Wednesday, 11 May 2016 12:37
በኢህአዴግ ብቻ እውቅና የተሰጠው የፕሬስ ነጻነት፣ መሬት ላይ ያለው እውነታ
እንደዛሬው የመገናኛ ብዙሃን ባልተስፋፉበት ዘመን አገረ ገዥዎች ከሚገዙት ህዝብ ላይ ያለውን ስሜት ለማወቅ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነበረ ይባላል። ይህ ዘዴ ደግሞ “እረኛ ምን አለ?” የሚል መጠይቅ እንደነበረ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር ይሰማል። ምክንያቱም እረኞች ማታ ቤታቸው ሲቀመጡ ከአሳዳሪዎቻቸው ወይም ከቤተሰቦቻቸው የሚሰሟቸውን ብሶቶችም ሆኑ ድሎቶች ቀን ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ በዜማ ያንጸባርቁት ስለነበረ ነው አገረ ገዥዎቹ የእረኛን ዜማ ትኩረት ሰጥተው የሚያዳምጡት ከእረኛው ዘፈን ላይ ምሬት ከሰሙ ለመስተካከል ድሎት ከበዛ ደግሞ ለመደሰት።ዛሬ እንደድሮው አይነት የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ቀርቶ ዓለም በቴክኖሎጂ አማካኝነት አንድ መንደር ሆናለች። በዚህም ምክንያት ከልዕለ ሀያሏ አሜሪካ እስከ ትንሿ ደቡብ ሱዳን ወይም እስከ ሰሜን ኮሪያ ባሉ ቤተመንግስታት ግቢ ውስጥ የተደረገ ድርጊት ሳይውል ሳያድር ለዓለም ህዝብ ይዳረሳል። ልክ እንደዜናው ለዓለም መዳረስ ሁሉ የአገራትና የመንግስታት ወይም የህዝቦች ተሞክሮም ከአንዱ ወደ ሌላው ለመተላለፍ የሰከንዶች ቢበዛ የደቂቃዎች እጅግ ቢበዛ ደግሞ የሰዓታት ጉዳይ እንጂ ከዚህ የዘለለ ጊዜ አይፈጅበትም። ለዚህ ደግሞ ቁልፉ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ መለዋወጫ መንገድ የሆነው የኢንተርኔት መስፋፋት ነው።
በኢኮኖምም ሆነ በትምህርትና በዴሞክራሲ የዳበሩ መንግስታት መገናኛ ብዙሃንን በሚገባ ይጠቀሙባቸዋል። በመገናኛ ብዙሃን በሚገባ ከመጠቀማቸውም በላይ ተገቢውን ሕጋዊ ከለላ እና ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። በተቃራኒው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ዴሞክራሲን መተግበር ያልቻሉት አገራት መንግስታት ግን መገናኛ ብዙሃንን በጥርጣሬ የሚያዩ ሲሆን አለፍ ሲልም ልጓም አበጅተው በተሰጣቸው ልጓም መሪነት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋሉ። አፈና እና እስርም ለመገናኛ ብዙሃኑ ባለቤቶችና ዋና አዘጋጆች የተዘጋጀላቸው ድግሶች እስኪመስሉ ድረስ የወህኒ ደጆችን መርገጥ የዘወትር ይትባህላቸው ሆኗል። በቅርቡ እንኳ የግብጽ መንግስት በስምንት ጋዜጠኞች ላይ የሞት ፍርድ መፍረዱ አንዱ የአንባገነን መንግስታት በመገናኛ ብዙሃን ላይ ያላቸውን አቋም ማሳያ ሊሆን ይችላል።
ባሳለፍነው ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፊንላድ ዋና ከተማ ሄልሲንኪ የተከበረው የነጻ መገናኛ ብዙሃን ቀንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግስትም በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አማካኝነት በዓሉን አክብሮ ውሏል። በበዓሉ ላይም በርካታ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃንን የሚመሩ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ቁጥራቸው እጅግ በጣም ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ የነጻው ፕሬስ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ስለፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ ያለውን ገጽታ በተመለከተ የተለያዩ ምንጮችን ተጠቅመን ያዘጋጀነው ሀተታ በዚሁ መልኩ ቀርቧል።
ፕሬስ በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ እና መገናኛ ብዙሃን ትውውቃቸው 100 ዓመት ያልበለጠ ሲሆን በእነዚህ ዓመታትም ዘርፉ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ እዚህ ደርሷል። አብላጫውን ጊዜ የጨረሰውም የገዥዎችን ፍላጎት ሲያስተጋባ ሲሆን በጀቱም ከመንግስታቱ ካዝና የሚወጣ ነበር። በዚህም ምክንያት የአንድ ወገንን ሀሳብ ብቻ የሚያስተናግድ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ የነበረው ሚና እዚህ ግባ የሚባል ነው ማለት አይቻልም።
የወታደራዊ መንግስቱን በነፍጥ የገለበጠውና አገሪቱን ላለፉት 25 ዓመታት ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር እየገዛ ያለው ኢህአዴግ የአራት ኪሎውን ቤተ መንግስት እንደተቀበለ ከወሰዳቸው ውሳኔዎች መካከል በአገሪቱ የነጻው ፕሬስ በተለይም የህትመት ወጤቱ እንዲስፋፋ መፍቀድ እና ቅድመ ምርመራ (ሴንሰር ሺፕ) እንዲቀር ማድረግ ነበር። ይህን ተከትሎም በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የህትመት ውጤቶች እየታተሙ ለአንባቢያን መድረስ ጀመሩ። ከሽግግር መንግስቱ ቻርተር ጀምሮ የነጻነት በሩ ገርበብ ብሎ ተከፍቶላቸው የነበሩት እነዚህ የህትመት ውጤቶች የኢህአዴግ መንግስት በ1987 ዓ.ም ባወጣው ህገ መንግስትም በአንቀጽ 29 የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት አወጀ። ይህን አንቀጽም በሌላ የህገ መንግስቱ ክፍል (አንቀጽ 9) ህገ መንግስቱ የአገሪቱ የበላይ ህግ ነው ሲል ለፕሬስ ነጻነት የሰጠውን መብት እውቅና ገለጸ። በህገ መንግስቱ መሰረትም በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ የሚወጡ ህጎችና አዋጆች ከህገ መንግስቱ የሚጣረሱ ከሆነ ውድቅ ይደረጋሉ ይላልና።
የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ
በኢህአዴግ ህገ መንግስት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 2 “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው። ይህ ነጻነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሁፍ ወይም በህትመት በስነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም አይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችንያካትታል” (ሰረዝ የተጨመረ) ሲል ይደነግጋል። ህገ መንግስቱ ለፕሬሱ ይህን ያህል ነጻነት የሰጠው ቢሆንም ከህገ መንግሰቱ መጽደቅ በኋላ የወጣው “የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ” ግን የመገናኛ ብዙሃኑን (በተለይም የነጻውን ፕሬስ) በነጻነት የማያሰራ መሆኑን በርካታ ምሁራን አንስተው አዋጁን ይተቻሉ። በአዋጁ ክፍል አራት አንቀጽ አንድ (ሀ) ላይ ስለ ህትመት ውጤት ዋና አዘጋጅና ምክትል ዋና አዘጋጅ ሲገልጽ “በመገናኛ ብዙሃን በቀረበ ፍሬ ነገር ዘገባ መልካም ስሙና ክብሩ የተጎዳበት ማንኛውም ሰው ዘገባው በቀረበበት መገናኛ ብዙሃን ላይ ያለ ክፍያ መልስ የመስጠት መብት አለው” ይልና የፕሬሱን ዋና አዘጋጅና ምክትል ዋና አዘጋጅ ግዴታ ሲጠቅስም “ዋና አዘጋጅ ወይም ምክትል ዋና አዘጋጅ የተላከለትን ምላሽ ዕለታዊ ጋዜጣ ከሆነ በሶስት ቀን ውስጥ ሳምንታዊ ጋዜጣ ከሆነ ደግሞ በዘጠኝ ቀን ውስጥ ወይም በሌላ አይነት ህትመት ከሆነ በቀጣይ እትም ያለእርማት የማውጣት ግዴታ አለበት” ሲል ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ ደግሞ የፕሬሱን ስራ በነጻነት የመስራት መብቱን ይነፍጋል ሲሉ ነው የሚተቹት።
ኢህአዴግ የአገሪቱን ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የፕሬስ ነጻነት በኢትዮጵያ መረጋገጡን በህገ መንግስቱ እውቅና መስጠቱን ቢገልጽም ከፕሬስ አዋጁ በተጨማሪ መሬት ላይ ባሉት እውነታዎች ግን ፕሬሱ ነጻነቱን መንፈጉን እንጂ ነጻነት አለመጎናጸፉን ያሳያል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በማስረጃነትም በአሁኑ ሰዓት እስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኞችን (እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎችም) በማንሳት ይከራከራሉ።
ኢህአዴግ የፕሬስ ነጻነት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የሚጫወተውን ሚና ሲያወሳ “የፕሬስ ነጻነት ለሀገራችን መሰረታዊ የልማትና የዴሞክራሲ እድገት መሳሪያ ነው። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያለፕሬስ ነጻነት ሊገነባ እንደማይችል እሙን ነው። የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ በአግባቡ ለመገንባት የፕሬስ ሚና የሚተካ አይደለም” ሲል ደጋግሞ ይናገራል።
ኢህአዴግ እንዲህ ቢልም በተለይ በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ሶስተኛው ዙር (ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ) አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ የህትመት ውጤቶች አዘጋጆችንና ባለቤቶችን በተለያዩ ወንጀሎች በመክሰስ ለእስር ዳርጓቸው እንደነበረ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ለእስር ከተዳረጉት የነጻው ፕሬስ ባለቤቶች መካከል አሁን እስር ላይ ያለው እስክንድር ነጋ ከእነ ባለቤቱ ይገኙበታል። እስክንድር ነጋም ሆነ ባለቤቱ ሰርካለም አሰፋን ጨምሮ ሌሎች የነጻው ፕሬስ ተዋንያን በይቅርታ ከእስር መፈታታቸውም ይታወሳል።
ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ከማድረግ ይልቅ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብቧል ተብሎ ከሚተችባቸው ምክንያቶች አንዱም ከላይ የተጠቀሰው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነትን የሚደነግገው አዋጅ ነው። በዚሁ አዋጅ መንግስት ከፍተኛ የመረጃ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ከመንግስት የሚገኙ መረጃዎችን የመገናኛ ብዙሃን ለማግኘት የግድ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተብለው የተሾሙ የመንግስት ባለስልጣናትን ደጅ መጥናት ግድ ሆኖባቸዋል። መንግስት በየመስሪያ ቤቱ የኮምዩኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተብለው የተሾሙ የመንግስት ካድሬዎች ደግሞ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃኑ ሲሰጡ ከመንግስት ወገን የሆኑትን በመለየት ወይም ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ብቻ ለይተው ይሰጣሉ። ይህም ባለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት በተጨባጭ ታይቷል። በዚህ መዋቅር ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ፕሬስም ነጻነቱ የቱ ላይ ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳበት ያደርጋል።
የመረጃ ብዝሃነት በኢትዮጵያ
ኢህአዴግ ያቋቋመው መንግስት በ1987 ዓ.ም ባወጣው ህገ መንግስት አንቀጽ 29 ቁጥር 5 ላይ “በመንግስት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል” (ሰረዝ የተጨመረ) ይላል። የህገ መንግስቱ ክፍል በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ መገናኛ ብዙሃን ብሎ የጠራቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን እንዲያስተናግዱ የደነገገ ቢሆንም በተደጋጋሚ ጊዜ የሚታየው ግን ከኢህአዴግ ውጭ የሌሎች ፓርቲዎችንም ሆነ ከኢህአዴግ የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ ምሁራንን ሀሳብ ተቀብለው በነጻነት ሲያስተናግዱ አይታዩም። ለዚህ ሀሳብ ማጠንከሪያ የሚሆነው ደግሞ በምርጫ ወቅት የሚሰሩ ዘገባዎችን እና የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የምስረታ ክብረ በዓላቸውን በሚያከብሩበት ወቅት የሚታየው የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ለሌሎች ፓርቲዎች ሲተገበር አለመታየቱን ነው አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች የሚያነሷቸው።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እነዚሁ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች በፕሮግራሞቻቸውና በዘገባዎቻቸው ከመንግስት ፍላጎት ውጪ ያሉ ሀሳቦችን የማያስተናግዱ መሆናቸውን ከሚያረጋግጡ ሁነቶች መካከል አንዱ ሚያዝያ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ለንባብ የበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ ነው። ጋዜጣው በዕለቱ “አጀንዳ” በሚለው አምዱ ስር “የፕሬሱ አካሄድ እንዲታረም እሻለሁ” በሚል ርዕስ የግል መገናኛ ብዙሃንን የተቸበትን ጽሁፍ እናገኛለን። ጋዜጣው “ሕገ-መንግስት ለፕሬሱ ልዩ ጥበቃ አድርጓል። ያለ መታደል ሆኖ በሀገራችን የበቀለው የግል ሚዲያ ይህንን ነጻነት ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞ የህብረተሰቡን የመረጃ ፍላጎት ማርካትና በህብረተሰቡ ውስጥ የተጋ የመረጃ ልውውጥ እንዳይደረግ የሚሰራ እና ይልቁንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስራ በይበልጥ እየሰራ የሚገኝ መሆኑ ነው ችግሩ” ሲል ነው የተቸው።
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከአንድ ፓርቲ አስተያየት ያልዘለለ ሀሳብን ብቻ የሚያስተናግዱ በመሆናቸውም በአገሪቱ የመረጃ ብዝሃነት አለ ብሎ መናገር እንደማይቻል በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው።
የዓለም አቀፍ ተቋማት መግለጫ
በቅርቡ በወጣ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ከታፈነባቸው ውስን አገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት ሲል አስታውቋል። በጥናቱ ከተካተቱት አገራት መካከልም የኢትዮጵያ ደረጃ አስፈሪ መሆኑን አመልክቷል። ይህን የዓለም አቀፍ ጥናት ሪፖርት ግን የኢህአዴግ መንግስት አይቀበለውም። “በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ መቅሰፍት ነው” ሲልም ያስተባብላል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከአስር ወራት በፊት አውጥቶት በነበረው ሪፖርት በወቅቱ 17 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ገልጾ በርካቶች ደግሞ ከአገር መሰደዳቸውንም አውስቷል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት (ሲፒጄ) በበኩሉ ከአምስት ወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት “ከአፍሪካ ጋዜጠኞችን በግፍ ከሚያስሩ አገራት መካከል ኢትዮጵያ በሶስተኛ ደረጃ ትገኛለች” ያለ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት ከታሰሩት መካከልም የቀድሞው የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቴሌቪዥን ዜና አንባቢ የነበረው ፈቃዱ መርካና ይገኝበታል።
ስንደቅ