አንፃራዊው የሶማሊያ ሰላም ምን ያህል ይዘልቃል?
የህንድ ውቅያኖስን ዳርቻ ተከትላ የከተመችው የሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ፣ ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ የፈጀው የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን ውድመትና ድቀት ዳግም ለመገንባት የምትጣደፍ ትመስላለች፡፡ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ ጦርነቶች ያስከተሉት ጠባሳ በቀላሉ በተለያዩ የከተማ ክፍሎች አሁንም እማኝ ሆነው ይታያሉ፡፡
በቱርክ የኮንስትራክሽን ድርጅት የተገነባው አዲሱ አደን አብዱላሂ ኤርፖርት የህንድ ውቅያኖስን የተጠጋና መጠኑም አነስተኛ ነው፡፡ በኤርፖርቱ የሚስተዋለው ከፍተኛ ጥበቃና ፍተሻ እጅግ በጣም የተጠናከረና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከወራት በፊት ኤርፖርቱ ውስጥ በነበረ አንድ አውሮፕላን ላይ ቦምብ መፈንዳቱ ከባዱን የፍተሻ ሒደት የበለጠ አስቸጋሪና ውስብስብ እንዳደረገው፣ በተደጋጋሚ ወደ አገሪቱ የሚሄዱ ተጓዦች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ኤርፖርቱ ከአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል በሶማሊያ (አሚሶም)፣ እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሶማሊያ ልዑክ በአጐራባችነት የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ሥፍራ በሞቃዲሾ ከተማ ካሉ ተቋማት መካከል ከፍተኛ የደኅንነት ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት ነው፡፡ ምናልባትም በከተማዋ ውስጥ በሰላም ለመንቀሳቀስ የሚቻልበት አካባቢም ነው፡፡
ይህ ሥፍራ በኡጋንዳ ወታደሮች የ24 ሰዓታት ያልተቋረጠ ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑ፣ በአካባቢው የሚካሄደው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በከፍተኛ የደኅንነት ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ነው፡፡
በአሚሶም ሥር ወታደሮቻቸውን ወደ ሶማሊያ በመላክ ለአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት መሥፈን እየሠሩ ከሚገኙ አገሮች የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ ከተማዋን እንዲጐበኙና አሚሶም በሶማሊያ እያከናወነ ያለውን የተለያየ እንቅስቃሴ ለመመልከት የአምስት ቀናት ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡
ከየአገሮቹ የተውጣጣው የጋዜጠኞች ቡድን ሞቃዲሾ እንደደረሰ በአሚሶም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አማካይነት ቆምጨጭ ያለ ወታደራዊ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ከተማዋን ለመጎብኘት በሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ 15 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን የጥይት መከላከያ ጃኬት መልበስና የራስ ቆቡን ማድረግ ግዴታ እንደሆነ የሚገልጽ ነበር፡፡
በተጨማሪም ኤርፖርቱ ካለበት አካባቢ ውጪ መንቀሳቀስ ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን፣ እያንዳንዱ እንቅስቃሴም በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች የታጀበ እንደሚሆን እንዲሁ ተብራርቷል፡፡
በዚህ መሀል በሶማሊያ አንፃራዊ ሰላም አለ እየተባለ እንዲህ ያለ አጀብና ጥንቃቄ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበ ሲሆን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ‹‹መቼ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም፡፡ አልሸባብ በመዳከሙ የተነሳ የውጊያ ሥልት ለውጥ በማድረጉ የተነሳ ቅጽበታዊ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሞቃዲሾ ዳግም ትገነባለች?
የተለያዩ የሕንፃ ግንባታዎች በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች የሚታዩ ሲሆን፣ አዳዲስ ሕንፃዎችም እንዲሁ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ የተጠናቀቁና በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ በርካታ ሕንፃዎች ይታያሉ፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ የተጠናቀቁና በግንባታ ላይ የሚገኙ ሕንፃዎች በተደጋጋሚ ለአልሸባብ ጥቃቶች የተጋለጡ ናቸው፡፡
አብዛኛዎቹ ሕንፃዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ የቦንብ አደጋ ጥቃት የተፈጸመባቸው ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ በዳግም ግንባታ መልሰው የተገነቡ ናቸው፡፡ የጥበቃ ሁኔታውም እንዲሁ ከአደጋው በኋላ ተጠናክሮ ሕይወት ይቀጥላል፡፡ በከተማዋ ውስጥ ረዘም ረዘም ያሉ ሕንፃዎች የሚታዩ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹም ለቢሮና ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ሕንፃዎች መካከል ሳፋሪ ሕንፃ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሕንፃው ለቢሮና ለመኖርያ የሚሆኑ ክፍሎች አሉት፡፡ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑ ሀብታም ሶማሌዎች በተለይም ከውጭ የተመለሱት ለመኖሪያነት ይመርጡታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሕንፃው ላይ የተለያዩ ቢሮዎች ይገኛሉ፡፡ እንደ አልጄዚራ፣ ቢቢሲና ሲሲቲቪን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የውክልና ሥራ የሚሠራው ሆርን ኮኔክት የተሰኘው ድርጅትም መቀመጫው እዚሁ ሕንፃ ላይ ነው፡፡ የሕንፃው የመጨረሻ ፎቅ ላይ በመውጣት ከሞላ ጐደል ሞቃዲሾን መቃኘት ይቻላል፡፡
ከዚሁ በተቃራኒ ደግሞ ከሳፋሪ ሕንፃ በቅርብ ርቀት ላይ የእርስ በርሱ ጦርነት ጠባሳ የሚታይባቸው የተደቆሱና ያረጁ፣ እንዲሁም የፈራረሱ ቤቶችንና መኖርያ መንደሮችን መመልከት ይቻላል፡፡
እነዚህን ሁለት ተቃርኖዎች ከማስተዋል ባሻገር ከተማዋ መንገዶቿን ለመገንባትና ቤቶችን እንደ አዲስ ለመሥራት ደፋ ቀና እያለች ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በሞቃዲሾ ወደብ አማካይነት ወደ አገሪቱ ከሚገቡ በርካታ ቁሳቁሶች መካከል ጣውላና የአርማታ ብረት በግንባር ቀደምትነት የሚታዩት፡፡
አሚሶም አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በአንፃራዊ ሰላም ተጠቃሚ የሆነው የቱርክ አክባር ድርጅት የሞቃዲሾ ወደብን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ወደቡም ሶማሊያን ዳግም ለመገንባት አስፈላጊ የሆኑት ቁሳቁሶችን ጭነው በየዕለቱ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስድስት መርከቦችን ያስተናግዳል፡፡
አክባር የተሰኘው የቱርክ ድርጅት የሞቃዲሾ ወደብን ማስተዳደር ከጀመረ ሁለት ዓመት እንደሆነው ከመግለጽና ባለፉት ሁለት ዓመታትም ይህ ነው የሚባል ከባድ ጥቃት እንዳልደረሰበት ከመግለጽ ውጪ፣ ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት በድርጅቱ የደኅንነት ኃላፊ ሳሚ ኤሮል እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሕይወት በሞቃዲሾ
የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ አይመስሉም፡፡ ምንም እንኳን በቀን ያለው ሙቀትና ወበቅ ለማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ የማይጋብዝ ቢሆንም፣ በምሽትም ቢሆን በሞቃዲሾ ጐዳናዎች ያን ያህል የተለየ ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ ማስተዋል አይቻልም፡፡
ከተማዋን ለመጀመርያ ጊዜ የሚጐበኝ ዕንግዳ የሰው እንቅስቃሴ እንደሌለ ሊሰማው ቢችልም፣ በሞቃዲሾ አብድል አዚዝ በተባለ ወረዳ ለሚኖረው መሐመድ ዳሂር አሊ ግን ሞቃዲሾ ሞቅ ደመቅ ያለችና በማደግ ላይ ያለች ከተማ ነች፡፡
መሐመድ ዳሂር የ32 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ባጃጅ በመንዳት የሚተዳደር ነው፡፡ በቀን በአማካይ ከ20 እስከ 25 ዶላር የሚያገኝ በመሆኑ፣ ምሽቱን ከጓደኞቹ ጋር በመሰብሰብ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ራሱን እንደሚያዝናና ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
‹‹እዚህ (ህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ) እናዝናናለን፡፡ እዚህ የምንዝናናው እኛ ብቻ አይደለንም፡፡ ከሌላ የከተማው ክፍልም እንዲሁ መጥተው የሚዝናኑ በርካቶች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ስለሞቃዲሾ የሚጽፉትና የሚዘግቡት መጥፎውን መጥፎ ብቻውን ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ሕይወት አለ፡፡ እዚህ ደስታም አለ፤›› በማለት ሰዎች እንደሚዝናኑና እንደሚንቀሳቀሱ ይገልጻል፡፡
ለመሐመድ ሞቃዲሾ በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡ በዚህ የተነሳም የከተማዋ መፃኢ ዕጣ ፈንታ መልካም ነው ብሎ እንዲያስብ አስችሎታል፡፡ ከዚህም በላይ በቅርብ ዓመታት ሞቃዲሾ ከዓለም ምርጥ ከተሞች አንዷ ትሆናለች የሚል ተስፋም ሰንቋል፡፡
እንዲህ ዓይነት የተስፋ አመለካከቶች በሶማሊያውያንና በባለሥልጣናቷ ዘንድ የሚገለጹ ቢሆንም፣ አሁን በከተማዋ ካለው ፍራቻ አንፃር እንዲህ ዓይነቱን ተስፋና ህልም ለመሳካት ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ነው የሚመስለው፡፡
በተለይ አልሸባብ በማቆጥቆጥ ላይ ያሉ ተቋማትንና መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረገው ጥቃቱ፣ የሶማሊያውያን ህልምና ተስፋ እንዳይሳካ ያደርገዋል የሚል ሥጋትም አለ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የማዕከላዊ መንግሥቱ በተወሰኑ ክፍሎች ተቀባይነት አለማግኘትና የመንግሥት ተቋማት በተለይ የደኅንነት፣ የመከላከያና የፖሊስ ተቋማት አለመጠናከር፣ በአልሸባብ የሚሰነዘረውን የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት መቋቋም አለመቻል ነገሮችን የተወሳሰበ እንደሚያደርጋቸው ይታሰባል፡፡
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ጋዜጠኛ በሶማሊያ ስላለው ሁኔታ ለሪፖርተር ሲያስረዳ፣ በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ የሰፈነው መንግሥት አልባነት፣ የደኅንነትና የመከላከያ ተቋማት አለመጠናከር መጪውን ጊዜ አስፈሪ ያደርጉታል ይላል፡፡
‹‹ተመልከት እዚህ አገር ውስጥ መንግሥት ምን ማለት እንደሆነ የማያውቅ ወጣት ነው ያለው፡፡ አንድ ሰው ጥቃት ቢደርስበት ወይ ወደ ጎሳው አምርቶ ለበቀል ይዘጋጃል፡፡ አሊያም ራሱ በቀሉን ያከናውናል፡፡ ጥፋተኛውን አካል ለፍርድ ማቅረብ የሚባል አስተሳሰብ የለም፡፡ ስለሆነም ይህን አስተሳሰብ በሶማሊያውያን ወጣቶች ዘንድ ለማስፈን ዘለግ ያለ ጊዜ ይወስዳል፤›› በማለት በአገሪቱ ያለውን ችግር ሥር መስደድ ያብራራል፡፡
በተጨማሪም ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ሶማሊያውያን መጪው ጊዜ መልካም ነገር እንደሚያመጣላቸው ቢያስቡም፣ የአልሸባብ የአጥፍቶ መጥፋት ስትራቴጂ ነገሮችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳደረጉት ይገልጻሉ፡፡
የሶማሊያን የእርስ በእርስ ጦርነት በቅርበት ከሚከታተሉና የተለያዩ ክስተቶችን በሥፍራው ተገኝቶ ለማየት ዕድሉን ካገኙት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ እንግሊዛዊው ጀምስ ፈርጉሰን ሲሆን፣ አልሸባብ የውጊያ ስትራቴጂ ለውጥ ማድረጉ በሶማሊያ ያለውን አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የማስፈን ሥራ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻል፡፡
‹‹አልሸባብ የውጊያ ስትራቴጂውን ከመደበኛ ውጊያ ወደ የታሊባን ዓይነት የሽምቅ የውጊያ ሥልት ቀይሯል፤›› በማለት የአልሸባብን የውጊያ ሥልት መቀየር አንደኛው የነገሮች መወሳሰብ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል፡፡
በአገሪቱ በተለይም በሞቃዲሾ ያለው ሁኔታ አስፈሪና አስቸጋሪ ቢመስልም፣ ብዙዎቹ ሶማሊያውያን ምንም እንዳልተፈጠረ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡
ለዚህም ማሳያ በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች የሚታዩት የሆቴል ግንባታዎች ሲሆኑ፣ ተከፍተው አገልግሎት የሚሰጡት ሆቴሎች ከአልሸባብ የቦምብ ጥቃት ጋር ተፋጠው ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሆቴሎች ቢያንስ አንድ ጊዜ የቦምብ ጥቃት ሲደርስባቸው ሁለት ሦስት ጊዜ ጥቃት የደረሰባቸው ሆቴሎችም ይገኛሉ፡፡
ለሦስት ጊዜያት ያህል የቦምብ ጥቃት የደረሰበት አንዱ ሆቴል ጀዚራ ፓላስ ሆቴል ሲሆን፣ ይህ ሆቴል የተለያዩ አገሮች ኤምባሲ መገኛም ነው፡፡
በሆቴሉ ውስጥ ኤምባሲያቸውን ከከፈቱ አገሮች መካከል ብሩንዲ፣ ግብፅና ኳታር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሦስተኛው አደጋ ከመድረሱ በፊት የቻይና ኤምባሲም መገኛው እዚሁ ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ለሦስተኛ ጊዜ ሕንፃው ላይ በደረሰው ጥቃት ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ወድሞ የነበረ ስለሆነ፣ ዳግም ተገንብቶ ኤምባሲዎች ቢሮዎቻቸውን እንደገና ቢከፍቱም የቻይና ኤምባሲ ግን ለመመለስ አልደፈረም፡፡
ወደ ሆቴሉ ለመግባት ከሆቴሉ በግምት ሦስት ወይም አራት መቶ ሜትሮች ጀምሮ ከፍተኛ ፍተሻ የሚከናወን ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ሦስት ከፍተኛ ቁጥጥርና ፍተሻ የሚካሄድባቸው የፍተሻ ኬላዎችን ማለፍ ግድ ይላል፡፡
አሚሳምና ሶማሊያ
ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተውጣጣውና በአፍሪካ ኅብረት የተሰየመው አሚሶም፣ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት ዓላማው አድርጐ የተዋቀረ የሰላም አስከባሪ ኃይል ነው፡፡
አሚሶም ሶማሊያ ከገባ በኋላ በአልሸባብ ተይዘው የነበሩ ቁልፍ ቦታዎችን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገ ሲሆን፣ ይህም አልሸባብን ለከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደዳረገው ይገለጻል፡፡
ምንም እንኳን አሚሶም በሶማሊያ አንፃራዊ ሰላም መስፈን ከፍተኛውን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ ቢሆንም፣ ተልዕኮውን እንደ ወረራ በመቁጠር በጥላቻ የሚመለከቱት ሶማሊያውያን አሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ድረ ገጾች አስተያየቶችን የሚያሰፍሩ ሶማሊያውያን፣ አሚሶም በሶማሊያ መቆየት የሚፈልገው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ሳይሆን የየአገሮቹን ጥቅም ለማስከበር ነው፡፡ ወታደሮቹም መቆየት የሚፈልጉት የሚከፈላቸው ደመወዝ በየአገራቸው ከሚከፈላቸው ደመወዝ የተሻለና ከፍተኛ በመሆኑ ነው በማለት የአሚሶምን አስተዋጽኦ ይሞግታሉ፡፡
በአንፃሩ ደግሞ አሚሶምን የሚያመሰግኑና የሚያወድሱ፣ እንዲሁም የአገሪቱ የመከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት ተጠናክረው በእግራቸው እስኪቆሙ ድረስ የአሚሶም ዕርዳታ ወሳኝ እንደሆነ የሚከራከሩም አሉ፡፡
እንዲህ ዓይነት ሙግቶች በሶማሊያውያን ዘንድ የሚደመጡ ቢሆንም፣ የተልዕኮው ልዩ ልዑኩ ሞዛምቢካዊው አምባሳደር ፍራንሲስኮ ማዴራ አሚሶም ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት እንዳለበትና ለወታደሮቹ ደመወዝ መክፈል እንኳን አለመቻሉን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ግጭቶችና ሰብዓዊ ቀውሶች መከሰት የምናገኘውን ዕርዳታ ቀንሶብናል፡፡ ይብዛም ይነስም የበጀት ምንጫችን አንድ ዓይነት ነው፡፡ አሁን የተፈጠረው ዓለም አቀፍ ቀውስ ተፅዕኖውን አሳርፎብናል፡፡ ስለሆነም የተለያዩ ሥልቶችን የሚጠቀመውን አልሸባብን ለመቋቋም የሚያስችሉ በቂ ቁሳቁስ የሉንም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
አሚሶም አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ የሚፈልጉ ሶማሊያውያን እንዳሉ ሁሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ እንዲቆይ ከሚፈልጉት አንዱ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት የ65 ዓመቱ መሐመድ መሐሙድ አባቡን ሲሆኑ፣ ‹‹አሚሶም ላደረገልን ነገር ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ ሕይወታቸውን ላጡትም ሐዘኔን እገልጻለሁ፡፡ አሚሶም በዚህ አገር ምንም አልሠራም የሚሉት ለአልሸባብ ስሱ የሆኑ ናቸው፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡
‹‹እኔ በሥርዓትና በመንግሥት ሥር መኖር ነው የምፈልገው፡፡ ሥርዓት አልበኝነትን አልፈልግም፡፡ ስለሆነም ሥርዓት እንዲሰፍን አሚሶም የሚያደርገው ጥረት የሚያስመሰግንና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤›› በማለት ያሰምሩበታል፡፡
በ1983 ዓ.ም. ከሥልጣን በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱት ዚያድ ባሬ ናቸው፡፡ የዚያድ ባሬን መንግሥት መውደቅ ተከትሎ አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታለች፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት በመፍረሱ ምክንያት የጦር አበጋዞችና የጐሳ መሪዎች አገሪቱን ለሁለት አሠርት ዓመታት ወደፈለጉት አቅጣጫ ሲዘውሯት ነበር፡፡
በአገሪቱ የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ሶማሊያ መንግሥት አልባ አገር በመሆን፣ ለተለያዩ ጽንፈኛ ኃይሎች መፈልፈያ ሆና ስታገለግል ነበር፡፡ በተጨማሪም የምዕራባውያን የውክልና ውጊያ ማዕከልም ነበረች፡፡
በአሚሶም የሚመራው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ሶማሊያ ከገባ ጀምሮ አገሪቱ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባት ቢመስልም፣ አሁንም ግን በተለይ ከጎሳ ውክልና ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች በአገሪቷ ላይ የተጋረጡ ከባድ ፈተና ናቸው፡፡
ከእርስ በርሱ ጦርነት መክሰም በኋላ ሶማሊያውያን በአገራቸው እ.ኤ.አ. በ2012 ምርጫ አካሂደው ሥልጣን ላይ ያስቀመጡት ማዕከላዊ መንግሥት ቢኖርም፣ በመንግሥት ዘንድም የጐሳ ውክልና እንዲሁ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡
የፊታችን መስከረም በሶማሊያ ምድር ሁለተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄድ ስለሆነ፣ የምርጫው ውጤት ለሶማሊያውያን ምን ይዞ እንደሚመጣ በሒደት የሚታይ ይሆናል፡፡
በድህነትና ባለመረጋጋት በተደጋጋሚ ስሟ የሚነሳው ሶማሊያ ከዚህ ስያሜ ራሷን ነፃ የምታወጣው መቼ ነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሲሆን፣ የአብዛኛዎቹ ሶማሊያውያን ህልምና ምኞትም ይኼው ነው፡፡ ይህ ህልምና ምኞት መቼ ዕውን ይሆን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ግን በእርግጠኝነት መናገር እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡
- ነአምን አሸናፊ’s blog
- 786 reads