Wednesday, 18 May 2016 14:15

በ 

ግብፅ ከኢትዮጵያ ከ14 እጥፍ በላይ የሚበልጥ የአሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ላይ ደረሰች

እንደ አህራም ኦንላይን ዘገባ ግብፅ በ2014 የነበራት አጠቃላይ ኤሌክትሪክ ኃይል መጠን 32 ሺህ 15 የነበረ ሲሆን ሰሞኑን የተመረቁት ስምንት የኃይል ማመንጫዎች ሲደመሩ የሀገሪቱን አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ወደ 35 ሺህ 615 ሜጋ ዋት ከፍ አድርጎታል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከ2 ሺህ 4 መቶ ሜጋ ዋት አይበልጥም።

ግብፅ በአሁኑ ሰዓት እያመነጨች ያለው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ከ15 እጥፍ በላይ የሚበልጥ መሆኑን ንፅፅሩ ያመለክታል። ኢትዮጵያ በ1932 አቃቂ ወንዝ ላይ በተተከለው ግድብ 6 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሀይልን በማመንጨት የጀመረች ሲሆን ከዚያም በጢስ አባይ አንድ፣ ቆቃ ግድብ፣ በአዋሽ አንድና ሁለት እንደዚሁም በፊንጫና በመልካ ዋክና  እስከ 4 መቶ ሜጋ ዋት ስታመነጭ ቆይታለች። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ቲስ አባይ ሁለት፣ ግልገል ጊቤ አንድና ሁለት እንደዚሁም ተከዜ፣ጣና በለስ  ወደስራ የገቡ ሲሆን የአዳማና የአሸጎዳ የነፋስ ሀይል ማመንጫን ጨምሮ በአጠቃላይ የሀገሪቱ የአሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 2 ሺህ 4 መቶ ከፍ ብሏል። 1870 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ግልገል ጊቤ 3 እና ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ ሜጋዋት የሚያመነጨው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከአስር ሺ ሜጋ ዋት በላይ ይደርሳል። ከዚህም በተጨማሪ ተከዜ ሁለትና ጊቤ አራትና አምስትም ታሳቢ የተደረጉ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች ናቸው።

 ግብፅ በአሁኑ ሰዓት የአሌክትሪክ ኃይልን የምታመነጨው ከውሀ፣ ከነፋስ፣ ከነዳጅና ከፀሀይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። አገሪቱ 27 ሺህ ሜጋ ዋት እያመነጨች በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ገጥሟት ከፍተኛ ለሆነ የኃይል መቆራረጥ ችግር ተዳርጋ ነበር።  አልሲሲ ወደ ስልጣን በመጡበት  ወቅት ለዚሁ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ ለህዝቡ ቃል የገቡበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን ይሄንንም ቃላቸውን በማሳካት ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይሏን በዋነኝነት በውሃ  ጥገኛ አድርጋለች በሚል የኃይል ማመንጪያ አማራጮቿን እንድታሰፋ አለም አቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ምክረ ሀሳባቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ከውሃ እስከ 45 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት እምቅ አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ውጪም ከነፋስ ኃይልም እስከ አንድ ሚሊዮን ሜጋ ዋት የሚደርስ የአሌክትሪክ ኃይልን የማመንጨት እምቅ አቅም ያላት መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።

ስንደቅ

Leave a Reply