በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የቆየውን ስብሰባ መነሻ በማድረግ፣ አዲስ አበባ የሚገኘው አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያሰራጨው አስገራሚ መግለጫ አፍሪካ ከሁለት አሥርት በፊት ከነበረችበት ይልቅ አሁን ደህይታለች ብሏል፡፡

የኮሚሽኑ መግለጫ ይፋ እንዳደረገው በሌላው ዓለም ያሉ ለውጦች እንደሚያሳዩት ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የድህነት ደረጃዎች መሻሻል ቢያሳዩም በአፍሪካ ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡

      የኮሚሽኑ የአፍሪካ ማኅበራዊ ልማት ጠቋሚ (አፍሪካን ሶሻል ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ) የተባለው ጥናት ሪፖርት አረጋግጧል በተባለው መሠረት ከሆነ፣ በአፍሪካ ለተንሰራፋው ድህነት፣ በሕዝቦች መካከል በተፈጠሩ የኑሮና ሌሎች መሠረታዊ ልዩነቶች ትልቁን ድርሻ ወስዷል፡፡ በመሆኑም ሴቶች፣ ወጣቶችና በገጠር የሚኖሩ ሕዝቦች ከፍተኛው የሰብዓዊ መገለል ገፈት በመቅመስ ለድህነት ሰለባ ሆነዋል፡፡

      ትኩረቱን በደቡባዊ አፍሪካ አገሮች ላይ ያደረገው የኮሚሽኑ ሪፖርት ስምንት አገሮችን ማለትም አንጎላን፣ ቦስትዋናን፣ ማላዊን፣ ሞሪሺየስን፣ ናሚቢያን፣ ስዋዚላንድን፣ ዚምባብዌንና ዛምቢያን የትኩረት አቅጣጫው መዘወሪያ አድርጓቸዋል፡፡

ምንም እንኳ እንደየአገሮቹ ሁኔታ ልዩነት ቢታይም፣ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚታየው ሁሉንም ሰዎች የማያካትት የልማት አካሄድ ጉልህ እንደሆነ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ለአብነትም በቦትስዋና በገጠርና በከተማ ነዋሪዎች መካከል የሚታየው የኑሮ ልዩነትና ሰዎች ከልማት ተጠቃሚነት አኳያ ያላቸው ተካቶነት ከፍተኛ መሆኑን ሪፖርቱ ማሳየቱን ኮሚሽኑ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ አልተካቶነት ዋናው መዘውር የሥራ አጥነት ችግር ነው ብሏል፡፡ በተመሳሳይም በዛምቢያና በማላዊም በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች መካከል ከፍተኛ የኑሮና የልማት ተጠቃሚነት ልዩነቶች ከፍተኛ ሆነው ከመታየታቸውም ባሻገር፣ በወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር ሳቢያ የታየው ልዩነት መባባሱም ታይቷል፡፡

ሴቶች በተለይም ልጃገረዶች ክፍያ በማይታሰብባቸው የክብካቤ ሥራ መስኮች ላይ ለመሰማራት እንደሚገደዱ፣ ከተከፈላቸውም እጅግ ዝቅተኛውን ገንዘብ እንደሚያገኙ፣ ካላቸው የትምህርት ደረጃ በወረደ መልኩ ከወንዶች ይልቅ ክህሎትና ዕውቀት በማይጠይቁ ዝቅተኛ ሥራዎች ውስጥ ለመሰማራት እየተገደዱ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ይህ ለድህነት መባባስ አንዱ መገለጫው ሲሆን፣ በገጠር አካባቢ ላለው መገለል ደግሞ ሰዎች ከከተሞች አኳያ የሚኖሩበት ርቀት አንዱ መንስዔ ተደርጓል፡፡ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች መሠረታዊ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች ተጠቃሚ ካለመሆናቸውም ባሻገር፣ የጤናና የአካባቢ ጉዳት በሚያስከትሉ የአኗኗር ሁኔታዎች ውስጥ ለማለፍ ይገደዳሉ፡፡ በርካታ እንስቶች ለብዝበዛና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለመፈጸም እንደሚገደዱም ጥናቱ አስፍሯል፡፡ ከተሞችም ቢሆኑ ችምችም ባሉና ለኑሮ በማይመቹ ጎስቋላ መንደሮች ውስጥ እንዲኖሩ የሚገደዱ በርካቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መግለጫ መሠረት በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ለሚታየው ድህነት መባባስ ትልቁን ድርሻ በመያዝ ተወቃሽ የተደረገው የሰዎች ከልማት፣ ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከፖለቲካዊ፣ ከተቋማዊ እንዲሁም ከባህላዊ ተፅዕኖዎች በሚመነጩ መገለሎች በርካቶች በድህነት እንዲያነክሱ መገደዳቸውን ሪፖርቱ አመላክቶ፣ በዚህ ሳቢያ በአፍሪካ ከ20 ዓመታት ወዲህ የባሰ ድህነት እየታየ መምጣቱንና በርካቶችም በእነዚህ ጊዜያት ከነበረው ድህነት ይልቅ የከፋ ድህነት ውስጥ ለመኖር መገደዳቸውን አሳይቷል፡፡