14 May, 2016
ከክርስቶስ ልደት ከ3000 ዓመት በፊት የነበሩት ሱሜሪያውያን ለሄፒታይተስ በሽታ የተለየ ምልከታ ነበራቸው፡፡ በሽታው ጉበትን በማጥቃት ይታወቃል፡፡ ጉበትን የነፍስ መቀመጫ አድርገው ለሚወስዱት ሱሜሪያውያኖች ግን በሽታው በባዕድ መንፈስ የሚፈጠርና በበሽታው የተጠቁ ሕመምተኞች ዓይንና ቆዳ ወደ ቢጫነት የሚለወጠውም ‹‹አሀዙ›› በተባለው ሠይጣን ድርጊት እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ በሽታውን በዚህ መልኩ ቢስሉትም፣ ልዩ ትኩረት ይሰጡት ነበር፡፡ ነገር ግን በሌላው ዓለም ትኩረት አልተቸረውም፡፡ ምን መሆኑ፣ መንስዔውና መድኃኒቱ ሳይታወቅ ለዓመታት ቆይቷል፡፡
አሁን ላይ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድም በሽታውን ለይቶ ማወቅ ቢቻልም ጡንቻውን አፈርጥሞ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ኤ››፣ ‹‹ቢ››፣ ‹‹ሲ›› ‹‹ዲ›› እና ‹‹ኢ›› በመባል የሚታወቁ አምስት የሄፒታይተስ ዓይነቶች አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እስከ ‹‹ጂ›› ያደርሱታል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጉበት ላይ የሚከሰት ቁስል ሲሆን፣ እንደየ ዓይነታቸው የሚከሰቱበት ምክያትም ይለያያል፡፡ ሄፒታይተስ ‹‹ኤ›› ንጽሕናው ባልተጠበቀ ምግብና ውኃ ‹‹ቢ››፣ ‹‹ሲ›› እና ‹‹ዲ›› የተባሉት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በሽታው ካለበት ሰው ጋር በሚፈጠር የደምና ሌሎች ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች ንክኪ ይከሰታሉ፡፡ ሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› እና ‹‹ቢ›› በጾታዊ ግንኙነትም የሚተላለፉ ቢሆንም ‹‹ሲ››ው በጾታዊ ግንኙነት ወቅት የመተላለፍ ዕድሉ ከ‹‹ቢ››ው ያነሰ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
በሄፒታይተስ የተጠቁ ሰዎች የዓይናቸውና የቆዳቸው ቀለም ወደ ቢጫነት ይለወጣል፣ የአካል መዛል፣ ማስመለስና የሆድ ሕመምም ሌላ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ተደብቆ ይቆያል፡፡ አልፎ አልፎም ቫይረሶቹ ጉበትን ሳያጠቁ በዙሪያው ተለጥፈው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታ የሚታይባቸው ሰዎችም የቫይረሱ ተሸካሚ ይባላሉ፡፡
የሚፈጠሩበት ምክንያት እንደሚለያየው ሁሉ የሚያጠቋቸው ሰዎችም እንደዚሁ ይለያያሉ፡፡ ሄፒታይተስ ‹‹ኤ›› በብዛት ሕፃናትን ያጠቃል፡፡ እንደሌሎቹ ዓይነቶች ግን ጠንካራ አይደለም፡፡ ዓይናቸውንና ቆዳቸውን ወደ ቢጫነት ከቀየረ በኋላ ወዲያው ተመልሶ ይጠፋል፡፡ ሰውነታቸውም በሽታ መከላከያ (አንቲ ቦዲ ፀረ ሄፒታይተስ ኤ) ያመርታል፡፡ ሄፒታይተስ ‹‹ኢ›› ደግሞ ነፍሰጡር እናቶችን በማጥቃት ይታወቃሉ፡፡ በንጽሕና ጉድለት የሚከሰቱት ሄፒታይተስ ‹‹ኤ›› እና ‹‹ኢ›› በወታደር ካምፖች፣ በስደተኛ መጠለያዎች አካባቢ በስፋት ይስተዋላሉ፡፡
በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ የሚችሉት እነዚህ የሄፒታይተስ ዝርያዎች በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆኑ ይታያል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በየዓመቱ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ አዳዲስ የሄፒታይተስ ኢንፌክሽኖች ይከሰታሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት ምልክት ሲያሳዩ፣ የተቀሩት አያሳዩም፡፡ ይህም በሄፒታይተስ ‹‹ኢ›› የተያዙና በሕክምና ዕርዳታ ሊድኑ የሚችሉ 56,600 ሰዎች በየዓመቱ እንዲሞቱ አድርጓል፡፡
በገዳይነታቸው ቀዳሚ የሚባሉ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ሲ›› ናቸው፡፡ በዓለም ዙሪያም ከ500 ሚሊዮን ሚበልጡ ተጠቂዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ለበሽታው ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንና ብዙ ጊዜ ምልክት አለማሳየቱ በየዓመቱ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እንዲሞቱ ያደርጋል፡፡
‹‹ቢ›› እና ‹‹ሲ›› የሄፒታይተስ ቫይረሶች በኢትዮጵያ ውስጥም ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ አናሳ ሲሆን፣ ሕክምናውም ለብዙዎች ተደራሽ አይደለም፡፡
የ52 ዓመቱ አቶ ፋንቱ (ስማቸው ተቀይሯል) ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በአንድ ጋራዥ ውስጥ በሜካኒክነት ይሠራሉ፡፡ የሥራቸው ባህሪ ጉልበት ይፈልጋል፡፡ ለዓመታት ሲያገለግሉም ሥራቸውን በአግባቡ ከሚወጡት መካከል ነበሩ፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት ግን እንግዳ ነገር ተከሰተ፡፡
ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት እስኪያቅታቸው ድረስ አካላቸው ይደክማል፣ ይዝላል፡፡ ‹‹ምን እንደሆነ ሳላውቅ በጣም ይደክመኝ ጀመረ፡፡ ሥራዬን መሥራት አቃተኝ፡፡ ምናልባት ሥራ አብዝቼ ይሆናል በሚል ሥራ ቀንሼም ነበር፡፡ ነገር ግን ለውጥ አላመጣም›› የሚሉት አቶ ፋንቱ፣ ነገሩ ግራ ቢገባቸው ሆስፒታል እንደሄዱ ያስታውሳሉ፡፡
ቀለል ያለ በሽታ የጠበቁ ቢሆንም፣ ውጤቱ ያልጠበቁት ሆነ፡፡ ደማቸው ተመርምሮ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› እንዳለባቸው ተነገራቸው፡፡ ይሁንና ስለሕመሙ ምንም የሚያውቀት አልነበረም፡፡ የቫይረሱ አደገኛነትና የሕክምናው ውድነት አስደነገጣቸው፡፡ ሕክምናውን ወዲያው መከታተል አልጀመሩም፡፡ ለጊዜው ሕመሙ የፈጠረባቸውን የድካም ስሜት የሚቀንስ መድኃኒት እየወሰዱ ለሁለት ዓመታት ያህል ቆዩ፡፡ በዚህ የተወሰነ እፎይታ አግኝተው ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ግን ነገሮች እንደገና መልካቸውን ቀየሩ፡፡ ድካሙ አገረሸ፡፡ በድጋሚ በተደረገላቸው የደም ምርመራም የቫይረሱ ቁጥር አምስት ሚሊዮን መድረሱ ተነገራቸው፡፡ መድኃኒት እንዲጀምሩ ቢነገራቸውም የታዘዘላቸውን መድኃኒት በቀላሉ የሚገኝና ዋጋውም በሳቸው አቅም የሚሞከር አልነበረም፡፡ የአንዱ መድኃኒት ዋጋ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
በመሆኑም ሌላ አማራጭ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ መድኃኒቱ ባንኮክ ውስጥ በቅናሽ እንደሚሸጥም ሰሙ፡፡ በአጋጣሚው ደስተኛ ቢሆኑም፣ ለመግዛት ግን አልቻሉም፡፡ ባንኮክ ውስጥ የሚገኙ ሐኪሞች ካላዘዙ በስተቀር መድኃኒቱ እንደማይሸጥ ተነገራቸው፡፡ ሌላ አማራጭ ግን አላጡም፡፡ መድኃኒቱን በግሉ እያመጣ የሚሸጥላቸው የቅርብ ሰው አገኙ፡፡ በ900 ብር እየገዙ መጠቀም ጀመሩ፡፡ ይህም ቢሆን ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ዘመዶቻቸውንና ሌሎች በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች እገዛ እንዲያደርጉላቸው ማስቸገራቸው አልቀረም፡፡
የበሽታውን መንስዔ በውል ያልተረዱት አቶ ፋንቱ ‹‹ወላጆቼ የሞቱት በጉበት በሽታ ነበር፤›› በማለት ምናልባት ከእነሱ ተላልፎባቸው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ምንም እንኳ በሽታው በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው የመተላለፍ ዕድል ቢኖረውም በአቶ ፋንቱ ቤተሰቦች ላይ የተፈጠረ ነገር አልነበረም፡፡
‹‹ልጆቼን የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ የሄፒታይተስ ክትባት አስከትቤያቸዋለሁ፡፡ ከባለቤቴም ጋር ቢሆን አልጋ ለይተን ማደር ከጀመርን ሰነባብተናል፡፡ በንክኪና በሌሎች ፈሳሾች ወደ ቤተሰቦቼ እንዳይተላለፍም እጠነቀቃለሁ›› ሲሉ ለቤተሰቦቻቸው ጤንነት የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ይናገራሉ፡፡ ከቀናት በፊት ባደረጉት ምርመራም አምስት ሚሊዮን የነበረው የቫይረሱ ቁጥር ወደ 30 ዝቅ ማለቱን፣ ይህም ነፃ እንደሆኑ ያህል እንዲሰማቸው ማድረጉን በእርካታ ይናገራሉ፡፡
በሽታው አብዛኛውን ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ቆይቶ በአጣዳፊ ሕመም ብዙዎችን ድንገት ሲያራውጥ ይታያል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም የምትሠራው የ23 ዓመቷ ቅድስት ዳኘው (ስሟ ተቀይሯል) ተመሳሳይ ገጠመኞች ከደረሰባቸው መካከል ነች፡፡ ከዚህ ቀደም ከቀላል ሕመሞች በስተቀር ምንም ዓይነት ከባድ በሽታ ነክቷት እንደማያውቅ ‹‹ምንም ዓይነት ሕመም ነክቶኝ አያውቅም፤›› ስትል የነበራትን ሙሉ ጤንነት ታስታውሳለች፡፡
አንድ ቀን የጀመራት ሆድ ቁርጠት ግን በቀላሉ አልተሻላትም፡፡ ከአሁን አሁን ይሻለኛል ብላ ብትታገስም አልሆነም፡፡ ሆስፒታል ለመሄድም ተገደደች፡፡ የመረመራት ዶክተር ሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› እንዳለባት ነገራት፡፡ ነገር ግን እንደ አቶ ፋንቱ ሁሉ እሷም ስለ በሽታው አታውቅም ነበር፡፡ ውጤቱን እንደሰማችም የተለየ ስሜት አላሳየችም ነገሩን ሐኪሙ ሲያስረዳት ግን ተደናግጣ አልቅሳ ነበር፡፡
ስለ ሁኔታው ከወንድ ጓደኛዋ፣ ከእህቷና ከወንድሟ በቀር ለማንም አልተናገረችም፡፡ ወላጆቿም ስለሆነው ነገር አልሰሙም፡፡ መድኃኒቱን ስትጀምርም በሚስጥር ነበር፡፡ በየሳምንቱ ለምትወስደው መርፌ 6,500 ብር እየከፈለ እስኪሻላት ያሳከማትም መሥሪያ ቤቷ ነው፡፡ ‹‹በምን ምክንያት እንደያዘኝ አላውቅም፡፡ ነገር ግን አሁን እየተሻለኝ ነው፤›› ስትል በውስጧ ተደብቆ የቆየው በሽታ ድንገት እንዳሰቃያት ትናገራለች፡፡
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የወፍ በሽታ በመባል የሚታወቀው ሄፒታይተስ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአገሪቱ በሥፋት ተንሠራፍቶ የሚገኘው ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር ሲነፃፀር በ99.9 በመቶ የመተላለፍ አቅም አለው፡፡ ይህም በአገሪቱ ያለው የበሽታው ሥርጭት እስከ 10 በመቶ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የሕክምናው ተደራሽ አለመሆንና በቂ ግንዛቤ አለመፈጠር ቁጥሩን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሳድገው እንደሚችልም ሥጋት አለ፡፡
ከበሽታው አደገኛነት አንፃር ሕመምተኞች ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ በታወቀ ቅፅበት ሕክምና ሊያገኙ ግድ ይላል፡፡ ይሁንና ካለው የአቅም ውስንነት አኳያ ተገቢውን ሕክምና የሚያገኙት ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በሰውነታቸው ውስጥ ከተሰራጨ በኋላ ነው፡፡ ሕክምና ለመስጠት ቫይረሱን ሥርጭት በምርምራ ማረጋገጥም ግድ ቢሆንም የቫይረሱን ሁኔታ ለመለየት የሚያስችል ምርመራ በአገር ውስጥ አለመሰጠቱ ሌላው ፈተና ነው፡፡
ተመሳሳይ የደም ምርመራዎችን ውጭ ልኮ ከሚያሠሩ ተቋማት መካከል አርሾ ሜዲካል ላቦራቶሪ አንዱ ነው፡፡ የተቋሙ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ መድኃኔ ተክላይ እንደሚሉት፣ በወር ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ የሄፒታይተስ ቢ እና ሲ ኬዞች ወደ ተቋሙ ይሄዳሉ፡፡ ለአንድ ምርመራም 3,213 ብር ያስከፍላሉ፡፡ ምርመራው የሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› ጄኖታይፕ (ዓይነት) በሚሆንበት ጊዜም የክፍያ ዋጋው 6,000 ብር ይሆናል፡፡
በአገሪቱ ከሌሎች የሄፒታይተስ ዓይነቶች በተለየ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› በስፋት ይገኛል፡፡ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት አለው የሚሉት ጠቅላላ ሐኪም፣ የውስጥ ደዌ እና የጉበት፣ የጨጓራ፣ የአንጀት፣ ስፔሻሊስቱ ዶክተር መንግሥቱ እርቄ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በሽታው በሁለት ዓይነት መንገዶች ይዛመታል፡፡ ቨርቲካል ወይም በቀጥታ የሚተላለፈው ሲሆን፣ አንድ ሕፃን ሲወለድ ከእናትየው አልያም ከአባትየው የሚተላለፍበት ከዚህ ይመደባል፡፡ ሆሪዞንታል ወይም አግድም የሚተላለፈው ደግሞ አንድ ሰው ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ በበሽታው የሚያዝበት ሁኔታ ነው፡፡
በሽታው ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ለሄፒታይተስ ታማሚዎች የሚሰጠው የኤችአይቪ መድኃኒት ነው፡፡ ከዚህ ሌላም ቫይረሱ ከዘረ መል ጋር የመቀላቀል ባህሪ አለው፡፡ ይህም በቀላሉ ለመለየት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› በሕክምና መዳንም አይችልም፡፡ ይሁንና የቫይረሱን ቁጥር በመቆጣጠር በጉበት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ማስቀረት ይቻላል፡፡
ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› በሰውነት ውስጥ ተደብቆ የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ሲሆን፣ ‹‹ሲ›› ደግሞ ከ20 እስከ 40 ዓመታት ድረስ ተደብቆ ሊቆይ ይችላል፡፡ በሰውነት ክፍል ውስጥ የሚኖረው የሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ቫይረስ ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፣ የጉበት በካንሰር የመጠቃት ዕድልም አብሮ ይጨምራል፡፡
ሌላው ከ‹‹ቢ›› ቀጥሎ በአዋቂዎች ላይ በብዛት የሚታየው ሄፒታይተስ ‹‹ሲ›› ነው፡፡ ከ‹‹ቢ›› በተሻለ የመዳን ዕድል ያለው ሲሆን፣ በስሩ ስድስት ዓይነት ዘረመሎች (ጄኖ ታይፖች) አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል በአገሪቱ በስፋት የሚታዩት ጄኖታይፕ 1 እና ጄኖታይፕ 4 የተባሉት ናቸው፡፡ ሕክምናቸው በጣም ውድ ከሚባሉት ተርታ ይመደባል፡፡ ሕክምናው በወር ከ100,000 ብር በላይ ይጠይቃል፡፡
‹‹የምናክመው በመርፌና በኪኒን ነው፡፡ ለአንድ መርፌ 25,000 ብር ያስከፍላል፡፡ መርፌው በየሳምንቱ ያስፈልጋል፡፡ ሕክምናውንም ለድፍን አንድ ዓመት መከታተል ግድ ነው›› የሚሉት ዶ/ር መንግሥቱ፣ በቅርቡ አዲስ መድኃኒት መምጣቱን ዋጋውም እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ መውረዱን፣ ሕክምናውም በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ካለው የበሽታው ሥርጭት አንፃር ይህ ብዙም ለውጥ እንደማይፈጥር ከሄፒታይተስ ዓይነቶች ‹‹ቢ›› ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝና የበለጠም ትኩረት እንደሚያስፈልገው ይገልጻሉ፡፡
ዶ/ር መንግሥቱ እንደሚሉት፣ አገሪቱ የሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› ታማሚዎችን ለማከም የምትከተለው መመሪያ የአሜሪካኖችን ነው፡፡ የአሜሪካኖች መመሪያ እንደሚለው ደግሞ፣ አንድ በሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› የተጠቃ ሰው መድኃኒት መጀመር ያለበት በደሙ ውስጥ ያለው የቫይረሱ ሥርጭት በ2,000 እና በ20,000 መካከል ሲሆን ነው፡፡ ይህ ግን በሽታው ሥር እንዲሰድ መንገድ ይከፍታል፡፡ በሽታው መኖሩ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ሕክምና መስጠት ቫይረሱን ለመቆጣጠር ዓይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን ካለው የአቅም ውስንነት አኳያ ይህን ማድረግ አልተቻለም፡፡
በሌላ በኩልም ክትባት በሽታውን ለመከላከል ወሳኝ መፍትሔ ነው፡፡ ነገር ግን ከሄፒታይተስ ‹‹ኤ›› እና ‹‹ቢ›› በቀር ሌሎቹ ክትባት የላቸውም፡፡ ክትባት ያላቸውንም ቢሆን ካለው የአቅም ውስንነት አንፃር ለሁሉም ማዳረስ አልተቻለም፡፡ ክትባቱን የሚያገኙት ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ እንደ ሕክምና ባለሙያዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የታማሚ ቤተሰቦችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
የተሻለ የሕክምና አማራጭ የተገኘለት ሄፒታይተስ ‹‹ሲ››ም ቢሆን ሕክምናውን በተገቢው መንገድ ለማዳረስ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ አንድ ሕመምተኛ መድኃኒቱን ሲጀምር በየተወሰነ ጊዜ በደሙ ውስጥ ያለውን የቫይረስ ሥርጭት መለካት ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች ቫይረሱን መለካት የሚችሉ ማሽኖች ቢኖሩም፣ የሚለኩበት በቂ ግብዓት ግን የላቸውም፡፡ ሕክምናውን መስጠት የሚችል በቂ የሰው ኃይልም የለም፡፡ ይህም ሕክምናውን ለማዳረስ እንቅፋት ሆኗል፡፡
‹‹ሊድንና ልንቆጣጠረው በምንችለው በሽታ ሰዎች ሊሞቱ አይገባም፡፡ መንግሥት በቂ ትኩረት ሊያደርግበትና የብዙዎችን ሕይወት ሊታደግ ይገባዋል›› ሲሉ ዶክተሩ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ብዙ ያልተነገረለት ሄፒታይተስ ብዙዎች በአልጋ ላይ እንዲማቅቁ፣ ለብዙዎች ህልፈትና ቤተሰብ መበተን ምክንያት ሆኗል፡፡ ማኅበረሰቡም ስለበሽታው በቂ መረጃ የለውም፡፡ ስሙን ሰምተው የማያውቁም ብዙ ናቸው፡፡
በተለይ ሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ሲ›› የኅብረተሰቡ የጤና ችግር ሆነዋል የሚሉት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ዳንኤል ገብረ ሚካኤል ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት የበሽታው ሥርጭት ከኤችአይቪ በላይ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በቂ ትኩረት ሳይሰጠው ዘመናት አልፈዋል፡፡ የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ትኩረትም በኤች አይ ቪ ላይ ነበር፡፡
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በሽታው ሳይታወቅ በስፋት እየተሠራጨ በመሆኑ፣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችና ሕመምተኞች በአገር ውስጥ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የሄፒታይተስ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ሲ›› መድኃኒቶች በቅናሽ ዋጋ በከነማ ፋርማሲዎች እያሠራጨ ይገኛል፡፡ እስከ 80,000 ብር ይፈጅ የነበረው ሕክምናም ከ20,000 ብር ባልበለጠ እንዲያልቅም እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ‹‹ይህ የሙከራ ፕሮግራም ነው፡፡ በቀጣይ ምንም አቅም የሌላቸው ሰዎች ሕክምናውን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት ታስቧል›› መታሰቡን ዶ/ር ዳንኤል ይገልጻሉ፡፡ ሁኔታው እንደ ቅድስትና አቶ ፋንቱ ላሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎች መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ይሁንና ዶ/ር መንግሥቱ የጠቀሷቸው ክፍተቶች ልብ ሊባሉ ይገባል፡፡
- ሻሂዳ ሁሴን’s blog
- 798 reads