Wednesday, 18 May 2016 14:11
 በይርጋ አበበ

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 14 ፓርቲዎችን ሰረዘ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ጠንካራ ፉክክር ያደርግ የነበረውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረትን (ኢዴኃኅ) ጨምሮ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በቦርዱ ውሳኔ መሰረት ከምዝገባ መሰረዙን አስታወቀ። ከተሰረዙት ፓርቲዎች መካከል አንዳንዶቹ በሽግግር መንግስቱ ወቅት የነበሩ እና ቀሪዎቹ ደግሞ ህልውናቸውን ቀድመው የተው ፓርቲዎችም ይገኙበታል።

የቦርዱ የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽነ ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ እንዳስታወቁት ፓርቲዎቹ ከምዝገባ የተሰረዙት በተሻሻለው የምርጫ ህግ አንቀጽ 532/1999 ዓ.ም እና በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ እንቅስቃሴያቸውን የመከታተል የመቆጣጠር ድጋፍ የማድረግና ህጉን አሟልተው ባልተገኙ ጊዜ የመሰረዝ ስልጣን እና ኃላፊነቱን ተጠቅሞ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቦርዱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በተገኘ መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው ከምርጫ ቦርድ መዝገብ የተሰረዙት 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች አሟልተው ያልተገኟቸው መስፈርቶች አራት ሲሆኑ በዋናነት የጠቅላላ ጉባኤ አለማካሄድ፣ በኦዲተር የተረጋገጠ የፋይናንሰ ሪፖርት አለማሳወቅ፣ በፓርቲው የተሾመ ህጋዊ የውጭ ኦዲተርና የተሾመው ኦዲተር ሹመቱን በፊርማው ያረጋገጠበት ሰነድ አለማቅረብ እና የዋና እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አድራሻቸውን አለማሳወቅ የሚሉት ይገኙበታል።

በመሆኑም ከግንቦት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ቦርዱ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የ14 ፓርቲዎችን ከመዝገብ የሰረዘ መሆኑን ገልጾ የተሰረዙት ፓርቲዎችም በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ መሰረዝ ወይም መፍረስ ውጤትን አስመልክቶ የተደነገገውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መወሰኑን የቦርዱ መግለጫ አረጋግጧል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዙ ፓርቲዎች ዝርዝር

1.  የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት (ኢዴኃኅ)

2.  የኮንሶ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኮሕዴኅ)

3.  የኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ፓርቲ (ኢአምፓ)

4.  ባሕረወርቅ መስመስ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ባመሕዴድ)

5.  የጠንባሮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ጠሕዴን)

6.  የሶዶ ጎርደና ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሶጎሕዴድ)

7.  የጋሞ ጎፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት (ጋጎሕዴአ)

8.  የሐረሪ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሐሕዴፓ)

9.  የጉራጌ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ጉሕዴግ)

10.የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት (ሶዴኃቅ)

11.የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት (ደኢዴኃአ)

12.የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ጋዴኅ)

13.የሀድያ ብሔራዊ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሀብአዴድ)

14.የአፋር ብሔራዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ናቸው።

ስንደቅ

Leave a Reply