Saturday, 14 May 2016 14:02
Written by  በይትባረክ ዋለልኝ
(yetebarek@yahoo.com)

“የአዲስ አበባ ልጅ” – አድናቆት እየተቸረው ነው

“የአዲስ አበባ ልጅ” - አድናቆት እየተቸረው ነው

ውብ ሃሳብ ከድንቅ የጥበብ ስራ ጋር የተሞሸሩበት አውደ ርዕይ
• “መዝገቡ በዲሲፕሊን ተግቶ የሚሰራ ሰዓሊ ነው” – ረ/ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን“እንዲህ አይነት

“እንዲህ አይነት ሰዓሊ  ስንት አንድ ነው የሚገኘው” – ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ

የዝነኛው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ “የአዲስ አበባ ልጅ” የተሰኘ የስዕል አውደርዕይ ባለፈው ረቡዕ በብሔራዊ ሙዚየም በደማቅ ስነስርዓት ተከፍቷል። ባለፈው “ንግስ” የተሰኘ  አውደ ርዕይ ላይ የቀረቡትንና በተመልካች ይደገምልን የተባሉትን 12 ስዕሎችንና 8 አዳዲስ የስዕል ስራዎችን አካትቶ በጠቅላላ 20 ግዙፍ የስዕል ስራዎቹን ለዕይታ አብቅቷል፡፡ በአውደ ርዕዩ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ ከተገኙ ተመልካቾችና አንጋፋ የጥበቡ ባለሙያዎች መካከል ጥቂቶቹ በሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ ሥራዎች ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡኝ ጠይቄ ነበር፡፡
በሙዚየሙ ያገኘሁት የህግ ባለሙያው ሔኖክ ከናፍር እንዲህ አለኝ፤ “የሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ “ንግስ” የተሰኘ በ2006 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም የቀረበውን የስዕል አውደ ርዕይ በእየቀኑ እየተመላለስኩ ነው የተመለከትኩት፡፡ በእውነት ስዕሎቹን ስመለከት ሌላ ስሜት ውስጥ እገባለሁ። በተለይ “ንግስ” የተሰኘውን ግዙፍ ስራ ሳይ በየቀኑ አለቅስ ነበር፡፡ ለምን እንደማለቅስ ለራሴም አይገባኝም፤ ብቻ የመዝገቡ ስራዎች ለእኔ የተለዩ ናቸው፡፡ የአሁኖቹ ደግሞ የሚገርሙ ናቸው፡፡”
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የስነጥበብ ት/ቤት መምህርና ሰዓሊ የሆነው ጌታሁን አሰፋ የነገረኝ የሄኖክን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ “ባለፈው ኤግዚቢሽኑ ላይ እኔ በአይኔ ያየሁትን ልንገርህ፤ ኤግዚቢሽኑን ለመመልከት የሚመጣው ሰው ከደስታ የተነሣ እየጮኸ ሲያለቅስ በአይኔ ተመልክቼአለሁ። እኛ ሀገር ይደገም የሚባለው ሙዚቃ፣ ፊልምና ቴአትር ሲሆን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የስዕል አውደ ርዕይ እንዲደገም የተጠየቀው የሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ የስዕል አውደ ርዕይ ብቻ ነው፡፡” ይላል፤ሰዓሊ ጌታሁን፡፡
በመክፈቻው ፕሮግራም ዕለት በተለይ በጥበቡ አድናቂዎች ላይ የተመለትኩት ልክ ሔኖክ እንደገለጸልኝ ያለውን ስሜት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ከስዕል ስራዎቹ ፊት ለረጅም ጊዜ በመደመምና በመደነቅ ስሜት ቆመው ሲመለከቱ አስተውያለሁ፡፡ በዚህም ሰዓሊው ከተደራሲው ጋር በእነዚህ ስራዎቹ አማካኝነት የፈጠረውን ጥብቅ ቁርኝት መመልከት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክርልኝን የዝነኛውን ደራሲ ቶልስቶይን ሐሳብ ልዋስ፡-
“ጥበብ የተለየ ስሜታዊ ትስስር በከያኒውና በተደራሲው መካከል መፍጠር ይኖርበታል፡፡ ይህ ማለት ግልፅ፣ እውነተኛና ጥልቅ ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህ ውበታዊ አቅሙ ከያኒው ውስጡ ያለውን ስሜት ሌሎች እንዲጋሩት፣ እሱ እንደተሰማው እነሱም እንዲሰማቸው ለማድረግ ያስችለዋል፡፡” ይላል ቶልስቶይ፤በከያኒውና በተደራሲው መካከል ስላለው ጥብቅ ግንኙነት ሲገልጽ፡፡ በመዝገቡ “የአዲስ አበባ ልጅ” የስዕል አውደ ርዕይ ላይም ይህን እውነታ ሁኔታ በሚገባ አስተውየዋለሁ፡፡ ለዚህም ነው የስዕል ጥበብ የራሱ የሆነ ጥልቅ ባህሪ አለው የሚባለው፡፡
የመዝገቡ የጥበብ ስራዎች የሰዎችን ነፍስ መግዛት የሚችሉ ናቸው፡፡ ተመልካቹንም የሚያማልሉ፣የሚማርኩ ብሎም ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ አንጋፋው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ይህን ሀሳብ ይጋሩታል፡፡ ስለ ሰዓሊው በሰጡት አስተያየትም፤ “እንዲህ አይነት ሰዓሊ ከስንት አንድ ነው የሚገኘው፤ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ከተባለ መዝገቡ ተሰማ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ ሰዓሊ እሸቱ፤ “የአዲስ አበባ ልጅ ቁ. 1” ስለተሰኘው ስራው ሲገልፁም፤ “የአዲስ አበባ ልጅ የሚለው ስራው ምክንያት አለው፤ ተነስቶ እጁን ዘርግቶ ሰላም የሚል እና የሚጠብቀው ሰው እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ እንደ ተመልካቹ አተረጓጎም ልናየው እንችላለን፡፡ ግን ስራው በሦስት አውታር መጠን 3D የተሰራ ሆኖ፤ አለባበሱን አኳኋኑን፣ ዘመናዊነቱን— የአዲስ አበባ ልጅ ከራሱ ባህል ጋር አነፃፅረን እንድናይ ነው የሰጠን፡፡ ከአዲስ አበባ ልጅ ውጭ ያሉት፤ የገጠሩን ህልማዊ የሆኑ ተራራዎች፣ ትልልቅ አለቶች —- ግሩም አድርጎ ነው የሰራው፡፡ በተለይ እኔ የምወደው “ንግስ” ራሱን የቻለ ታላቅ የጥበብ ስራ ነው” ሲሉ ያወድሱታል፡፡
የሰዓሊውን ወደ አለማቀፍ መድረክ መቅረብ በተመለከተ ተጠይቀውም፤ “የሰዓሊው ስራ መስራት ነው፡፡ የሰዓሊውን ስራ ለህዝብ የማሳወቅ፣ ለዓለም የማድረስ ስራ የሌሎች ባለሙያዎች ኃላፊነት ነው፡፡ አሁንም ጥበቡ ጥሩ ሐያሲ፣ ጥሩ ፀሐፊ ይፈልጋል፤ ጠቢቡ ሁሉን መሆን አይችልም፡፡” ሲሉ መልሰዋል። ይህን የአንጋፋውን የጥበብ ባለሙያ ሀሳብ እራሱ ሰዓሊው መዝገቡ ተሰማ ይጋራዋል፡፡ ሆኖም በእሱም ሆነ በጓደኞቹ እንዲሁም በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሰዓሊዎች ስራ ላይ አተኩረው ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ፣ ሂስ የሚሰጡ ጸሃፊያንና ሐያሲያን  እንደሌሉ ይናገራል፤መዝገቡ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን በበኩሉ ስለ ሰዓሊውና አዳዲስ ስራዎቹ እንዲህ ይላል፡- “መዝገቡ በዲሲፕሊን ተግቶ ብዙ የሚሰራ ሰዓሊና ግሩም መምህር ነው፡፡ የዛሬዎቹ ስራዎች ከቀድሞ ስራዎቹ ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው፡፡ በተለይ ተራሮቹ… ገደሎቹ… ካደገበት ከኖረበት አካባቢ ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ ሐይለኛ ገደሎቹን፤ የሰውን ልጅ ውክልና ወስዶ ዲሲፕሊን ባለው መንገድ የሚሰራ ሰዓሊ ነው። በተለይ የአሁኖቹ ስራዎች የመግዘፍ የመመሰጥ ነገር አላቸው፡፡ ተመልካቹን ስሜት ውስጥ መክተት ብሎም ከፍሬም በመውጣት መግዘፍ ይታይባቸዋል። መዝገቡ ድሮ የጀመረውን የአሣሣል ጥበብ ይዞ፣ በዲሲፕሊን እያሳደገው፣ ግዙፍ እያደረገ የመጣ ሰዓሊ ነው፡፡”
በሦስት አውታር የሰራቸው ስራዎችን በተመለከተ ሰዓሊ በቀለ መኮንን ሲናገር፤ “እንደዚህ የሚሰሩ የሌሎች አገራት ሰዓሊያን አሉ፡፡ ከምን አንፃር እንደሆነ ባለቤቱ የሚለውን ወይ የፃፈውን ማየት ይጠይቃል፡፡ የሰራበትን ፍልስፍና ከእሱ መረዳትን ይፈልጋል” ብሏል፡፡  ከሰዓሊ በቀለ መኮንንና ከሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ጋር ተቀራራቢ የሆነ አስተያየት የሰነዘረው ደግሞ የአለ የስነጥበብ ት/ቤት መምህርና የጉራማይሌ ጋለሪ ባለቤት ሚፍታህ ነው። “የአዲስ አበባ ልጅ” የሚለው ስያሜ አውደ ርዕዩን እንደማይወክልለት የተናገረው ሚፍታህ፤“የአዲስ አበባ ልጅ” የተሰኘውን የጥበብ ስራን ግን እንደሚያደንቅ አልሸሸገም፡፡
“ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ እዚህ ጋ ደርሷል፡፡ በስራዎቹ ላይ ተንታኝ ያስፈልጋል፡፡ ሂስ ያስፈልጋል፤ ከሃይፐርሪያሊዝም አንፃር እነዚህን ነገሮች ተንትኖ የሚያቀርብልን ባለሙያ ሊኖር ይገባል፡፡ ለስራዎቹ ግዘፍ ሰጥቷቸው ከሸራ ውጭ አድርጐ ሲሰራ የሆነ ነገር እየነገረን ነው – ስለ ሐገራችን፣ ስላለን ነገር– ። ስለዚህ በስራዎቹ ዙሪያ ሂስ፣ተንታኝ ያስፈልጋል እላለሁ” ሲል አስተያየቱን ገልጿል – ሚፍታህ፡፡
የመዝገቡን ስራዎች በአማርኛና በተለያዩ ቋንቋዎች የሚተቹ ሐያሲያን፣ ፀሐፊያን  ሊኖሩ ይገባል ግን የሉንም ያሉት ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በበኩላቸው፤መንግስት እንደእነዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖችን እያዘጋጀ ከሐገሩ ባሕል ጋር ማዋሃድ አለበት ብለዋል፡፡
ሰዓሊና መምህር ታደሰ መስፍን፤በመዝገቡ ተሰማ የባለ 3 አውታር (3D) ስራዎቹ በእጅጉ እንደሚደነቅ ይናገራል፡፡ ለሌሎች ሰዓሊዎችም ጥሩ መነቃቃትን ይፈጥራል የሚል ጽኑ እምነት አለው፡፡
“ከሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሦስት አውታር ስራዎች መካከል በተለይ “ገራርታ” የተሰኘው ስራው በግዝፈቱ፤ በቀለም አጠቃቀሙ አስገራሚ ክህሎት የሚታይበት ነው፤ ከፍተኛ ደረጃ  ያለው ስራ እንደሰራ የሚያሳይ ነው፡፡
በዚህ ግዙፍ ስራው ውስጥ ብርሃንና ጥላ ሳይጋጩ ሃርሞናይዝ አድርጎ ማቅረብ መዝገቡ የደረሰበትን ደረጃ በግልጽ ያሳያል፡፡ በጥበቡ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሄደ የሚያመላክትና ሌሎች ሰዓሊዎችንም የሚያነቃቃ ነው፡፡ ሰዓሊ መዝገቡ ይህን ስራ ለመስራት ምን ያህል ለጥበቡ ራሱን እንደሰጠና ዲሲፕሊኑን በሚገባ ያሳያል፡፡ እነዚህን ስራዎቹን በራሱ መንገድ ስላሳደጋቸው ለማንኛውም ሰዓሊ ጥሩ ማነቃቂያዎች ናቸው፡፡” ይላል ሰዓሊ ታደሰ መስፍን፡፡
ሰዓሊና መምህር ጌታሁን አሰፋም በመዝገቡ የባለ 3 አውታር ስራዎቹ በእጅጉ ተደምሟል። “መዝገቡ ባለፈው ካሳየን የምርምር ስራዎቹን ከፍ በማድረግ፣ የተለየ ነገር በመጨመር ማሳደጉን የአዲስ አበባ ልጅ በሚለው ስራው ላይ በሚገባ አሳይቷል። ይህ ጥናትና ምርምሩን በደንብ እያበሰለው መምጣቱን ነው የሚያረጋግጠው፡፡ ክህሎቱም የሚገርም ነው፡፡ በእውነት እኛ እድለኞች ነን፤አዳዲስ ነገሮችን እየጨመረ ሰርቶ ለመመልከት በመቻላችን” ብሏል፤ ሰዓሊና መምህር ጌታሁን፡፡
ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤በዚህ የስዕል አውደ ርዕዩ፣ እንደ ትላንቱ ሁሉ የጥበቡን ባለሙያዎችና የጥበቡን አፍቃሪዎች ማስደመሙን ቀጥሏል፡፡ በስዕል አውደ ርዕይ ታሪክ ህዝብ እንደ ጎርፍ ስዕል ለመመልከት ሲመጣ ያየሁት፣ በመዝገቡ የጥበብ ስራዎች አውደ ርዕይ ላይ ብቻ ነው፡፡
“የአዲስ አበባ ልጅ” ለአንድ ወር ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ ለ30 ቀናት በመዝገቡ ስራዎች ላይ መደመሙ፣መደነቁ፣መወያየቱ —- ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

Leave a Reply