‹‹ሰንበሌጥ [ለቤት ክዳን የሚሆን ሳር] ውስጥ ሆኖ ሲተኩስ አየው ነበር፡፡ ድንገት ፊቱን ወደኔ መለስ አደረገ፣ ወደቀም፡፡ እኔም የያዝኩትን ቦታ ለቅቄ ወደ እሱ ሄድኩኝ፤ ሞቶ ነበር፡፡ በወንዙ ሌላኛው አቅጣጫ በጎን በኩል የጠላት ወታደሮች ተጠግተው ነበር፡፡ ከነበርኩበት ቦታ ከማፈግፈጌ በፊት ወደ ወንዙ አቅጣጫ ተኩስ ከፈትኩ፣ ሦስት ሰዎችንም ገደልኩ፡፡ ከዚያም የባሌን አስከሬኑንና መሣሪያውን እየተጎተትኩ ወደ ኋላ አፈገፈኩ፤ የተቀሩትና ከኔ ጎን ተሠልፈው የነበሩት ሁሉ ግን ደህና ነበሩ፡፡ ወደ ጦር ሠፈሩ ተመለስኩ፡፡ በማግሥቱም አስከሬኑን በዲርማ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስቀበርኩ፡፡››
እናት አርበኛዋ እመት ልኬለሽ በያን በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ (1928 እስከ 1933) ባለቤታቸው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ያዩትንና እሳቸው የፈጸሙትን ጀብዱ ያመለከቱበት ነበር፡፡ ፀሐይ ብርሃነ ሥላሴ ‹‹Women guerrilla fighters›› በሚለው ድርሳናቸው እንደገለጹት፡፡
የፋሺስት ወረራ
‹‹… ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ…››
ከ80 ዓመታት በፊት ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923 እስከ 1967 ዓ.ም.) ርእስ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፋሺስት ኢጣሊያን ወረራ አስመልክቶ በጄኔቭ የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ሸንጎ ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ኃይለ ቃል ነው፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1888 ዓ.ም.) ዓድዋ ላይ ድል የተመታው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስቱ ቤኔቶ ሙሶሎኒ አማካይነት ኢትዮጵያን መውረሩና በተለይ በዓለም የተከለከለው የመርዝ ጋዝ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሠራዊት በ1928 ዓ.ም. መፈታቱ ይታወሳል፡፡
እርመኛ አርበኞች የአገሪቱን ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ መራር ተጋድሎ ማድረጋቸውም ባይዘነጋም የፋሺስት ወንጀለኞች በታኅሣሥ 1928 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት፣ በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዝ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡
በስደት ወደ አውሮፓ የዘለቁት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከክብር ተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ማድረጋቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ አንዱና ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ አባል ለሆነችበትና መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ላደረገው የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) የግፍ ወረራውን በመቃወም ለሥዩማኑ አቤት ማለት ነበር፡፡
በአንድ በኩል የኢጣሊያው አምባገነን ቤኒቶ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በመጠቅለል በአፍሪካ የኢጣሊያ ግዛት መመሥረቱን አገሪቱንም መያዙን ሲያውጅ፣ አዲስ አበባንም ፋሺስቶች ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ከመያዛቸው አስቀድሞ የተሰደዱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሙሶሎኒን መግለጫ በመቃወም ለመንግሥታቱ ማኅበር አቤት ቢሉም ድጋፍ አላገኙም፡፡ አብዛኛዎቹ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል አገሮች ለኢጣሊያ ወረራ እውቅና ሰጥተው ነበርና፡፡
የአርነት ተጋድሎው ግን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቀጥሏል፡፡
ሴቶችና ተጋድሏቸው
በሰሜን የማይጨው ግንባር ከዘመቱት ሴቶች መካከል ከአርሶ አደር ቤተሰብ እስከ ልዕልታቱ ይገኙባቸዋል፡፡ ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ፣ ‹‹Fighting Fascism Ethiopian Women Pafriots 1935 – 1941›› በሚለው ጥናታቸው እንደጠቀሱት፣ እመት ዘነበች ወልደየስ ባለቤታቸውን ተከትለው የዘመቱት አርበኛ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙ ሲሆኑ፣ ሌላዋ ዘማች ልዕልት ሮማነወርቅ ኃይለ ሥላሴ ከባለቤታቸው ከባሌው ገዢ ጋር አብረው ከትተዋል፡፡ በተመሳሳይም የሸዋው ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልጅ ወ/ሮ ላቀች ደምሰው ከባለቤታቸው ደጃች መንገሻ አቦዬ ጋር የወንድ ልብስ ለብሰው ሽጉጣቸውን ታጥቀው ዘምተዋል፡፡ ወ/ሮ ዘነበች ወልደየስ ከባለቤታቸው ከራስ አበበ አረጋይ፣ ወ/ሮ ሸዋነሽ አብርሃም ከባለቤታቸው ከደጃች ኃይሉ ከበደ (ሌተናል ጄኔራል) ጋር እንዲሁ ከትተዋል፡፡ አንዳንድ ሴቶች አባቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውንም ተከትለዋል፡፡ ሴቶች ከባለቤታቸው ጋር ቢዘምቱም የግድ በነሱ እዝ ውስጥ መዋሉን አይመርጡም ነበር፡፡ አንዱ ማሳያ የደጃች ሀብተሚካኤል ባለቤት የወሰዱት ቆራጥ ዕርምጃ ነው፡፡
ሰው ተጎድቶባቸው ነበርና በዶሎ ግንባር የመጣውን የጣሊያን ጦር ለመግጠም ያመነቱትን ባለቤታቸው ደጃች ሀብተሚካኤል አቋም ባለመቀበል 150 ወታደሮች ይዘው ክተት ያሉት በቅሎ ላይ ፊጥ ብለው ነበር፡፡ የጣሊያንን ሠራዊት ገጥመው ሠራዊታቸው በርካታ የፋሺስት ወታደሮችን ገድሏል፡፡ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ማርኳል፡፡ ስማቸው በውል ባለመገለጹ አንዳንድ ጸሐፍት ‹‹ስሟ ያልታወቀው›› እያሉ ይጠቅሷታል፡፡
የእመቤት ሆይ ከበደች ሥዩም መንገሻ ባለቤት ደጃች አበራ ካሳ፣ ለፋሺስቶች እጅ መስጠትና መገደል፤ እመቤት ሆይ ከበደችን ከተዋጊነት አልመለሳቸውም፡፡ አርባ ወታደሮችን ይዘው ከሌሎች ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ፍልሚያውን ተቀላቅለውታል፡፡
ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል፡፡ ባላቸው በ1929 ዓ.ም. ወደ ጣሊያኖች ቢገቡም በርሳቸው ሥር የነበሩትን አርበኞች ይዘው ወደ ኬንያ ማፈግፈጋቸው ተጽፏል፡፡
የጠላትን ሁኔታ ለመሰለል፣ ምስጢራዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፤ ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ችሎታ ለማሳየታቸው አንዷ ተጠቃሽ የውስጥ አርበኛዋ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተድላ ዘገየ እንደጻፉት፣ አርበኞች የአዲስ ዓለምን ምሽግ ደጋግመው ለማጥቃትና ለመጨረሻም ለማስለቀቅ የቻሉት በቆፍጣናይቷ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ድጋፍ ጭምር ነው፡፡
በሕክምና ሥራም የረዱ ብዙ ናቸው፡፡ ሰው በቆሰለ ጊዜ ደሙን አጥበው፣ መግሉን አጥበው፣ የተገኘውን የአገር ባህል መድኃኒት አድርገው፣ መግበውና ውኃ አጠጥተው ያድናሉ፡፡ የሞተባቸውም እንደሆነ ለማያውቁት ሰው ጭምር እርር ብለው አልቅሰው ቀባሪ ለምነው ያስቀብራሉ፡፡
ሕክምናን በተመለከተ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩና ወ/ሮ ጽጌ መንገሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹ኢጣልያ በኢትዮጵያ – ከወልወል እስከ ጎንደር›› በተሰኘው የአቶ ተድላ ዘገየ መጽሐፍ እንደሚያብራራው፣ ወይዘሪት ስንዱ በአዲስ አበባ ከአባታቸው ከከንቲባ ገብሩ ጋራ ጎሬ ከተማ ገቡ፡፡ ወይዘሪት ጽጌ መንገሻ ደግሞ ከወንድማቸው ከአቶ ይልማ መንገሻ ጋር አምቦ ከተማ፣ ከጥቁር አንበሳ ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች ጎሬ ካለው ሐኪም ቤት ያገኙትን ያህል መድኃኒት ወስደው ጦሩ በየሄደበት ቦታ ሁሉ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት እስከ መጨረሻው አገልግለዋል፡፡ ደንበኛውን የቀይ መስቀል መለዮ አድርገው፣ እንደ ወንድ ኮትና ሱሪ ለብሰው፣ ቡሽ ባርኔጣ አድርገው በጦርነት ጊዜ የቆሰለውንና የታመመውን በማከም ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በአምስቱ ዘመን በተለያዩ ግንባሮች በውጊያው አውድማ ውስጥ ከዘመቱት በሺዎች ከሚቆጠሩት ሴቶች መካከል ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ አንዷ ናቸው፡፡ ከ14 ዓመት በፊት የ90 ዓመት አረጋዊት ሳሉ ያነጋገራቸው ሺበሺ ለማ እንደጻፈው በ1928 ዓ.ም. ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሲወር ባለቤታቸው በጅጅጋ በኩል ወደ ጂቡቲ ለስድስት እንዲሄዱ ቢገፋፏቸው አገራቸውን ትተው እንደማይሄዱ ተጋድሏቸውን እንደሚቀጥሉ ነግረዋቸው ተለያይተዋል፡፡ በምሥራቅ ግንባር ሰርጎ የገባው የፋሺስት ወራሪን ሱሪ ታጥቀው፣ ዝናር ታጥቀው ብረት አንግተው ተፋልመዋል፡፡ ከወረራው 10 ዓመት በፊት ያረፉትን የአባታቸውን ፊታውራሪ ገብረአምላክ ውብነህ ማዕረግን የያዙት ፊታውራሪ በላይነሽ፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለኢትዮጵያ ድል 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ ያሳተመው ‹‹እኔ ለአገሬ›› መጽሔት የፊታውራሪ በላይነሽን ገድል ዘርዝሮታል፡፡
‹‹ጣሊያን አሁንም ዋጩ በሚባል አገር ለአሰሳ መጣ፡፡ ኃይለ ማርያም መብረቁ ለሚባሉ አርበኛ ወረቀት ጻፍኩና፣ ‹‹ኑ ዕርዱኝ›› አልኩ፡፡ እኔን ለመርዳት ብዙዎች ብረት ይዘው መጡልኝ፡፡ ለጋራሙለታው ሰው ለፊታውራሪ ሺመልስ ሀብቴም ወረቀት ጽፌ መሣሪያ ይርዱኝ ብዬ ላኩባቸው፡፡ እሳቸውም አንድ መትረየስና 15 ጠመንጃ ላኩልኝ፡፡ ከዚህ በኋላ አርበረከቴ የነበረውን ጣሊያንን እንዲህ እያልን እያቅራራን እንወጋው ጀመር፡፡
እናንተም ወዲህ ኑ እኛም
እንመጣለን
አረበረከቴ ላይ እንገናኝ፡፡
ተጋዳይ፣ ተጋዳይ፣ ተጋዳይ አርበኛ
ገዳይ እቁኒ ላይ ሾላ መገናኛ፡፡
ምናባቱ ፋሽስት፣ ምናባቱ
በረዢም ቁመቱ፣
በደንዳና ባቱ፣
እንወጋዋለን በገዛ ብረቱ፡፡
‹‹ጣሊያን መልሶ ማጥቃት ሲያረግብን ቦረዳ የሚባል አካባቢ ሄደን ተዋጋን፡፡ ከዚያም ከሺመልስ ሀብቴ ጋር ሆነን ወደ ሸዋ አቅጣጫ ውጊያ ጀመርን፡፡ እስከ አርባጉጉ ድረስ እየተዋጋን ቀጠልን፡፡ ነገር ግን በዚያ መቆየት ስላልቻልን ወደ ባሌ ተጓዝን፡፡ ጣሊያንም እዚያ ድረስ ተከታትሎን መጣ፡፡ እኛም መልሰን ወጋነው፤ ፊታውራሪ ሺመልስ ሲዋጉ፣ ሲዋጉ ቆይተው ሲዳሞና ባሌ ጠረፍ ላይ ሞቱ፡፡ የጣሊያን ኃይል እያየለ በመምጣቱና በሌሎቹም ችግሮች ምክንያት አቅማችን ስለተዳከመ መበታተን የግድ ሆነብን፡፡ እኔም ወደ ሸዋ መጣሁ፡፡
‹‹ሸንኮራ፣ ደጃዝማች ፍቅረማርያም የሞቱበት አገር እንዳለሁ፣ አሁንም ጣሊያን ተከትሎኝ መጣ፡፡ እጄን ሳልሰጥ ስዋጋ ቆይቼ ወደ አድአ አፈገፈግሁ፡፡ ጣሊያንም እንደገና ዱካዬን አፈንፍኖ መጣ፣ ቢሾፍቱ ቡርቃ የሚባል፣ ምንጃር ቡልጋ የሚገኝበት ቦታ ጦርነት ገጠምነው፡፡
‹‹እዚያ በጥይት ተመትቼ ቆሰልኩ፡፡ ከዚያም ብረቴን ቀብሬ ቁጭ አልኩ፡፡ እዚያ እየበላሁ፣ እየጠጣሁ፣ ባንዳው እንዳያሳብቅብኝ፣ ጣሊያንም እንዳያገኘኝ ጎፈሬዬንም ተቆርጬ እያለሁ የጃንሆይን ወደ አገር መግባት ሰማሁ፡፡ የእሳቸውን መምጣት ስንሰማ አዲስ አበባ ለመቀበል መጣን፡፡ ግን አልመጡም አሉን፡፡ ገሚሱ እሳቸውን ለመቀበል ጎጃም ሄደ፣ እኔ ተመለስኩ፡፡
‹‹ጃንሆይ ከገቡ በኋላ እንደገና መጣሁና እየፎከርን ገብተን ጃንሆይን አገኘናቸው፡፡ እኔ ቀሚስ ለብሼ ከአርበኞቹ ተለይቼ ጃንሆይን እጅ ነሳሁ፡፡ የእኔ ዝና ቀድሞውንም ተሰምቶ ነበርና፣ ደጃዝማች ይገዙ ሀብቴ እጄን ይዘው ለጃንሆይ ፣ ‹ጉድ ላሳይዎት› ብለው አቀረቡኝ፡፡ እኔም ቆንጆ ሆኜ የከተማ ሰው መስዬ ነበር የቀረብኩት፡፡
‹‹ጄኔቭ በነበርንበት ጊዜ፣ በላይነሽ የምትባለው ሴት ትዋጋለች እየተባለ የምንሰማው እሷን ነው?› ብለው ጠየቁ፡፡ ደጃዝማች ይገዙም ‹አዎ› ብለው አቀረቡኝ፡፡ ጃንሆይም በፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ ‹አለሽ እንዴ! ማን ትባያለሽ?› አሉኝ፡፡ እኔም፣ ‹ፊታውራሪ በላይነሽ ነኝ› አልኳቸው፡፡ ‹በስምሽ ተጠሪበት› ብለው ሹመቱን አፀደቁልኝ፡፡››
በስም ያልተጠቀሰችው አርበኛ- ‹‹እስከዳር››
በስም ከሚታወቁት ውጪ ሱሪ ታጥቀው ጠመንጃ አንግተው ፍልሚያውን የተቀላቀሉ በርካታ ሴቶች ነበሩበት፡፡ ከነዚህ በስም ከማይታወቁት ሴቶች መካከል ስለ አንዷ እንስት ታዋቂው ደራሲና አርበኛ፣ ሚኒስትርና ዲፕሎማት አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ትዝታ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ከገጽ 84 እስከ 86 ሐተታ ታሪክ ጽፈውላት ነበር፡፡ ይህን ታሪክ ያነበቡት ባሕር ማዶ የሚገኙት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ስሟ ላልተጠቀሰው አርበኛ ‹‹እስከዳር›› የሚል መጠርያ በመሰጠት ታሪካዊ ልብ ወለድ ጽፈው በ2002 ዓ.ም. አሳትመውላታል፡፡ ደራሲው ዳዊት በመግቢያቸው ላይ እንዲህ ከትበውላታል፡፡
‹‹[አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ] ከገጽ 84 እስከ 86 ስለአንዲት ሴት የጻፉት ለብዙ ጊዜ በሐሳቤ ውስጥ ሲንገዋለል ቆይቷል፡፡ በሐሳቤ ‹ይህች ሴት ማን ትሆን? ከየት ነው የመጣችው? ትውልዷ ምንድነው? እንዴት እዚህ እሳት ውስጥ ገባች?› እያልኩ ራሴን ስጠይቅ ቆይቼ ዛሬ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞከርኩኝ፡፡ ይህችን ስም ያልነበራትን ሴት ስም ሰጠኋት፡፡ እስከዳር አልኳት፡፡ ታሪክ አበጀሁላት፡፡ በኢትዮጵያ የሴት አርበኞች ያሸበረቀ ታሪክ ውስጥ አስቀመጥኳት፡፡ ይኸ መጽሐፍ የወይዘሪት እስከዳር ልብ ወለድ ታሪክ ነው፡፡››
እዚች መጣጥፍ ላይ ልብወለዱን ሳይሆን የምናነሣው አቶ ሐዲስ ስለእርመኛዋ አርበኛ በደራሲ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ስያሜ ‹‹እስከዳር›› ያወጉትን ነው፡፡
‹‹ያንለትና ከዚያ በፊት በነበረው ሌሊት ከዚህ በላይ ባጭሩ እንደ ተረክሁት፣ መንገድ ለመንድ ይታይ የነበረውን የመከራና የስቃይ ትርዒት ሳስታውስ ከሁሉም ጎልቶ ባይነ ህሊናዬ ፊት የሚታየኝ ባንድ ሴት ላይ ሲደርስ ያየሁት ነው፡፡ አንድ ያይሮፕላን ቡድን ደብድቦን ካለፈ በኋላ ዛፍና ቁዋጥኝ ወይም ሌላ ተገን ወዳለበት መሸሹን ያልረሳን ሰዎች ከየተሸሸግንበት ወጥተን ስንሄድ እንደቆየን አይሮፕላኖች ከኋላችን እንደገና ቦምብ እየጣሉ ሲመጡ ሰማን፡፡ ያን ጊዜ የደረስንበት ቦታ የዘንባባ ዛፎችና ሌሎች ዛፎች አለፍ አልፍ ብለው የበቀሉበት ስለነበረ መንገዱን ይዞ ከሚጉዋዘው ሠራዊት መካከል ጥቂታችን ዛፎች ወዳሉበት እየሸሸን ተጠጋን፡፡ በበቅሎ ተቀምጣ ከሠራዊቱ ጋር የምትሄድ አንድ ሴት ነበረች፡፡
ይች ሴት ባለማኅደር ዳዊት ባንገቷ አግብታ ካንድ ብብትዋ ሥር አንጠልጥላ አንድ አጭር ዲሞትፈር ጠመንጃ እንዲሁ ባንገቷ አግብታ በጀርባዋ አዝላ ባንድ እጇ የተቀመጠችበትን በቅሎ ዛብ በሌላ እጇ የተጫነች አጋሰስ በረዥም ላኰ ይዛ ከኋላዋ እየሳበች ትሄድ ነበር፡፡ በክፉ አጋጣሚ አይሮፕላኖች እዚያ ቦታ ሊደርሱ ሲቃረቡ አጋሰስዋ ገረገረችባት (ቆማ ወደ ኋላ ሳበቻት)፡፡ ዘወር ብትል ያጋሰስዋ ጭነት ባንድ ወገን አጋድሎ ከጀርባዋ ወደ ሆዷ ወርዷል፡፡ ከዚያ ሴትዮዋ ከበቅሎ ወርዳ ያጋደለውን ጭነት ወዳጋሰሷ ጀርባ መልሳ ለመጫን ትታገል ጀመር፡፡ ያን ጊዜ ሁላችንም ያይሮፕላኖችን መድረስ አይተን ‹ሴትዮ አይሮፕላኖች መጡብሽ በቅሎዎችን ተይና ነይ! እባክሽ ተያቸውና ወዲህ ነይ!› እያልን ከያለንበት ጮህን፡፡ እሷ የእኛን ጩኸትም ሆነ በምብ እየጣሉ የመጡትን አይሮፕላኖች አታይም አትሰማም ነበር፡፡ ዓይኗንም፣ ጆሮዋንም፣ አሳቧንም ሁሉ ተሰብስቦ ያተኮረው ያን ያጋደለ ጭነት መልሳ ለመጫን በጀመረችው ትግል ላይ ብቻ ነበር፡፡ ከየዛፉና ከየቁዋጥኙ ሥር ስንጮህ ከነበርነው መካከል አንድ ሰው ሴትዮዋን ለማዳን ወደሷ ሮጦ ነበር፡፡ ነገር ግን አይሮፕላኖች ስለቀደሙት ከመሀል መንገድ ወደ መሸሸጊያው ተመለሰ፡፡ ያች ሴት እንዲያ ካጋሰስዋ ጭነት ጋር በመታገል ላይ እንዳለች አይሮፕላኖች ከጣሉዋቸው ቦምቦች አንዱ እስዋና በቅሎዎችዋ በቆሙበት መሀል ወደቀ፡፡ ወዲያው ያ የቆሙበትና በዙሪያው የነበረው መሬት ሁሉ ተጎርዶ ብዙ ሜትር ወደ ሰማይ ሲነሳ የስዋና የበቅሎዎችዋ፣ የመሬቱ፣ የድንጋዩ፣ የሳሩና የቁጥቁዋጦው ብጥስጣሽ ባንድነት ተደባልቆ ባየር ውስጥ ከጓነ በኋላ ተመልሶ ቦምቡ መሬቱን ጎርዶ ሲያስነሳው እስር ተቆፍሮ በቀረው ሰፊ ጉድጉዋድ ዙሪያ ተበተነ፡፡ ታዲያ የሚያስገርመው አይሮፕላኖች እዚያ ባጠገባችን በጣሉት ብዙ ቦምብ ከዚያች ሴትና ከበቅሎዎቹ በቀር ከዚያ ሁሉ ሠራዊት ሞቶ ወይም ቆስሎ ሲወድቅ ያየነው አልነበረም፡፡
‹‹አይሮፕላኖች ከሄዱልን በኋላ ከየዛፉ ስር ወጥተን መንገዳችንን ስንቀጠል ሴትዮዋን ለማዳን ሩጫ ጀምሮ የነበረው ሰው እንደነገረን ያቺ ሴት ያንድ መኰንን በጣም የሚዋደዱት የጭን ገረድ ኖራለች፡፡ ከሁለት ቀን በፊት የመኰንኑ አሽከሮች እጦርነቱ ውስጥ አልቀው እሳቸውም ክፉኛ ሲቆስሉ ከሞትም ከመቁሰልም የዳኑ እስዋና አንድ ወንድ አሽከራቸው ብቻ ኖረዋል፡፡ ጌትየው በጽኑ ቆስለው በጣእር ውስጥ እንዳሉ እስዋ ባጠገባቸው ሆና ስታስታምማቸው እንደማይተርፉ ተረድተውት ኖሮ ‹አንቺና ተስፋ (ወንዱ አሽከራቸው) ከሞት ተርፋችሁ አገራችሁ ለመግባት የበቃችሁ እንደሆነ፤ መሣሪያየንና አባቴ ሲሞቱ ለመታሰቢያቸው የሰጡኝን ዳዊቴን ለልጄ ለንጋቱ እንድታደርሱልኝ አደራ፡፡ እሱ እስኪያድግ የናቱ ወንድም ብላታ በየነ ባላደራ ሆነው ይጠብቁለት፤› ብለው ተናዘው ሞተዋል፡፡ እንግዲህ ይቺ፣ ሰው ሁሉ ነፍስዋን እንድታድን ያን ያክል ሲማፀናት ዓይኗን እያየ በቦምብ ተቃጥላ የሞተች የወዳጇን ያደራ ኑዛዜ ለመፈጸም ኖሮዋል! ምን ዓይነት እስከ ሞት የሚያደርስ ታማኝነት፣ ምን ዓይነት ኃያል ፍቅር ቢሆን ነው? ‹‹ለሃይማኖትዋ ብላ ለማተብዋ ብላ እንዲያ ተቃጥላ ሞተች!›› አለ ሰውየው የሴትየዋን ታሪክ ከተረከልን በኋላ እየተከዘ፡፡
‹‹እንዴት ለሃይማኖትዋ ብላ? ያይሮፕላን ቦምብ ስንቱን አቃጥሎ ሲጨርስ እያየች ካጋሰስ ጭነት ጋር ስትታገል መሞትዋ ‹ሃይማኖተኛ› የሚያሰኛት መስሎዋት ነው? እንዲህ ያለው ሞኝነት ወይም እብደት ነው እንጂ ሃይማኖተኛነት አይደለም!›› አለ ጤናው ከማዘኑ የተነሳ ቆጣ ብሎ ግን ኃያል ፍቅር ሞኝም፣ እብድም፣ ሃይማኖተኛም ሁሉንም ያደርጋልኮ!››
‹‹ሚያዝያ 27 የድላችን ቀን …››
በባሕር ማዶ በስደት ሳለ ሕይወቱ ያለፈው ድምፃዊ ተስፋዬ ገብሬ፣ ኢትዮጵያና አርበኞቿ የአምስቱን ዓመት የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ (1928 እስከ 1933 ዓ.ም.) በድል አድራጊነት የተወጡበትን ታሪክ በዘፈኑ፡-
‹‹መጋቢት 28 የድላችን ቀን
ይከበር ዘላለም በሀገራችን፣
መጋቢት 28 በያመቱ ይምጣ
የናንተ መሣሪያ ጦር ጋሻው ይምጣ›› እያለ አቀንቅኖት ነበር፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከ1934 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የድሉ በዓል ይከበር የነበረው ሚያዝያ 27 ቀን ሲሆን፣ ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ በዓሉን ወደ ‹‹መጋቢት 28›› ለውጦት ከወደቀም በኋላ እስከ 1987 ዓ.ም. ሲከበር ኖሯል፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በወጣ በአምስተኛ ዓመቱ በነባር አርበኞቹና በኅብረተሰቡ ጥያቄ፣ በታሪክ ምሁራንም አረጋጋጭነት በዓሉ በ1988 ዓ.ም. ወደ መሠረታዊ ቀኑ ሚያዝያ 27 ቀን ተመልሶ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ አዲስ አበባን በያዘበት ሚያዝያ 27 ቀን (1928 ዓ.ም.) በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ የድልን ቀን ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) ተበሰረ፡፡ 75ኛ ዓመቱንም ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ተዘከረ፡፡
ዘውዴ ረታ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ታሪካዊቷ ሚያዝያ 27 እንዲህ ጽፈዋል፡፡
‹‹ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት፡፡ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አሥር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ፡፡››
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስደት መልስ መናገሻ ከተማቸው ሚያዝያ 27 ቀን ገብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከማውለብለባቸው አራት ወር ግድም በፊት ጥር 12 ቀን ሱዳን ድንበርን ተሻገረው ኢትዮጵያ ገብተው ያውለበለቡት ኦሜድላ ላይ ነበር፡፡
ከሰባ አምስት ዓመታት በፊት የድሉን ብሥራት አስመልክተው ባለቅኔው የእንጦጦ ራጉኤሉ ብርሃኑ ድንቄ (ከስድስት አሠርታት በፊት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩ ) ፡-
‹‹ኢትዮጵያ ከማር ለሚጣፍጥ ለስምሽ አጠራር ሰላም ይገባል፡፡
ባምላክ እጅ ለተሠራ ለራስ ፀጉርሽም ሰላምታ ይገባል፡፡
ምሳሌ የሌለሽ መቅደስ ኢትዮጵያ፤
ጠላት ኢጣሊያ ስላረከሰሽና መሠዊያሽን ስላጠፋ ፈንታ፣
ከእንግዲህ ወዲህ ተቀደሽ፣ ኃይልንም ገንዘብ አድርጊ፤›› ብለው ተቀኝተውላት ነበር፡፡
‹‹እናታችን ኢትዮጵያ ሆይ
ለታረዙ ልብስ ነሽና
በባንዲራሽ ጥላ ሰብስቢ ልጆችሽን›› እያሉም ዘመሩላት፡፡