል ብዙም ሳልርቅ ሊረዱኝ የሚችሉ የአገሬ ልጆችን ማፈላለግ ያዝኩ፡፡
ካርቱም በንዳድ ትጠበሳለች፡፡ ካርቱም እንዲህ ናት፡፡ አመት ሙሉ በጋ ናት፣ ዘለለት ሙቀት፡፡ ይህ ወቅት ግን፣ ከመቼውም ጊዜ የከፋ ነው፡፡ ይህ ሰሞን የካርቱም ሙቀት የላይኛውን ጣራ የሚነካበት፣ ምድሯ በግለት የሚጣበስበት የንዳድ ጊዜ ነው፡፡
ዛሬ የካርቱም ሙቀት 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ የሚፋጅ ሙቀት ውስጥ ነኝ፡፡ በላብ እየተጠመቅኩ… በወበቅ እየጋየሁ… ተስፋን ይዤ በካርቱም ጎዳናዎች ላይ እመላለሳለሁ፡፡ ስለታሰሩት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መረጃ የሚሰጡኝን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ፍለጋ፣ ዙሪያ ገባውን እማትራለሁ፡፡ ከወጪ ወራጁ መካከል ኢትዮጵያዊ ፊት እበረብራለሁ፡፡ ችግሩ ግን፣ ሱዳናዊ ፊትን ከኢትዮጵያዊ ፊት መለየት፣ እጅግ አስቸጋሪ ተልዕኮ ነበር፡፡ እኛና ሱዳኖች፣ ዕጣችን እንጂ ፊታችን አይለያይም!…
ከንቱ ድካም ነበር…
በንዳድ እየተጠበስኩ ከመባዘን ውጪ፣ ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳላገኝ ነበር፣ በድካም ዝዬ ወዳረፍኩበት ሆቴል የተመለስኩት፡፡ እንደ እሳት የሚጋረፈውን የካርቱም ሙቀት መቋቋም ተስኖኝ፣ አልጋዬ ላይ ተዘርሬያለሁ፡፡ የኑር ሁሴንን ምላሽ ሳላገኝ ከቀረሁ፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አሰላስላለሁ፡፡
ምንም እንኳን ዋነኛ ትኩረቴ በእስር ቤት የሚማቅቁት ወንድሞቼ ቢሆኑም፣ ወደ ሊቢያና ግብጽ ለማቅናት አስበው፣ ድንበር አቋርጠው በሁመራና በመተማ በኩል ካርቱም የገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተመለከተም የቻልኩትን ያህል መረጃ ማሰባሰብ እንዳለብኝ አስቤአለሁ፡፡
አመሻሽ ላይ ወደ ማረፊያዬ ስገባ፣ ከአንድ የባህላዊ ጌጣጌጦች ሻጭ ሱዳናዊ ጋር በር ላይ ተገናኝተን ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ሲያውቅ፣ በፈገግታ ቀርቦ ተግባብቶኛል፡፡ የቴዲ አፍሮን ላምባዲና እየተኮላተፈ አንጎራጉሮልኛል፡፡  ተጨዋውተን ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚገኙበትን አካባቢ እንዲጠቁመኝ ስጠይቀው፣ በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው መድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያን አመልክቶኛል፡፡
ሲነጋ ወደዚያው መሄድ አለብኝ…ጥያቄው ግን ይነጋል ወይ ነው?…እንዲህ በላብ እየተዘፈቁ፣ በሙቀት እየጋዩ፣ በቋያ እየተጠበሱ ሰላም ማደርና ማንጋት አለ ወይ ነው ጥያቄው?…በካርቱም በህይወት ለመኖር ካሰብክ፣ አራተኛ መሰረታዊ ነገር ያስፈልግሃል – ቬንቲሌተር!…ቬንቲሌተር በላዬ ላይ እየተሸከረከረብኝ፣ ሄሊኮፕተር የመሰለ አልጋ ላይ እርቃኔን ተዘርሪያለሁ… ሙቀቱ ግን፣ ቬንቲሌተርም አልገታው!… ልብሶቼን በሙሉ አውልቄ አዳምን መስያለሁ… ያም ሆኖ ሙቀቱ ትንፋሽ ነስቶኛል… ጉድ እኮ ነው!… እንግዲህ ቆዳዬን አላወልቀው!?…
.እኩለ ሌሊት ላይ…
የቫይበር መልዕክት መጣልኝ፡፡ በደስታ ፈንጥዤ እየተንቀጠቀጥኩ ከፈትኩት፡፡
እሱ ነበር የላከልኝ!… በእኩለ ሌሊት ጨለማውን ሰንጥቆ የደረሰልኝ የኑር ሁሴን ምላሽ፣ ሙቀቱንም፣ ድካሙንም፣ ምሬቱንም አስረሳኝ!… ለእቅዴ መሳካት አቅም የሚሆነኝን ብርታት ሰጠኝ!… በእስር የሚማቅቁትን ስደተኞችን በተመለከተ ልሰራው ላሰብኩት ዘገባ፣ ሙሉ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን አበሰረኝ፤ የእኔን ጥያቄ መስማቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረለት ነገረኝ፤ ከልቡ አመሰገነኝ – የወንዜ ልጅ ኑር ሁሴን፡፡
እስኪነጋና እስካገኘው ቸኮልኩ፡፡ መሃል ካርቱም በሚገኘው አክሮፖል ሆቴል እንዳረፍኩ በመግለጽ፣ በነጋታው ጠዋት መምጣት ይችል እንደሆን ጠየቅኩት፡፡
ጥቂት ቆይቶ የላከልኝን ምላሽ ሳነብ ግን፣ በድንጋጤ ክው አልኩ!…
“እኔም እኮ እስር ቤት ውስጥ ነው ያለሁት!…” ይላል መልዕክቱ፡፡
ምን እያለ ነው ኑር ሁሴን?…ግራ ተጋባሁ!…
ኑር ሁሴን በእስር ቤት ከሚማቅቁት የወንዜ ልጆች አንዱ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ስለሚማቅቁት እስረኞች መረጃ የሚሰጠኝ ከአጥሩ ውጭ የሚገኝ ስደተኛ እንጂ፣  ግምቴ ስህተት ነበር፡፡ እሺ ግድ የለም፣ ግምቴ ስህተት ነው ልበል… ግን… እስር ቤት ነኝ እያለኝ እንዴት ቫይበር ይጠቀማል?… ይሄንኑ ጥያቄ ለራሱ በቫይበር ላክሁለት…
“በድብቅ ሞባይል አስገብተን እንጠቀማለን… እርግጥ ፖሊሶች እንዳይቀሙን ቀኑን ሙሉ አሸዋ ስር ደብቀነው ውለን፣ ሌሊት ብቻ ነው እያወጣን የምንጠቀመው!…” ሲል መለሰልኝ፡፡
ማለዳ ለላክሁለት ጥያቄ፣ ምላሽ ሳይሰጠኝ የቆየውም፣ በሌሊት ካልሆነ ሞባይሉን ከደበቀበት አውጥቶ መክፈት ባለመቻሉ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ታሳሪዎችን በተመለከተ መረጃ ይሰጠኛል ያልኩት ሰው፣ ራሱ ታሳሪ ነው…
“ታዲያ ምን ይሻላል?…” ስል ጠየቅሁት፡፡
እሱ እስር ቤት ውስጥ ከሆነ፣ ያሰብኩትን ለማሳካት የምችልበት መንገድ መጥበቡ እየተሰማኝ ነው፡፡
“ለምን ታራሚ ጠያቂ ነኝ ብለህ፣ እስር ቤት አትመጣምና አልነግርህም!?…” አለኝ ኑር ሁሴን፡፡
መጀመሪያ ደንገጥ አልኩ…ከዚያ ራሴን አደፋፈርኩት… እስር ቤቱ ድረስ ሄጄ ሃሳቤን ለማሳካት የቻልኩትን ሁሉ መስዋዕትነት መክፈል እንዳለብኝ ተሰማኝ…
“ማንም ሰው እስር ቤቱ ውስጥ መግባት ይችላል እንዴ?…” ስል ጠየቅኩት፡፡
“ምንም ችግር የለውም!… ያለንበት እስር ቤት ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያውያንን አፈላልገህ ብትጠይቃቸው አቅጣጫውን ይነግሩሃል…” በማለት መለሰልኝ፡፡
አላመነታሁም…
“እንደምንም ብዬ ለመምጣት እሞክራለሁ!… እስር ቤቱ ምን እሚባል አካባቢ ነው ያለው?…” ስል መልዕክት ላክሁለት፡፡
ምላሽ አልሰጠኝም…
“እኔ ካለሁበት አካባቢ ብዙ ይርቃል?…” ስል ደግሜ ላክሁለት፡፡
አሁንም ምላሽ የለም…
በሃሳብ ተውጬ ስተክዝ ቆይቼ፣ አይኖቼን ወደ ሞባይሌ መለስኩ…
“ተጠቃሚው ከስድስት ደቂቃዎች በፊት መስመር ላይ ነበር” የሚል ጽሁፍ፣ የቫይበር መልዕክት ሰሌዳው ራስጌ ላይ አየሁ፡፡ እንደዚያ የጓጓለትን ጥያቄዬን አጠናቅቆ ሳይመልስልኝ፣አንድ ነጥብ ላይ ሳንደርስ፣ጉዳዩን ሳንቋጨው፣ ምልልሳችንን በድንገት ማቋረጡ ግራ አጋባኝ፡፡
ወዲያው ግን ጠረጠርኩ…
ምናልባት አንዱ ፖሊስ፣ በእኩለ ሌሊት አድብቶ ከተፍ ብሎበት ይሆን?…
ብዙ ነገር አሰብኩ… ብዙ ነገር እያሰብኩ፣ አንድ ነገር በጆሮዬ ደጋግሞ ያስተጋባል… ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ… ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ… ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ…
ፎጣ ቢጤ ጣል አድርጌ፣ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘውን የማረፊያ ክፍሌን የጓሮ በር ከፈትኩና፣ ወደ በረንዳው ወጣሁ…ትኩስ ጨለማ ፊቴን ገረፈኝ…በረንዳው ላይ ቆሜ፣ ጥቁር ካርቱምን ቁልቁል አየኋት…
እዚህ ጥቁር ስር፣ ወንዜ አለ… ከነጭ መንታው ጋር የሚቀላቀል፣ ጥቁር አባይ!… እዚህ ጥቁር ስር፣ የወንዜ ልጆች አሉ…የመተማን ድንበር አልፈው፣ የሁመራን በረሃ አቋርጠው፣ ከገዳሪፍ እስከ ጋላበት፣ ጥሻ ጥሻውን የተጓዙ፣ ከሙዲን እስከ ካርቱም የስደት መከራን የተጎነጩ፣ ሊቢያና ግብጽን እያማተሩ ሲንከላወሱ፣ በአሸዋ ላይ የተረጩ የአገሬ ልጆች አሉ…
እንጀራን ፍለጋ በየአቅጣጫው ከየተረጩበት እንደ እንክርዳድ ተለቅመው፣ ከያሉበት በፖሊስ ቆመጥ ታድነው ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ የሚሉት ሌላ ጨለማ ውስጥ የታጎሩ፣ የእድሜያቸውን እኩሌታ በሰው አገር ወህኒ ይገፉ ዘንድ የተፈረደባቸው የወንዜ ልጆች አሉ…
ጨለማ ካርቱምን በአይኖቼ አሰስኳት…በየት በኩል ይሆን፣ ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ?…
በዕለተ ስቅለት…
ማለዳ ላይ…
ስትጣበስ ውላ ብታድር የማይሰለቻት፣ ማለዳና ቀትር የማትለይ፣ ምሽትና ንጋት የማታውቅ፣ የዘለለት ግለት፣ የሌት ተቀን ቋያ – እሳት ካርቱም!… ማልዳ ነው ብላ የማትቀዘቅዝ – ግለት ካርቱም!…
ካርቱም ከተማ ውስጥ የሚገኘው መድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ፣ አንድ ጥግ ላይ ተቀምጬ በሙቀት እጠበሳለሁ፡፡ እኝ እኝ እያለ ያሰለቸኝን የሸገር ዝናብ፣ ቋያ ላይ ተጥጄ በሩቅ እናፍቃለሁ፡፡ ሳማርራት የሰነበትኳትን የአዲስ አበባ ጸሃይ፣ ጥግ ይዤ ይቅር በይኝ እላለሁ፡፡
የአዲስ አበባን ጸሃይ፣ ጥግ ስር ተጠልለህ ታመልጣታለህ፡፡ ዣንጥላ ዘርግተህ ትገታታለህ፡፡ መላ ፈልገህ ትቋቋማታለህ፡፡ ቀትር ላይ ብትጨክንብህ፣ ሲመሻሽ ቀዝቀዝ ትልልሃለች፡፡ የዋህ ናት – የአገሬ ጸሃይ!…
የካርቱም ጸሃይ ግን፣ በማይበርድ እሳት ስትጠብስህ ውላ፣ ረመጥ ላይ ጥዳህ ነው ወደ ቤቷ የምትገባው፡፡ ሌላ ፍም ይዛ ነው ማልዳ ከተፍ የምትለው፡፡ ለስግደት ይቅርና ለመተንፈስ የሚሆን አቅም አጥቼ፣ ቤተ ክርስቲያኑ ጥግ ላይ በላብ እጠመቃለሁ፡፡ ግቢውን የሞላው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ግን፣ ሙቀቱን ተቋቁሞ ተግቶ መስገዱን ተያይዞታል፡፡ ይሄ ወገቡን አስሮ የሚሰግደው ስፍር ቁጥር የሌለው ስደተኛ፣ ሙቀቱን ብቻ አይደለም ተቋቁሞ የሚኖረው፡፡ ብዙ በደል፣ ብዙ ስቃይ፣ ብዙ ሰቆቃ፣ ብዙ አሳር መከራን በጀርባው አዝሎ ነው፣ ደፋ ቀና የሚለው፡፡
ከኑር ሁሴን ጋር የነበረኝ ግንኙነት ትናንት ምሽት ድንገት ተቋርጦ ቢቀርም፣ ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ ቢያንስ ወንድሞቼ የሚማቅቁበትን እስር ቤት ስም አውቄያለሁ፡፡ አቅጣጫውን ደግሞ፣ እዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከማያቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አንዱ ሊጠቁመኝ ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ማልጄ ወዲህ የመጣሁት፡፡
ጥቂት አረፍ እንዳልኩ…ራቅ ብሎ ሲሰግድ የቆየ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ከአጠገቤ መጥቶ ተቀመጠ…ሰበብ ፈልጌ ተዋወቅኩትና፣ ጨዋታ አስጀመርኩት… ደረጀ ይባላል…
“ኑሮ እንዴት ነው?…” አልኩት እንደዋዛ፡፡
እንደዋዛ ጠየቅኩት እንጂ፣ እንደዋዛ አልመለሰልኝም… በስደት ወደ ሱዳን ከመጣ ከሰባት አመታት በላይ ያስቆጠረው ደረጀ፣ከአገሩ ከወጣ ጀምሮ ለአመታት ያስተናገደውን ግፍና መከራ ይቆጥርልኝ ጀመር፡፡ ኢትዮጵያዊው ስደተኛ በሱዳን የሚጎነጨውን የመከራ ዶፍ ይተርክልኝ ያዘ፡፡
“እኛ ለእነሱ ሰዎች አይደለንም!… እንደፈለጉ ያስሩናል እንደፈለጉ ይፈቱናል!… ሰበብ ፈልገው ይደበድቡናል፤ የሰራንበትን ገንዘብ ቀምተው፣ እስር ቤት ያስወረውሩናል!… ስንቱን መከራ ልንገርህ?!…” አለኝና አቀርቅሮ ማሰብ ጀመረ፡፡
በእስር ላይ ስለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ለመዘገብ እንደመጣሁ ነግሬው፣ ስለ ጉዳዩ ያውቅ እንደሆነ ስጠይቀው፣ በደስታ ዘልሎ መናገር ጀመረ፡፡
“እንደዚያ ከሆነማ አሪፍ ነው!… በጫትና በሚጣቃ (ጊዚያዊ የስደተኞች የመኖሪያ መታወቂያ) ምክንያት የታሰሩ ብዙ ልጆችን አውቃለሁ!… ከፈለግህ፣ የታሰሩበት ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ የሚባል እስር ቤት ሁሉ ልወስድህ እችላለሁ!… እንዲያውም፣ ወንድሙ የታሰረበት ጓደኛ አለኝ፣ እሱን እጠራውና አብራችሁ ትሄዳላችሁ!…” አለኝ ደረጀ በደስታና በጉጉት ስሜት ተውጦ፡፡
ከእሱ በላይ ደስ አለኝ!… ከእሱ በላይ ጓጓሁ!… ወደምፈልገው ቦታ የሚመራኝን ሰው አገኘሁት – ወደ ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ!…
ተሲያት ላይ…
እኔ፣ ወንድሙ የታሰረበት ናስር እና ጓደኛው ሙስጠፋ በአነስተኛ መኪና ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን፡፡ ከመሃል ካርቱም ተነስተን፣ ሻረኒል ጎዳናን ተከትለን፣ በአባይ ወንዝ ላይ የተዘረጋውን ኩብሪገዲ ድልድይን ተሻግረን፣ ወደ ስላጢቢ እንገሰግሳለን…
ከበስተቀኛችን የሚታየው ሰፊ ግቢ፣ ጃማኒሌ የካርቱም ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
እኛ ከእሱ ጉዳይ የለንም፡፡ ጉዟችን እውቀት ወደሚቀሰምበት ሳይሆን፣ አሳር ወደሚታይበት ግቢ ነው፡፡ ከበስተኋላችን ትተነው፣ ወደፊት መገስገሳችንን ቀጥለናል…እንደ እሳት በሚጋረፍ ትኩስ ንፋስ ተጠበስን፡፡
አሁን ከካርቱም እየወጣን ነው… መውረዳ የተባለቺው ሰፈር ላይ ስንደርስ፣ ወደ ቀኝ ታጥፈን ወደ ኡምበዳ ሰቢር የሚያቀናውን መንገድ ተያያዝነው…ይህ መንገድ፣ ከሁመራና ከመተማ ተነስቶ ካርቱም ላይ አረፍ የሚለው የአገሬ ልጆች የስደት ጉዞ ቀጣይ የስቃይ ምዕራፍ የሚጀምርበት ነው…ይህ መንገድ ከድንበር ጠባቂዎች አይን ተሰውረው በበረሃና በጫካ ሲሰቃዩ ከርመው፣ የደላላ ዱላና ፍጥጫን ተቋቁመው፣ ርሃብና ውሃ ጥምን ችለው፣ አሳር መከራቸውን አይተው ካርቱም ለመግባት የታደሉ የወንዜ ልጆች፣ ወደ ሊቢያ ሌላ የመከራ ጉዞን የሚቀጥሉበት ነው…
ሊቢያና ዳሬሰላም የሚባሉትን አካባቢዎች አልፈን፣ ሁምዱርማንን ተሻግረን መጓዛችንን ቀጠልን፡፡
ወንድሙ በእስር የሚማቅቅበት የጅማው ልጅ ናስር፣ ስለ ስደተኞች መከራ ይተርክልኛል… እሱን ለማስፈታት ሲል የከፈለውን ውጤት አልባ መስዋዕትነት ያወጋኛል… የናስርን ልብ የሚሰብር ትረካ፣ ከአገሩ ልጅ ከሙስጠፋ መኪና የሚንቆረቆረው የታደለ ገመቹ አንጀት የሚበላ ዜማ ያጅበዋል…
ታደለ ምን እያለ እንደሆነ አይገባኝም… ዜማው ውስጥ ግን አንዳች አንጀት የሚበላ ነገር ይሰማኛል… የሆነ የሚያንሰፈስፍ ነገር አለው፣ የታደለ ድምጽ ውስጥ… ኦሮምኛ ለማይሰማ የኔ ቢጤም የሚገባ፣ የሆነ ሰው መሆንን ብቻ የሚጠይቅ የሚያንሰፈስፍ ቅኝት አለው…
ጭው ያለ በርሃ…ትንፋሽ የሚያሳጥር፣ የሚያቃትት፣ በላብ የሚዘፍቅ ረመጥ ሙቀት…ግራና ቀኙን የተነጠፈ ወሰን የለሽ የአሸዋ መስክ…አልፎ አልፎ ከሚታዩ የጭነት መኪኖች በቀር፣ የሚንቀሳቀስ ነገር የሌለበት ኦና በረሃ…ይጓዝበት የሌለው፣ በረሃ ላይ ሌጣውን የተዘረጋ ቀጥ ያለ መንገድ… እሱን ተከትለን፣ ዝም ብለን… በየራሳችን ተውጠን፣ ረጅም መንገድ ተጉዘን…ከአንድ ሰዓት ከሩብ በኋላ…የመጨረሻው ቦታ ላይ ደረስን!…
ጭንቀትና ሙቀት እያቃተቱኝ፣ በዝግታ ከመኪናዋ ወረድኩ…አፍንጫ እሚለበልብ ትኩስ ንፋስ አፈነኝ!…እየቃተትኩ፣ እየፈራሁ፣ እየሰጋሁ እንደ ምንም አሻግሬ ተመለከትኩ…
ያው እዚያ ማዶ!…
ሰጥ ረጭ ያለ በረሃ ውስጥ፣ የሽቦ ጥለት በታጠቀ አመዳም አጥር ዙሪያውን የተከበበው የመከራ አጸድ!…የወንዜ ልጆች ታጉረው የሚማቅቁበት – ያው ኡምዱርማን ስጅን ሁዳ!…አሻግሬ እያየሁ ፈራሁት!…
(ይቀጥላል)

Leave a Reply