Wednesday, 11 May 2016 12:31

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ አሁን ባለው ሁኔታ እድልም ስጋትም ሊሆን ይችላል

በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ እየጣለ ያለው ዝናብ በቀጣይ ወደ ጎርፍ የሚቀየርበት ሁኔታ እንደሚኖር የሜትሮሎጂ ትንበያዎች አመልክተዋል። ያለፈው አመት የዝናብ ሁኔታ ከሚጠበቀው መጠን በላይ ያነሰ በመሆኑ በርካታ ዜጎች ለድርቅ ተጋልጠው የመንግስትንና የረድኤት ድርጅቶችን እጅ መጠበቅ ግድ ሆኖባቸው ቆይተዋል። የተዘራው ዘር በሀሩር ፀሀይ ተቃጥሎ ቀርቷል። ባህሩና ወንዙ በመድረቁ ለሚጠጣ ውሃ ሳይቀር በቦቴ ማመላለስ ግድ ሆኖ ቆይቷል። የመንግስት የውሃ ስራዎች በየቦታው ለከርሰ ምድር ውሃን ቁፋሮ ሲሯሯጡ ታይቷል። በዚህ መሃል ግን በድንገት የአየሩ ሁኔታ ተቀይሮ በመላ ሀገሪቱ በሚያስብል ደረጃ ከፍተኛ የዝናብ መጠን በመጣል ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ለህዝቡም ሆነ ለመንግስት ተስፋም ስጋትም ሆኖ እየታየ ነው።

ውሃ የነጠፉ መሬቶች ውሃ እስኪተፉ መረስረሳቸው፣ ሳርና ዛፎች መለምለማቸው፣ ወንዞችና ኩሬዎች ውሃ መሙላታቸው ብሎም ገበሬውን ከእጅ ጠባቂነት እንደዚሁም ከብቱ ከድርቅ እልቂት መዳኑ ትልቅ ተስፋ ነው።አሁን ባለው የዝናብ ይዞታ ገበሬው ለእለት ጉርሱ የሰው እጅ ከመጠበቅ ይልቅ ቢያንስ ድንችና ጎመን በመሳሰሰሉ የጓሮ አትክልቶች ራሱን እየደጎመ ይቆያል። መንግስትም ቢሆን የእለት ምግብን በየጎጡ ለማቅረብ የሚያወጣውን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ እንደንሚቀንስለት ጥርጥር የለውም።

ክቡር የሆነው የሰው ልጅ በረሃብ አለጋ እንዳይቀጣ ብሎም ህይወቱ እንዳያልፍ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለእርዳታ እህል ግዢ ሲወጣ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ቀላል አይደለም። ከግዢ ባለፈ የቀለብ እህሉን ከወደብ እስከ ቀለብ ማከፋፈፊያ ቀበሌና የገጠር ጎጥ ድረስ ለማድረስ ከፍተኛ የሆነ ሎጂሰትክስን ማንቀሳቀስን ጠይቋል።

መንግስት ከእለት ተዕለት ስራው በሻገር አብዛኛው መዋቅሩን ለዚሁ የእለት ደራሽ ስራ ሲጠቀም ቆይቷል። ከዝናቡ ጋር በተያያዘ አሁን ያለው የእለት ተዕለት የረድኤት ስራ ቀስ በቀስ እየቀነሰ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም። ይህ ለመንግስትም ሆነ ለሀገሪቱ ታላቅ እፎይታ ነው።  በመልካም እድልነቱም የሚታይ ነው።  በሌላ አቅጣጫ ደግሞ አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ በቀጣይም እየከበደ የሚሄድ በመሆኑ በየአካባቢው ከባድ ጎርፍ የሚያስከትል መሆኑ ከወዲሁ ታውቋል። ይህ በስጋትነት የሚታይ ነው። መንግስት የዝናቡን እድልና ስጋት በመለየት እድሉን በመልካምነት፤ ስጋቱን ደግሞ በቂ የቅድመ መከላከል ዝግጅትን በማድረግ  ቢቻል ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ማስቀረት፤ ያ ካልሆነ ደግሞ መቀነስ መቻል አለበት።

በጎርፍ ሊጠቁ የሚችሉ የየክልሉ ወረዳዎች ተለይተው የታወቁ ናቸው። የዝናቡ ሁኔታ እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር የወንዝ ሙላት የሚጠበቅ ነው። በዚህ ወቅት ዜጎች በውሃ ሊከበቡ ይችላሉ። መንገዶች የማይሰሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። እገዛው ምን አልባትም ሄሊኮፕተር ሳይቀር ሊጠይቅ ይችላል። የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን በመጠለያ ማሰባሰብ ሊጠይቅ ይችላል። እነዚህ ሁሉ ሰፊ የሆነ ቅድመ ዝግጅትን የሚጠይቁ ናቸው። በመሆኑም መንግስት ድርቁ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ርብርብ ከዝናቡ ጋር በተያያዘ መልካም እድልና ሰጋት ብሎ በለያቸው አቅጣጫዎች ላይ ትኩረቱን ሊያደርግ ይገባል።

ስንደቅ

Leave a Reply