Wednesday, 18 May 2016 14:18
ስለካንሰር ያለው የግንዛቤ እጥረት ከአገልግሎቱ አለመስፋፋት የተነሳ መሆኑ ተገለፀ
አስረኛውን “የማህፀን ጫፍ፣ የጡት እና የፕሮስቴት ካንሰርን ከአፍሪካ እናጥፋ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን ጉባኤን አስመልክቶ ትናንት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ክብርት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እንደገለፁት፣ ስለችግሩ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር የአገልግሎቱ አለመስፋፋት ዋና እንቅፋት ነው። ወ/ሮ ሮማን እንደገለፁት፤ በሽታውን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት ከተሰሩ በኋላ በቂ አገልግሎት መስጠት ስለማይቻል አንድ እንቅፋት ሆኗል። ግንዛቤው ቢኖራቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ወደ የጤና ተቋማት በእርግጠኝነት ለመመርመር ይመጣሉ ያሉት ወ/ሮ ሮማን፤ ከተመረመሩት ውስጥ በሽታው የሚኖርባቸው ስለማይጠፋ የግድ ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል። ነገር ግን ህክምናውን በሚፈለገው መጠን ለመስጠት በቂ አገልግሎት ባለመኖሩ፣ ቅስቀሳውን ከማድረግ መቆጠባቸውን ገልፀዋል። ይህ የአገልግሎቱ አለመስፋፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ስለበሽታው ቅስቀሳ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ ሮማን፣ በቅርቡ ግን ማዕከላቱን በማስፋፋት ወደ ቀጣይ እርምጃ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይ የማህፀን ጫፍ ካንሰር መንስኤው ኢንፌክሽን በመሆኑ፤ ችግሩን ማስወገድ የሚቻለው እድሜያቸው ከ10 እስከ 14 ዓመት የሆኑ ልጃገረዶችን መከተብ ነው ያሉት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ በበኩላቸው፤ ይህን አይነቱን አገልግሎት መስጠት እስከሚቻል ድረስ ግን እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች በዓመት አንድ ጊዜ ምርመራ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው ብለዋል። ልጃገረዶችን የመከተብ ስራውን በአሁኑ ወቅት በጅማ እና በመቀሌ በሙከራ ደረጃ እያከናወኑ መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት በሁሉም ሆስፒታሎች የማህፀን በር ምርመራ እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም በጤና ጣቢያ ደረጃ እንዲሰጥ ለማድረግ በመሰራት ላይ መሆኑን እና መሳሪያዎችንም በመግዛት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ ስለበሽታው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም ይሰራል ብለዋል።
በሀገራችን በየዓመቱ ከ64 ሺህ በላይ ሰዎች በካንሰር የሚያዙ ሲሆን፤ በሀገሪቱ ያለው የማስተናገድ አቅም ከችግሩ ጋር ሲነፃፀር አናሳ በመሆኑ፣ በበሽታው የሚደርሰው ጉዳት እንዲባባስና የችግሩ ሰለባዎች ቁጥርም እንዲጨምር አድርጐታል ተብሏል። በሴቶች ላይ እጅግ የከፋ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙት የማህፀን ጫፍ እና የጡት ካንሰርም በሀገራችን በካንሰር በሽታ ሳቢያ ለሚከሰቱ ሞቶች ዋንኛ መንስኤ እንደሆኑ ወ/ሮ ሮማን ገልፀዋል። ከሐምሌ 17 እስከ 20 ቀን 2008 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በሚካሄደው አስረኛው ጉባኤ ላይም ሀገሪቱ በተለይ የማህፀን ጫፍ፣ የጡት እና የፕሮስቴት ካንሰርን ለማጥፋት እና ህክምናውን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትብብሮችን ለመመስረት ታቅዷል። በጉባኤው ላይ በሀገራችን እና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ስለ ችግሩ የተደረጉ ጥናቶች የሚቀርቡ ሲሆን፤ ከዚያ ቀደም ብሎም የማህፀን በር ምርመራ እና ህክምና አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል። በጉባኤው ላይ ከሦስት ሺህ በላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንደሚገኙም ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።
በተያያዘ ዜና ስለ የሚጥል በሽታ ያለው ግንዛቤ የተሳሳተ በመሆኑ ሳቢያ ህክምናውን የሚያገኙት ሰዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተገለፀ። በሀገራችን አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ህክምናውን የሚያገኙት አምስት በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ከግንቦት ሰባት እስከ 14 ቀን 2008 ዓ.ም “ትኩረት ለሚጥል በሽታ” በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ ያለው የሚጥል በሽታ ሳምንት አስመልክቶ ባለፈው አርብ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አዳራሽ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ ማኅበረሰቡ ስለበሽታው ያለውን ግንዛቤ የተሳሳተ ከመሆኑ የተነሳ ህሙማኑ ህክምና ካለማግኘት በተጨማሪም ከማኅበረሰቡ መገለልና መድሎ እየደረሰባቸው እንዲሁም ወደ ተሳሳቱ አመለካከቶችና መሸማቀቅ በማምራት በወቅቱ የመታከም እድሉን እያጡ ነው።
የሚጥል በሽታን ለማከም የታማሚውን ቤተሰብ እና የማኅበረሰቡን ድጋፍ እንደሚጠይቅ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህን ለማድረግም በበሽታው ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና የአገልግሎቱን ተደራሽነትም በማስፋት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ስንደቅ